በማንኛውም ስራ ተናቦ መስራት ውጤታማ ያደርጋል። ይህ ውጤት እንዲገኝ ግን መጀመሪያ የጋራ ስራ የሚሰሩ ወገኖች ለአንድ አላማ መሰለፋቸውን ተረድተው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በተለይ ደግሞ የሰውን ሕይወት ከአደጋ ለመታደግ የሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። የሰሞኑ የጌድኦ ዞን ጉዳይ ሰብዓዊነትን ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ይልቅ ዜጎችን ከጉዳት ለመታደግ የሁሉንም ርብርብ አስፈላጊነት ማሳያ ነው።
በሃገራችን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ በሆነ ችግር ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀልና የምግብ እህል እርዳታ ጠባቂ መሆን አዲስ ታሪክ አይደለም። ከቅርብ ዓመታት በፊት እንኳን በሃምሳ ዓመታት ተከስቶ የማያውቅ ድርቅ አጋጥሞ መንግሥትና ህዝብ በአደረጉት ርብርብ መቋቋም ተችሏል። ከምግብ እህል አልፎ ለእንስሳት መኖ ማቅረብም ተችሏል። ይህን ማድረግ የተቻለውም ተቀናጅቶና በጋራ ተረባርቦ መስራት በመቻሉ እንዲሁም መንግሥትም ድርቁን መቋቋም የሚያስችል አቅም በመፍጠሩ ነው።
ይህ አቅም አሁንም አለ። ነገር ግን በጌድኦ ዞን በመረጃ ክፍተትና አለመናበብ የተነሳ ዜጎች ጉዳት ላይ ሊወድቁ የቻሉበት እንዲሁም መንግሥት ለዜጎቹ ደንታ የሌለው ነው ተብሎ እንዲተች እድል የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ተስተውለዋል። ይህ በቀጣይ መስተካከል አለበት። ችግሮች እንኳ ቢያጋጥሙ ለመፍትሄው መረባረብ እንጂ ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም መሯሯጡ ትዝብት ላይ ይጥላል፤ ተገቢም አይደለም። ሰብዓዊነት መቅደም አለበትና።
በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹ ወገኖች አሉ። ክልሎች በራሳቸው አቅም ያለፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ዜጎችን እየደገፉ ያለበት ሁኔታም አለ። ድጋፍ ሲያሻቸው ደግሞ ፈጥነው ፌዴራል መንግሥትን መጠየቅ ይችላሉ። በብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አሰራር መሰረትም 72 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፈጣን ምላሽ ይሠጣል። ስለሆነም ከክልሎች የእርዳታ ድጋፍ ተጠይቆ በመዘግይቱ የሚፈጠር ችግር አይኖርም።
ፌዴራል መንግሥት በሃገሪቱ ከምግብ እህል ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮች መፍታት የሚችል አቅም አለው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ክልሎች በወቅቱ ባለመጠየቃቸውና ባለማሳወቃቸው የሚፈጠር ችግር ካለ ኃላፊነቱ የክልሎች እንደሆነ መታወቅ አለበት።
ከብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን በተገኘ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ ስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የምግብ እህል ተረጂዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በግጭት የተነሳ የተፈናቀሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በድርቅ የተጎዱ ናቸው።
ለእነዚህ ተረጂዎች ድጋፍ የሚደረገው በሶስት የተለያዩ አካላት ሲሆን መንግሥት አምስት ሚሊዮን፤ የአለም ምግብ ፕሮግራም በሱማሌ ክልል ያሉትን አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን፤ ቀሪዎቹን ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህብረት ይሸፍናል። ይህም በየአካባቢው ያሉ ዜጎች የሚደርጉትም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያሳያል። ስለዚህ መንግሥት ዜጎቹን ለመታደግ አስፈላጊውን ስራ እየሰራ መሆኑ መታወቅ አለበት። ሌሎችም ከፖለቲካ ትርፍ በፊት ሰብአዊነት ስለሚቀድም ለሰብአዊነት ሊሰሩ ይገባል።
እንደ ኮሚሽኑ መረጃ፤ የጌድኦ ዞን በተመለከተም የፀጥታ ስጋት ያለባቸው 54 ሺህ 858 ዜጎች በአዲስ መልክ መፈናቀላቸውን መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ ለኮሚሽኑ ደርሷል። በዞኑ በገደብ ጎቲቺ 38 ሺህ 252፣ በገደብ ከተማ 7ሺህ 263፣ በዲላ ዙሪያ (ጫጩ) 9ሺህ 343 ዜጎች በቋሚነት የሚረዳው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህብረት ነው። እሱ እስከሚረከባቸው ድረስ ግን ብሔራዊ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን 200 ኩንታል ብስኩት፣ 200 ኩንታል አተር ክክ፣ 200 ኩንታል ዱቄት እና 2000 ሊትር ዘይት እንዲሁም ከተረጂዎች መካከል 35 በመቶው አጥቢ እናቶችና ነፍሰ ጡሮች ይሆናሉ ተብሎ ስለታሰበ 200 ኩንታል አልሚ ምግብ መላኩን መረጃው ያመለክታል። ነገር ግን በክልሉና በፌዴራል ደረጃ ያሉ አካላት አለመናበብ በተፈጠረ ክፍተት ፌዴራል መንግሥት ዜጎችን የዘነጋ በሚመሰል መልኩ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶበታል። ይህ ተገቢ አይደለም።
በአጠቃላይ ዜጎች በማንኛውም መልኩ ጉዳትና አደጋ ሲደርስባቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ተናበው በመስራት ችግሩን በአፋጣኝ ሊቀርፉ ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኃላፊነቱን ያልተወጣ አካል ሲገኝና በዚህም ህዝብ ተጎጂ ሲሆን ደግሞ ችግሩን የፈጠረው አካል ተለይቶ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011