ደስታንም ሆነ ኀዘንን ተካፍሎ መኖር የቆየ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው። በችግር ጊዜ መረዳዳትም ከትውልድ ትውልድ ተሻግሮ የመጣ የኢትዮጵያውያን እሴት ነው። ይህ መረዳዳትና ኀዘንንና ደስታን ተካፍሎ መኖር ታዲያ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ ደረጃ ደርሶ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህንኑ እሴት ተከትለው አረጋውያንን፣ የአእምሮ ህሙማንን፣ የተለያዩ ችግሮች የገጠሟቸው ሴቶችንና ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚረዱ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም በተለያዩ ጊዜያት ተቋቁመው ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ከነዚህ ውስጥም እንደነ ሜቄዶንያ፣ ሙዳይ፣ ጌርጌሲኖንና ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንም በዋቢነት መጠቀስ ይቻላል። እነዚሁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በየጎዳናው የወደቁ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን በማንሳትና በመንከባከብ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ትልቅ ሰብአዊ ድጋፍ ፈፅመዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ለተጋለጡ ሴቶችና ወላጅ አልባ ለሆኑ ሕፃናትም ጥላ ከለላ ሆነዋል። በዚሁ ሰብአዊ ተግባር ሌሎችም እንዲሳተፉም ትልቅ አርያ ሆነዋል።
እምብዛም አልታወቁም እንጂ በየመንደሩና በየሰፈሩ ተመሳሳይ የሰብአዊ ድጋፍና እንክብካቤ የሚያድርጉ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች አልጠፉም። በአዲስ አበባ ከተማም በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች የበጎ አድራጎት ማህበራትን በማቋቋም በአካባቢያቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና አቅመ ደካማ ሰዎችን በተለያዩ መንገዶች በመርዳት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ይህ አርያነት ያለው የወጣቶች ተግባር ታዲያ በተለይ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ በጉልህ ታይቷል። በርካታ ወጣቶችም የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ገቢያቸው አነስተኛ በሆኑ የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅእኖ አስቀድመው በመገመት ከኪሳቸው አውጥተው፣ የአካባቢያቸውን ሰዎች ለምነውና ሌሎች የግል ድርጅቶችን አስቸግረው ዘይት፣ ስኳር፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ስንዴ እና ሌሎችንም የምግብና የፍጆታ ዕቃዎችን አሰባስበው ለግሰዋል።
በዚህ በጎ ተግባር ተሳትፈው የአካባቢያቸውን አቅመ ደካማና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎችን ከረዱና አሁንም እርዳታ እያደረጉ ካሉ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል አንዱ ‹‹የላምበረት ልጆች ለላምበረት ነዋሪዎች›› በሚል መርህ የተመሠረተው የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።
አቶ ደጉ መኮንን የላምበረትና አካባቢው «ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት» ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። እርሱ እንደሚለው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከመመስረቱ በፊት የላምበረትና አካባቢው ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አረጋውያን ይረዱ ነበር።
ይሁንና በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም የኮሮና (ኮቪድ- 19) ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ በተከሰተ ወቅት የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት በሚል ሕጋዊ ሰውነት ይዞ በሰባ አባላት ተመስርቷል። ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋነኛ አላማም በተለያዩ ምክንያቶች ታመው አልጋ ላይ የቀሩ፣ አቅመ ደካሞችንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የላምበረትና አካባቢውን ሰዎች ለመርዳት ነበር።
ድርጅቱ እንደተመሠረተም በላምበረትና አካባቢው የሚኖሩና በውጭ ኑሯቸውን ያደረጉ የላምበረት ተወላጆች ጋር በመተባበር በአካባቢው ላይ ረጅም ጊዜ የኖሩ፣ ተጠግተው የሚኖሩና አቅመደካማ የሆኑ ሰዎችን በገንዘብና በቁሳቁስ መርዳት ጀመረ። በተለይ ደግሞ ወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተበት ጊዜ እንደመሆኑ ድርጅቱ አባላቱ ገንዘብ እንዲያዋጡ በማድረግና በውጭ አገራት ያሉትም ገንዘብ እንዲልኩ በማድረግ አቅመ ደካማ ለሆኑና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ አድርጓል።
ድርጅቱ በወቅቱ ያደረገው ድጋፍም በአብዛኛው የምግብና የቁሳቁስ ነበር። ከእነዚህ ውስጥም ምግብ ነክ የሆኑት እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዱቄትና የመሳሰሉት ይገኙበታል። ምግብ ነክ ካልሆኑት ውስጥ ደግሞ እንደ ሳሙና፣ ሶፍትና የመሳሰሉትን ለተረጂዎች አበርክቷል።
ሥራ አስኪያጁ እንደሚለው የኮሮና ወረርሽኝ ወደ አገሪቱ እንደገባ የድርጅቱ አባላት ከአምስት እስከ አስር ሺህ ብር በመዋጣት እርዳታ ጀምሯል። ይሁንና የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የመጀመሪያውን እርዳታ ከጨረሰ በኋላ እርዳታው ዘላቂ እንዲሆንና ሁልጊዜ መዋጮ እንዲኖረው በሚል በውጭ የሚኖሩ የላምበረት ተወላጆች በየስድስት ወሩ ስድስት ሺህ ብር እንዲያዋጡ ወስኖ በዚህ መልኩ መዋጮው እየተሰበሰበ ይገኛል። በተመሳሳይ እዚሁ ላምበረት የሚኖሩ የድርጅቱ አባላት ደግሞ ከሃምሳ ብር ጀምሮ እንደየአቅማቸው ለድርጅቱ በየወሩ መዋጮ ያደርጋሉ።
የበጎ አድራጎት ሥራው በድርጅቱ በኩል ሲጀመር በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ አባላት ከ300ሺህ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን በዚሁ ገንዘብ ምግብ ነክ የሆኑና ያልሆኑ ቁሶችን በመግዛት 300 የሚሆኑ የላምበርትና አካባቢው አቅመ ደካማና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን መርዳት ተችሏል።
የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ የበጎ አድራጎት ድርጅት በአሁኑ ጊዜ አባላቱ የየራሳቸውን ሥራ በግላቸው ያከናውናሉ። ሆኖም በዚህ ድርጅት አማካኝነት የአካባቢው ወጣት አንድ ሆኖ ወርሃዊ መዋጮ በማድረግ አቅመ ደካማና በኑሮ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎችን ይረዳል። ድርጅቱ ለነዚህ ሰዎች ርዳታ የሚያደርገውም በአብዛኛው አመት በዓልን አስታኮ ነው። ባለፈው የፋሲካና የኢድ በአላት ወቅትም ድጋፍ አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አመት ሲመጣ በገቢ ዝቀተኛ ቤተሰብ ላላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ይረዳል።
የድርጅቱ አባላት በአሁኑ ጊዜ ሰባ የሚጠጉ ሲሆን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖሩት የሚጠበቅባቸውን የአባላት መዋጮ እንደየአቅማቸው በየስድስት ወሩና በየወሩ ያዋጣሉ። ከእነዚሁ አባላት የሚሰበሰበው መዋጮም ለአካባቢው አቅመ ደካማና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉ ነዋሪዎች እርዳታ ይውላል።
ቅድሚያ የሚረዱትም ታመው አልጋ ላይ የዋሉ፣ በህመም ምክንያት መንቀሳቀስና ሥራ መሥራት የማይችሉ፣ አቅመ ደካሞችና ገቢ የሌላቸው አረጋውያን ናቸው። እርዳታው የሚሰጠውም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ከአራራት ሆቴል እስከ እስራኤል ኤምባሲ ባለው አካባቢ ለሚኖሩ ተረጂዎች ነው።
