እ.ኤ.አ ሰኔ 19 ቀን 1942 ዓ.ም፤ የአባጅፋር አገር ጅማ ከተማ፤ የኦሮሞ ብሔር አባል ከሆኑት ኢትዮጵያዊ እናቱና ከየመናዊ አባቱ ተወለደ ፤ ዓሊ አብደላ ኬይፋ። በልጅነቱ ከጅማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ጣልያን ሰፈር የመጣው ዓሊ፣ መርካቶ አካባቢ በሚገኘው የመን ማህበረሰብ ትምህርት ቤት በመግባት የአረብኛ ቋንቋ መማር ጀመረ። በዚህ ት/ቤት ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገባ።
ከልጅነቱ ጀምሮ እግር ኳስ መጫወት በጣም ይወድ ነበርና ለትምህርት ቤቱና ሀረር መስፍን ተብሎ ይጠራ ለነበረ የእግር ኳስ ቡድን፤ በመቀጠልም በጊዜው ተወዳጅና ታዋቂ ለነበረው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡
ዓሊ ገና የ14 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር የእንጀራ አባቱ ከጅማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ቡና እየላኩለት ይሸጥ ነበር። ታዳጊው ዓሊም ለበርካታ ጊዜያት የቡና ንግዱን ካከናወነ በኋላ የእራሱን ንግድ መጀመር በሚያስብበት ጊዜ ወላጅ እናቱ በአስገራሚ ሁኔታ የንግድ መነሻ ገንዘብ እገዛ እንዴት እንዳደረጉለት ሲናገር። “የራሴን ንግድ ስራ ለመጀመር የቻልኩት ወላጅ እናቴ በወቅቱ የነበራትን የወርቅ ቀበቶ ሸጣ መነሻ የሚሆነኝን ገንዘብ ስለሰጠችኝ ነው፡፡” ብሏል። በዚህ ገንዘብ ዓሊ ቺፖሊኒ ተብሎ ይታወቅ የነበረ ከአስመራ ከተማ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ሸራ ጫማ ብቸኛ ወኪል በመሆን ያከፋፍል ነበር።
ዓሊ ለስድስት ዓመታት ያህል ብቸኛ ወኪል በመሆን የቺፖሊኒ ጫማ ሲያከፋፍል ከቆየ በኋላ የሶኒ /Sony/ ምርት የሆኑ እንደ ሬዲዮ፣ ቴፕ ሪከርደር፣ ቴሌቪዥን፣ የሶኒ ካሴቶች የመሳሰሉ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማከፋፈል ጀመረ። በዚህ የሶኒ ምርቶች ማከፋፈል ሥራ ላይ ተሠማርቶ በነበረበት ወቅት ዓሊ ሪል ቴፕና ካሴት የሚያጫውት ሪከርደር ነበረው፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን አንድ የማይታወቅ ግለሰብ ይህንን ሪከርደር በዱቤ ሸጥልኝ ብሎ ይጠይቀዋል። ዓሊም “ምንም ችግር የለም” በማለት ቴፑን በ3000 ሺህ ብር በዱቤ ይሰጠዋል። ሆኖም ግን ግለሰቡ እዳውን ሳይከፍል እልም ብሉ ይጠፋል።
ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ ይህ ዱቤ ሳይከፈል የቀረው ግለሰብ በመሐል ፒያሣ ካሊፕሶ ሙዚቃ ቤት መጨረሻ ፋሽን እና አንድ መጽሐፍ ቅዱስ መሸጫ መደብር በአጠቃላይ ሦስት ሱቆች እንዳሉት አሊ በመረዳቱ ወደ ግለሰቡ ሱቅ ሄዶ እዳውን እንዲከፍለው ሲጠይቀው ግለሰቡ እዳውን ለመክፈል ባለመቻሉ ካሊፕሶ ሙዚቃ ቤት በሚባለው የንግድ ቤቱ ተደበቀ። ተደብቆም አልቀረም፤ ከዓሊ ዓይን ለማምለጥ ሳይችል ቀረ፡፡
ከዚያም “ዓሊ ገንዘቡን ለምን አትከፍልም?” ብሎ ቢጠይቀው ግለሰቡም በጊዜው መክፈል እንደማይችል ይነግረዋል። ዓሊ ግን “በቃ ገንዘቤን መክፈል ካቃተህ ይህንን ሱቅ ገንዘብ ጨምሬልህ ለእኔ ሰጠኝ!” በማለት 3,000 ሺህ ብር ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስት ሺህ ብር ከፍሎ ካሊፕሶ ሙዚቃ ቤትን ወደ ታንጐ ሙዚቃ ቤት በመለወጥ የእራሱ አደረገው።
ዓሊ ካሊፕሶ ሙዚቃ ቤትን የእራሱ ካደረገው በኋላ በሙዚቃ ቤቱ ውስጥ የእንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና የፈረንሣይኛ ሙዚቃ ሸክላዎች ያገኛል። ይህ አጋጣሚ ዓሊ ወደ ሸክላ መቅረፅ ሥራ እንዲገባ አነሳሳው። ከዚያ በኋላ ነው ዛሬም ድረስ የምንሰማቸው የነ አስቴር አወቀ ፤ ሙሉቀን መለሰ ፤ ንዋይ ደበበ፤ አሊ ቢራ፤ መሀሙድ አህመድ ፤ ብዙነሽ በቀለ ፤ ሂሩት በቀለ እና ሌሎች ተወዳጅ ድምጻውያን ካሴቶች እጃችን ላይ ደርሰው በሙዚቃ ሀሴት ያደረግነው፡፡
ታንጎ ሙዚቃ ቤት ካይፋ ሪከርድስ በተለይም ለወጣት ድምፃውያንና ለሌሎችም ዕውቅ ድምፃውያን ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1977 ዓ.ም. ብቻ 53 የሚሆኑ የሙዚቃ ሥራዎችን አሳትሞ ለሕዝብ አቅርቧል። እሱ ይህን ሲሰራ ከዝነኛው ሴኮ ሰዓት ጋር ያስተዋወቀው ደግሞ ወንድሙ መሀመድ ነው። ሌላኛው ወንድሙ አህመድ ቡከር ደግሞ እንደ አሊ ኳስ ተጫዋች ሆኖ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስከ መጫወት ደርሷል።
ታዋቂው የሙዚቃ አሳታሚ አሊ ከአመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30 /2014