ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እያጋጠማትና በብዙም እየተፈተነችበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለፈም ሀብቱን በአግባቡ የማስተዳደር ችግር መኖሩም ጎልቶ ይታያል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ ከሚፈለግበት ምክንያቶች መካከል በአገር ውስጥ የማይገኙ የተለያዩና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ምርቶችን ከውጭ ገበያ በመግዛት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንዲቻል የሚያደርግ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘወትር ፈተና የሆነባት ኢትዮጵያ በተለይም በዘንድሮ ዓመት በከፍተኛ መጠን ችግሩ የበረታባት ስለመሆኑም ይነገራል፡፡ የኑሮ ውድነቱም ሆነ የሸቀጦች ዋጋ መናር አገሪቷ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚገናኝ በመሆኑ ተባብሶ መቀጠሉ ሁነኛ ማሳያ ነው፡ ፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እጅጉን እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
በዋነኝነት በአገር ውስጥ የማይገኙ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልገው የውጭ መንዛሪ እጥረት ሲያጋጥም በተመሳሳይ ከውጭ ገበያ በሚገቡ ምርቶች ላይ እጥረት ይፈጠራል፡፡ የምርት እጥረት መፈጠር ደግሞ ለዋጋ ንረት አይነተኛ ምክንያት ነውና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በአገሪቱ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት የጎላ ድርሻ አበርክቷል።
በአገሪቱ እየታየ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል ታዲያ መንግሥት በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት ችግሩን ለማቃለል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የአገር ውስጥ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በተወሰነ መጠን መጠቀም መቻሉ አንዱ ሲሆን፤ በዚህ መንገድ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪም እጅግ አስፈላጊና አንገብጋቢ ለሆኑ ምርቶች ሲያውል ይስተዋላል፡፡ ለአብነትም መድኃኒትን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦች ማለትም የህጻናት ወተት፣ የምግብ ዘይትና ሩዝ እንዲሁም ለሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ምርቶችን ሲያስገባ ቆይቷል፡፡
መንግሥት በድጎማ ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገባቸው የተለያዩ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በርካታ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡት አስመጪና ላኪ የተባሉት ትላልቅ ነጋዴዎች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አስመጪና ላኪው በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን ልክ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ሲሆን፤ ነጋዴው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በገጠመው ጊዜም የምርት እጥረት የሚፈጠር ይሆናል፡፡ የምርት እጥረቱን ተከትሎም የዋጋ መናር ይከሰታል፡፡ በመሆኑም ነጋዴው አገሪቱ ልትሻገር ያልቻለችው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማቃለል ያስችላል ያለውን አማራጭ ሁሉ መጠቀም እንዲችል ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ የውጪ ምንዛሪ እጥረቱን ለማቃለል ነጋዴውን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች ከሚያነሱት ሀሳብ መካከል ፍራንኮቫሉታ ይፈቀድ የሚለው አንዱ እንደነበር ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡
እንደምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጻ፤ ፍራንኮቫሉታ ማለት የውጭ ምንዛሪ ከአገር ውስጥ ሳይወጣ ነጋዴዎች በራሳቸው መንገድ ምርቶችን ከውጭ ገዝተው ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚቻልበት አሰራር ነው፡፡ ይህም ዕቃው እጅጉን የሚፈለግ በመሆኑ አስመጪው የውጭ ምንዛሪውን ከአገር ውስጥ ሳያወጣ በራሱ የውጪ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ ምርት ከውጪ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባበትን አሰራር መፍጠር ነው፡፡
