በመላው ዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ ዘርፎች መካከል አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ነው። ይህ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ከ7ነጥብ 68 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስገኝም መረጃዎች ያሳያሉ። ውድድሮችን በማዘጋጀት፣ ስታዲየሞችንና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባት እንዲሁም በስፖርቱ አዝናኝና ሳቢ ክንውኖችን በማሰናዳት በርካታ ሃገራትና ከተሞቻቸው ተጠቃሚ ሆነዋል። በአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነው የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መካሄድ ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ይህ ሲሆን፤ በርካታ ሯጮችና ጎብኚዎች በስፖርቱ የስመ ጥር አትሌቶች መገኛ ወደ ሆነቸው ኢትዮጵያ ይመጣሉ። አሁን ደግሞ ስፖርትን ማዕከል ያደረገ ቱሪዝም ፊቱን የአትሌቶች ምንጭ ወደሆነችው በቆጂ የመለሰበት አበረታች ጅምር እውን ሆኗል።
ኢትዮጵያ በበጎ ስም እንድትጠራ ካደረጉት ነገሮች መካከል ቀዳሚ የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት ሲነሳ በቆጂ የማትዘነጋ ስፍራ ናት። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረኮች ተሳትፎዋ ከሰበሰበቻቸው 58 ሜዳሊያዎች መካከል 18 የሚሆኑት (10የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሃስ) ሜዳሊያዎች የተመዘገቡት የሯጮቹ ምድር በቆጂ ባፈራቻቸው ብርቅዬ አትሌቶች በመሆኑ ነው። ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ፋጡማ ሮባ፣ እጅጋየሁ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ቲኪ ገላና፣ መስታወት ቱፋ እና ትዕግስት ቱፋን የመሳሳሉት የኦሊምፒክ፣ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች የአትሌቲክስ ታላላቅ መድረኮች ቻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች ፈልቀውባታል።
በርካታ ምርጥና ድንቅ አትሌቶችን ያፈራችውና አሁንም ታዳጊና ተተኪ አትሌቶች እየፈለቁባት የምትገኘው ይህቺ የሯጮች ምድር፤ የአየር ሁኔታዋ፣ የቦታ አቀማመጧ እንዲሁም የአኗኗር ሁኔታው ለስፖርቱ ምቹ ያደርጋታል። ‹‹የሯጮቹ ምድር›› በሚል የምትታወቀው በቆጂ በበርካታ የስፖርቱ ቤተሰብ ህሊና በመቀረፅ ዘጋቢ ፊልም ከማድረግ ባለፈ ጉብኝት ያደርጉባታል። ይሁን እንጂ ስፍራው ሊያገኝ የሚገባውን ድጋፍ ያላገኘ፣ አትሌቶችና ነዋሪዎቹም የሚገባቸውን ጥቅም ያላገኙበት ስፍራ መሆኗ የሚያስቆጭ ነው።
ይህ ስፍራ በእንቁ አትሌቶች አብቃይነቱ በተለየ ይታወቅ እንጂ የተለየ ድጋፍና እገዛ ተደርጎለት አያውቅም። በመሆኑም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ስፍራውን የአትሌቲክስ ማዕከል በማድረግ ከስፖርት ቱሪዝም ተጠባቂ እንዲሆን ወደ ተግባር ገብቷል። በዚህም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመሆን ‹‹ኢትዮጵያ ትሮጣለች›› በሚል መልዕክት የሩጫ መርሃ ግብር ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል። በዚህም ከጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በተወጣጡ አትሌቶች መካከል፣ ከ11 ዓመት በታች እንዲሁም አትሌቶችንና የጤና ሯጮችን ያካተተ የታላቁ በቆጂ 7 ኪሎ ሜትር ሩጫ ተደርጓል። ከአትሌቲክስ ጎን ለጎንም የተራራ መውጣት እና የሳይክል ውድድሮች ተካሂደዋል።
አትሌቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የውጪ ሃገር ዜጎች እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደው ውድድር ላይም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢው ነዋሪ ተገኝቶ ድጋፉን ሰጥቷል። በአዋቂዎች ዘርፍ በተደረገው ውድድርም በሴቶች መሰረት ሂርጳ፣ ቀነኒ ዲቻ እና ሃዊ ጉደታ አሸናፊዎች ሆነዋል። በወንዶች ደግሞ ደጀኔ ኃይሉ፣ ቱሉ አበበ እና ብርሃኑ ቱሉ ተከታትለው በመግባት ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው ሊያጠናቅቁ ችለዋል። የውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችም የ5ሺ ብር ሽልማት ሲያገኙ፤ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ያጠናቀቁት ደግሞ 4ሺ እና 3ሺ ብር ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም በቀጣዩ ወር እንደ በቆጂ ሁሉ የኬንያዊያን አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው የኤልዶሬት ከተማ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ተካፋይ የመሆን እድል አግኝተዋል።
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት፤ በርካታ አትሌቶች ከዚህ ስፍራ በመውጣት የሃገራቸውን ስም ማስጠራታቸው የአትሌቶች መፍለቂያ ብቻም ሳይሆን በቆጂን ታሪካዊ ስፍራ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል። በመሆኑም ይህንን በስፖርት እምቅ አቅም ያለው አካባቢ በመሆኑ፤ ከሩጫ ጎን ለጎን ከስፍራው የተገኙ ትልልቅ አትሌቶች ያደጉበትን ቤትና ልምምድ ያደርጉበት የነበሩበትን አካባቢ በማስጎብኘት፣ ስፍራው ተራራ ለመውጣት እና ብስክሌት ለመጋለብ አመቺ በመሆኑ ጎብኚዎችን በመሳብ ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በመሆኑም በየዓመቱ በቆጂ ላይ የሩጫ ውድድር በማድረግ፤ ስፖርቱን በማነቃቃት እንዲሁም ታዳጊዎችም ወደ ስፖርቱ እንዲቀላቀሉ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2014