የፌዴራል ፖሊስ በመላ ሀገሪቱ እየተንቀሳቀሰ የሀገሪቱን ሰላምና ድህንነት በማስከበር ላይ ይገኛል:: በአሁኑ ወቅትም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ዘርፈ ብዙ ተልዕኮዎችን በመወጣት ላይ ነው:: ኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በዕውቀት እና በክህሎት የበቃ ሰራዊትና ተልዕኮውን በአግባቡ የሚወጣ የፖሊስ አመራር ለማሟላት የተመሰረተ ተቋም ነው:: ዩኒቨርሲቲው የፖሊስ አባላትን ብቃት በመገንባትና የዘርፉ ተመራማሪዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል::
በዛሬው ዕትማችንም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከሆኑት መስፍን አበበ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮችና ዩኒቨርሲቲውን አስመልክቶ ቆይታ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ ሪፎርምሥራ በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ኮሚሽነር መስፍን፡- የሪፎርም ሥራው ቀደም ሲል በፊት የነበሩ ክፍተቶችን በደንብ በመዘነ መንገድ በጥናት የነበሩብንን ክፍተቶች እንደ ፖሊስ ለህዝብ ከምንሰጠው ተልዕኮና በህግ ከተቋቋምንበት ዓላማ አኳያ የነበሩብን ክፍተቶች በመለየት በሰው ሃይል ልማት፣ በግብዓት፣ አደረጃጀት፣ አሰራር፣ መዋቅር፣ ተልዕኮ አፈፃፀምና በሌሎችም የነበሩ ጉድለቶችን መለየትና፤ የተለዩትን ደግሞ የሚሞሉበትን ስትራቴጂ በመንደፍ ሥራዎችን መሥራት ነው:: ከዚህ አኳያ ሰፋፊ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በክፍተቶች ላይ ደግሞ በጥናት ተለይተው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል::
በዋናነት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በመምራት፣ ሰራዊቱ ውስጥ ያሉ ትልልቅ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ጥናቶችም ተደርገዋል፤ በዚህም መሪ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል:: የአስር አመት ዕቅድ እና መሪ ስታንዳርድ ማሻሻል የሚችል ሰነድ ተዘጋጅቷል:: ቀደም ሲል የፖሊስ ዶክትሪን አልነበረንም:: የተለያዩ ነገሮችም በተቆራረጠ መንገድ እንጂ እንደአሁኑ በመርህ ላይ የተመሰረተ አልነበረም::
ማንም ሰው ስለፖሊስ ሲያስብ ሊሆን እና ሊከተለው የሚገባው ዶክትሪን ያልነበረ ሲሆን፤ ሪፎርሙ በአባላት ጭምር በሚገባ ተገምግሞ፣ እንዲተች ከተደረገ በኋላ በሌሎች ባለድርሻ አካላት በደንብ እንዲገመገም ተደርጓል:: የክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች፣ ፖሊስና ፀጥታ ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት እንዲመለከቱት ተደርጎ እና የፖሊስ እውቀት ያላቸው አካላት ተችተውት ብሎም ለመንግስት ቀርቦ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስተሩ ጭምር የራሳቸውን መልዕክት አስተላልፈው የመጨረሻው የማጽደቅ ስራ ተሰርቷል::
