ባሕላዊ እሴቶቻችን ሰዎች በማኅበራዊ ሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ከሰዎች ጋር እየተጋሩ እንዲሻገሯቸው እንጂ ብቻቸውን እንዲጋፈጧቸው የሚጋብዙ አይደሉም:: መረዳዳትና መደጋገፍ ኢትዮጵያዊ ወጋችንና ባሕላችን ነው:: ደካማን ማገዝ፣ ያዘነን ማጽናናት፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ መብላት ባሕላችን ያወረሰን ጸጋችን በመሆኑ ትውልድ ይህን መልካም እሴት (ስነልቦናዊ ሕክምና) እየተጠቀመ በርካታ ችግሮችን ድል እያደረገ ኖሯል::
በሰዎች እገዛ ከችግራቸው ተላቀው መልሰው ለብዙዎች የተረፉ፣ የተደረገላቸውን በእጥፍ የሚከፍሉ /ወርቅ ላበደራቸው አልማዝ የሚመልሱ/መልካም ሰዎችን ቆጥረን ላንዘልቃቸው እንችላለን:: የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ውለታ ቢሶች መኖራቸውንም አንክድም:: ለጊዜው ትኩረታችንን በመልካሞቹ ላይ አድርገን ወደ ጉዳያችን እንግባ::
የዛሬው የ”ሀገርኛ” አምድ ዝግጅታችን ስለአንዲት በጎ አድራጊ ግለሰብ ያስቃኘናል:: ግለሰቧ ኑሮዋን በአውሮፓ ያደረገች ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነች። ልጅ እያለች የአካባቢዋ ሰዎች በሚያደርጉላት ድጋፍ በርካታ ችግሮችን አልፋለች:: ዛሬ ለቁም ነገር በቅታ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቿን በመርዳት ላይ ትገኛለች:: የግለሰቧ የበጎ አድራጎት ሥራ በርካቶችን የታደገና ለሌሎችም ምሳሌ ሆኖ ስላገኘነው የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርጋት ወ’ደናል::
ፀሐይ አካሉ ትባላለች:: ትውልዷኗ እድገቷ አርባ ምንጭ ከተማ ነው:: በልጅነቷ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቤተሰቦችዋ ድጋፍና እንክብካቤ አድጋለች:: ከፍ ካለች በኋላ ግን ወላጆቿ የሚከተሉትን ሃይማኖት ትታ የሌላ ሃይማኖት እምነትን መከተል በመጀመሯ ከቤተሰቦቿ ጋር መጋጨት ትጀምራለች:: ቤተሰቦቿ የምትከተለውን ሃይማኖት እንድትተው ካልሆነ ግን ቤቱን ለቅቃ እንድትሄድ አማራጭ ይሰጧታል:: እርሷም ያመንኩበትንና የገባኝን ሃይማኖት አልተውም ብላ የወላጆቿን ቤት ትታ ትሰደዳለች::
ገና በልጅነቷ ኑሮዋ ከአንዱ ቤት ሌላ ቤት፤ ከአንዱ አገር ሌላ አገር ይሆናል:: ይሁንና በስደት ዘመኗ የሰዎች ድጋፍ አልተለያትም ነበር:: በተለይም አራት ዓመት ያህል በወላይታ ዞን፣ ቦዲቲ ከተማ ስትኖር የተደረገላትን መልካም ነገር አትረሳውም:: ያኔ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የቤት ኪራይ ወጪዋን የሚሸፍኑላት በሃይማኖት ምክንያት የተዋወቀቻቸው መልካም ሰዎች ነበሩ::
የእነዚህ ሰዎች በጎነት ለወግ ማዕረግ እንድትበቃ አድርጓታል፤ ያም ብቻ ሳይሆን የተቸገረ ሰውን የመርዳት ፍላጎት አሳድሮባታል:: የተደረገላትን እያስታወሰች ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ የተቸገሩ ሰዎችን እንድትረዳ የሚያደርግ አዎንታዊ አስተሳሰብ ፈጥሮላታል::
ፀሐይ ዛሬ ኑሮዋ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኤደንብራ ከተማ ነው፤ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች:: አውሮፓ እየኖረችም ቢሆን ያን የልጅነት የችግርና የመከራ ሰዓት ታስታውሰዋለች:: ችግሯን በድል እንድትሻገር ያደረጋትን ማኅበረሰብ ውለታም አትረሳም:: ካለው ላይ አካፍሎ ሲደግፋትና ፍቅርን እየሰጠ ሲንከባከባት የነበረውን ወገኗን ለአፍታም አትዘነጋውም:: ያለፈውን ማንነቷን ባስታወሰች ቁጥር ወደ ትውልድ ሃገሯ ሄዳ ለተቸገሩ ሰዎች አቅሟ የፈቀደውን እንድትረዳ ውስጧ ይጎተጉታታል::
