ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ቦታ አለው። ለዚህም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ባህሎችን ማስታወሱ በቂ ምስክር ናቸው። ከጥንታዊው የአደን ሕይወት ጀምሮ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግንነት ከባህል ጋር የተሳሰረ ነው። ከዘመን ዘመን የተለያየ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ጀግንነት ትልቅ ዋጋ አለው። ለምሳሌ በቀድሞው ጊዜ ‹‹አንበሳ ገዳይ፣ ነብር ገዳይ›› እየተባለ ይሞገስ ነበር። አነጣጥሮ ዒላማውን የሚመታ ሰው ‹‹ተኳሽ›› እየተባለ ይጠራ ነበር።
እንደየዘመኑ የተለያየ መሆኑን የምናውቀው ደግሞ አሁን ላይ በምናየው የጀግንነት ትርጉም ነው። ጀግንነት እንደ ዘመኑ ሁኔታ ትርጉሙ እየሰፋ መጥቷል። ጀግንነት ከጦር ሜዳ ውሎ ወደ የልማትና መሰል ጉዳዮች መግለጫም እየሆነ ነው። ለምሳሌ በገጠር አካባቢ አንድ አርሶ አደር ለእርሻ አስቸጋሪ የሆነን ማሳ አሳምሮ አለሳልሶ ከታየ ‹‹እገሌ እኮ ጀግና ነው›› ይባላል። በዝናብ ሲያርስ ፣ ሲያርም የታየ ገበሬ ‹‹አይ ጀግና›› እየተባለ ሲሞገስ ይሰማል። ወደ ትምህርት ቤትም ስንሄድ አንደኛ የሚወጣ ተማሪ ‹‹የእገሌ ልጅ ጀግና እኮ ነው›› ይባላል፤ በጓደኞቹ ዘንድም ትልቅ ክብር ይሰጠዋል።
ሌላው ጀግንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል መሆኑን የምናውቀው በሰርግ እና በሌሎች የድግስ ጉዳዮች ላይ ሲጫወቱ የሚወዳደሱት ጀግንነትን መሰረት በማድረግ መሆኑም ላይ ነው። በእዚህም የቀደምት አባቶችን ገድል መዘከር ብቻ ሳይሆን የአሁን ልጅም ጀግና መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ። አባቴ ጀግና ነበር ማለት ብቻ ሳይሆን ራሱ ጀግና ሆኖ ማሳየት እንዳለበት ለመጠቆም እንዲህ እየተባለም ይዘፈናል።
አርገው ሞቅ ሞቅ እንደ ደሬ ፍም
የአባት ጀግንነት ለልጅ አያልፍም!
ደሬ የሚባለው የዛፍ አይነት ነው፤ ሲደርቅ ማገዶ ይሆናል። የደሬ እንጨት ፍሙ ቶሎ አይጠፋም። ለዚህም ነው ደሬ የተባለውን እንጨት የመረጡት። የአባቱ ጀግንነት ብቻውን እንደማይበቃና ልጁም ጀግና መሆን እንዳለበት ለማስገንዘብ የሚቋጠሩ ስንኞች ናቸው።
የእረኞችን ጨዋታ እንኳን ብናስተውል በማሸነፍና በመሸነፍ ላይ የተመሰረተ ነው። ድንጋይ በማቆም ዒላማ መጫወትን ለእዚህ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ከርቀት ሆኖ የቆመውን ድንጋይ በተወርዋሪ ድንጋይ መምታት መቻል የጀግንነት ምልክት ነው። እረኞች ከኮባ ወይም ከሸንበቆ የተዘጋጀ ጠመንጃ መሰል ነገር መያዝ ይወዳሉ። ይሄ እንግዲህ ከማህበረሰቡ ተነስተው በአቅማቸው ልክ የትጥቅን አስፈላጊነት የሚገልጹበት ነው፤ ከስር ከስር እያሉ የሚያድጉበት።
ጀግንነት ጥበብ ነው። በጦርነት ታሪክ ውስጥ በተለይም ኢትዮጵያውያን በጥበብ እንደሚያሸንፉ በብዙ የታሪክ ጸሐፍት ተጽፏል። ታላቁን የዓድዋ ድል እንኳ ብንወስድ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው የጣሊያን ሰራዊት በጦር፣ በጎራዴና በኋላቀር መሳሪያ ነው ውርደትን የተከናነበው። ለዚህም ኢትዮጵያውያን አርበኞች የተጠቀሙት ጥበብ ነው።
ዛሬ በምናከብረው የአርበኞች የድል ቀን እንኳ ብዙ ጥበብ የተሞላባቸው አሸናፊነቶችን መጥቀስ እንችላለን። ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› በሚለው በታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው ራስ አበበ አረጋይ ይህን ስልት ተጠቅመዋል።
በ1932 ዓ.ም ራስ አበበ አረጋይ ለጣሊያን ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት ጣልያንን አጃጅለውት ነበር። ይህ መጭበርበር የደረሰበትም ምክትል እንደራሴና የሸዋ ገዥ የነበረው ጄኔራል ናዚ ነው። ራስ አበበ አረጋይ ለናዚ ‹‹እጄን ሰጥቻለሁ›› በማለት ለአርበኞች ጓደኞቻቸው ‹‹አይዟችሁ እንዲህ እያልኩ እያታለልኳቸው ነው›› እያሉ ይልኩባቸው ነበር። ናዚም ምንም ሳይጠረጥር እውነት መስሎት የሰላም ድርድሩን ተያያዘው። በኋላም ራስ አበበ አረጋይ ጦሩ ቀደም ሲል ከደረሰበት ጥቃት ማገገሙን ሲያረጋግጡ ጣሊያንን ‹‹ዞር በል!›› በማለት ትግላቸውን ቀጠሉ።
ሌላኛው የጦርነት ስልታቸው ደግሞ በወቅቱ የማይጠረጠሩትን ሴቶችን ማሰለፍ ነበር። ለዚህም እነ ሸዋረገድ ገድሌና አርበኛ ከበደች ሥዩም ተጠቃሽ ናቸው። እዚህ ላይ በዓድዋው ጦርነትም የእቴጌ ጣይቱ ጥበብ ተዳጋግሞ መጠቀሱን ልብ ይሏል። የጣሊያን ምርኮኛ መስለው የሰራዊቱን ጥንካሬና ድክመት ያጠኑ ሰላዮችም ነበሩ።
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ መንገድ ያታልሏቸው ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያውን በባዶ እግራቸው የሚሄዱም ስለነበሩ የእግራችንን ዳና እየተከተለ ጠላት ያጠቃናል ብለው የጠረጠሩ አርበኞች አንድ ዘዴ ፈጠሩ። ለምሳሌ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ መሄድ ፈልገው ከሆነ የእግር ዳና በመፍጠር ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ይሄዳሉ። ከዚያም የእግር ዳና ሳይፈጥሩ ወደ ምዕራብ ይመለሳሉ። ጠላት ወደዚያ የሄዱ መስሎት ዳና ተከትሎ ሲሄድ ከኋላ ያጠቁት ነበር።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጀግንነትን ነገር እናንሳ ከተባለ እያንዳንዷ ዕለት ጀብዱ የተፈጸመባት ትሆናለች። ዳሩ ግን ሦስት ቀኖች ደግሞ በተለየ መልኩ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ናቸው። የካቲት 12፣ የካቲት 23 እና ሚያዚያ 27 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው። የካቲት 12 ግፈኛው ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈበት ሲሆን ፣ የካቲት 23 የአድዋ ድል ፣ሚያዚያ 27 ጀግኖች አርበኞች አምስት አመት ሙሉ ፋሽስት ጣልያንን ተዋግተው ያሸነፉበት የድል በአል ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ሦስት ቀናት ከጣሊያን ወረራ ጋር የተያያዙ ናቸው።
እነዚህን ሁሉ ድሎች ከየት አመጣናቸው ከተባለ፤ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የኢትዮጵያ ባህልና ጥበብ ስለሆነ ነው። ለዚህም ነው የጥበብ ሥራዎቻችን ጀግንነትን ገላጭ የሆኑት። እነዚህ የጥበብ ሥራዎች ደግሞ የህዝብ የቃል ግጥሞች ናቸው። የመድረክ ቴአትሮች ወይም ፊልሞች ቢሆኑ ኖሮ ከእነዚህ ድሎች በኋላ የታሰበ ሊመስለን ይችል ነበር። እንዲያውም ፊልሞቻችን ናቸው ሕዝባዊ የጥበብ ሀብቶቻችንን መነሻ አድርገው የተሰሩት።