አገር ውስጥ መግባት ያለባቸው እንደ መድኃኒት፣ የምግብ ሸቀጦችና ሌሎችንም ምርቶች ወደ አገር ውስጥ በፍራንኮቫሉታ ለማስገባት የራሱን የውጭ ምንዛሪ ይጠቀማል፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ በአገር ውስጥ ከውጭ ገበያ ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ ምርቶች አስመጪው ፈቃድ ይሰጠኝ ብሎ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ይሁንና የውጭ ምንዛሪው ያለው መሆኑ ተጣርቶ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን በማለፍ ባንኮች እርስ በርስ መረጃ ተለዋውጠው ገንዘቡ የሚከፈልበትና ምርቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ዕቃው ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡
ይሁንና ሂደቱ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መካሄድ ያለበት ስለመሆኑም ባለሙያዎች አጽንኦት በመስጠት ያነሳሉ፡፡ ይህም ሲባል የውጭ ምንዛሪው በምን መንገድ የተገኘና ከአገር ውስጥ ያልወጣ ስለመሆኑ ማረጋጋጥ በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ፍራንኮቫሉታ ይፈቀድልን የሚሉ አካላት የውጭ ምንዛሪውን ከአገር ውጭ የሚያገኙበት ሌላ መንገድ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም የጥቁር ገበያው የተንሰራፋበት ሁኔታ በመኖሩና የውጭ ምንዛሪውን ከጥቁር ገበያው ገዝተው የሚያመጡ ከሆነ ህጋዊ ሂደቱን በማደናቀፍ መደፈን ያለበት ሌላ ቀዳዳ እንደመክፈት ነውና ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
የፍራንኮቫሉታ መፈቀድ ኢኮኖሚውን ይበልጥ ይጎዳዋል ብለው የሚሞግቱ የምጣኔ ሀብት ምሁራን የመኖራቸውን ያክል ፍራንኮቫሉታ የበረታ ቁጥጥር ከታከለበት ለአገር ይጠቅማል ብለው ሀሳብ የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ ይሁንና ሁለቱንም አስታርቆ ለመጓዝና ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ወደ አገር ውስጥ ምርቶችን የሚያስገቡ አካላት ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ማድረግ አንደኛው አማራጭ ነው፡፡ ነጋዴው ምርቱን ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ያስገባው የውጭ ምንዛሪውን ከጥቁር ገበያ ገዝቶ ነው ወይስ ከአገር ውጭ ባለው አማራጭ ተጠቅሞ ነው የሚለውን በሚገባ ማጥናት፣ መከታታልና ቁጥጥር ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ዘርግቶ መቆጣጠር ይጠበቅበታል ሲሉም ይሞግታሉ፡፡
ነገር ግን መንግሥት ይህን ማጣራት የሚችልበት መንገድ የሌለው ከሆነና ማጣራት ካልቻለ ሁሉም ነጋዴ ፍራንኮቫሉታ ይፈቀድልኝ በማለት ጥቁር ገበያ እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይበልጥ ጉዳቱ አመዝኖ ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል ይላሉ፡፡ የፍራንኮቫሉታ መፈቀድ ለአገር የሚኖረው ጠቀሜታ ምንድነው ጉዳቱስ ምን ይሆን ስንል ላነሳነው ጥያቄ የኢኮኖሚክስ ምሁር ዶክተር ተሾመ አዱኛ ባለሙያዎች ያነሷቸውን ሀሳብ በማጠናከር የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
ፍራንኮቫሉታ ማለት መደበኛ የሆነ ዶላር ሳይጠይቁ ከውጭ ገበያ የተለያዩ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡበት ሥርዓት ወይም ዘዴ ነው፡፡ ብዙ ያደጉ አገራት የዶላር ችግር የሌለባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለያዩ ያደጉ አገራት ውስጥ ዶላር ከመንግሥት አስተዳደር ወጥቶ በገበያ ሥርዓት የሚተዳደር እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገራት ከፍተኛ የሆነ የዶላር እጥረት በመኖሩና እጥረቱ ደግሞ ይበልጥ እንዳይባባስ በሚል ዶላሩን ገበያው ከሚያስተዳድረው ይልቅ መንግሥት ቢያስተዳድረው የተሻለ እንደሚሆን ታምኖበት መንግሥት እያስተዳደረው ይገኛል፡፡ እስካሁን ያለው ሂደትም ይህንኑ ያስረዳል፡፡ ይሁንና ይህ አሰራር በተፈለገው ጊዜና መጠን ዶላርን ማግኘት አላስቻለም፡፡ ለዚህም ሲባል በተለያየ መንገድ ዶላር ያላቸውና ዶላሩን ማግኘት የሚችሉ ሰዎች ዶላር እንዲያመጡ መፍቀድ አንዱ አማራጭ ሆኗል፡፡
የዶላር እጥረት በሚፈጠርበት ወቅት መንግሥት ያሉትን አማራጮች ሁሉ መጠቀሙ የግድ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ተሾመ፤ ወደ አገር ውስጥ መግባት ያለባቸው መሰረታዊ የሆኑ ምርቶች በተለይም በአገር ውስጥ መመረት የማይችሉትን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዶላር የግድ ይሆናል፡፡ ዶላር የግድ አስፈላጊ እንደመሆኑም ፍራንኮቫሉታን መፍቀድ መንግሥት በአገር ውስጥ የተፈጠሩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት የሚሄድበትን ርቀት የሚያሳይ እንደመሆኑ ጥሩ ጎኑ የሚያመዝን መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህም በርካታ ጠቀሜታዎችን የሚሰጥ ነው፡፡
