እአአ በ2019 በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ወክላ በተገኘችበት የግማሽ ማራቶን ውድድር ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ተዋወቀች፡፡ መንገዷን በስኬት የጀመረችው አትሌቷ አሸናፊነቷን የውድድሩ ክብረወሰን በሆነ ሰዓት (1:10:26) ደርባ ነበር ያስመዘገበችው፡፡
በተመሳሳይ በዚያው ዓመት በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ላይ የውድድሩን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ስኬቷን ለማጣጣም ችላለች፡፡ ከመነሻው ብቃቷን በማሳየት የስፖርት ቤተሰቡን በማሳመን በተለይ በጎዳና ላይ ሩጫዎች አገሯን በክብር እንደምታስጠራ ተስፋ ያሳየችው ይህቺ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ትባላለች፡፡
ታታሪነት መገለጫዋ የሆነው አትሌቷ፣ በዚያው ዓመት በህንድ (ዴልሂ) እና በቻይና (ዚመን) ግማሽ ማራቶን ተሳትፎዎቿ የብር እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር ብቃቷን ማስመስከር ችላለች፡፡ በቀጣዩ ዓመትም በዴልሂ ግማሽ ማራቶን በድጋሚ ተሳትፎዋ አሸናፊ ስትሆን ቀድሞ ከገባችበት ሰዓት ሁለት ደቂቃ ማሻሻል ችላለች፡፡ በዓመቱ በግሏ ከተሳተፈችባቸው የግማሽ ማራቶን እና የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች ባለፈ በፖላንድ በተካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና በድጋሚ አገሯን የመወከል ዕድል አግኝታ በግሏ የነሐስ ሜዳሊያ ስታጠልቅ፤ በቡድን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡
በመላው ዓለም በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በርከታ የአትሌቲክስ ውድድሮች ለመሰረዝና ለማራዘም ቢዳረጉም ያለምዘርፍ ግን ይህንን ጊዜ በስኬት ነበር ያሳለፈችው፡፡ ያለፈውን ዓመትም በተመሳሳይ በምርጥ አቋም ያሳለፈችው ሲሆን፤ በኢስታምቡል እና ቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶኖች ተካፋይ ነበረች፡፡ በቫሌንሺያ የሮጠችበት 1:03:51 የሆነ ሰዓትም በርቀቱ የዓለም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት የግሏ ነው፡፡
ይሁንና ዓመቱን ይበልጥ ስኬታማ ያደረገላት በአየርላንድ በተደረገው የአንተሪም ኮስት ግማሽ ማራቶን ያስመዘገበችው ሰዓት ነበር፡፡ ደስታና ኀዘን በእኩል በተንጸባረቁበት በዚህ ውድድር ያለምዘርፍ ርቀቱን የሸፈነችው 1ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ44ማይክሮ ሰከንድ በመሆኑ የዓለም ክብረወሰንን መስበር ችላለች፡፡ ነገር ግን በውድድሩ ላይ በድጋሚ በተደረገው ማጣራት የውድድሩ አዘጋጆች ርቀቱን በለኩበት ወቅት በተፈጸመ ስህተት ፈጣኑ ሰዓት እንደማይመዘገብ ይፋ ሊሆን ቻለ፡፡
ዜናው ከአትሌቷ ጥረትና ብቃት አንጻር ልብ ሰባሪ ቢሆንም ታታሪዋ ያለምዘርፍ ግን በቀላሉ እጅ የማትሰጥ መሆኗን አሳይታለች፤ ሁኔታው በድጋሚ በሌሎች ውድድሮች ተሳትፎዋ ህልሟን እውን ከማድረግ ሊያግዳት አልቻለም፡፡ በዚህ ዓመትም ሩጫዋን በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ አሸናፊነት ነበር የጀመረችው፡፡ ከሁለት ወራት በፊትም በስፔን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ 24 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ ከ14 ማይክሮ ሰከንዶች በመሮጥ የዓለም ክብረወሰኑን ከእጇ በማስገባት በድጋሚ ድሏን ለማጣጣም በቅታለች፡፡
በርካታ የዓለም ምርጥ አትሌቶችን ባቀፈው ‹‹ኤንኤን ማናጅመንት›› ስልጠና ቡድን አባል የሆነችውና በአሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ የምትሰለጥነው ብርቱዋ አትሌቷ፣ ግማሽ ማራቶንን ከ10 ጊዜያት በላይ በመሮጥና አሸናፊም በመሆን ከፍተኛ ልምድ አላት፡፡
ከትናንት በስቲያ ደግሞ በጀርመን የሃምቡርግ ከተማ ሌላኛው የስኬት መንገዷን ጀምራለች፡፡ የጀመረችውን ውድድር በአሸናፊነት መደምደም ልምዷ የሆነው አትሌቷ አስቀድሞ በስፖርት ቤተሰቡ ባገኘችው ግምት መሠረት አሸናፊ ሆናለች፡፡ የገባችበት 2:17:23 የሆነ ሰዓትም በግሏ የማራቶን ፈጣን በሚል ሲያዝላት፤ እአአ በ2016 በአገሯ ልጅ መሰለች መልካሙ ተይዞ የነበረውን 2:21:54 የሆነ ሰዓት በማሻሻል የስፍራውን ክብረወሰን ለመረከብ ችላለች፡፡
ውድድሩ የተካሄደበት የአየር ሁኔታ ፀሐያማ ቢሆንም በዕለቱ የነበረውን ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በመጠቀም ያለምዘርፍ ከመነሻው በፍጥነት ሮጣለች፡፡ በሁለተኛው የርቀቱ አጋማሽ ፍጥነቷን ብትቀንስም እርሷን ትከተላት ከነበረችው አትሌት ወደ ዘጠኝ ደቂቃ የሚጠጋ ልዩነት እንደነበረው አትሌትስ የተሰኘው ድረገጽ በዘገባው አስነብቧል፡፡
አትሌቷ ከድሏ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ‹‹ሃምቡርግ የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድር ያደረኩበት ቦታ ሲሆን፤ ውድድሩ ፈጣን ቢሆንም ምቹ ነበር፡፡ ከተመልካች ይሰጠኝ የነበረው ድጋፍ ደግሞ በተለይ ረድቶኛል›› ብላለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014