ከዚህም ባሻገር ለሰራዊቱ እስከ ታች ወርዶ በዶክትሪኑ መሰረት ሠራዊቱ ራሱን እንዲቃኝ፣ ራሱን እንዲገነባ፣ በእያንዳንዱ ተልዕኮ አፈፃፀም መርህ ተከትሎ እንዲሰራ የማድረግ ጅማሮ ነበር:: ከዚህ ቀጥሎ በመዋቅር ስራው ከአዲሱ የፖሊስ ተልዕኮ ጋር በሚጣጣም መንገድ ተሰርቷል:: ባለፈው ሥርዓት የነበረውን ክፍተት በመለየት ለመጪው ዘመን ጭምር የሚጠቅም ጠንካራ የፖሊስ መወቅር እና በሁሉም ቦታ ተደራሽ የሆነ የፖሊስ አገልግሎት በሚገባ እንዲኖር በወንጀል መከላከል ሥራ፣ በምርምራ ሂደት፣ በሀገር ደህንነት ጥበቃ፣ በህዝብ አገልግሎት፣ በህግ ማስከበርና ሌሎች ተልዕኮዎች ላይ የሚፈለገውን ሥራ በሚፈለገው ወቅት ደርሰን ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሯል:: የተለያየ ባህሪ ያላቸው ተልዕኮዎች የተለያየ አደረጃጀት ይፈልጋሉ:: ለዚህ ያግዛል ብለን ባሰብነው አግባብ መዋቅራችንን አስተካክለናል፤ ወደ ስራም ገብተናል:: በየደረጃው አስፈላጊው አመራር እና ባለሙያም ተመድቧል:: የተቀሩ ሥራዎችን እያጠናቀቅን ነው:: አደረጃጀቶችን ካጠናቀቅን በኋላ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሰራዊት በማሟትና በመመደብ ለተልዕኮ የሚመጥኑ ስራዎችም ጎን ለጎን እየተሰሩ ነው::
ተቋማዊ የሆነ አሰራር እና የማደራጀት ሰፊ ስራ ተሰርቷል:: ከዚህ ጎን ለጎን ለፖሊሳዊ ስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከዩኒፎርም ጀምሮ ለተልዕኮ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ግብዓቶችን አሟልተናል:: ስፔሻላይዝድ የሆኑ ትጥቆችን አሟልተናል:: በርግጥ ሰፊ ጉድለት ነበረብን:: በተለይ በዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለይተን ጥናትም አድርገን በመንግሥትም ተቀባይነት አግኝቶ አስፈላጊ ግብዓቶችን የማስገባት ሥራ ተሰርቷል::
በመሆኑም መጪው ዘመን በተለመደው ተለምዷዊ አሰራር አገልግሎት መስጠት አይቻልም:: ቴክኖሎጂ፣ ዕድገት፣ ተግባቦት አዳዲስ የሆኑ ሂደቶች እየሆኑ ነው:: ለፖሊስ ይህን ለመከላከል አቅም እየተፈጠረ ነው:: ስለዚህ ቴክኖሎጂን በሚገባ መጠቀምና መታጠቅ የሚያስችል ጥናት አድርገን በቴክኖሎጂም የማጠናከር ሥራ ሰርተናል:: በሀገሪቱ ማናቸውም ሥፍራ ላይ የሚከናወን ሁነትን በፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግና አጠቃላይ ሁነቱን በቴክኖሎጂ ከማዕከል ሆኖ መከታተልና ማናቸውንም አደጋዎች መቀልበስ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል:: ጥሩ ውጤቶችም አይተናል:: ለአብነት የአፍሪካ ህብረትን ስብሰባ ማንሳት ይቻላል:: ያለ አንዳች ችግር ከላይ አመራር እስከ ታች ያለው ባለሙያ በመናበብ በሰላማዊ መንገድ የተከናወነ ነው:: ይህ የሪፎርሙ አንዱ አካል ነው:: ግብዓት እና ዘመኑ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ እያሟላን ነው:: በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በኩልም ብዙ ስራዎች በጥናትና በስልጠና እየታገዙ በስፋት እየተሰሩ ነው::
በሀገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ትልልቅ ተቋማት፣ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች የሚበራከቱባቸው ስፍራዎች፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችና መሰረተ ልማቶችንም በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥበቃ እየተደረገ ሲሆን በቀጣይም የበለጠ ለማጠናከር አስፈላጊው ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው:: በቀጣይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመታጠቅ ሂደቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል::
አዲስ ዘመን፡- ከሪፎርሙ በኋላ በተለየ ሁኔታ ለአብነት የሚነሳ ለውጥ ታይቷል ማለት ይቻላል?
ኮሚሽነር መስፍን፡- በጣም አሉ:: በጣም የሚታወቁና ግልፅ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ:: ግን ዋና ተልዕኳችንን ማዕከል አድርገን ስንመለከት የወንጀል መከላከልና የህዝብ ድህነትን ማስከበር ስራዎቻችን በብዛት ኃይልን የበለጠ በመጠቀምና ተለምዷዊ በሆነ አሰራር የሚከናወኑ ነበሩ:: በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይም ጉዳቶች የሚስተናገዱበት ነበር:: በፖሊስም ሰፋፊ ስህተቶች የሚሰሩበት ነበር:: በዚህም በህዝብና መንግሥት ዘንድ ቅሬታዎች ነበሩ:: በአሁኑ ወቅት ግን በትልልቅ ክስተቶችም ጭምር ፖሊስ በሚሰራው ሥራ ለውጦች አሉ:: በቴክኖሎጂ በመታገዝም ብዙ አካባቢዎችንም በመሸፈንና በማየት ያለችግር ትልልቅ ፕሮግራሞችን በሠላማዊ መንገድ ማከናወን ተችሏል::
ለአብነት ማንሳት ቢያስፈልግ በዚህ ዓመት የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ውጥረት በተሞላበትና በሀገሪቱ ላይ ጫና በበረታበት ሁኔታ ነበር:: ነገር ግን ህዝቡም ዘንድ ብዙ ቅሬታ ሳይኖር ከእያንዳንዱ አባል ጋር በመናበብ ብሎም በቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ ውጤታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል:: በቅርቡ የዒድ በዓል ሲከበር የተፈጠረው ክስተት ወደ ከፋ ደረጃ ሳይሸጋገር ወደ መደበኛው ሁኔታ መመለስ ተችሏል:: ከተወሰነ የንብረት ጉዳት ውጪ ከመስመር ሊወጣ የነበረን ሁኔታ በቀላሉ መቆጣጠር ተችሏል:: ሁኔታዎችን በቴክኖሎጂ በመከታተልም የከፋ ጉዳት ሳይደርስ አደጋን መከላከል ተችሏል:: ይህ ሁሉ ለውጥ የመጣው በፖሊስ ላይ በሠራነው የሥነ ባህሪ እና ሪፎርም ሥራ ነው:: በተለያዩ ቦታዎች ላይ የህዝብን ሠላም ለመንሳትና ሀገር ለማሸበር ሲወጠን የነበረ የሽብር እንቅስቃሴ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከክልል ፖሊሶችና የፀጥታ መዋቅር ጋር በመሆን ሥምሪት ወስዶ ትልልቅ መሥዕዋት እየከፈለ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል::
ከዚህ አኳያ የአደረጃጀት፣ የትጥቅ እና የውግያ አቅማችን የመከላከል ብሎም የሽብር ኃይላትን የመከላከልና ማጥቃት አቅማችን በጣም ጎልብቷል:: ወንጀል ፈፃሚዎችን በፍጥነት፣ ማሰስ፣ ማግኘትና የምርመራ ሥራዎችንም በተቀላጠፈ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን የወንጀል ምርመራ ሥራችን በጣም ጨምሯል::
በተለይም በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ የወንጀል ምርመራ ስራችን በጣም ተሻሽሏል፤ አስተማማኝ ምርመራም እየተደረገ ነው:: የምርመራ ክህሎትን ለማሳደግ ብሎም እያንዳንዱ ምርመራ ጣቢያዎቻችንም በካሜራ ዕይታ የተቃኙ ናቸው:: የምርመራ ሂደቶችንም መሪዎችና አመራሮች የሚያውቁበት ሂደት አለ:: ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጥሯል ተብሎ ከታሰበም እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ለመሄድ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል:: መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ መርሐ ግብሮችም ላይ ፖሊስ የመሪነት ሚና እየተወጣ ነው:: በቅርቡ ሐዋሳ ላይ የተከበረውን ጨምበላላ በዓል በሚገባ ለማክበር ፖሊስ ትልቅ ሚና ነበረው:: ይህ የሚያሳየው ፖሊስ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በአግባቡ ሥራውን በቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ እየተወጣ መሆኑን ነው::