ከተቋቋመ ሦስት አመታትን ሊደፍን የተቃረበው የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ ድርጅት የራሱ መሰብሰቢያ ቦታና ቢሮ እንደሌለው የሚናገረው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፤ የድርጅቱ አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ መገናኛ አካባቢ ያለውን ቢሯቸውን በበጎ ፍቃደኝነት ሰጥተውት እየተገለገለበት እንደሚገኝ ይገልፃል። ድርጅቱ የቢሮ ችግሩ ቢቀረፍለት ለዚህም ደግሞ ወረዳው ድጋፍ ቢያደርግለት ከዚህም በላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማል። ይህንኑ ችግሩን ለወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር በተደጋጋሚ አሳውቆ እንደነበርና ነገር ግን እስካሁን ድረስ በቂ ምላሽ እንዳላገኘም ይጠቅሳል።
‹‹እንደ በጎ አድርጎት ድርጅት እዚህ ደርሰናል፤ ነገ ደግሞ ድርጅቱ አድጎ የተሻለ ነገር እንዲሠራ በተለይ የየካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር ከድርጅቱ ጎን ነውና ወደ ፊትም ድርጅቱ ለሚያስፈልገው ድጋፍ ሁሉ ከጎኑ እንደሚሆን አልጠራጠርም›› ይላል ሥራ አስኪያጁ አቶ ደጉ መኮንን። ድርጅቱ ያሉበት ችግሮች ቢቀረፉ እኛም ትልቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ ሲልም ስሜቱን ይገልፃል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ወዲህ የአካባቢውን አቅመ ደካማና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች እየረዳ የሚገኘው የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት በቀጣይ እርዳታውን በስፋት ማዳረስ እንደሚፈልግ ሥራ አስኪያጁ ይገልፃል። የተረጂዎችን ቁጥር በማሳደግ የሚያደርገውን እርዳታ መጠንና ዓይነት የመጨመር ሃሳብ እንዳለውም ይናገራል።
ከእርዳታው ባሻገር ድርጅቱ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በአካባቢው ላይ በመገንባት ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ የማድረግ አላማን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ያስረዳል። ከዚህ አኳያ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን መጀመሩንም ሥራ አስኪያጁ ይጠቅሳል።
የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት እየፈፀመ ያለው በጎ ተግባር በአርያነት የሚጠቀስ ነው። በተለይ ወጣቶች ከዚህ ትልቅ ትምህርት ወስደው በአካባቢያቸው የሚገኙ አቅመ ደካሞችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ለመርዳት እንደሚነሳሱ ይጠበቃል።
አቶ ደጉ መኮንንም ወጣቱ ልስራ ካለ ጉልበቱም፣ እውቀቱም ሆነ ገንዘቡም እጁ ላይ ያለ በመሆኑ ነገ ዛሬ ሳይል ባለው አቅም ሁሉ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት እንደማይቸገር ይገልፃል። ሁሉም ወጣት በየአካባቢው እንዲህ ዓይነቱን በጎ ተግባር ቢፈፅም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባይቀርፍ እንኳን ችግሩን ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችልም ይናገራል።
እንዲህ ዓይነቱን በጎ ተግባር የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት የጀመረው ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ተሞክሮ በመውሰድ መሆኑንም ገልፆ፤ በተመሳሳይ የሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎችም ከ’ኛም ሆነ ከሌሎች ተሞክሮውን ወስደው ሰዎችን ይርዱ ይላል። ይህን ማድረግ ከቻሉ የአእምሮ እርካታ ከማግኘት በዘለለ ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ስሜትም እንደሚሰማቸው ይገልፃል።
እኛም የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት ‹‹የላምበረት ልጆች ለላምበረት ነዋሪዎች›› በሚል እያከናወኑ ያሉትን በጎ ተግባር እያደነቅን በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎችም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች ከዚህ ተግባር በመማር ተመሳሳይ አርያነት ያለው በጎ ተግባር እንደሚፈፅሙ እናምናለን። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014