እግሯ የአውሮፓ ምድርን መርገጥ እንደጀመረ አስቀድማ ታስብ የነበረው ከልጅነት እድሜዋ ጀምሮ ችግሯን እየተጋሩ ለቁምነገር ያበቋትን ወገኖቿን ውለታ መመለስ ነበር:: ለዚህም የገቢ ምንጭ ሊኖራት ይገባል:: በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል ሃገር ውስጥ እያለች ትሠራ በነበረው የጸጉር ሥራ ተቀጥራ መሥራት ትጀምራለች:: በትርፍ ጊዜዋ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ የወንጌል ትምህርት ማካፈል ትጀምራለች:: በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን መርዳት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ከጥቂት ሰዎች የተወሰነ ድጋፍ ታሰባስባለች:: በጸጉር ሥራውም፣ ከሰዎች የምታገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ማጠራቀም ትጀምራለች:: ያም ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ናቸው የምትላቸውን ቁሳቁስና አልባሳት ከስር ከስር እየገዛች ታስቀምጣለች::
ሁል ጊዜ በህሊናዋ የሚመላለስባት የሃገሯ ሰው መልካምነትና በተለይም በገጠሩ አካባቢ የሚኖረው ወገኗ የሚያሳልፈው የችግር ሕይወት ነው:: በዚህም ላይ ካለው ላይ አካፍሎ የሚኖር መሆኑን ስታስብ አንጀቷ ይላወሳል:: አንድ ቀን ፍቅሯን የምትገልጽበት፤ ምስጋና የምታቀርብበት ገጸ በረከት ይዛ በሚስኪኑ ማኅበረሰብ ፊት ለመቅረብ አቅዳለች::
ፀሐይ ውጭ መኖር በጀመረችባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ ሃገሯ በመምጣት ያሰበችውን የበጎ አድራጎት ሥራ ለማከናወንና የውስጧን ፈቃድ ለመፈጸም ሞክራለች::
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሃገሯ የመጣችው ከአስር ዓመት ቆይታ በኋላ ነው:: ስትመጣ በበርካታ ሻንጣዎች የታጨቀ ሶስት መቶ ኪሎ ግራም የሚመዝን ልብስ እና ውስን ገንዘብ ይዛ ነበር:: ያመጣችውን ልብስ ወደ ትውልድ አካባቢዋ /አርባ ምንጭ/ ከከተሞች ርቀው ወደ ሚኖሩ ሰዎች ይዛ በመሄድ ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ማለትም ለእናቶች፣ ለአባቶች፣ ለወጣቶችና ሕጻናት ታድላለች:: አንዳንዶቹ ተቀያሪ ልብስ እንኳን ስላልነበራቸው ልብሳቸውን አጥበው እዚያው አድርቀው የሚለብሱ ስለመሆናቸው መረጃ ነበራት::
ሴቶችም የውስጥ ልብስ /ሞዴስ፣ ፓንት፣ ጡት ማስያዣ/ የመሳሰሉትን ሲያገኙ በእጅጉ ደስተኛ ሆነው ታያለች:: እነርሱ ተደስተው ስታይ ባደረገችው ርዳታ የበለጠ እርካታ ታገኛለች:: በአንዳንድ አካባቢዎች የምሳ ግብዣ አደረገች፤ የባሰ ችግር ላለባቸውም እንደ ፓስታ፣ ሞኮሮኒ፣ ዱቄት፣ ዘይት የመሳሰሉትን እየገዛች ሰጠች፤ አባት እናት ለሌላቸው ሕጻናትም የትምህርት ቤት ቁሳቁስ አሟላችላቸው፤ ለኤች አይቪ ኤድስ ታማሚዎችም ለተወሰነ ወራት የምግብና የወተት ወጪያቸውን ሸፈነችላቸው፤ ባዶ እግራቸውን ለሚሄዱ የተወሰኑ እናቶችም ጫማ ገዝታ አደለች:: በመጀመሪያ ዙር በመጣች ጊዜ እንዲህ አይነት ድጋፎችን እያደረገች ለወራት ቆይታ ተመልሳ ሄደች::
