ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱስ እንዴት አለፈ? ዓመት በዓልስ እንዴት ነበር? ጥሩ ነበር? ያው ልጆች ዓመት በዓል አልፎ በዚህ ሳምንት ትምህርት ጀምራችኋል:: የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ትምህርት ሊጠናቀቅ ደግሞ የቀሩት ግዜያት ጥቂት ናቸው:: ታዲያ ልጆች በነዚህ ግዜያት በርትታችሁ መማርና ማጥናት ይኖርባችኋል:: ያልገባችሁ ትምህርት ካለ ደግሞ መምህራኖቻችሁን፣ ወላጆቻችሁንና አስጠኚዎቻችሁን መጠየቅ አለባችሁ::
ልጆች ለመሆኑ እናንተ በምን አይነት መንገድ ነው የምታጠኑት? በትምህርታችሁ የተሻለ ውጤት ለማምጣትስ የተለየ የአጠናን ዘዴ ትከተላላችሁ? መቼም መልሳችሁ ‹‹አዎ›› እንደሚሆን አልጠራጠርም::
ሁሉም ልጆች የሚመቻቸውንና ለውጤት የሚበቃቸው የአጠናን ስልቶችን ይከተላሉ:: በተመሳሳይ ወላጆችም ልጆቻቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በተለያየ መንገድ ልጆቻቸውን ያስጠናሉ:: እናንተም የራሳችሁ የሆነ የአጠናን ስልት ሊኖራችሁ እንደሚችል እገምታለሁ::
ይሁን እንጂ በአብዛኛው ተማሪዎች በጥናት የሚጠመዱት በፈተና ወቅት እንጂ በመደበኛው የትምህርት ወቅት አይደለም:: ወላጆችም በብዛት ልጆቻቸውን ሲያስጠኑ የሚታዩት በዚሁ የፈተና ወቅት ነው:: ይህ ባለመሆኑ ታዲያ ልጆች በፈተና ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌላ ግዜም ማጥናት አለባችሁ:: ወላጆችም ልጆቻችሁን ዘወትር ማስጠናት ይጠበቅባችኋል::
ማንም ቢሆን እንዴት ማጥናት እንዳለበት አውቆ የተወለደ የለም:: ለዚህም ልጆች የተወሰኑ የማጥናት ክህሎቶችን መማርና መለማመድ ያለባችሁ:: ይህም ትምህርታችሁን በቀላሉ ለመከታተልና በክፍል ውስጥም ጥሩ አፈፃፀም እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል::
ከዚህ በታች የተዘረዘሩትና ትምህርትን በተሻለ ሁኔታ ለማጥናት የሚያስችሉ ስድስት ደረጃዎች ናቸው :: እናንተም ልጆች እነዚህን ስድስት ደረጃዎች ተግባራዊ በማድረግ ብታጠኑ በትምህርታችሁ የተሻለ ውጤት እንደምታመጡ ተስፋ አደርጋለሁ::
1ኛ፡-ትኩረት አድርጉ፤ጥሩ ጥናት የሚጀምረውም በክፍል ውስጥ ነው!
መምህራኖቻችሁ በክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ በትኩረት የምትከታተሉና ማስታወሻ የምትይዙ ከሆነ የመማርና የማጥናት ሂደት ውስጥ ገብታችኋል ማለት ነው:: ለዚህም ታዲያ ትኩረታችሁን ከሚስቡ ነገሮች ራቁ:: በተቻለ አቅም ከፊት ለፊት በመቀመጥ ትኩረታችሁን በመሰብሰብ ትምህርታችሁን ለመከታተል ጥረት አድርጉ::
2ኛ፡- ማስታወሻ ያዙ፤ የጥናት ቀላሉ መንገድ ነው!
በክፍል ውስጥ መምህራኖቻችሁ ሲያስተምሩ የሚዘረዝሯቸውን እውነታዎችንና በሰሌዳ ላይ የሚጽፏቸውን ነጥቦች ጻፏቸው:: ማስታወሻችሁን በደብተራችሁ ላይ ስታሰፍሩ በጥሩ የእጅ ጽሑፍ ይሁን:: ይህም በኋላ ላይ በቀላሉ ለማንበብ ያግዛችኋል:: ማስታወሻዎቻችሁን በየትምህርት አይነቱ ለይታችሁ መያዝም አይከፋም::
3ኛ፡- አስቀድማችሁ አቅዱ
ለዓርብ ፈተና ለማጥናት እስከ ሐሙስ ምሽት ድረስ መጠበቅ ሞኝነት ነው:: የተሻለ ውጤት ለማምጣትም አስቸጋሪ ይሆናል:: ስለዚህ ከፈተና በፊት አስቀድሞ ማቀድና ማጥናት አስፈላጊ ነው::
የፈተናና የቤት ሥራ የተሰጠበትን ቀን መዝግባችሁ ያዙ:: ይህም ከክፍል በኋላ በእያንዳንዱ ቀን ምን ምን ማድረግ እንዳለባችሁና በእያንዳንዱ ርዕስ ላይ ምን ያህል ግዜ ማጥፋት እንዳለባችሁ ለማቀድ ይረዳችኋል::
4ኛ፡-ከፋፍላችሁ ለማጥናት ሞክሩ
የምታጠኑት ትምህርት በርከት ያለ ከሆነ በየትምህርት አይነቱና እንደየርዕሰ ጉዳዩ በመከፋፈል ነጣጥሎ ማጥናቱ ይጠቅማችኋል:: ጠቅለል ባለው የትምህርት አይነት ላይ አተኩሮ ከማጥናት በውስጡ የያዘውን ርዕሰ ጉዳይ በመነጣጠል ማጥናቱ ይመረጣል::
ሌላኛው ትምህርትን ከፋፍሎ ለማጥናት የሚያግዘው መንገድ በየቀኑ ማጥናት ነው:: ይህም ሁሌ ማስታወሻዎቻችሁን ለመከለስና የተማራችኋቸውን ምዕራፎች ለመቃኘት ያግዛችኋል::
5ኛ፡- ግርታ ከተፈጠረ እርዳታ ጠይቁ
የትምህርት መሣሪያውን በሚገባ ካልተረዳችሁ በአግባቡ ማጥናት አትችሉም:: ያልገባችሁ ነገር ካለ መምህራኖቻችሁን ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ:: የተፈጠረውን ግርታ ማስታወሻዎቻችሁን ዳግም በማንበብም መፍታት ትችላላችሁ:: በቤታችሁ ሆናችሁ ያልገባችሁ ነገር ካጋጠማችሁ ደግሞ ወላጆቻችሁን በመጠየቅ መረዳት ይቻላል::
6ኛ፡- በቂ እንቅልፍ ውሰዱ
እንበልና ፈተና ነገ ነው:: እናንተ ደግሞ የጥናት እቅዳችሁን ተከትላችሁ ለፈተናው ደርሳችኋል:: ይሁንና በድንገት ያጠናችሁትን ላታስታወሱ ትችላላችሁ:: ሁለት ሲደመር ሁለት ስንት እንደሆነ ሊጠፋባችሁም ይችላል:: አትረበሹ ልጆች!
አዕምሯችሁ የሰጣችሁትን ሁሉንም መረጃዎች እስኪያጣጥም ድረስ ግዜ ይፈልጋል:: ለአዕምሯችሁ እረፍት ከሰጣችሁትና ጥሩ እንቅልፍ ከወሰዳችሁ ታዲያ በጧት ወደ እናንተ በሚመጣው ነገር ትገረማላችሁ::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም