ከኦሊምፒክ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው ጠረጴዛ ቴኒስ እአአ ከ1988 በታላቁ መድረክ ውድድር እየተደረገበት ይገኛል። በዚህ ስፖርት እንደ ቻይና ያሉ አገራት በውጤታማነት ተጽእኖ ፈጣሪዎች ሲሆኑ፤ በአንጻሩ በአፍሪካ የናይጄሪያ እና የሰሜን አፍሪካ አገራት የበላይነቱን ይይዛሉ። የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት በኢትዮጵያ እንደ መዝናኛ ተዘውታሪ ከሆኑ ስፖርቶች አንዱ ቢሆንም ትልቅ ትኩረት ባለማግኘታቸው በውጤታማነት መራመድ ካልቻሉ ስፖርቶች መካከልም ይጠቀሳል።
ፈጣን እንቅስቃሴና ቅልጥፍናን የሚጠይቀው ይህ ስፖርት በተለይ በታዳጊ እና ወጣቶች በስፋት ይዘወተራል፤ ስፖርቱ ለአእምሯዊም ሆነ አካላዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ባለሙያዎች ያረጋግጣሉ። ይሁንና ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝቧ ወጣት በሆነው ኢትዮጵያ በስፖርቱ ተጠቃሚ መሆንም ሆነ በትልቅ ደረጃ ስኬታማ ለመሆን አልቻለችም። ነገር ግን በጥቂት ክለቦችና በግለሰቦች የግል ጥረት በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ከሆኑ አገራት ተርታ ኢትዮጵያም ልትሰለፍ ችላለች።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖች አባል ከሆነችባቸውና ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ ስፖርተኞች መካከል አንዱ የጠረጴዛ ቴኒስ ሲሆን፣ የዓለም አቀፉ ጠረጴዛ ቴኒስ አባል የሆነችው 1964 ዓ.ም መሆኑ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። እአአ በ2013 የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ማህበር ሲቋቋምም ከመስራቾቹ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች።
ኢትዮጵያ በቀጣናው መልካም የሚባል እንቅስቃሴ እና ተቀባይነት ያላት አገር በመሆኗም የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮናን ለማዘጋጀት በቅታለች። ኢትዮጵያ ከ28 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ቻምፒዮና ታዘጋጃለች፤ ይኸውም ለአገር ገጽታ ግንባታ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል። ከዓመታት በኋላ ለሚደረገው ለዚህ ውድድር ሲደረግ የቆየው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆም ቻምፒዮናው ትናንት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መጀመሩን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባዘጋጀችው ቻምፒዮና ሜዳሊያ ውስጥ መግባት መቻሏ ይታወሳል። በውድድሩ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበችውም ዩጋንዳ እአአ በ2019 ባስተናገደችው ውድድር ነበር። በወቅቱም አንድ የወርቅ እና ሁለት የነሃስ ሜዳሊያ መገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን በስሩ 14 አገራትን ያቀፈ ቢሆንም በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እየሆኑ የሚገኙት ስምንት አገራት መሆናቸውም ታውቋል። እነርሱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኮሞሮስ፣ ሲሼልስ፣ ሞሪሺየስ፣ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ ናቸው። ውድድሩ በነጠላና በቡድን የሚደረግ ሲሆን፤ የውድድሩ ተሳታፊ አገራት በወንድና በሴት እስከ አምስት አትሌቶች የማሳተፍ እድል አላቸው። ኢትዮጵያ በበኩሏ የውድድሩ አዘጋጅ አገር በመሆኗ ተጨማሪ ተወዳዳሪዎችን የማሳተፍ እድል ይኖራታል። በዚህም መሰረት 10 ወንድና 10 ሴት ተጫዋቾች ዝግጅት አድርገው በውድድሩ ላይ እየተካፈሉ እንደሚገኙ ታውቋል።
ውድድሩ ከሚያዚያ 27 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ለሶስት ቀናት የሚደረግ ይሆናል። ይህ ውድድር ለአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና እንደ ማጣሪያ የሚያገለግል ውድድር ሲሆን፤ በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር በአልጄሪያዋ አልጀርስ በሚካሄደው ቻምፒዮና በነጠላ ከ1 እስከ 8 ባለው ደረጃ ውድድራቸውን የሚያጠናቅቁ እንዲሁም ሁለት ቡድኖች ተካፋይ እንደሚሆኑ ታውቋል። በዚህ ውድድር የተሻሉት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና አፍሪካን ወክለው ይወዳደራሉ።
ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ከተቻለም በቀጣይ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ለማዘጋጀት እድል እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ ገልጸዋል። ቻምፒዮናው በኢትዮጵያ መካሄዱ አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ እንዲሁም ለቱሪዝምና ለሆቴሎች ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልፀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 /2014