
ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታወቅ ካደረጉ ነገሮች መካከል በውስጧ ያሉ ሀይማኖቶች ተከባብረው፣ ተዋደውና ተቻችለው በጋራ መኖራቸው ግንባር ቀደሙ ነው። ይህ የአብሮነት ማሳያ ዘመናትን ሲሻገር ቢመጣም ዛሬ ላይ ይህ አንድነት እንቅልፍ የነሳቸው አንዳንድ አካላት ይህንን አንድነት ለማደፍረስ እና የእምነቱን ተከታዮች ለማናቆር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደር ይስተዋላል፡፡ በዚህ የተነሳም በሃገራችን አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶች ይስተዋላሉ፡፡
በሌላ በኩል በሃገራችን እነዚህ የተለያዩ ሃይማኖቶች ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት እና በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ጥምረት ፈጥረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ የጋራ ተቋማቸውም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነው፡፡ እኛም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚከሰቱ ችግሮች መነሻ ምንድነው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሃይማኖት ተቋማት ሚና ምንድነው፤ ይህንንስ ሚናቸውን በምን ያህል መጠን እየተወጡ ነው፤ በሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከጉባኤው ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጋር ቆይታን አደርገናል፤ መልካም ቆይታ፡፡
አዲስ ዘመን ፦ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ እምነቶች አብሮ በመኖር ሂደት ውስጥ ያላቸውን የቆየ ታሪካዊ ዳራ እንዴት ይገልጹታል፤
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፦ በኢትዮጵያ የሃይማኖቶች የአብሮነት ታሪክ ከሺ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ሁሉም ያውቃል።በተለይም እስልምናና ክርስትና ሃይማኖቶች ከሺ አራት መቶ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መሆናቸው ይታወቃል።እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የኢትዮጵያ ክርስቲያን ንጉስ እንዲሁም መላው ዜጋ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ቢሆኑም እንኳን የእስልምናው ዋናው መስራች ነብዩ መሐመድ ተከታዮቻቸው በአረብ አገርና በመካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ እንግልቶችና ግፎች ሲደርሱባቸው እንዲሁም እምነቱ ከአለም ጋራ ሲያጣላቸው ወደ አበሻ ምድር ሄዳችሁ ተጠለሉ መባላቸው ይታወቃል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዓለም ፊት በመቻቻል እሴት በተለይም በእስልምናና በክርስትና ሃይማኖት መካከል ትልቅ ቦታ ያላት አገር ነች። ከዚህ አንጻር የመቻቻል ታሪካችን ትልቅ ቦታ ይዞ አብረንም ለሺ አመታት ኖረናል፤ እየኖርንም ነው። ይህንን መሬት ከማውረድ አንጻር በተለይም ለሙስሊሞቹ ማምለኪያ ቦታ እስከመስጠት እንዲሁም የመቀበሪያ ቦታ እንዲያገኙ እስከማድረግ ፤ በአንጻሩ ለክርስቲያኑም የመቀበሪያ አጸደ የቤተክርስቲያን መገንቢያ ቦታ እስከመስጠት እና በግንባታው ላይ እስከመሳተፍ የደረሰ ቁርኝት እንደነበራቸው ይገለጻል።ይህ ደግሞ አሁን ድረስም ቢሆን አብሮን ያለ ታሪካችን ነው።