የአቅም ግንባታ ስራዎችም ከዚሁ ጋር ተቃኝተው የሚሄዱ ናቸው:: ዩኒቨርሲቲያችን ሁሉንም የፖሊስ ትምህርት፣ ስልጠና፣ ጥናት ምርምርና ማማከር ሥራዎችን በሙሉ እንዲመራ በአዲሱ አደረጃጀት ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ከዚህ አኳያ ትልልቅ ስልጠናዎችን በስፋት መስራት ጀምረናል:: ችግሮችን በጥናት የመለየት በለየነው መንገድ ደግሞ ሥራዎች እንዲሰሩ የማድረግ፣ በሚሰሩት ሥራዎች ደግሞ በደንብ ተጨብጠው ወደ ውጤት እንዲመጡ ሥራ እየተከናወነ ነው:: ከዚህ አኳያ ዩኒቨርሲቲውን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ነው:: ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ አድጓል:: እንደ ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የትምህርትና ስልጠናና ሌሎች ፕሮግራሞችን ለማከናወን የሚያስችል ብቃት ላይ እንዲደርስ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራን ነው::
አዳዲስ ተቋማትን ጭምርም መገንባት ጀምረናል:: በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ትልልቅ ትምህርት ቤቶችና ተቋማት ይገነባሉ:: የምርምር ማሰልጠኛ አልነበሩንም:: የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተቋማት ውስጥ ነው የምናሰለጥነው:: በአሁኑ ወቅት ግን የራሳችን ምርምር ማሰልጠኛ ለመገንባት በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ቦታ ተሰጥቶናል:: ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ዋና ዋና ግንባታዎችን እንጀምራለን:: ምናልባትም በአንድ ጊዜ 10ሺ ምልምል አባላትን ለማሰልጠን የሚያግዝ እንዲሆን አስበን ዲዛይኑን አጠናቀናል:: ግንባታው ተከታታይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችንም ለመስጠት ያስችለናል::
አዲስ ዘመን፡- ፖሊስ በሕወሓት የበላይነት ሲመራ በነበረበት ወቅት የነበሩ በርካታ አመራሮችና ባለሙያዎች ከድተው ወደ ትግራይ መሄዳቸው ይነገራል:: እነዚህን ለማሟላት ምን ተሰርቷል?
ኮሚሽነር መስፍን፡- በርግጥ ችግሮች ነበሩ:: በሪፎርሙ አንዱ የሰራነው ነገር ቢኖር በለውጡ ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ክፍተቶችን ትልቅ ጉዳት ሳያስከትሉ ቶሎ መሙላት ነው:: እነዚህን ክፍተቶች በሽግግር እንዴት ይሞላል፤ በዘላቂነትስ እንዴት መሞላት አለበት በሚል ስትራቴጂካዊ እሳቤ ውስጥ በማስገባት መስራት ነበረብን:: መሰል ችግር እንዳያጋጥምስ ምን መሰራት አለበት በሚለው ላይ በማተኮር ሲሠራ ነበር:: በዚህም የሀገርና ህዝብን ደህንነት የሚጠብቅ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል በሰፊው ተሰርቷል::
አንደኛው ሰራዊትን በሰፊው ማሰልጠን ነው:: ሁለተኛው በየደረጃው ያለውን ባለሙያም አመራርም የሚገባውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ለተመደበለት ቦታ እና ግዳጅ ብቁ እንዲሆን ማድረግ ነው:: ጉድለቶች የሚሞሉበትን አሰራርና ሥርዓት መከተል ነው:: ከዚህ አኳያ በመዋቅር ያሉብንን ክፍተቶች በደንብ በመለየት እነዚህን መሙላት የሚያስችሉ የአጭር እና መካከለኛ ጊዜ ሥርዓት ነድፈን የሰው ኃይላችን በማብቃት እየሞላን የመሄድ ሥራ አከናውነናል፤ ክፍተቱም እንዲሞላ ሆኗል:: ቀደም ሲል እንደነበረውና ወደ አንድ አካባቢ ያደላውን በማስተካከል የፌዴራል ፖሊስ ሀገሪቱንና ህዝቡን መስሎ አደረጃጀቱና አሰራሩ እንዲስተካከል ሰዎች በብቃት ብቻ የሚመሩበት ስርዓት እንዲኖር ተደርጓል:: በተግባር እየተማሩ እየሄዱ ክፍተቶችን ማስተካከል ተችሏል:: ክፍተቶች ባሉበት ቦታ ደግሞ በጋራ እንዲሰራ በማድረግ የላቀ ሥራ ማከናወን ተችሏል::
ከምንም በላይ ግን ሰፊውን የሰራዊታችን አባላት ሀገሪቱን መስሎ እንዲበቃ ለማድረግ ትልቅ የሰው ኃይል እያሰለጠንን ነው:: በሁለት ዓመት ብቻ ትልቅ ቁጥር አስገብተን አሰልጥነናል:: እጅግ በብዙ እጥፍ ከፍተኛ ኃይል አለን:: ክፍተቱን በመሙላት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ቀጣይ ዓመታትን አስበን ሰርተናል:: የቀጣይ 10 ዓመታት እቅድ አውጥተን በፅናት እየሰራን እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች በስፋት እየተስተዋሉ ሲሆን ይህ ደግሞ ነገሮችን ቀደሞ በመከላከል ረገድ የፌዴራል ፖሊስ ቸልተኛ ስለሆነ ነው በሚል ይተቻል:: እርስዎ በዚህ ሃሳብ ላይ ምን ይላሉ?