ፀሐይ ወደ ውጭ ከተመለሰች በኋላ ባየቻቸው አንዳንድ ነገሮች ምክንያት አእምሮዋ ፍጹም እረፍት ስላልነበረው እዚህ ካሉ ሰዎች ጋር እየተደዋወለች ለተወሰኑት ድጋፍ ማድረጓን ቀጠለች:: በተለይም ተጥለው የተገኙና ወላጅ አልባ የሆኑ ሕጻናትን ሰብስቦ ለሚረዳው ድርጅት እርዳታ እያስተባበረች ያገኘችውን ትልክ ጀመር::
ፀሐይ እንደምትናገረው እርሷ በምትኖርበት ሃገር ዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለታዳጊ ሕጻናት ነጻ የእንክብካቤና የማቆያ ቦታ ያዘጋጃል:: እናቶች ሕጻናትን በተዘጋጀላቸው ቦታ አስቀምጠው የራሳቸውን ሥራ ሠርተው የሚውሉበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል:: ይህን ስትመለከት ሁል ጊዜ ስለ ትውልድ ሃገሯ ሕጻናት እያሰበች ውስጧ ይረበሻል:: ስለሆነም እነዚህን ወላጅ አልባ ሕጻናት በመርዳት አንድ ቁምነገር ላይ የማድረስ ኃላፊነት ስላለባት ያገኘችውን ሥራ ሁሉ በመሥራት የገንዘብ አቅሟን ማሳደግ ነበረባት::
በርካታ አሳዛኝ የሕይወት ገጽታዎችን ተመልክታ ከተመለሰች በኋላ የተሻለ ገንዘብ የምታገኝበትን ሥራ ሠርታ የወገኖቿን ችግር መጋራት እንዳለባት በመወሰን በተለይም ቅዳሜና እሁድ ሙሉ ቀን የጽዳት ሥራዎችን መሥራት ትጀምራለች::
እንደ ሃይማኖቷ አስተምህሮ ‹‹ለደሃ የሰጠ ለእግዚአብሄር አበደረ ነው›› ትላለች:: ስለሆነም የቀጣይ እቅዷን ለማሳካት ከራሷ ጥረት በተጨማሪ የጓደኞቿም ድጋፍ እንደሚያስፈልግና ለሰዎች መስጠት በፈጣሪ ዘንድ አደራ ማቆየት መሆኑን በመግለጽ ድጋፍ ታስባስብ ጀመር::
እዚያው ሆና በተለይም ኮቪድ-19 በተከሰተ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ በማስተባበር ሰዎች በሰጧት ጥቆማ አማራ ክልል፣ ዳንግላ ከተማ ለሚኖሩ ሰዎች ድጋፍ አድርጋለች:: ጣሊታ ለተባለና በይርጋለም ከተማ የተጣሉ ህጻናትን ለሚያሳድግ አንድ ድርጅትም እስከ አራት ሺህ ዩሮ ገንዘብ አሰባስባ በመላክ ሶስት የወተት ላሞች እንዲገዙ አድርጋለች::
በዚህ አጋጣሚ ከውጭም ከአገር ውስጥም ሀሳቧን ደግፈው የተባበሯትን ሁሉ ታመሰግናለች:: በተለይም እርሷ ለ’ዚሁ ዓላማ ወደ ሥራ በምትሰማራበትና ወደ ኢትዮጵያም በምትመጣባቸው ጊዜያት ልጆቿን የሚንከባከበውንና የሚያበረታታትን ባለቤቷን በእጅጉ ታመሰግነዋለች::
ፀሐይ በዚህም በዚያም ብላ ያሰባሰበችው ገንዘብ እጇ ላይ ጠርቀም ሲል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ትውልድ ሃገሯ ትመጣለች:: ድጋፍ ያደረገችው ከሃዋሳ ማረሚያ ቤት ጀምራ ነበር:: ለ130 ሴት እስረኞች /ታራሚዎች/ ለሶስት ቀን የምሳ መርሐ-ግብር በማዘጋጀት የሚስፈልጋቸውን የውስጥ ልብስና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለግሳለች:: በመቀጠልም ይርጋለም በሚገኘውን የጣሊታ ሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት ተገኝታ ውጭ ሆና በማስተባበር የገዛቻቸውን የወተት ላሞች ከጎበኘች በኋላ ይዛ የመጣችውን የሕጻናት መጫወቻና የመመገቢያ ቁሳቁስ አስረክባለች:: ከዚያም ባሻገር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ድርጅቱን እንዲረዱት ሚዲያ ላይ ቀርባ ከፍተኛ የማስተዋወቅና የማስተባበር ሥራ ሠርታለች:: አሁን ድርጅቱ እርሷና ሌሎች በሚያደርጉት ድጋፍ ተጥለው የሚገኙና እናት አባት የሌላቸውን ሕጻናት እያሳደገ ይገኛል::