ከዚህ አንጻር የመቻቻል እሴቶቻችን ተቻችሎ ከመኖር እስከ መዋለድ ድረስ በአንድ ቤት ውስጥ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተስማምተው እስከመኖር ድረስ ይደርሳል።ይህ ደግሞ የትም አለም ላይ የማናየው የእኛና የእኛ ብቻ የሆነ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን ።ይህ ደግሞ በጣም በአለም ላይ በመቻቻል እንዲሁም በመከባበር ላይ ያላት ልምድና ተሞክሮ የሌለ መሆኑን ያሳያል።ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለሌሎች የአለም አገራት ጥሩ ማሳያ ናት ብለን ብንወስድ ምንም ማጋነን የለውም።እንግዲህ ይህ ነው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የመቻቻል እሴታችንን በጣም የላቀ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን የሚያሳየው።
በነገራችን ላይ ከላይ የጠቀስኳቸው የመቻቻል አብሮ የመኖር ሁኔታን የሚያሳዩ ገለጻዎች በጣም ከብዙ በጥቂቱ እንደሆኑም ሊታወቅ ይገባል።ምክንያቱም የእኛ መቻቻል ካለው የረጅም ዘመን ታሪክ አንጻር በአጭሩ ተገልጾ የሚያልቅ ስላልሆነ።
አዲስ ዘመን ፦ በዓለም ላይ የግሎባላይዜሽን መስፋፋት በእምነቶች ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት ይታያል፤
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፦ ይህ ነገር ምናልብትም እንደ አረዳዱ የሚወሰን ይመስለኛል።ምናልባትም ከስልጣኔ ጋር አያይዘን የምንወስዳቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ።በተለይም ደግሞ ከስልጣኔ ጋር ተያይዞ በፊት የነበረንን የጋራ እሴቶቻችንን የመሸርሸር፣ የማጠልሸትና ያልነበሩንን አዳዲስ ተሞክሮዎች እያስተናገድን እንደሆነ ይታያል።
ለምሳሌ አብሮ የኖረን ህዝብ አብሮ እንዳይኖር ከማድረግ አንጻር አዳዲስ እሳቤዎች አዳዲስ አስተምሮዎች ጠልቀው እየገቡ ነው። ነገር ግን እነዚህ ሁኔታዎች በእኛ በሀይማኖት ተቋማት ቦታ እንደሌላቸውና እነዚህ ባዕድ ጥገኝነቶች እንዲሁም መሰልጠን እየተባለ ወደማክረርና ጽንፍ የመውጣት ከእኔ ውጪ ሌላ አይኑር፤ ለዚህች ምድር የማስፈልጋት እኔ ብቻ ነኝ የሚሉ እሳቤዎች በሰዎች ላይ እየነገሱ መምጣታቸው ሁኔታው መጠፋፋት ካልሆነ በቀር አብሮ ለመኖር አያበቃንም።ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ሃይማኖት ውስጥ አስተምሮውን እየተቀላቀሉ የመጡ ነገር ግን መሰረታዊውን አስተምሮ የማይዳስሱ የማይወክሉ እሳቤዎች አሉ።ይህ ደግሞ በእኛ ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ በፍጹም ቦታ ሊኖረው የማይችል እኛ ኢትዮጵያውያንን የማይወክል የቀደመ ማንነታችንን የማይገልጽ ነው።እኛ ተዋልደናል፣ ተጋብተናል፣ ተጋምደናል፣ ተዋህደናል፤ በመሆኑም እኛን ኢትዮጵያውያንን ለመነጣጠል መሞከር በራሱ ለእኔ ከንቱ ድካም ነው።
እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ባነሳልሽ ሰርገኛ ጤፍ አለ፤ ይህ ጤፍ ነጩ ከጥቁሩ የተደባለቀ ነው፤ ለቅሜ አንዱን ከሌላው ልለያየው ማለትም ትርፉ ድካም ካልሆነ በቀር በፍጹም የሚታሰብ አይደለም።ኢትዮጵያውያንም እንደዛ ነን። ሁላችንም የየራሳችን የሆነ እምነት አመለካከት እንዲሁም ማንነት ያለን ህዝቦች ነን፤ ይህንን እኛነታችንን ይዘን ደግሞ አብረን ስንኖር ቆይተናል፡፡ ወደፊትም እንኖራለን። ከዚህ አንጻር ሁላችንም ስልጣኔ የሚባለው ነገር ባመጣብን ጣጣ ሳንነጠል ጥሩ ጥሩ ነገሮችን እየወሰድን የማይወክልንና ከእኛነታችን ውጪ የሆኑትን ነገሮች እያስወገድን አባት እናቶቻችችን ከኖሩት በላይ ተዋደን ተስማምተን እርስ በእርሳችን ተከባብረን መኖር ነው ያለብን።አንዳንድ አስተምሮውን ተቀላቅለው የመጡ ከመሰረታዊው ሃይማኖታዊ እሴቶች ያፈነገጡ መገዳደልን፣ መፈነቃቀልን፣ መጠላላትን፣ ከእኔ በቀር ሌላ አይኖርም ማለትን አላስፈላጊ መሆናቸውን ተገንዝበን መኖር አለብን።
አዲስ ዘመን ፦ በሃገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእምነት ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች በመጤ ባህሎች የመዋጥና ከአስተምህሮ ውጭ የሆኑ ድርጊቶች የሚፈፀሙበት ሁኔታ እየሰፋ መምጣቱ ይነገራልና ይህንን እንዴት ይገልጹታል፤
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ፦ እዚህ ላይ ከአስተምሮ ውጪ የግል ፍላጎቶች ሊመጡ የቻሉት ቤተ እምነቶቹ ስላልተፈተሹ ነው።በእኔ እምነት ኦርቶዶክስም ስለ አስተምሮዋ ልትፈትሽ ሃይማኖቱ ከሚፈቅደው ውጪ የሚሰጥ አስተምሮ ካለ ይህ ከእኔ ፍቃድ ውጪ ነው ብሎ መሞገት ያስፈልጋል።በሙስሊሙም በተመሳሳይ ወጣ ያሉ አብረን ተቻችለንና ተከባብረን እንዳንኖር የሚያደርጉ ትምህርቶች ካሉ መሰረታዊ ፍላጎታቸው ይህ አለመሆኑን ማስረዳት፣ተው ማለት መከልከልና ማገድ ይገባል።እዚህ ላይ ሁላችንም እንደየእምነታችን አብረን እየኖርን ነገ ሰማያዊ መንግሥትን መውረስ ከሆነ ፍላጎታችን ሳንገፋፋ ሳንጣላ በጣም በጥንቃቄ ባዕድና ከመሰረታዊው አስተምሮ ያፈነገጡትን በመመከት ቤተ እምነቶች ሚና ሊኖራቸው ይገባል ብለን እየሰራን እንገኛለን።በመሆኑም ሁሉም ቤተ እምነት ይህንን ባዕድ የተቀላቀለ ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጽ የእኛ እሴት ያልሆነና አብሮነታችንን የማያሳይ ሁኔታን መሰረታዊውን አስተምሮ በማንሳት መሞገት፣ መውቀስና እኛን አይወክልም ማለት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን ፦በሃገራችን በቀደመው ዘመን የሃይማኖት አባቶችና ታላላቅ የሃገር ሽማግሌዎች የመደመጥ አቅም ከፍተኛ እንደነበር እና ይህ ግን አሁን አሁን እየቀነሰ መምጣቱ ይነገራል፤ ለመሆኑ ይህ ምን ያህል እውነትነት አለው፤ እውነት ከሆነስ ምክንያቱ ምንድነው፤
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ፦ ይህ እንግዲህ በተለይም ስልጣኔ ብለን ቅድም ካነሳነው አንጻር ሊታይ የሚችል ነገር ነው።አሁን አሁን እየመጡ ካሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማለትም ማህበራዊ ሚዲያዎች
