ሰሞኑን በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ግርግሮች ተፈጥረው ታይተዋል፤ በጎንደር በአንድ የእስልምና እምነት አባት ቀብር ስነስርአት ወቅት በአንዳንድ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የተከሰተን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ በተቀሰቀሰ ግርግር በሙስሊሞች ላይ አስነዋሪ ድርጊት ተፈጽሟል። ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎችንም የክልሉ መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሏል። ግርግሩ አንዳንድ ከተሞችን እየነካካና እያስፈራራ አዲስ አበባም ጎራ ብሏል።
የጎንደሩ ድርጊት በቁጥጥር ሥር ውሎ፤ ተጠርጣሪዎችም ተይዘዋል በተባለበት ሁኔታ፤ ጥፋትን በጥፋት ለመመለስ በተደረገ ሙከራ ተጨማሪ ጥፋቶች በስልጤ ዞን ወራቤ ተፈጽሟል። በዚህም የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ አብያተ ክስርቲያናት ተቃጥለዋል። እነዚህ ተጨማሪ ጥፋቶች ደግሞ የሽብር ድርጊት የተጫናቸው ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ፖለቲካዊ ዓላማዎች ያላቸው ናቸው።
ግርግሩን በየአካባቢው ለማስነሳት እንደመሞከሩ የተቀናጀ ነበር ለማለት ያስደፍራል፤ በአዲስ አበባ በኢድአልፈጥር በአል ላይ በመስቀል አደባባይ የተከሰተው ግርግር በንብረትና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት አስከትሏል። በከተማዋ ከበአሉ ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ከአፍጥር ስነስርአት በሁዋላም በአንዳንድ አካባቢዎች የማወክ ድርጊቶች ታይተዋል።
ከትናንት በስቲያ ከሽሮ ሜዳ ወደ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት እየሄድኩ ነበር። ታክሲ ውስጥ አንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ሕጻን ልጅ ይዘው ገቡ። በማህበራዊ ገጾች ሲዘዋወር የነበረውን ተንቀሳቃሽ ምስል እና ፎቶዎች ብዙ ሰው አይቶ ስለነበር ምን እንደተፈጠረ ስለሁኔታው ጠየቅናቸው። በእውነቱ ምን ተፈጥሮ እንደሆነ አያውቁም፤ እርሳቸው የሚያውቁት ግርግርና ወከባ መፈጠሩን ብቻ ነው።
እርግጥ ነው እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው ወደቦታው የሄደው ሰው ይህን አያውቅም፤ ይህን የሚያውቁት ተልዕኮ ይዘው የሄዱ ጥቂት አካላት ብቻ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ምስክሩ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው መሄዳቸው ነው። መቼም ሁከትና ግርግር ያሰበ ሰው ሕጻን ልጁን ይዞ ይሄዳል ተብሎ አይታሰብም። በተፈጠረው ግርግር በርካታ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ተነጥለው የማፈላለግና የማገናኘት ሥራዎች ሲሰሩ ውለዋል።
የጠፋው የሰው ህይወትና የወደሙ ንብረቶች ሲታሰቡ ግርግሮች ጉዳት እንጂ የሚያመጡት ጥቅም እንደሌለ እንረዳለን፤ እርግጥ ነው ግርግር የሚጠቅመው ለሌባ ነው፤ ግርግር የሚጠቅመው ራሱን ግርግር ፈጣሪውን ብቻ ነው። ህብረተሰቡን አይጠቅምም፤ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ነገሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ ሲፈጸሙ ነው።
የጠላቶቻችን እጆች አሳምረን እናውቃለን፤ እነ ጭር ሲል አልወድም አሁንም አለመተኛታቸውን ከእነዚህ ግርግሮች መረዳት አያዳግትም። ግርግሮቹ የውጭና የአገር ውስጥ ጠላቶቻችን ተላላኪዎችና ጥቅመኞች ሴራ ነው። በተላላኪዎቻቸው ባለፉት አመታት በርካታ የሽብር ድርጊቶች ፈጽመዋል። ግርግሮቹም የዚያው ሴራ ሌላ ምእራፍ ነው።
እንዲያ ካልሆነ ታዲያ የራስን ንብረት ማውደም፣ የሌላን እምነት ተቋም ማቃጠል ለማን ይጠቅማል? የሌላን እምነት ተቋም ማቃጠል በአጸፋው የራስ ወገን የእምነት ተቋም ጉዳት እንዲደርስበት በር መክፈት መሆኑስ እንዴት ይዘነጋል? ለነገሩ አሸባሪና ተላላኪው ለእዚህ ግድ የላቸውም፤ የሰው ህይወት ጠፋ፣ አካል ጎደለ፣ ንብረት ተዘረፈ፣ ተቃጠለ የሚሉት ለእነሱ ጉዳያቸው አይደሉም፤ ሕጻናትና ሴቶች አዛውንቶች በተገኙበት ታላቅ በአል ላይ ግርግር በመፍጠር የጥፋት አላማን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ አላማችንን ለማሳካት ሁነኛው ቀዳዳ ይሄ ነው ብለው ነው።
ከትናንት በስቲያ መስቀል አደባባይ ከተፈጠረው ግርግር ብዙ ነገሮችን ታዝቤያለሁ። የበአሉ ታዳሚዎች የግርግሩን መነሻ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፤ በመንግሥት በኩል በተሰጠው መግለጫ ችግሩ ሁከትና ግርግር መፍጠር በፈለጉ ሰዎች የተፈጠረ ነው ተብሏል። በዕለቱ ብቻ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ 76 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም በመንግስት ተገልጸል።
በግርግሩ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሀውልትን ጨምሮ በባንኮችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል። ይህ የሚያመለክተው ድርጊቱ ታስቦበት መፈጸሙን ነው። በአካባቢው የታዩ መፈክሮችና ምስሎች ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው። ‹‹የአጼውን ሥርዓት ቀብረነዋል›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ከካርቶን የተዘጋጀ የሬሳ ሳጥን ቅርጽ ተይዟል። ከሥር ስድብ የተጻፈባቸው የመገናኛ ብዙኃን አርማ እና ሌሎች መፈክሮች ነበሩ። እነዚህ ነገሮች ታስቦባቸው የተዘጋጁ እንጂ በቅጽበት የተፈጠሩ አይደሉም።