መንግሥት ፍራንኮቫሉታን በፈቀደበት አግባብና መንገድ መጠቀም ከተቻለ የሚኖረው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ይገልጻሉ። አንደኛ ዶላሩን ከአገር ውጭ ጤናማ በሆነ መንገድ ማግኘት ከተቻለና የተለያዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ከተቻለ ምርት ይትረፈረፋል፣ የሸቀጦች ዋጋን በከፍተኛ መጠን በመቀነስ ገበያን ማረጋጋት ያስችላል፡፡ በመንግሥት የሚታየውን የዶላር ጫናም የሚቀንስ ይሆናል፡፡ ይህ መልካም ጎኑ ነው፡፡
በተመሳሳይ ደግሞ ፍራንኮቫሉታ በአገር ውስጥ መፈቀዱ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖም አለው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ሰዎች ዶላሩን ከጥቁር ገበያ ገዝተው የሚጠቀሙ ከሆነ ምንም ጥቅም አይኖረውም፡፡ እንደውም ጉዳቱ አመዝኖ ችግሩ ይበልጥ የሚባባስበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ምክንያቱም መንግሥት ፍራንኮቫሉታን ተጠቅመው ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ ሲፈቅድ በአገር ውስጥ ያለውን ዶላር ሳይጠቀሙ ከውጭ አገር በተለያየ አጋጣሚ በሚያገኙት ዶላር እንዲጠቀሙ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ዶላሩን ከጥቁር ገበያ ገዝተው ምርቶቹን ከውጭ የሚያመጡ ከሆነ አንድም መንግሥት ላይ ያለውን የዶላር ጫና መቀነስ አይችሉም፡፡ ሁለትም የጥቁር ገበያውን ዋጋና የመደበኛውን የዶላር ዋጋ ይበልጥ ያባብሰውና የማክሮ ባላንሱ መቀነስ ሲገባው ይበልጥ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ሸቀጡን በመደበኛ መንገድ በሚያስገቡበት ጊዜ ገቢና ወጪያቸው በግል የሚታወቅ በመሆኑና ነገር ግን በፍራንኮቫሉታ ወጪ ገቢያቸው የማይታወቅ በመሆኑ የመንግሥትን ገቢም ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ከላይ እንደተጠቀሰው ተጠያቂነትን መሰረት አድርገው መሥራት ከቻሉ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ጉዳቱ የሚያመዝን ይሆናል፡፡
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ አማራጮችን ማምጣቱ መልካም ጎን ያለውና የግድ ቢሆንም ጎን ለጎን መሥራት ያለበትና መፍትሔ ነው ያለው ፍራንኮቫሉታም የበለጠ ችግር ይዞ እንዳይመጣ ምን መደረግ አለበት ስንል ላነሳነው ጥያቄም ዶክተር ተሾመ ሲመልሱ፤ ፍራንኮቫሉታ በሚፈቀድበት ጊዜ አስቀድሞ ሊታሰቡ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ። ይሄውም መጀመሪያ በንግዱ ላይ መሳተፍ ያለባቸውን ሰዎች በሚገባ ማወቅና መለየት ፤ በተለይም ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ መንግሥት በሚያስበው መንገድ ማሰብ የሚችሉ፤ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት የሄደበትን ርቀት መረዳት የሚችሉና እነሱም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁነት ያላቸው ሰዎች መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም አስፈላጊና ተገቢ የሆነ ቁጥጥርና ክትትል መደረግ አለበት፡፡ በተለይም ነጋዴው ዶላሩን ከየት እንደሚያመጣ ግልጽ በሆነ መንገድ አስቀድሞ ማሳየት አለበት፡፡ ማስረጃውንም ለመንግሥት ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥትም እነዚህን ነገሮች ማረጋጋጥ የሚችልበትን መንገድ ዘርግቶ መከታተልና መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ በገባነው ቃልና ባስቀመጥነው አማራጭ የመጓዝ ከፍተኛ ችግር አለብን›› ያሉት ዶክተር ተሾመ፤ ብዙ ጊዜ በአገሪቱ በርካታ የተጀማመሩ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲቀጥሉ የማይታዩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም ፍራንኮቫሉታ ብዙ ጊዜ ተጀምሮ ሲቋረጥ የነበረ መሆኑን አንሰተው ተጀምሮ በመቋረጡ ምንድነው የተማርነው ነገር ብለን ተቋማዊ በሆነ መንገድ እና ተጠያቂነት ባለው አካሄድ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ተቋማዊ በሆነ መንገድና ከፍተኛ ትኩረት በተሰጠበት አግባብ መስራት ከተቻለና ቀጣይነት እንዲኖረው ከተደረገ ፍራንኮቫሉታን በመጠቀም አገሪቷ የገጠማትን የዶላር እጥረት ማቃለልና የኑሮ ውድነቱንም ማረጋጋት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፍራንኮቫሉታን መጠቀም ከሚቻልበት አግባብ ውጭ ከተጠቀምንበት ከሚሰጠው ጥቅም በበለጠ የሚኖረው ጉዳት ያመዝናልና ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ መከናወን ይኖርበታል በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 /2014