ጋር አቆራኝቶ ማየትም ሳያስፈልግ አይቀርም። እዚህ ላይ ትልልቆቹ አባቶቻችንና ጸሃፊያን እነዚህን ማህበራዊ ሚዲያዎች አይጠቀሙም ፤እነሱን የምናገኝበት መንገድም የለንም። አሁን የሚያወሩ፣ የሚናገሩ፣ የሚንጫጩ ሁሉ በዚህ ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ ያሉ አካላት ናቸው። እየገነኑ የመጡትም ብዙ ተከታይ ያፈሩትም ህዝቡ ቁጭ ብሎ በሚውልበት መንገድ በመምጣታቸው ነው።እነዚህ ሰዎች በልመና በተለያዩ መንገዶች ተከታይ ያሰባስቡና ቆየት ብለው ለጥፋት ይጠቀሙበታል። እንዳጀማመራቸው ሰላማዊ ይመስላል፤ ነገር ግን ያገኙትን ተከታይ የሚጠቀሙበት አፍራሽ ለሆነው አስተሳሰባቸው ማራመጃነት ነው። ሁኔታቸውም ተሰሚነት ስለሚሰጣቸው ትንሹን ትልቅ እያደረጉ በማቅረብ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ይሰበስቡበታል።
ለምሳሌ አሁን ሀጂ ሙፍቲ ምንም ዓይነት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ አይደሉም፤ በመሆኑም በመገናኛ ብዙሃን በኩል ካልሆነ እንደዚህ ነው ብለው የሚያስረዱበት መንገድ ጠባብ ነው።ሌሎቹም የሃይማኖት አባቶች እንዲዚሁ ናቸው፡፡ በመሆኑም አሁን በአገራችን ለምንመለከተው ጽንፍ የወጣ ችግር መባባስ ምክንያት እየሆኑ ካሉ ነገሮች አንዱ የማህበራዊ ሚዲያው ነው። ከተቋም ይልቅ ግለሰቦች እየገነኑ መምጣታቸው ነው። እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ ራሳቸው ተቋም አድርገው ራሳቸውን ተራራ ላይ ያስቀምጣሉ፤ እነሱን የሚከተሉ ደግሞ እነሱው በመሯቸው መንገድ ይፈሳሉ ማለት ነው።እነዚህ ሰዎች እኮ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን የሚያሳዩ ቢሆኑ፤ ተዋደዱ፣ ተቃቀፉ፣ የሰላም እሴቶችን ገንቡ፣ ተካፍለህ ብላ፣… የሚሉ ቢሆኑ እኮ ምንም አልነበረም፤ ነገር ግን አብዛኛውን የሚመሯቸው ወደ እሳት ነው።ሂድ አቃጥል፣ መንገድ ዝጋ፣ ግደል፣ አፈናቅል፣ ወዘተ ነው። በመሆኑም አሁን ላይ መደረግ ያለበት እንዲሁም እነሱን የሚከተለውም ሆነ ሌላው ሰው ማድረግ ያለበት ጥሩውን ከመጥፎ እሳቱን ከውሃ መለየት ነው።
አባቶች አሁንም በጾም ጸሎታቸው በአስተምሯቸው በትህትናቸው በጠቅላላው በበጎ ስራቸው ላይ አሉ። የቀነሰ ነገርም የለም።ከወንበራቸውም አላፈነገጡም። የምናያቸው ነገሮች ግን አለም ሌላ መንገድ እየተከተለች ስለሆነ ዛሬ አሜሪካን ላይ የሚደረገው ነገር በኢትዮጵያ ገጠር ውስጥ ይታያል ።በመሆኑም እሱ የፈጠረው ተጽዕኖ እንጂ እኛ እንደሚመስለን አባቶች እየተሰሙ ስላልሆነ እነሱም እየመከሩ ስላልሆነ አይደለም።
በሁሉም ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ትልልቅ አባቶች ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ አይደሉም።ይህ ሁኔታ የፈጠረውን ክፍተት ደግሞ ለእምነቱ ቀናይ በመሆኑ በበጎ እሳቤ ልባቸው በተሞላ ምእመናን የሚካካስ ይሆናል።ነገር ግን አሁንም አባቶች ለአገራችን ሰላም ለህዝባችን አንድነት፣ አብሮነት፣ መቻቻል፣ ለሃይማኖቶቻችን ተከባብሮና ተዋዶ መኖር እየሰሩ፣ እየጸለዩ፣ እየመከሩ፣ እየዘከሩ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ በሌላ በኩል በሃገራችን የሃይማኖቶች መቻቻል ለዓለም ጭምር ተምሳሌት የሚሆን እንደነበር በተለያዩ አጋጣዎች ይገለፃል፤ አሁን አሁን ግን በሃይማኖት ስም ግጭቶች ጭምር ሲከሰቱ ይሰማል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖትን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት የማዋል ሁኔታ መኖሩን የተለያዩ ሰላም ወዳድ ዜጎች ጭምር ይገልጻሉና ይህንን እንደ ሃይማኖት ተቋማት ህብረት እንዴት ይመለከቱታል?
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፦ ፖለቲካና ሃይማኖት ለመጋባት ከድሮም ጀምሮ ቢሆን ጥረት ያደርጋሉ፤ ሲጋቡም አላስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ።ምክንያቱም ብዙ አብረው መጓዝ አይችሉም ፤መንፈሳዊ ተቋማት የሚሰብኩት ሰማያዊ መንግሥትን ነው፤ ፖለቲከኞች ደግሞ ለማኖር የሚሰብኩት ምድራዊ ንጉስን፣ ስልጣንና ስርዓትን ነው።በመሆኑም ሁለቱም እንደሚከተሉት አካሄድ ሁሉ ልዩነታቸውም የሰማይና የምድር ያህል ነው።በመሆኑም እነዚህን ማጋባት በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን ሰማያዊውም ምድራዊውም ተባብሮ መስራት ይችላሉ ።ለሰላም ስለሰላም አብሮ መዘመር ይችላሉ ።ስለልማት አብሮ መስራት ይችላሉ።ነገር ግን ከዛ ባፈነገጠ መልኩ አብረው ሆነው ሚናቸውን ተቀያይረው ቢታዩ ምንም ጥቅም ካለመኖሩም በላይ የሚሰማቸውም አይኖርም።
በመሆኑም ሁለቱም ሳይቀላቀሉ መቀጠል አለባቸው እላለሁ። አሁን ላይ ግን ሁለት ካባ መልበሳቸው ነው አስቸጋሪ እየሆነ የመጣው። በቤተ መንግስት ውስጥ ሆነው መንፈሳዊ ካባ ይለብሱና ነገሮችን ሁሉ ስብከት ያደርጉታል፤ በኋላም አድማጭ ያጣሉ።በቤተ እምነት ውስጥም ሆነው የፖለቲካ ስብከት የሚሰብኩ ነገር ግን መንፈሳዊ ካባ ያጠለቁ ሰዎች ተቀላቅሎባቸው ብዥታ ውስጥ ስለገቡ ነው። በመሆኑም እነዚህ አካላት ሚናቸውን መለየት አቀማመጣቸውን አሰላለፋቸውን መለየት ይገባቸዋል።ምክንያቱም እነሱ ባቀላቀሉት ልክ የሚሄድ ከሆነ ተከታዮቻቸውም ብዥታ ውስጥ ይወድቁባቸዋል።ይህንን ማጥራት በጣም አስፈላጊ ነው።
ግጭቶች ሲፈጠሩ ወደሃይማኖት ሊያላክኩ የሚፈልጉ ፖለቲከኞች ዋና አላማቸው የሰውን ስስ ስሜት መቀስቀስው ነው ።ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ሰዎች ለሃይማኖታቸው ስስ በመሆናቸው ሃይማኖትህ ተነካ ስለ ሃይማኖትህ ብትሞት ትጸድቃለህ ሲባል ቶሎ ይነሳል፤ አያገናዝብም፣ ምክንያታዊም አይሆንም፣ በመሆኑም ሰውን ወደስሜት ለማስገባት ሃይማኖትን ሽፋን ያደርጉታል።በማንነቱም ሲመጡበት ስሜቱ ተመሳሳይ ነው፤ በመሆኑም እነዚህን ሁለቱን መቀላቀል በጣም ከባድ አደጋም እንዳለው ፖለቲከኞች ያውቃሉ።ፖለቲከኞች ደግሞ ሁኔታዎችን አስልተው አጥንተው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ምንም የማያውቀው ህዝብ ደግሞ ይቀላቀልበትና ዝም ብሎ ይከተላል፡፡ መጨረሻ ላይ ግን እሳቱ ከነደደ በኋላ ገደል ላይ መሆኑ ሲገባው ነው ወደኋላ የሚመለሰው።