ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአውሮፓ ከተሞች የተለያዩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ተካሂደዋል:: በእነዚህ ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተለመደ ድንቅ አቋም በማሳየት ድላቸውን አጣጥመዋል::
በፖርቹጋል የተካሄደው የሊዝበን ግማሽ ማራቶን በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ እጅግ ተጠባቂ የነበረ ውድድር ሲሆን፤ እጅግ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ በነበረው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸናፊ ሆናለች::
በስፖርቱ ወዳጆች ዘንድ ታዋቂና ተመራጭ በሆነው በዚህ የግማሽ ማራቶን ውድድር ከመላው ዓለም የተውጣጡ 35ሺ የሚሆኑ ሯጮች የተካፈሉበት ነበር:: በታዋቂ አትሌቶች መካከል በነበረው ውድድርም በተለይ የሴቶቹ ምድብ ብርቱ አትሌቶችን በማካተቱ ማን አሸናፊ ይሆናል የሚለው ተጠባቂ ነበር::
እስከ ውድድሩ ማብቂያ ማን ያሸንፋል የሚለውን መለየት ባይቻልም በውድድሩ በስተመጨረሻ አካባቢ፤ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፀሐይ ገመቹ አስደናቂ በሆነ አጨራረስ ተስፈንጥራ በመውጣት የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቷን ኬንያዊት አትሌት እጅ አሰጥታለች:: ከባድ በነበረው ፉክክር ኬንያዊቷ ብሪጌድ ኮስጌይ(ከሁለት ወራት በፊት የቶኪዮ ማራቶንን ያሸነፈች) በለመደችው አሸናፊነት ውድድሩን ለማጠናቀቅ ከባድ ፍልሚያ ብታደርግም ፀሐይ ግን በቀላሉ የምትበገር አትሌት ባለመሆኗ በሁለት ሰከንዶች ቀድማ በመግባት ልታሸንፋት ችላለች::
በ5ሺ ሜትር የዓለም ምርጥ አራተኛዋ አትሌት የሆነችው ፀሐይ ፊቷን ከመም ወደ ጎዳና ያዞረች መሆኗ ይታወቃል፤ በዚህም ስኬታማ በመሆን በ1ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ርቀቱን በመሸፈን አሸናፊ ሆናለች:: አትሌቷ ከሩጫው በኋላ በሰጠችው አስተያየትም ‹‹አሸናፊ በመሆኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ:: የአየር ሁኔታው ሞቃታማ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ኮስጌይ ያለች ጠንካራ አትሌት መርታት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ›› ብላለች:: ጎይቶም ገብረሥላሴም ይህን ውድድር ሦስተኛ በመሆን ፈጽማለች::
በሌላኛዋ አውሮፓዊት አገር ስፔን ባርሴሎና በተደረገ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያኑ የበላይነቱን ተቆጣጥረውታል፤ የገቡበት ሰዓትም ፈጣን የሚባል ሆኗል:: እ.አ.አ ከ1978 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር ዘንድሮ ለ44ኛ ጊዜ ተካሂዷል::
በዚህ ውድድር በወንዶች በኩል ይሁንልኝ አዳነ ባለ ድል መሆን ችሏል፤ 2ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ53 በሆነ ሰዓት ሩጫውን አጠናቋል:: አትሌቱ ለማራቶን ውድድር አዲስ አይደለም፤ ባለፈው ዓመትም የሊዝበንን ማራቶን ተሳትፎ በሦስተኛነት ያጠናቀቀ ጠንካራ አትሌት ነው::
በዚህ ውድድር ጥቂት ሰከንዶችን ብቻ በመዘግየት በተከታይነት የገባው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ገብሩ ረዳኸኝ የገባበት ሰዓት 2ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቦለታል:: ሌላኛው አትሌት ከበደ ዋሚ ደግሞ አንድ ደቂቃ ዘግይቶ በመግባት ሦስተኛው አትሌት ሊሆን ችሏል::
በዚህ ሩጫ ላይ በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አምስት ባለው ደረጃ ተከታትለው በመግባት የቦታውን አሸናፊነት የግላቸው ማድረግ ችለዋል:: በዚህም፤ መሠረት ደቀቦ 2ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ቀዳሚዋ አትሌት ለመሆን ችላለች:: አትሌቷ የገባችበት ይህ ሰዓት ከዚህ ቀደም በዙሪክ ማራቶን ባሸነፈችበት ወቅት ካስመዘገበችው በአራት ደቂቃዎች የዘገየ ቢሆንም በባርሴሎና ማራቶን ግን፤ ባለፈው ዓመት በአገሯ ልጅ ታዱ ተሾመ ከተመዘገበው በ42 ደቂቃዎች የተሻለ ሆኖ ተመዝግቦላታል::
ውድድሩን በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው አያንቱ ኩመላ በሁለት ሰከንዶች ዘግይታ ገብታለች፤ ዘነቡ ፈቃዱ ደግሞ እርሷ ከገባች ሰከንዶች በኋላ ሩጫዋን አጠናቃለች:: አትሌት ዘርፌ ልመንህ እና ታደለች በቀለ ደግሞ አራተኛ እና አምስተኛ ሆነዋል::
በቼክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ፕራጉ በተካሄደው ማራቶንም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአገራቸውን ስም ማስጠራት ችለዋል:: በሴቶች በኩል በቀለች ቦሬቻ አሸናፊ ስትሆን፤ ስንታየሁ ኃይለሚካኤል ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች:: በወንዶች በኩልም ከልክሌ ወልደአረጋይ ኬንያዊውን አትሌት ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል:: ሌላኛው አትሌት ይታያል ዘሪሁን ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀ አትሌት ሆኗል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014