አርባ ምንጭ ከተማ ተገኝታ ለ22 ሰዎች የገንዘብ፣ የፉርኖ ዱቄት፣ የዘይት ድጋፍ አድርጋለች:: የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግም ለተወሰኑ አቅመ ደካሞች ለዓመት በዓል መዋያ የሚሆን ገንዘብ ሰጥታለች::
ፀሐይ ሰዎች በሰጧት ጥቆማ መሰረት በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ መንዲዳ ከተማ ተገኝታ ተመሳሳይ የሆነ እገዛ ለአቅመ ደካሞች አድርጋለች:: ተረጂዎቹ አካል ጉዳተኞች፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አዛውንቶች፣ የሚላስ የሚቀመስ ያጡ መሆናቸውን ትናገራለች:: ሰባት ኩንታል ጤፍ፣ ለዶሮ መግዣ የሚሆን የተወሰነ ገንዘብና ዘይት ለግሳለች:: ድጋፍ የተደረገላቸው ሰዎች ልክ እንደ አርባ ምንጭ ለ22 ሰዎች ነው::
አብዛኛዎቹ ከቤታቸውና ከመንደራቸው ርቀው መሄድ የማይችሉ አቅመ ደካሞች በመሆናቸው ለእያንዳንዳቸው 25 ኪሎግራም ዱቄት ቤታቸው ድረስ በመውሰድ አድላለች:: ከነዚህም ውስጥ ማረፊያ ቤት እንኳን የሌላቸው እንዳሉ ነግራናለች:: አንዳንዶቹም ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰ ነው:: በአጠገባቸው የሚያነጋግረቸውም ሆነ የሚረዳቸው ሰው የሌላቸውም አሉ::
ፀሐይ መንዲዳ ከተማ ያየቻቸው ችግረኞች ጉዳት ልቧን ክፉኛ አድምቷታል፤ በቀጣይ ድጋፍና ርዳታ ለማድረግ ትኩረት ከሰጠቻቸው አካባቢዎች አንዱ መንዲዳ ነው:: መንዲዳ አካባቢ ያሉ ተረጂዎች የመጀመሪያ ጥያቄያቸው መጠለያ ነው:: የሚጎርሱትን የሚቀምሱትን ነገር የአካባቢው ሰዎችም ሊረዷቸው ይችላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ ትልቁ ችግር ከዝናብና ከፀሐይ የሚከልላቸው መጠለያ ነው ትላለች:: እመጫት ጣሪያና ግድግዳ በሌለው ቤት መሰል ነገር ውስጥ ከልጆቿ ጋር ተኝታ መመልከቷ ፀሐይን ክፉኛ አሳዝኗታል::
ፀሐይ የልጅነት ዘመኗ በሰዎች ቀና ትብብር ፈር ይዞ ውጤታማ ስለሆነች ሁልጊዜ ‹‹ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው›› የሚለውን ብሂል ታምንበታለች:: እርሷም የተደረገላትን ባስታወሰች ቁጥር የሰዎችን ችግር ለመካፈል ትጓጓለች:: እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ባላት አቅም ልክ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ለራሷ ቃል ገብታለች::
ነገር ግን የተረዳችውና ሰዎችም የሰጧት ሀሳብ በየጊዜው የተወሰነ ነገር ይዞ እየመጡ ለጥቂት ሰዎች ሰጥቶ መሄድ ጥሩ አለመሆኑን ነው:: ከዚያ ይልቅ የሚመረጠው እውቅና ያለው ድርጅት መሥርቶ ተረጂዎችን በመለየት በቋሚነት መርዳት ነው::
ፀሐይ በተለይም አልባሳት ከውጭ ይዛ ስትመጣ ታክስ የምትከፍለው ገንዘብ እንዳማረራት ትናገራለች:: የተቸገሩ ወገኖቿን ለመርዳት በምታስገባው ልብስ እንደ አንድ ጥሬ እቃ ቀረጥ ተጥሎባት ክፈይ መባሏ ያስቆጫታል:: ‹‹ሕጋዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ቢኖረኝ ኖሮ አላስፈላጊ ወጪ አላወጣም›› ነበር ትላለች:: ከዚህ አንጻር አሁን ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ለማቋቋም በሂደት ላይ እንዳለች ነግራናለች:: በቀጣይ ‹‹ፀሐይ ጎልጎታ የኅብረተሰብ ድርጅት››ን የመመሥረት ራዕይ ይዛለች:: ራዕይዋ እውን ሆኖ ለበርካታ ችግረኛ ወገኖቻችን ደራሽ እንድትሆን ተመኘን::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም