ለወደዳችሁት ሰው ባማሩ ቃላት የተከሸነ ማራኪ መልዕክት ለመጻፍ ተጨንቃችሁ አታውቁም ? ያለንበት ዘመን በተዋበ ቋንቋ የወደድነውን ለማማለል ቃላትን ከውስጣችን ለማውጣት ጭንቅ፤ ጥብብ የምንልበት አይደለም። ጭንቀታችን አስጨንቋቸው የማረከንን ሰው ምርኮ ማድረግ እንድንችል የሚያደርጉ ጥዑም የፍቅር መልዕክቶችን በእጅ ስልካችን ሊያቀርቡልን ከቴሌ ፍቃድ የወሰዱ ንግድ ድርጅቶች አሉ። ችግሩ ሀሳባችን ሰምሮ ከወደድነው ሰው ጋር ተቀራርበን ማውራት ደረጃ ስንደርስ ከአንደበታችን የሚደመጡት ቃላት እየገዛን ከላክናቸው መልዕክቶች ጋር አለመጣጣማቸው ነው።
የዱሮዎቹ የፍቅር ደብዳቤዎችም ሆኑ የአሁኖች መልዕክቶች አብይ ጉዳይ ውበትን መግለጽ ነው። ምክንያቱም መሸነፍን ለመንገር የተማረኩበትን ውበት መግለጽ አስገዳጅ መንደርደሪያ ነው። ታዲያ ውበትን መግለጽ የሚችሉት ጥበብ የተገለጸላቸው ናቸው። ለዚህ ነው ብዙዎች እርዳታ ፍለጋ የሚያማትሩት።
“ውበት ቁንጅናሽን በቃል ለማስረዳት
የቋንቋ እውቀት ያለው ያስፈልጋል ረዳት” ያለው ማን ነበር? እውነቱን ነው እኮ። በተለይ አሁን አሁን አንዳንዶች ውበትን የሚገልጹበት መንገድ አግራሞትን ያጭራል። ፖለቲካዊ እሳቤዎችን፣ ሞያዊ ጉዳዮችንና ታዋቂ ሰዎችን ውበትን ለመግለጽ ማንጸሪያ አድርገው የሚጠቀሙ ሰዎች ብቅ እያሉ ነው።
እስኪ ወደኋላ መለስ ብለን ከዛሬ 110 ዓመት በፊት ውበት እንዴት ይገለጽ እንደነበር እንመልከት።
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ በ1900 ዓ.ም በጻፉት ልቦለድ መጽሐፋቸው ጦቢያ የተባለችውን ገጸ ባህሪ ውበት እንደሚከተለው ገልጸውታል።
“ሽፋሽፍቷ እንደ በልግ ሳር ተጨብጦ የሚታጨድ ይመስላል። ጸጉሯ እንደ ሰኔ ቡቃያ ወይም እንደ አዲስ መሬት ጤፍ እየጋሸበ የሀር ነዶ መስሏል። አፍንጫዋ ቀጥ ያለ፣ ከንፈሯ መፈንዳት የጀመረ የማለዳ ጽጌሬዳ ይመስላል። ብርሌ የመሰለ አንገቷ እንደ ደከመ እያረፈ የወጣ ነው። ያለአጥንት የተሰራው የእጅ ጣቷ እጅ ስራ ከበዛበት አመልማሎ ጋር ይፎካከራል። ተረከዟ ባቷ ይቆጡኛል ያለ፣ የተሰራ የተቀጣ ነው። ስትፈራ ስትቸር የምትገልጸው ጥርስና ከንፈሯ ከአተያይዋ ጋር ብርቱውን ያዝላል፤ ሰነፉን ይገድላል።”
የኛን ዘመን የውበት አገላለጽ ሌላ ጊዜ ልመለስበት ቃል እየገባሁ ከቀደመው ዘመን ሁለት በማለት ባለቅኔው መንግሥቱ ለማ ውበትን በገለጹበት አንድ ግጥም ልሰናበታችሁ።
ያገር ልጅ
አካሄድሽ ይምጣ አረማመድሽ ፤
ጥርስ አገላለጥሸ የከንፈሮችሽ፤
ትህትናሽ አይለይ ከቅንነትሽ።
አንገትሽ ብርሌ ወይኒቱ ማር ነሽ።
እቀፉኝ ቢል እንኳ ደግፉኝ አይልም ምርኩዝ የማያሻው አቋቋመ መልካም
ወጣቱ ጡትሽ።
ጨዋታ አዘውታሪ ቀበጥ ነው ዳሌሽ።
ተረከዘ ሎሚ ጫማ የሌለሽ
ነይልኝ ያገር ልጅ አውቃለሁ አለሽ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
የትናየት ፈሩ