ይህ ደግሞ ንብረት ከወደመ የሰው ህይወት ከጠፋ በኋላ ይሆናል።ስለዚህ ፖለቲከኞች ችግሮቻችሁን ይዛችሁ ወደሃይማኖት ተቋማት አትጠጉ፣ አትቀላቀሉ። አሁንም ምክራችን ይኸው ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በሃገራችን ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሃይማኖት አባቶች እና የእምነት ተቋማት መሪዎች ሚና ምን መሆን አለበት፤ ይህንን ሚናቸውንስ ለመወጣት ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ፦ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸው የታወቀ ነው፤ ተልዕኳቸውም ሰማያዊ ነው። የሚያወርሱትም የሚወርሱትም ሰማያዊ ነገር ነው። ፖለቲካ ምድራዊ ነው። ሰማያዊ ሆኖ አያውቅም። በመሆኑም ሁሉም ሚናቸውን በትክክል ሊያውቁ ይገባል።
ከዚህ ውጪ ግን የእምነት ተቋማት ከመለኮት የተሰጠን ተልዕኮ አለ ።የተሰጠንን ተልዕኮ ወደመሬት አውርደን ተግባራዊ ስራን ምእመናኖቻችን ላይ መስራት ይጠበቅብናል። ለምሳሌ በክርስትና እምነት ምዕመናን በስጋቸው እንዲጠበቁ፣ በመንፈሳቸው እንዲታደሱ፣ ለሰማያዊው መንግሥት እንዲበቁ ማድረግ ተልዕኳቸው ነው። በመሆኑም ካህኑ፣ ዲያቆኑም፣ ሰባኪውም ፣ ጳጳሱም ማድረግ ያለበት ይህንን ነው ።
በተመሳሳይም የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድም እህቶቻችንን ለአላህ መንግሥት እንዲበቁ ለማድረግ ከክፉ ስራ ተቆጥበው ለወገናቸው አዝነው ተዛዝነው እንዲኖሩ በጾም ጸሎት እራሳቸውን ጠብቀው ህሊናቸውን ለፈጣሪያቸው እንዲያስገዙ ለማድረግ የኡለማው የሼሁ የኡስታዙ ስራ ነው ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ውጪ ሌላ ተልዕኮ አለ ብዬም አላስብም።ፉክክር ውስጥ መግባት አለብንም ብዬ አላስብም።
በመሆኑም ወደ ትብብር መጥተን እንደ ድሮ አባቶቻችን ተከባብረን ሃይማኖታዊ አስተምሮው በሚያዘው መሰረት መኖር አለብን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። እንደ ሃይማኖት አባትም በዚህ ልክ ከሄድን ምንም ዓይነት ግጭት በአገራችን ላይ አናይም እላለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው ተነስቶ የኔ እምነት እንዲህ አይነት ችግር ደረሰበት ሲል ተከታዩ ቆም ብሎ ከማጣራት ይልቅ ለግጭት የሚነሳሱ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፤ ይህ ደግሞ ከፍ ያለ አደጋ አለውና እንደው ከግጭት በፊት ሰዎች ማድረግ ስላለባቸው እና ስለስክነት በጥቂቱ ቢነግሩን፦