ኮሚሽነር መስፍን፡- የዓለምንም ሆነ የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ ስናይ ሽግግር የተወሰኑ ክፍሎችን ይነካል፤ ጥያቄዎችን ያጎላል:: ስለዚህ ጥቅም የተነካበትና ጥያቄ ያላቸው በሰላማዊ መንገድ ከመሄድ ይልቅ በኃይል ፍላጎት ለማሳካት የመፈለግ ዝንባሌ አለ:: ከዚህ ጀርባ ደግሞ የሀገርን ሰላም የማይፈልጉ የሀገርን ጸጥታ ለማደፍረስ ይሯሯጣሉ፤ይህን እንገነዘባለን::
የጂኦ ፖለቲክሱ ሁኔታም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት:: እኛ ግጭቶች ባሉበት እንደርሳለን:: ከግጭቶች ስፋት አኳያ ግን ቅሬታ ሊኖር ይችላል:: ሌላው የማህበራዊ ሚዲያም ነገሮችን ስለሚያገነው ቅሬታዎችን የሚያነሳ የህብረተሰብ ክፍል ሊኖር ይችላል:: አንዳንድ ቦታዎችን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ላንደርስ እንችላለን:: ነገር ግን ማንኛውም በሀገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን መከላከል የክልልና የፌዴራል ፖሊስ አጋዥ አካላት ሥራ ነው::
አንዳንዶቹም ደግሞ የተዛቡ መረጃ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ቅሬታዎች መኖራቸውም የሚጠበቅ ነው:: ግን ሰራዊታችን ያለ ዕረፍት ወራትን እየሰራ ነው:: ራሱንም ለከፍተኛ መሥዕዋት ዳርጎ እየሰራ ያለው በዚህ የሽግግር ዘመን ነው:: በሀገር ላይ የተደቀኑ በርካታ አደጋዎችን መቀልበስ ተችሏል:: ቀድሞ እንደነበረው የህዝብ ግጭቶች በብዛት የሉም:: ሆን ተብሎ ተልዕኮ የተቀበሉ በተለይም ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድንና ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ግብጽ ብሎም የኢትዮጵያን ሠላም የማይፈልጉ አካላት የሚደገፉና ስልጠና ወስደው ተደራጅተው የሚታዩና ችግር የሚፈጥሩ አሉ:: ይህም ሆኖ ጉዳቱን መቀነስ የሚያስችል ሥራ ተሰርቷል:: ግን አልፎ አልፎም ቢሆን ችግሮች ይስተዋላሉ፡
አዲስ ዘመን፡- ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል እንኳን መንቀሳቀስ ከባድ እየሆነ ባለበት ሁኔታ ፖሊስ ያለዕረፍት እየሰራ ነው የሚለው ሐሳብ እርስ በእርሱ አይጋጭም?
ኮሚሽነር መስፍን፡- አይጋጭም:: ሽግግር ከሚፈጥረው ሁኔታ አንዱ ነው:: ሁለተኛው የሀገራችን ፖለቲካ ሁኔታ የፈጠራቸው የሽብር ኃይላት አሉ:: ትልልቅ አቅም፣ ኔትወርክና ከጀርባ ድጋፍ ያላቸው ናቸው:: እነዚህ አካላት የፈጠሯቸው ችግሮች አሉ:: ይህ የፖሊስን ሥራ ጨምሮታል:: በተረፈ ግን ትልቅ መስዕዋት እየከፈለ እና ያለእረፍት እየሰራ ነው:: ሀገሪቱ ጦርነት ላይ ነበረች:: ፌደራል ፖሊስም የዚሁ አካል ሆኖ ሲመክት ነበር:: ኢትዮጵያን ለመበተን ከውጭ ኃይል ጭምር ዝግጅት ተደርጎ ሲሰራበት የቆየ ሲሆን ይህን ለመመከት በጣም በጥንቃቄና ትጋት ሲሠራ ነበር:: በዚያው ልክ ደግሞ ከውስጥ ሆነው ሀገሪቱን ለማፍረስ እና አደጋ ለመጣል የሚለፉ ኃይሎች ነበሩ:: ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትልልቅ ልማት ፕሮጀክቶችንና መከላከልና መጠበቅ ተችሏል:: ለዚህም ትልቅ መስዋዕት ተከፍሏል:: በዚህ የለውጥ ዘመን የተከፈለው መስዋዕት ከዚህ በፊት ከተከፈለው የበለጠ ነው::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥት ሸኔ ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የህብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ ምን እየተሰራ ነው?
