ኮትዲቯር በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ አዘጋጅ የሆነችበት የአፍሪካ ዋንጫ በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል:: ይህን ተከትሎም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) የዚህን የ34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የምድብ ድልድሉን በቅርቡ ይፋ አድርጓል:: ከወራት በኋላ ለሚካሄደው የአህጉሪቷ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር ከመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ አንስቶ አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ ይጀምራሉ::
ኢትዮጵያም በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር መደልደሏ ይታወቃል:: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በዚህ ዙሪያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ድረ-ገጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ በቅድሚያ ድልድሉን እንዴት አገኙት የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ የተካተተችበት ድልድል ጠንካራ ቡድኖች ያሉበት መሆኑን አስታውቀዋል::
አሠልጣኙ ግብጽ በካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ የዋንጫ ተፋላሚ የነበረች እንዲሁም በውድድሩም ትልቅ ታሪክ አላት ሲሉ ጠቅሰው፣ ከሁለተኛዋ አገር ጊኒ ጋር የቀደመ ታሪክ ቢኖረንም በወቅታዊ አቋሟ በአፍሪካ ዋንጫው 16 ውስጥ መግባት ችላለች፤ ማላዊም በተመሳሳይ:: ስለዚህም ምድቡ ጠንካራ የሚባል ነው ሲሉ አ ብራርተዋል::
አሠልጣኙ እንዳሉት፤ ብሄራዊ ቡድኑን እየመሩ ከማላዊ ጋር ከዚህ ቀደም በወዳጅነት ጨዋታ የተገናኙ ሲሆን፤ በአፍሪካ ዋንጫውም የነበራቸውን አቋም ለመመልከት ችለዋል:: በአንጻሩ ከግብጽ እና ከጊኒ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የመገናኘት እድሉን አላገኙም:: በመሆኑም ከሌሎች ጨዋታዎች በመነሳት ያላቸው ምልከታ፤ ጊኒ በጋምቢያ ተሸንፋ ከአፍሪካ ዋንጫው ውጪ እስከምትሆን ድረስ ጥሩ ቡድን እንደነበራት ታዝበዋል::
ብሄራዊ ቡድኑ ከግብጽ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ተገናኝቷል ያሉት አሠልጣኝ ውበቱ፣ ከሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወዲህ መልካም ታሪክ እንደሌለ ተናግረዋል:: በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከግብጽ ጋር መጫወት ትልቅ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፤ ‹‹ከግብጽ ጋር የሚያያዙ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም እርሱን ወደ ጎን ትተን ኳሱ ላይ ትኩረት እናደርጋለን›› ብለዋል:: በመልሱ ጨዋታ ሜዳችን ቢፈቀድና ተመልካች ስታዲየም እንዲገባ ቢደረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚቻልም አመላክተዋል::
ተጋጣሚ ቡድኖች ይህንን ይምሰሉ እንጂ የአሠልጣኙ ዋነኛ ትኩረት ግን የራሳቸውን ቡድን በመገንባት ላይ መሆኑን ተናግረው፣ አሠልጣኙ ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ያጋጠማቸው አንድ ችግር ተጫዋቾችን ለሰፊ ጊዜ አለማግኘት መሆኑን ይጠቅሳሉ:: የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እየተካሄደ መሆኑን ተከትሎ ውድድር አቋርጦ ዝግጅት ማድረግ አለመቻል ሌላኛው ፈተና መሆኑን አስታውቀዋል:: በዚህ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ከዝግጅት ውጪ መሆን እንደማይቻልም ገልጸው፣ በተቻለ መጠን ከተጫዋቾች ጋር የአንድ ለአንድ ግንኙነት እያደረጉ መሆናቸውንም አሠልጣኙ ይጠቁማሉ::
አሠልጣኙ በቀጣይ ደግሞ በጋራ ልምምድ ወደማድረግ ይገባሉ:: የቡድኑ አባላት ከሊግ ውድድር መምጣታቸው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የገለጹት:: ከተለያየ የሥልጠና እና የአጨዋወት ሁኔታ የተወጣጡትን ተጫዋቾች በረጅም ጊዜ ቆይታ ወደ ቡድን እና የህብረት ስሜት እንዲገቡ ለማስቻል እንደሚሰራ አስታውቀዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ቡድናቸው ከአፍሪካ ዋንጫው መልስ ከኮሞሮስ ብሄራዊ ቡድን ጋር በቅርቡ የማጣሪያ ጨዋታ አከናውኗል:: በወቅታዊ አቋም የተሻለ ከሆነው የኮሞሮስ ቡድን ጋር ከሜዳ ውጪ በተደረገው ጨዋታም መልካም ነገሮች ታይተዋል:: በቡደኑ ስብስብ ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማካተትም ተስፋ ለማየት ተችሏል::
በቀጣይም በአፍሪካ ዋንጫው ተካፋይ ለመሆን የሚያስችል ጥረት እንደሚያደርጉም አሠልጣኙ ይገልጻሉ:: ያሉበት ምድብ ጠንካራ ቢሆንም በርካታ የአፍሪካ አገራት ከሜዳ እጥረትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ክልከላ እንደተጣለባቸውም ጠቁመዋል:: ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጥረት አድርጎ ኢትዮጵያ በሜዳዋ መጫወት ከቻለች በማጣሪያው ቆይተው የውድድሩ ተካፋይ ለመሆን አተኩረው አንደሚሠሩም አመላክተዋል::
ብሄራዊ ቡድን ሲባል ከፊት ያለው ታላቁ አካል ነው ያሉት አሰልጣኙ፣ የሚወከለው ጥቂት ቁጥር ባላቸው ባለሙያዎች ይሁን እንጂ የመላው ኢትዮጵያ ነው ብለዋል:: ብሄራዊ ቡድኑ ከመንግስት፣ ከስፖርት ባለሙያዎች እንዲሁም ከስፖርት ቤተሰቡ ሰፊ ድጋፍ እንደሚፈልግም አስታውቀው፣ በቡድኑም በኩል ከየትኛውም አካል ለሚሰጥ አስተያየት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል:: እነዚህ አካላት በመተባበር ለአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፎ እውን መሆን እንዲሰሩም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ አቅርበዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 /2014