በአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ «የአፍሪካ ዋንጫ» በውጭ አገራት ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ ኮከቦች እንጂ በየአገራቸው ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች በአሰልጣኞች ዘንድ ቅድሚያ ተሰቷቸው በብዛት ሲመረጡ አይስተዋልም። በዚህም በአገራቸው ሊጎች የሚጫወቱ ኮከቦች በውጭ ሊጎች በሚጫወቱት ተውጠው የመታየት እድላቸው እንደጠበበ ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህም የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ካፍ በአገራቸው ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የራሳቸው የአፍሪካ ዋንጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ በማመን የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮና(ቻን) የሚባለውን ውድድር እንደ ዋናው የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት አመቱ ማዘጋጀት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል።
በቀጣዩ ጥር በአልጄሪያ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የ2023 የቻን ዋንጫ በአስራ ስድስት አገራት መካከል እንደሚካሄድ ቢታወቅም የተሳታፊ አገራት ቁጥር ወደ አስራ ስምንት ማደጉን የውድድሩ አዘጋጅ አገር አልጄሪያ ሰሞኑን ማስታወቋን የኦል አፍሪካ ዶት ኮም ዘገባ ያመለክታል።
የአልጄሪያ እግር ኳስ ማህበር ከቀናት በፊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሳወቀው በመጪው የቻን ዋንጫ አስራ ስምንት አገራት እንዲሳተፉ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የተሳታፊ አገራትን ቁጥር በሁለት ለማሳደግ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የአልጄሪያ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት አምራ ቻራፍ ኤዲን፣ የካፍ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቻን ውድድር ኮሚሽን ሊቀመንበር ሴይዶ ቦንቦ ኖያ እንዲሁም የካፍ ዋና ጸሐፊ ቬሮን ሞሴንጎ ሰሞኑን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
ውይይቱን ያደረጉት የሥራ ኃላፊዎች የተሳታፊ አገራት ቁጥርን በተመለከተ በካፍ አንቀጽ ሰባ የተቀመጠውን ሕግ በማሻሻል አስራ ስምንት አገራት በአልጄሪያው የ2023 የቻን ዋንጫ እንዲሳተፉ ተደርጓል። በዚህም በውድድሩ አስራ ስምንቱ ተሳታፊ አገራት በአምስት ምድብ ተከፍለው የሚጫወቱ ይሆናል።
አስራ ስምንቱ አገራት በሚሳተፉበት የቻን ውድድር አዲስ ይዘት ከአምስቱ ምድብ በሦስቱ ምድቦች አራት አራት አገራት የሚፋለሙ ሲሆን፣ በሁለቱ ቀሪ ምድቦች ሦስት ሦስት አገራት የሚፋለሙ ይሆናል። ይህንንም የአልጄሪያ እግር ኳስ ማህበር ባለፈው ረቡእ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል። በአዲሱ የውድድር ሕግ አራት አራት አገራት ከሚፋለሙበት የመጀመሪያ ምድብ ሁለት ሁለት አገራት ወደ ሩብ ፍጻሜ ሲያልፉ ሦስት ሦስት አገራት ከሚፋለሙበት ሁለቱ ምድብ አንድ አንድ አገር ብቻ ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላል።
ከቀጣዩ የቻን ዋንጫ ጀምሮ የተሳታፊ አገራት ቁጥር በሁለት በማደጉ የትኛው የአፍሪካ ዞን ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል የተጠቀሰ ነገር የለም። ይሁን እንጂ በአልጄሪያው ውድድር ለመሳተፍ አርባ ሰባት አገራት በተለያዩ ዞኖች ተከፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያካሂዱ ይታወቃል።
በዋናው የአፍሪካ ዋንጫም ይሁን በቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ ደካማው የአፍሪካ ዞን የምሥራቅ አፍሪካ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ዞን በነዚህ ውድድሮች የሚሳተፉ አገራት ቁጥርም ዝቅተኛ ነው። በዚህም ካፍ በቻን ተሳታፊ አገራት ቁጥር መጨመር የምሥራቅ አፍሪካን እግር ኳስ ለማነቃቃት ተጠቃሚ ሊያደርግ ወይም ኮታውን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰጡ ነው።
የውድድሩ ሃሳብ ከአስራ አምስት አመት በፊት በካፍ የተጠነሰሰ ሲሆን እኤአ 2009 ላይ የመጀመሪያው ውድድር በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ሊካሄድ ችሏል። የመጀመሪያው ውድድር በስምንት አገራት መካከል ቢካሄድም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመሳተፍ ፍላጎታቸው በመጨመሩ በሁለተኛው ውድድር በቀጥታ ወደ አስራ ስድስት ሊያድግ ችሏል። ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሞሮኮ ይህን ዋንጫ ሁለት ሁለት ጊዜ በማንሳት ስኬታማ ሆነው የሚጠቀሱ ሲሆን ሊቢያና ቱኒዚያ አንድ አንድ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት በመሆን ታሪክ አላቸው።
በቀጣዩ አመት በአልጄሪያ የሚካሄደው የቻን ዋንጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቀድሞ ሊካሄድ ከነበረበት ጊዜ ተራሞ የሚካሄድ ሲሆን፣ አልጄሪያ ውድድሩን ለማስተናገድ በይፋ ኃላፊነቱን የወሰደችው በ2018 እንደነበር ይታወሳል። ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ ይህን በአፍሪካ ሁለተኛውን ትልቅ የእግር ኳስ ውድድር በአራት የተለያዩ ስቴድየሞቿ ለማስተናገድ ዝግጅቷን ከጀመረች ቆይታለች።
ውድድሩን የሚያስተናግዱት ስቴድየሞችም በመዲናዋ አልጄርስ፣ በኦራን ከተማ የሚገኘው ኦሊምፒክ ስቴድየም፣በአናባ የሚገኘው ቻሂድ እንዲሁም በሃምሎይ የሚገኘው ኮንስታንቲን ስቴድየሞች ውድድሩን ለማስተናገድ ተመርጠዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014