ኮሚሽነር መስፍን፡- በአንድ ወቅት ችግሩ ገኖ ነበር:: አሁን ግን ሸኔም ሆነ ሌላው አሸባሪ ቡድን ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ የተፅዕኖ ቀጣናቸው ቀንሷል:: በቅርቡ የሚወሰደው እርምጃ ነገሮችን ያስተካክላል:: ህዝብ ወደ ልማት እየተመለሰ ነው:: በሚወሰደው እርምጃ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ ነው:: ቤኒሻንጉል እና ወለጋ አራቱም ዞኖች፤ ጉጂ ዞን ጥሩ ስራዎች እየተሰሩ ነው:: ባለማወቅ ከጠላት ጋር የተሰለፉት በምክር ወደቤታቸውና ማህበረሰቡ እንዲመለሱ እየተደረገ ነው:: በመሆኑም ጥሩ ለውጦች አሉ::
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የግጭቶችን ነባራዊ ሁኔታ የማወቅ እና ሁኔታዎችን መተንበይ አቅምስ ምን ላይ ደርሷል?
ኮሚሽነር መስፍን፡- እኔ ቀደም ሲል የክልል አስተዳደርና ፀጥታ የግጭት መከላከል ሥራ ላይ ነበርኩ:: ከኦሮሚያ የሚዋሰኑ ሁሉም ክልሎች ግጭቶችን እንዴት እንደምንፈታ እና ቀድሞ ማወቅና ግጭትን ለመከላከል ቅድመ ስራዎችን በሚገባ ስንሰራ ነበር:: አሁን ላይ የሚታዩት ግጭቶች በባህሪያቸው ለየት ያሉ ናቸው:: አሁን ላይ የሚበዛው ችግር በህዝቦች መካከል ሳይሆን በታሪካዊ ጠላቶቻችን፣ በሀገር አፍራሽ አካላት፣ እንዲሁም በለውጡ ምክንያት ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት በህቡዕ የመፈፀም ጥፋት ነው:: ሀገርን አፍነው ይዘው ለተወሰነ ቡድን ጥቅም ሲሰሩ የነበሩ እንደ ሕወሓት ዓይነት የጥፋት ሃይሎች የሚተበትቡት ወንጀልና ተንኮል ብሎም የሚያሰማሯቸው ሸኔ በመሰለ ሃይል የሚፈፀም ጥፋት ነው::
ጥፋቱን በግልጽ እያየን ነው:: የህዝብን ሃብት ማቃጠል፤ መቀማት፣ ማገት እና ተራ የወንጀል ስራ እየሰሩ ነው:: በአሁኑ ወቅት እኛ የምንከተለው ይህን ለመከላከል የሚደረግ ልዩ ስምሪት አለን:: ይህም ቢሆን ህዝብ ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን ጉዳቶችን ከወዲሁ በማወቅ መከላከል የሚያስችል አቅምና እነዚህን የሽብር ኃይላትን ማጥፋትና ምቹ ሁኔታን እንዳያገኙ ማድረግ ላይ እየተሰራ ነው:: እነዚህ ሥራዎች ሲሰሩ ግን ጉዳት አላደረሱም ማለት አይደለም:: ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ምንም የማያውቁ ሠላማዊ ዜጎችን መጉዳትና ማገት አልፎ አልፎ ይሰማል::
አዲስ ዘመን፡- የጥፋት ኃይሎች የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት መንግሥትን ከመገዳደር ይልቅ ለምን ሠላማዊ ዜጎችን መጉዳት ላይ ያነጣጥራሉ?