እንግዲህ ሕዝበ ሙስሊሙ በሰላማዊ መንገድ በዓሉን ሊያከብር ሲሄድ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ዓላማ ለማሳካት ተቀላቅለው የሄዱ ነበሩ ማለት ነው፤ አማኙ ይህን ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም። ሃይማኖታዊ በዓል በሚከበርበት ዝግጅት ላይ እንደዚያ አይነት መፈክሮች ተይዞ ሊወጣ አይችልማ።
ሌላው የታዘብኩት በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ግርግሩን ለማስቆምና መረጋጋት ለማምጣት እጆቻቸውን ዘርግተው ‹‹እባካችሁ!›› እያሉ መማጸናቸውን ነው። በእርግጥም እነዚህ የሰላም መልእክተኞች በማህበራዊ ሚዲያዎች የበአሉ ታዳሚ ሙስሊም እንዲረጋጋ ሲጥሩ ታይተዋል፤ አረ እነዚህ ሰዎች ይብዙልን፤ ግርግሩ በቀላሉ በቁጥጥር ሥር የዋለውም በእነዚህ አማኞች ሰላም ፈላጊነት ጭምር ነው ማለትም ይቻላል፤ ለእዚህ ተግባራቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
ግርግሩን አስበውበትና ተዘጋጅተውበት የሄዱ ስለመኖራቸው ግን ጥርጥር የለውም፤ ያ ባይሆን ኖሮ ሃይማኖታዊ በዓል ላይ ግጭት ቀስቃሽ ምልክቶች ባልተገኙ ነበር። የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ‹‹እነዚህ ፀረ ሰላም ግለሰቦችና ቡድኖች ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተደራጅተው በአንዳንድ አካባቢዎች ስለታማ ነገሮችን፣ የውጭ አገር አክራሪዎችን አርማና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመያዝ ጥቃትና በቀል ለመፈፀም ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣታቸውን ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች እጅ ይዟል›› ሲል ከገለጸው መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው፡፡
በተንቀሳቃሽ ምስሎች ከታዩት ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና ምስሎች በተጨማሪ ስለታማ ነገሮች ሁሉ መኖራቸው ምን ማለት እንደሆነ ማንም ይገነዘበዋል። ሰላም ወዳዱ አማኝ እና የፀጥታ ኃይሉ በቀላሉ ባይቆጣጠሩት ኖሮ የታሰበው ከፍተኛ ብጥብጥ መፍጠር ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ድርጊቱ ሴራና ሽብር የተጫነው ለመሆኑ ደግሞ ሌላኛው ምልክት በዕለቱ ማታ የተሰማው ዜና ነው። ዜናው፤ የጦር መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሞከሩ የአልሸባብ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያመለክታል። በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ኤልከሬ ወረዳ ለሽብር ጥቃት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሞከሩ የአልሸባብ ቡድን አባላት ከጦር መሳሪያ እና ጥይቶቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በዕለቱ አስታውቋል። ይህም ሌላው የሽብር ሴራ ማሳያ ነው። አሁን ነገሩ የሽብር እንቅስቃሴ መሆኑ ግልጽ ሆኗል። ይህ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ግልጽ ማሳያዎች አይኖሩም፡፡
የጠላቶቻችን ሴራ ከሽፏል፤ በቀጣይም ከሁላችንም የሚጠበቀው ሰላም ፈላጊ መሆን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ሃላፊነት አለበት። በፀጥታ አካላት ላይ ብቻ የተጣለ ሥራ አይደለም። የእኔ ሃይማኖት የሚከበረው የሌላው ሃይማኖት ሲከበር ነው። ጥፋትን በጥፋት ለማካካስ መሞከርም ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ማስከተል ነው። ስለዚህ ሁሉም ይህን ልብ ሊል ይገባል፡፡
መንግሥትም የፀጥታ ሃይሉን ማጠናከር አለበት፤ በተለይም ከሽብር ድርጊት ጋር የሚያያዙ የትኛውንም ሃይማኖት ይሁን ብሄርን ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን መታገስ የለበትም። ከትናንት በስቲያ በተፈጠረው ችግር ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መግለጫ አውጥተዋል፤ የመግለጫቸው ይዘትም ድርጊቱ የአሸባሪ ኃይሎችን ተልዕኮ የሚያራምዱ ሰዎች እንቅስቃሴ መሆኑን ጠቁሟል። ስራቸው መግለጫ ከማውጣት በተጨማሪ ከህዝቡ፣ ከጸጥታ ኃይሎችና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በቅንጅት መስራትም ይኖርባቸዋል። በአዲስ አበባ የኢድ አልፈጥር በአል ሲከበር የተፈጠረውን ግርግር ለማስቆምና ህዝቡን ለማረጋጋት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያደረገው ጥረት ትምህርት ሊወሰድበትና ሊሰፋ የሚገባው ነው። ይህ ርብርብ የአሸባሪንና ተላላኪውን ሴራ በቅንጅት ማርከስ እንደሚቻል አሳይቷል፤ በቀጣይም በእዚህ መልኩ ነው መሰራት ያለበት፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014