ዛሬ የአርበኞችን ቀን እያከብርን ነው። ቀኑ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶችን በማስታወስ ይከበራል። በዚህ ዓምድ ደግሞ አርበኝነትን የሚገልጹ የሕዝብ ቃል ግጥሞችን እናስታውሳለን።
የኢትዮጵያ ጀግኖች ስማቸው ሲነሳ
በሩቅ ያስፈራሉ እንደ ዱር አንበሳ
ይህ የአርበኝነት ስንኝ በተለይም በዘፈኖች ውስጥ ነው የሚሰማው። ምናልባትም መነሻው የሕዝብ ሆኖ ይሆናል በብዙ የአርበኝነት ዘፈኖች ውስጥ የምንሰማው፤ እንዲህ እንደ አርበኞች ቀን አይነት የድል በዓል ሲከበር ደግሞ ኢትዮጵያውያን በቡድን በቡድን ሆነው በሕብረ ዝማሪ ይጫወቱታል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ጀግንነት ባህል ነው ብለናል። ኢትዮጵያዊ መደፈርን አይቀበልም፤ ይህ መደፈርን ያለመቀበል ባህል ነው ወራሪን ሁሉ እያሳፈረ የመለሰው። ለዚህ የጀግንነት ባህል ደግሞ ፉከራዎቻችን ምስክር ናቸው። ትዕግስትንም ይችልበታል፤ ታግሶ ታግሶ ካልሆነ ግን ልኩን ያሳየዋል።
እልም ነው ውሃ አይላመጥም
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም!
ይህ ስንኝ የሚነግረን ጠንካራ አለመሆንን ሳይሆን ጠላትን በቆራጥነት የመዋጋትን ፋይዳ ነው። የፈሩኝ ከመሰለው ጭራሽ እየባሰበት ነው የሚሄድ። በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የጀግንነት ባህል ውስጥ ፀብን ቀድሞ መጀመር የፈሪ ምልክት ነው። ኢትዮጵያውያን ጸብ የማይቀር ከሆነ ይዋጣልን ብለው ይፋጠጣሉ፤ መሳሪያ እስከማስመረጥ ይደርሳሉ እንጂ ቀደመው አይጀምሩም፤ በሌላም በኩል ጀግና ማለት በትዕግስት የሚያሸንፍ መሆኑን ይገነዘባሉ። ታግሰው ታግሰው አውጥተው አውርደው የማያዳግም እርምጃ ይወስዳሉ፤ አትድረሱብን ባይ ናቸው ፤ ሲደረስባቸው ደግሞ አይምሩም።
ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን ከነብር ጋርም ያመሳስሉታል።
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው! ይላሉ።
ነብር በባህሪው እንደ ሌሎች እንስሳት ቀድሞ የመተናኮል ባህሪ የለውም፤ ከተተናኮሉት ግን አይለቅም። የጦር መሳሪያ የያዘ ሰው ሳይቀር ይተናነቃል። የጀግንነት መጀመሪያው ፀብን ቀድሞ አለመጀመር መሆኑን ለመግለጽ ነው ነብርን ተምሳሌት ያደረጉት።
ተመክሮ ተመክሮ አልመለስም ያለ ጠበኛ ዋጋውን ማግኘት እንዳለበት ያምናሉ። ዳግም እንዳያስበው አድርገው አይቀጡ ቅጣት መቀጣት እንዳለበትም ነው የሚያምኑት፤ ለዚህም ይመስላል ፡-
በክላሽ መንጥሮ በምንሽር ማረስ
አረም አያበቅልም እስከወዲያው ድረስ እያሉ የሚያንጎራጉሩት።
ከዕለት ከዕለት ሥራዎቻቸው ጋር አገናኝተው ይገልጹታል ማለት ነው። ምንጣሮ ለእርሻ የሚሆን ማሳ ማዘጋጀትን ይመለከታል፤ ዛፎችን፣ ቁጥቋጦዎችንና ሌሎች ነገሮችን በማንሳት መሬቱን ለእርሻ ዝግጁ ማድረግ ማለት ነው። በሚገባ ተመንጥሮና ተለሳልሶ የታረሰ መሬት አረሙ አያስቸግርም። ይህን ሁኔታም በክላሽ መንጥረን መንጥረን ከጣልነው ድጋሚ አያንሰራራም ማለታቸው ለእዚህ ነው።
እነዚህ ጀግኖች አስቀድመው ‹‹ተው ሰላም ይሻለናል›› ብለው የሚለማመጡ ናቸው። ፈሪ ግን ሲታገሱት የፈሩት ይመስለዋል።
ኧረ ተው አንተ ሰው ስሸሽ አታባረኝ
ለአንተም ግፉ በዛ እኔንም መረረኝ! ይለዋል።
ይህን ብሎት ካልተመለሰ አባራሪው የግፉን ዋጋ ይከፍላል ማለት ነው። አንዳንድ ሀብታም ምናልባት የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ስላለ የሚፈራ ይመስለው ይሆናል። ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ እንደሚያደርጉት ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ቆራጡ ድሃ ፡-
አትንኳት ጎጆዬን በአንድ እግሯ ቆማለች
ትልቁን አዳራሽ ይዛው ትጓዛለች! ሲል ይገልጻል።
አንተ ሀብታም ነኝ፣ ባለጊዜ ነኝ ብለህ ብትመጻደቅም የሌሎችን ጎጆ ካላከበርክ ያንተም ህንጻ ይፈርሳል፤ ይደረመሳል፤ እንዲያውም ከእኔ በላይ አንተ ትጎዳለህ ማለቱ ነው።
አሁን ደግሞ ከሕዝብ ስነ ቃል እንውጣና ከፋሽስት ጣሊያን ጋር የተያያዙ ግጥሞችን እንጠቃቅስ። እነዚህ ግጥሞችም መነሻቸው የኢትዮጵያ የጀግንነት ባህል ነው። ግጥሞቹን ከተክለጻድቅ መኩሪያ የታሪክ መጽሐፎች ላይ ያገኘናቸው ናቸው።
ጣሊያን ኮሶ ጭኖ ሸዋን ሊያጠጣው
ገና ሲበጠብጥ ዳኘውን ቀናው
ቅዳሜ ተግዞ እሁድ ተበራየ
መስኮብም ገረመው ጣሊያንም ጉድ አየ!
አገርክን ምኒሊክ እንዳሁን ፈትሻት
ባያይህ ነውና ጠላትህ የሚሻት!
እነዚህ በዓድዋ ጊዜ የተገጠሙ ስንኞች በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜም ለኢትዮጵያ አርበኞች ትግል ወኔ መቀስቀሻ በመሆን አገልግለዋል። ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ተዘጋጅታ ስትመጣ ‹‹እስኪ ያንኑ የለመደችውን መድኃኒት (ጎራዴና ጥይት) ስጧት›› ተብሏል።
እስኪ ለጣሊያኖች መድኃኒት ስጧቸው
የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው
በማለትም ኢትዮጵያውያን ተቀኝተዋል። ጣሊያኖችም በድጋሚ በመጣ እግራቸው የእጃቸውን አግኝተው ተመልሰዋል።
የሞሶሎኒ አሽከሮች ሁሉም ሎጋ ሎጋ
ሲመጡ በፈረስ ሲመለሱ በአልጋ
ተብሎላቸዋል። የሞሶሎኒ አሽከር የነበሩት እነ ግራዚያኒ በጀግኖች በእነ ሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ ቦምብ ተጥሎባቸው ቆሳስለው ነው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት።
በዚህ የአርበኞች ቀን የሚታወሱት በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ የተሳተፉት ብቻ አይደሉም። በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ያስከበሩ ጀግኖች ናቸው። ስለዚህ እኛም በአርበኞች ስም ሁሉንም እያመሰገንን ከተወደሱባቸው ስንኞች በሚከተሉት እንሰናበታለን።
በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈፀመ ጣሊያን ሐበሻ እንዳይደርስ
ጣሊያን ሰሀጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ
እንደ ገብስ ቆላው አሉላ አባ ነጋ
ዮሐንስ መብቱን ላሉላ ቢሰጠው
እንደ ቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው
ጣልያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው
አጭዶና ከምሮ እንደ ገብስ አሰጣው!
አሉላ አባነጋ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተኩሶ!
አሉላ አባነጋ ካስመራ ቢነሳ
ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ።
ጣሊያን በሀገርህ አልሰማህም ወሬ?
የበዝብዞች አሽከር የነ ሞት አይፈሬ
ዘለው ጉብ ይላሉ እንደ ጎፈር አውሬ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27 /2014