ኮሚሽነር መስፍን፡- የሽብር ኃይላት ህዝብን ማሸበር ነው ስራቸው:: ንፁሃንን ዒላማ የሚያደርጉበት ዋንኛ ዓላማው መንግስት የህዝብን ሠላም መጠበቅ አልቻለም የሚል ፕሮፓጋንዳ ለማስፋፋት ነው:: ሌላው አሸባሪዎች የህዝብ ሰላምና ደህንነት ደንታ አይሰጣቸውም:: ስለዚህ ማንም ምንም ቢያጠፋ እንደመንግሥት ኃላፊነት አይጣልባቸውም:: እነርሱ የሚፈልጉት መንግሥትን ማሳጣት፣ ብሎም እዚህም አለን ለማለት፣ ለመዝረፍና ለማሸበር ህዝቡን ለማንገላታትና የሚፈልጉትን ለመውሰድ የሚጠቀሙት ዘዴ ነው:: በጥላቻ የሚወስዱት ዕርምጃ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ፌዴራል ፖሊስ በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ይሰራል:: የክልል ልዩ ኃይሎችም በጣም እየተደራጁና ዘመናዊ ትጥቅም እየታጠቁ ነው:: በተልዕኮ ላይ የጎራ መደበላለቅ አይፈጠርም?
ኮሚሽነር መስፍን፡- ይህ የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው:: ኢትዮጵያ ፌዴራል አስተዳደር ስርዓት ስትከተል ክልሎች የተገለፁበት መንገድ አለ:: ክልሎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን በጋራ ለመተዳደር በህግ መንግሥት ወስነዋል:: በፌዴራል እና ክልሎች መካከል ሽኩቻ ቢኖርም እርስ በእርስ ጠላቶች አይደሉም:: አንዱ ለሌላው ሥጋት አይሆንም:: ግጭት ሊኖር ይችላል፤ ግን ወደ ጦርነት የሚወስድ ዕድል የለም:: የክልል ፀጥታ አካላትና ፌዴራል ፖሊስ የየራሳቸው ተልዕኮ አላቸው፤ በጋራም የሚሰሩትም አለ:: ከእነዚህ አካላት ጋር የጋራ መድረክ አለን::
የፌዴራል ፖሊስም የራሱ መስፈርት አለው:: በጋራ በሚሠራው ላይ በጋራ ይፀድቃል:: የፌዴራልም ሆነ የክልል ፖሊስ ያው ፖሊስ ፖሊስ ነው:: የሚለየው የተልዕኮ ቦታ ስፋት ብቻ ነው:: አንዱ በአንዱ ላይ በጠላትነት የሚሰልፍበትና መገዳደር አይኖርም:: እስካሁን የነበረው በሰላማዊ መንገድ ነው:: ለየት የሚለው የትግራይ ክልል ነው:: ክልሉንም ህዝቡንም እንደ ቀብድ አስይዞ ወደ ግጭት የገባባት ሂደት የተለየ ነው:: ሆኖም እርሱም በተገቢው መንገድ ምላሽ የተሰጠው ነው::
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል የፈፀመውን ክህደት ሌሎች ክልሎች እንዳይደግሙት ምን እየተሠራ ነው?
ኮሚሽነር መስፍን፡- በጋራ የምንሠራበት የጋራ መድረክ አለ:: የጋራ ሰነዶች አሉን:: በሰነድ ላይ የተቀመጠውን ነው የምንተገብረው:: የሰሜኑን ጦርነት ለመመከት ህዝባዊ መነሳሳትና ለአሰራር አመቺ እንዲሆን የተፈጠረ ስምሪት አለ:: ይህ የተፈጠረውን ነገር ለመከላከል የቆየ ልምዳችንን ተጠቅመን የፈጠርነው የህዝብ ንቅናቄ ነው:: ይህ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ እንጂ በተለመደው መንገድ ይቀጥላል የሚል አይደለም:: ይልቁንም መንግሥትን የሚገዳደር ኃይል መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ከትግራይ ልዩ ኃይል እንዲማሩ ነው ያደረገው::
በሌሎች ጉዳት ላይ የሚፈጠር ጥቅም መጨረሻው አደገኛ መሆኑን ለማወቅ ይረዳል:: ሆኖም ሥጋት የለም ተብሎ መቀመጥ የለም:: የጦር መሳሪያ አያያዝ ሥርዓት መኖር አለበት:: በህገወጥ መንገድ ምክንያት እዚህ ሀገር ላይ የተበተነው የጦር መሳሪያ ምናልባትም ለመቆጣጠር የሚያሰጋ ጭምር ነው:: ስለዚህ ይህን ሥርዓት ማስያዝ ይፈልጋል:: ቀጣይ በስፋት የሚሰራ ይሆናል:: የፀጥታ አካላትና ህዝባዊ አደረጃጀቶችም በጋራ ለአንድ ዓላማና ሀገራዊ ተልዕኮ የሚሰሩበት አሰራር መፍጠር ግዴታ ነው::
የስምሪት ለውጥም ሊደረግ ይችላል:: የጦርነት ወቅት ሥምሪት ከሌላው ወቅት ሥምሪት የሚለይ በመሆኑ ይህም ማስተካከያ የሚደረግበት ይሆናል:: የህዝባዊ አደረጃጀት ከጦርነት በኋላ ሌላ ጦርነት ይጠብቀዋል፤ ወደ ልማት ግንባር በመዞር የተሻለች ሀገር መፍጠርና የማትደፈር ሀገር መገንባት ይገባል:: በመሆኑም በሽግግሩ ላይ የተፈጠሩ ነገሮች ሊያሰጉን አይገባም::
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ጭምር የሚከላከል ነው:: በዚህ ደረጃ እውቀትና ቴክኖሎጂ ታጥቋል፤ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትስ ጋር ትስስር ፈጥሯል ?
