ከእናቱ ጋር ጎን ለጎን ቁጭ ብሏል። እድሜ ድሩን አድርቶባቸው እናቱን ወደ እርጅና እሱን ደግሞ ወደ ጉልምስና ወስዷቸዋል። የእናቱ አዛውንት እጅ እንደ ልጅነት ጊዜው ከበራ ጭንቅላቱ ላይ ሊወጣ ሲታከከው ይታየዋል።
‹አይ እማ! ዛሬም ድረስ እጆችሽ ይፈልጉኛል› አለ ደስ ባለው ፊት ወደ እናቱ እያየ።
‹እናት አይደለሁ፤ እንዴት አልፈልግህም! የእናት እናትነት የሚያበቃው ስትሞት ብቻ ነው..። በሕይወት እስካለሁ ድረስ ሁሌም ትንሽ ልጄ ነህ› አሉት።
‹ያኔ ጸጉሬን ነበር ዛሬ ምኔን ትዳብሺዋለሽ ራሰ በራ ነኝ..› አለ በራውን በእጁ እያሻሻ።
‹እናት ለልጇ የፍቅር ቦታ አታጣም። በራህም ቢሆን ለእጆቼ የብዙ ፍቅር መገኛዎች ናቸው› አሉት ከቡናው ፉት እያሉ።
‹ዛሬ ላይ ለኔ ራሰ በራ መሆን ያንቺ እጆች ያሉበት ይመስለኛል። ለአስራ ስምንት አመት ያህል እጅሽ ከራሴ ላይ አልወረደም ነበር። ሲል በኃይል ሳቀ። ሳቁ እናቱንም አስቋቸው አብረው ሳቁ።
ከሳቁ መልስ መቆሚያ አላገኘም፤ እናቱን አጠገቡ አስቀምጦ ወደ ልጅነት ዘመኑ በሀሳብ መነነ። ምናኔው ውስጥ በልጅነት ገዳሙ ውስጥ የልጅነት ጸዳሎቹን ካባ ለብሰው አገኛቸው። ምናኔው ውስጥ የማለዳ ድርሳኖቹን ጤዛ ለብሰው አትሮኖስ ላይ አገኛቸው። ምናኔው ውስጥ የጠዋት ተንስኦውን በልጅነቱ አጥቢያ ውስጥ አገኛቸው። ምናኔው ውስጥ ባለቀለም ቡረቃውን ዘመን ለብሰው አገኛቸው።
ልጅነቱ የሕይወት ታሪኩ ነው። ሲሞትም ሆነ ሲኖር እንዲወራለት የሚፈልገው ያ የጠዋት ገድሉ ነው። ከአምና በቀር ለማንም የሚነግረው ሌላ ታሪክ የለውም። ከእናቱ ጋር አልቦና ክርን፣ መስቀልና አንገት ነበር።
የእናቱ ድምጽ ያን ሁሉ የዘመን ገደል ማሚቱ፣ ያን ሁሉ የዘመን ጥቀርሻ አልፎ ዛሬም ድረስ ይሰመዋል። ድምጽዋ የሚጎላበት ከእሷ በቀር ማንም ጠርቶት በማያውቀው የብቻ ስሟ ስትጠራው ነው። ‹ጌታዬ ነው› የምትለው..። ስሙ ይስሀቅ ሆኖ ሳለ ጌታዬ ብላ ነው የምትጠራው። ለምን ጌታዬ እንደምትለው አንድም ቀን አስቦት፣ አንድም ቀን ነግራው አታውቅም። በቃ ጌታዬ ትለዋለች።
ያ ጥሪ፣ ያ እናትነት ተመልሶ በአንድ ጎጆ ውስጥ ዳግሞ ቢበቅል ይላል። አሁንም ከእናቱ በቀር ማንም ጌታዬ የሚለው የለም። በይስሀቅ ውስጥ የበቀለውን ያን ሁሉ ተጽዕኖ ችላ ዛሬም ድረስ ጌታዬ ነው የምትለው። ዓለም ብዙ ሆኖ ይስሀቅ ይለዋል፤ እናቱ አንድ ሆና ጌታዬ ትለዋለች። ከዛ ሁሉ እልፍና ከዛች አንዲት ድምጽ መሀል የእናቱ ድምጽ ብቻ ነው የሚሰማው።
ከምናኔው ውስጥ ሌላም የትዝታ ሰበዝ መዘዘ። በልጅነቱ የእናቱ እጅ ካናቱ ላይ ወርዶ አያውቅም ነበር። አጠገቧ ካለ እጇ አናቱ ላይ ነው መገኛው። ታሻሸዋለች፣ ትዳብሰዋለች፣ ያልበላውን ታክለታለች። የጭንቅላቱን ግርጌና ራስጌ በጣቶቿ ትሄድበታለች። በጣቶቿ አናቱን እየቆፈረች ተባይ ይሁን ሌላ ነገር ትፈልጋለች።
አንዳንድ ጊዜ ጭኗ ላይ ደገፍ ታደርገውና፣ ጉያዋ ውስጥ ወሸቅ ታደርገውና፣ ክንዷ ላይ ጋደም ታደርገውና፣ ደረቷ ላይ ጣል ታደርገውና ትደባብሰዋለች። የእናቱ እጆች አይረሱትም..ታሞ፣ ተከፍቶ ዳብሰው ፈውሰውት ያውቃሉ። ርቦት፣ ጠምቶት አርክተውት ያውቃሉ። አዝኖ፣ ተክዞ አጽናንተውት ያውቃሉ። ታርዞ፣ ተራቁቶ አልብሰውት ያውቃሉ።
የእናቱ እጆች እንደ እግዜር እጆች ሰዎች ያላወቋቸው እሱ ብቻ ተዳብሶ የዳነባቸው መለኮታዊ ይመስሉታል። የእናቱ ጣቶች ባህር የሚከፍሉ በትረ ሙሴ ሆነው እልፍ ቀን ታዝቧቸው ያውቃል። ብዙ ጊዜ ተገርሞና ተደንቆ እጆቿን በተለይም ጣቶቿን ወደ አይኑ አቅርቦ አስተውሏቸው ያውቃል። ብዙ ጊዜ ያልደረሰበት የተሸሸገ ሚስጢር ካለው ብሎ የመዳፏን መስመሮች፣ የጣቶቿን አፈጣጠር ታዝቦት ያውቃል፤ ግን አዲስ ነገር አላገኘባቸውም ፤ግን ይፈውሱታል፤ ያጽናኑታል።
የእናቱ ጉያ የጽድቅ መንገዱ ነው፤ ቡና ስታፈላ ወይም ደግሞ ሰው ቤት ቡና ተጠርታ ስትሄድ ጉያዋ ውስጥ አይጠፋም። የልጅነቱ ብዙ ጊዜ በእናቱ ጉያ ውስጥ ያለፈ ነው። ጉያዋ ውስጥ ዛሬም ድረስ ያልደረሰበት አንዳች የጸጋና የበረከት መና አለው። አድጎ የሚያላምጠው፣ ጎልምሶ የሚያመነዥከው የሕይወት እንጀራ። በሕይወት ውስጥ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚመጡ የተፈጥሮ ጸጋዎች እንዳሉ ዛሬ ነው
የሰው ልክ ከዛሬ ካልሸሸ፣ ከአሁን ፈቀቅ ካላለ የትዝታ ሙጀሌ አይበላውም። ዛሬ ትላንት ሲሆን ሁሉም ትዝታ እንደሆነ የገባን ጥቂቶች ነን። ትላንት ላይ ሆኖ ያ የልጅነት ጊዜው እንዲህ እንደሚናፍቀው ቢያውቅ መጽናኛ ያስቀር ነበር። የሚፈጀን የሕይወት ረመጥ በዛሬና በትላንት መካከል ያነደድነው እቶን ነው። የምናከው የትላንትን እከክ ነው። ዛሬ እከክ የለውም። ወደ ነገ እንጂ ወደ ትላንት የሚሮጥ የተፈጥሮ ህግ የለንም፤ ትተንው ወደመጣንው አምና የምንመለሰው እንዲህ ባለው የትዝታ ረመጥ ነው።
አድጎ እንኳን የእናቱ እየሱሳዊ ጣቶች ይናፍቁታል። አድጎ እንኳን የእናቱ ጉያ ይመጣበታል። ዛሬ ላይ ያልሄደበት፣ ያላየው ውድና ቅንጡ ሕይወት የለም። የሰላምና የደስታ ስፍራ ወደተባለ ዓለማዊ ቦታ ተዝናንቶና ውድ ገንዘብ ከፍሎ ያውቃል።
እንደ እናቱ ጉያ ምቹና ሰላም ያለው ስፍራ ግን አላገኘም። ከሁሉም በኋላ ተመልሶ ልጅ መሆን ያምረዋል። ከሁሉም በኋላ ተመልሶ በእናቱ ማህጸን ውስጥ መብቀል ያምረዋል። ከሁሉም በኋላ በእናቱ ተምጦ መወለድ ከዛም ጌታዬ ብላ ስትጠራው የነበረው ልጅነታዊ ዓለም ያምረዋል። ምድር ላይ አንድ እድል አግኝቶ ወደኋላ የመመለስ ስልጣን ቢያገኝ ልጅ ሆኖ ራሱን እናቱ ጉያ ውስጥ ይፈጥረው ነበር። የልጆቹ ልጅነት ያስቀናዋል። በየጎዳናው የሚያያቸው ልጆች ልጅነት ያስቀናዋል።
ከሀሳቡ መልስ እናቱን ያገኛት ሶፋው ላይ እንቅልፍ ጥሏት ነበር። ባንቀላፋችበት በደንብ አያት፤ ነጭ ሽበቷ የሻሿን ድንበር ጥሶ ግንባሯ ላይ አጮልቋል። ለእሱ ኖረው ለእሱ ያረጁት እጆቿን፣ እሱን በማቀፍ የሰለሉት ክንዶቿን፣ እሱን በመዳበስ የጃጁት ጣቶቿን፣ እሱን በማየት ኖረው የሞጨሞጩት አይኖቿን አስተዋላቸው።
ለዚህ ሁሉ የሚሆን ምን ውለታ አለው? ምንም። እንደልጅነት ጊዜው አዛውንት ክንዷን ተንተርሶ አጠገቧ ጋደም አለ። እሱ ሲያንቀላፋ እሷ ነቅታ ነበር። ልጇን ክንዷ ላይ፣ እቅፏ ውስጥ ስታገኘው የተሰማት ደስታ እንደ ጥንቱ ነበር። በተኛበት አዛውንት እጇን ልካ መላጣ ራሱ ላይ አሳረፈችው..እንደልጅነቱ ልትዳብሰው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 /2014