የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይከናወናሉ። በዚህ ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጅ አገር ኮትዲቯርን ጨምሮ አስራ አራት አገራት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በገለልተኛ ሜዳ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሰሞኑን ከካፍ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሜዳዋ እንዳታከናውን ከታገደች ከአንድ አመት በላይ ሆኗታል፤ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች እገዳውን ለማንሳት ካፍ ስቴድየሞቿን በሁለት የተለያዩ ጊዜዎች ከገመገመ በኋላ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ ታውቋል። ካፍ በስቴድየሞቹ መስፈርት ዙሪያ ግምገማውን ጨርሶ ብቁ ሆነው ካልተገኙ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን የምታደርግበት ገለልተኛ ሜዳ እንድታሳውቅ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊና ጊኒ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ ከወር በኋላ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከማላዊ አቻዋ ጋር ከሜዳዋ ውጪ ታደርጋለች። በመጪው ሰኔም ከግብጽ ጋር በሜዳዋ ትጫወታለች። ካፍም ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሜዳዋ ውጪ በማድረጓ ለጊዜውም ቢሆን ገለልተኛ ሜዳ በአስቸኳይ የመምረጥ ግዴታ ውስጥ እንዳትገባ ማድረጉ ይታመናል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ጨዋታ በሜዳዋ የምታከናውን በመሆኑ ቢያንስ ከወር ባልበለጠ ጊዜ መስፈርት የሚያሟላ ስቴዲየም የማዘጋጀት ግዴታ ይኖርባታል።
ለዚህም ቀጣዩን የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚያስተናግደው የባህርዳር ስቴድየም ባለፉት በርካታ ወራት በካፍ ግብረመልስ መሰረት የተደረገለት እድሳት ተጠናቆ ብቁ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተደርጓል። ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳታስተናግድ ከአመት በፊት በካፍ ከመታገዷ አስቀድሞ የባህርዳር ስቴድየም በብቸኝነት አለም አቀፍ ጨዋታዎች ሲካሄዱበት መቆየቱ ይታወቃል። ስቴድየሙ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የነበረውም በካፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ከስር ከስር የማሻሻያ ስራዎችን እንዲያከናውን ተደርጎ ነበር። የማሻሻያ ስራዎቹ እየተከናወኑ በነበረበት ሁኔታም ካፍ በቂ ማሻሻያ አልተደረገም ብሎ በማመን ለእገዳ ዳርጎታል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለኳታሩ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታዎች ጋናንና ዚምቡዋቤን ከሜዳው ውጪ ለመግጠም ተገዶ እንደነበር ይታወሳል።
ኬንያ፣ ዩጋንዳና ርዋንዳም ስቴድየሞቻቸው ከተገመገሙ በኋላ ገለልተኛ ሜዳ መርጠው እንዲያሳውቁ ካፍ እድል እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ከስቴድየሞች የካፍን መስፈርት አለሟሟላት፣ ከጸጥታና ሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ በርካታ አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበትን ገለልተኛ ሜዳ ከወዲሁ እያሳወቁ ይገኛሉ። ቡርኪናፋሶ፣ ሌሴቶ፣ ናሚቢያ፣ ደቡብ ሱዳንና ቡሩንዲን የመሳሰሉ አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን በሞሮኮ ለማድረግ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፤ ታንዛኒያን የመሳሰሉት አገራት በሜዳቸው ጨዋታዎችን ማስተናገድ ካልቻሉ ገለልተኛ ሜዳ መርጠው በቅርቡ ለካፍ ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጋምቢያ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ዚምባቡዌ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በሴኔጋል ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል፤ ጊኒና ዛምቢያም ሴኔጋል ላይ ጨዋታቸውን የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውና ውሳኔ ላይ ግን እንዳልደረሱ ታውቋል።
የአፍሪካ ዋንጫውን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ የምትገኘው ኮትዲቯር የማጣሪያ ጨዋታዋን የምታደርግበትን ስቴድየም ለካፍ አለማስመዝገቧ አነጋጋሪ ነው። ኮትዲቯር የካፍን መመዘኛዎች የሚያሟላ ስቴድየም ከሌላቸው አገራት ተርታ ተፈርጃ የመጨረሻ አለም አቀፍ ጨዋታዋን በቤኒን ማድረጓ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ እየተገነባ የሚገኘውንና ሃያ ሺ ተመልካች የሚይዘውን ያሙሱክሮ ስቴድየምን ለቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታዎች ለመጠቀም ከካፍ ፍቃድ ጠይቋል።
የአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጅ ኮትዲቯርን ጨምሮ የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያካሂዱበት ገለልተኛ ሜዳ እንዲያሳውቁ ካፍ ጥያቄ ካቀረበላቸው አስራ አራት አገራት መካከል ማላዊ፣ ጋምቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ዚምባቡዌ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳው፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክና ርዋንዳ ይገኙበታል።
ካፍ ዝቅተኛውን መስፈርት አያሟሉም ያላቸው ሃያ የአፍሪካ ስቴድየሞች ምንም አይነት አለም አቀፍ ጨዋታ እንዳያስተናግዱ ባለፈው አመት ማገዱ ይታወቃል። ካፍ በስቴድየሞቹ ላይ የጣለው እገዳ አሁንም ያልተነሳ ሲሆን አባል አገራቱም የስቴድየሞቻቸውን ደረጃ ለማሻሻል የእድሳት ስራዎችን ጨምሮ አዲስ ግንባታዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ካሜሩንን የመሳሰሉ ከአምስት ያልበለጡ አገራት ብቻ የካፍን መስፈርት የሚያሟሉ ስቴድየሞች እንዳሏቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014