ኮሚሽነር መስፍን፡- የፌዴራል ፖሊስ ተቋምም በምስራቅ አፍሪካ አስር ከሚሆኑ ሀገራት ጋር በመቀናጀት በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ሲሆን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ውጤታማ ተግባራትን በመናከናወን ላይ ነው:: ከቀጣናው ሀገራት ጋር በስልጠና የመተሳሰር ብሎም ለምስራቅ አፍሪካም የፖሊስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ተቋማት እየተገነቡና በሰፊው እየተሰራበት ነው:: የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ሀገራት ጋር ወዳጅነት በመፍጠር ላይ ነው:: 193 ሀገራት አባል የሆኑበት የኢንተር ፖል አባል በመሆኑም በጋራ የትብብር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው:: ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምተናል:: ኮሪያ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አውሮፓ ህብረት እና ከመሳሰሉት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነቶች አድገናል:: የኢትዮጵያ ፖሊስ ዓለም አቀፋዊ ዕውቀትና ክህሎት እንዲላበስ እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ ለተልዕኮው መሳካት ከህዝቡ ምን ይጠብቃል?
ኮሚሽነር መስፍን፡- ህዝቡ ለእኛ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲሰራ እንፈልጋለን:: ለሠላም እና ደህንነት አጋዣችን ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ብሎም ለአሸባሪዎችና ህገወጦች ምሽግ እንዳይሆን እንፈልጋለን:: ወንጀልን በመከላከል ከህዝብ ጋር መስራት አለበት:: ሠላም ማጣት የሚያስከፍለንን ዋጋ እየተመለከትን ነው:: ብዙ ነገሮች ይናጋሉ:: በመሆኑም ሠላማዊ ሁኔታ እንዲኖር ፖሊስና ማህበረሰቡ ተናበው መሥራት አለባቸው:: ሠላም ማረጋገጥ የጋራ ስራ መሆን አለበት የሚል አቋም መወሰድ አለበት::
አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ፖሊስ በቀጣይ ስጋት ናቸው ብሎ የሚያስባቸው ነገሮች አሉ?
ኮሚሽነር መስፍን፡- ቴክኖሎጂ ወለድና የተደራጁ ወንጀለኞች በቀጣይ ስጋት ናቸው:: በቀጣናው የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ በዩክሬንና ራሺያ መካከል የሚደረገው ጦርነትም እኛን ተጋላጭ እያደረገን ነው:: የዋጋ ግሽበት፣ የእንቅስቃሴ ገደብ፣ የውጭ ሸቀጦች ላይ ጥገኛ መሆን አስጊ ነው:: የቀጣናው ጂኦ ፖለቲክስ ስጋታችን ነው:: በየዘመናቱ መሪዎቻችን ሲፈተኑ ነበር:: አሁንም ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል:: ግጭቶችን እንዴት አሸንፈን እንዴትስ በጋራ እንኖራለን የሚለው የሁል ጊዜ ስጋት ነው:: የሽብር እንቅስቃሴ እስካልጠፋ ድረስ አሁንም ስጋት ነው:: የፖለቲካ አካላትም ተግባብተው እስካልተንቀሳቀሱ ድረስ አሁንም ለእኛ ስጋት ነው::
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ስለሆኑ በአንባብያን ሥም አመሰግናለሁ::
ኮሚሽነር መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም