የወቅቱ የረጅም ርቀት ድንቅ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈችበት ከሚገኘው የረጅም ርቀት ውድድሮች በቅርቡ ፊቷን አዙራ ወደ ማራቶን ለማተኮር እንዳሰበች ፍንጭ ሰጥታለች። ለዚህም በቀጣዩ ሐምሌ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን ለማድረግ የስፔኗን ከተማ ቫሌንሲያን ምርጫዋ እንዳደረገች ታውቋል።
አርባ ሁለተኛው የቫሌንሲያ ማራቶን ከወራት በኋላ ሲካሄድ የአለማችን የረጅም ርቀት ኮከብ የሆነችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር የመጀመሪያ ውድድሯን በሩጫዋ ከተማ ቫሌንሲያ ለማድረግ የወሰነችው ካለምክኒያት አይደለም። ቫሌንሲያ የሩጫ ከተማ ብቻ ሳትሆን የተለያዩ የዓለም ክብረወሰኖች ከቅርብ አመታት ወዲህ የሚሰበርባት ሆናለች። በተለይም ይህች ከተማ ለለተሰንበት የተለየ ቦታ አላት። ለተሰንበት ባለፉት ጥቂት አመታት የዓለማችንን ታላላቅ አራት ክብረወሰኖች በማሻሻል አስደናቂ ብቃቷን ስታሳይ ሁለቱን ማሳካት የቻለችው በቫሌንሲያ ከተማ ነው።
የ2022 የዓለም ትልቁ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአሜሪካ ፖርትላንድ ኦሪገን ከጥቂት ወራት በኋላ እንደሚካሄድ ይታወቃል። የዓለማችን ድንቅ ድንቅ አትሌቶች ለራሳቸው ዝናና ስኬት እንዲሁም ለአገራቸው ክብር እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በሚያደርጉበት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለተሰንበትም በአስር ሺ ሜትር እንደምትወዳደር ይጠበቃል። ከዓለም ቻምፒዮናው ጥቂት ወራት በኋላ ግን በረጅም ርቀት ጣፋጭ ድሎችን በተቀዳጀችባት ቫሌንሲያ ከተማ በማራቶን ተጨማሪ ስኬት ለመጎናጸፍ እንደምትዘጋጅ የውድድሩ አዘጋጆች ማረጋገጣቸውን ሰሞኑን አሳውቀዋል።
“የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሬን በቫሌንሲያ እንደማደርግ ስገልጽ በደስታ ነው፣ ከቫሌንሲያ ጋር የተለየ ግንኙነት አለኝ፣ 2020 ላይ የ5ሺ ሜትር ክብረወሰንን፣ 2021 ላይ ደግሞ የግማሽ ማራቶን ክብረወሰንን በቫሌንሲያ በማሻሻል ልዩ ትዝታ አለኝ፣ በመጪው የቫሌንሲያ ማራቶንም ድንቅ ጊዜ እንደማሳልፍ ተስፋ አለኝ” በማለት ለተሰንበት መናገሯን አትሌቲክስ ዊክሊ ጽፏል።
የውድድሩ አዘጋጆች በበኩላቸው “የዓለማችን ድንቅ አትሌት ከሆኑት አንዷ ለተሰንበት ግደይ በቫሌንሲያ ማራቶን እንደምትሳተፍ ማረጋገጧ ከተማችንን የዓለማችን የሩጫ መዲና ለማድረግ እያሳየነው ያለውን ትጋት ያረጋግጣል፣ብዙ የዓለማችን ከተሞች እንደ ለተሰንበት ያሉ ድንቅ አትሌቶች የመጀመሪያ የማራቶን ውድድራቸውን እነሱ ጋር እንዲያደርጉ ፍላጎት አላቸው፣ ለተሰንበት እኛን ምርጫዋ በማድረጓ ኩራት ይሰማናል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ለተሰንበት ከቫሌንሲያ ጋር የተዋወቀችው 2020 ላይ አስደናቂውን የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ነበር። ይህች ኮከብ አትሌት ለአስራ ሁለት አመታት በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት የረጅም ርቀት ፈርጥ ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የ5ሺ ሜትር ክብረወሰን 14:06:62 በመሮጥ አሻሽላ ዓለምን አስደምማለች። ከአመት በኋላ ወደ ቫሌንሲያ ተመልሳም 2021 ላይ የመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሯን በማድረግ 1:02:52 በሆነ ሰዓት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ጨብጣለች።
ባለፉት ሁለት አመታት አስደናቂ ብቃቷን በተለያዩ የረጅም ርቀት ውድድሮች በማሳየት አራት ታላላቅ ክብረወሰኖችን በእጇ ያስገባችው ለተሰንበት በቫሌንሲያ ካሻሻለቻቸው ሁለት ክብረወሰኖች በተጨማሪ በኔዘርላድስም ትልቅ ስም ያስገኙላትን ሁለት ክብረወሰኖች መስበሯ ይታወቃል። ይህም በ2019 ኒጅመን አስራ አምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የርቀቱን ክብረወሰን 44:20 በሆነ ሰዓት ያሻሻለችበት ነው። ለተሰንበት በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያውያን ማጣሪያ ውድድር ሄንግሎ ላይ የሰበረችው የ10ሺ ሜትር ክብረወሰን ግን ከሁሉም የላቀ ነበር። የዚህን ርቀት ክብረወሰን ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን በእጇ አስገብታ አርባ ስምንት ሰዓት ሳይሞላው ለተሰንበት በሄንግሎው የማጣሪያ ውድድር 29:01:03 በሆነ ሰዓት የግሏ ማድረግ የቻለችበት አጋጣሚ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያስደመመ ታሪክ ሆኖ ይታወሳል።
ለተሰንበት እነዚህን ታላላቅ ክብረወሰኖች እጇ ባስገባችበት የውድድር አመት በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተለይም በ10 ሺ ሜትር ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷት የነበረ ቢሆንም አስራ ዘጠኝ ዙሮችን ለብቻዋ እየመራች የሚያግዛት ሌላ ኢትዮጵያዊ አትሌት ባለማግኘቷ የወርቅና የብር ሜዳሊያውን በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የኔዘርላንድስና የባህሬን አትሌቶች ሲፈን ሃሰንና ቃልኪዳን ገዛኸኝ ተነጥቃ የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014