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፦ አዎ ሰው ሰውነቱ የሚታወቀው ወይንም ደግሞ ከእንስሳት የሚለየው አርቆ በማሰቡ ይህንን ባደርግ ነገ ምን ሊፈጠር ይችላል፤ ባላደርግስ በእኔና በአገሬ ላይ ምን ጥቅም አመጣለሁ የሚለውን ቆም ብሎ ማሰብ በመቻሉ ነው።አልያ ግን ስሜት የሚነዳው የፈለገውን ነገር በሚፈልገው ሰዓት ካላገኘ የሚያመው ሌሎችን አስተባብሮ አገርን ለማፍረስ ወገኑን ለመጉዳት ጦር የሚሰብቅ ድንጋይ የሚወረውር ቅዱስ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ላይ እጁን የሚያነሳና በእሳት የሚያቃጥል ሰው እውነት ለመናገር እንኳን ከሰው ከእንስሳቱም ያነሰ ነው የሚሆነው።
በመሆኑም ማንም ሰው ነኝ የሚል፤ በተለይም ደግሞ ለእምነቴ ለሃይማኖቴ ቀናይ ነኝ የሚል አካል እርጋታ ሊኖረው የግድ ነው።ምክንያቱም መንፈሳዊነት በራሱ እርጋታን የሚጠይቅ ነገር በመሆኑ።ቤተ እምነቶቻችን ጋር ስታይ እርጋታ ያለ ነገር ነው የሚስተዋለው እንደ መርካቶ ውክቢያ የለም፤ አሁን በያዝነው ልክ ግን ቤተ እምነቶቻችንን መርካቶ ካደረግናቸው በጣም ከባድ ነው። ነገሮችን ማጤን ስክነት በጣም ወሳኝ ነው።“ስድስት ጊዜ ለካ በሰባተኛው ቁረጥ” ነው የሚለው መጽሃፉም፤ ይህ አባባል ቀላል አይደለም፤ በጣም እንድንሰክን እንድንረጋጋ የሚያመለክት ነው። ፈጣሪ እኮ ሲፈጥረን አንድ አፍ ሁለት ጆሮ ነው የሰጠን፡፡ ምናልባት እኮ አንድ ጆሮም በቂያችን ነበር፡፡ ነገር ግን ከመናገራችን በፊት ማድመጥ በደንብ ማሰብ ያዳመጥነውን ደግሞ በእርጋታ በአንድ አፋችን ማውራት እንዳለብን ሲያሳየን ነው።
በመሆኑም መረጋጋት ፣ማሰብ፣ መስከን ከሁሉም ይጠበቃል። አንዳንድ ጊዜ የሚመጡ ንፋሶችንም ጥግ ይዞ አልያም ጎንበስ ብሎ ማሳለፍ ሊያስፈልግ ይችላል። ምክንያቱም የሚመጣው ንፋስ አንዳንድ ጊዜ አዋራ ድንጋይ ሊቀላቅል፣ ዝናብም በረዶም ሊኖረው ይችላል። በመሆኑም ይህንን ሁኔታ በጥንቃቄ ማሳለፍ ካልተቻለ ለአደጋም መጋለጥ ይኖራልና በደንብ መጠንቀቅ በጣም መዘጋጀት አስፈላጊ ነው።
አንድን ውሳኔ ከመወሰን በፊት ደጋግሞ ማሰብ ውጤቱን መገመት በጣም ያስፈልጋል፤ ካለፈ በኋላ የሰው ህይወት ከጠፋ ንብረት ከወደመ ቤተ እምነት ከተቃጠለ በኋላ ጸጸት ነው ትርፉ፤ ምን ሆኜ በምን ቀን ነው ያደረኩት የሚባልበት ጊዜ ይመጣል። ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስራ ከመስራት መቆጠብ ከሁላችን ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 /2014