በቀጣይ የፈረንጆች አመት 2023 ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ኮትዲቯር በምታዘጋጀው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የአገራቱ የምድብ ማጣሪያ ድልድል ባለፈው ሳምንት ይፋ መደረጉ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ጠንካራ በሆነው ምድብ አራት ከግብጽ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር መደልደላቸው ይታወሳል።
የአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ጨዋታዎቹም ከመጪው ግንቦት መጨረሻ አንስቶ ይካሄዳሉ። ኢትዮጵያም በአህጉሪቱ ታላቅ የእግር ኳስ መድረክ ተሳታፊ ለመሆን በቅርቡ ዝግጅት እንደምትጀምር ይጠበቃል።
ይሁንና ባለፈው የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ከስምንት አመት በኋላ ተሳታፊ የነበሩት ዋልያዎቹ ዳግም በመድረኩ ለመታየት ከተጋጣሚዎቻቸው ጥንካሬ ባሻገር ሌላ ፈተና እንደተደቀነባቸው የስፖርት ቤተሰቡ ስጋት አድሮበታል። ይህም ስጋት የኢትዮጵያ ስቴድየሞች ካለፈው አመት ጀምሮ የካፍን መመዘኛ ባለማሟላታቸው ዋልያዎቹ በሜዳቸው አለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያከናውኑ ታግደው መቆየታቸው ሲሆን፣ ይህም የስቴድየሞች ጉዳይ መፍትሔ ሳይበጅለት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች መቅረባቸው ነው።
የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚያስተዳድረው ካፍ ከቀናት በፊት ለየአገራቱ አባል ፌዴሬሽኖች በአንድ ሳምንት ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስቴድየሞችን እንዲያሳውቁ ደብዳቤ መጻፉ መረጃዎች ወጥተዋል።
ካፍ እያንዳንዱ አገር የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስቴድየሞችን እንዲያሳውቅ የሚያስቀምጠው ቀነ ገደብ የቱንም ያህል ቢራዘም ከወ የዘለለ እድሜ እንደማይሰጥ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ የወጣላቸው መርሃግብር አስረጂ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ይሁን የተለያዩ ስቴድየሞችን የሚያስተዳድረው የመንግስት አካል ባለፉት ጊዜያት ስቴድየሞች በካፍ ይሁንታ ማግኘት በሚችሉበት ደረጃ ስራዎችን ማከናወን እንዳልቻሉ ሚስጥር አይደለም።
ሁሉም የኢትዮጵያ ስቴድየሞች በካፍ ከመታገዳቸው በፊት በብቸኝነት አለም አቀፍ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የቆየው የባህርዳር ስቴድየም በመጨረሻም በጥቃቅን ነገር ግን ትኩረት በሚፈልጉ ክፍተቶች ከእገዳ እንዳልዳነ ይታወቃል። አሁንም ይህ ስቴድየም ጥቃቅን ክፍተቶቹን በመሙላት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይደርሳል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ቢኖርም፣ ስቴድየሙ አሁን ያለበት ሁኔታ ከካፍ እገዳ እንደማያድነው የብዙዎች ስጋት ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የባህርዳር ስቴድየም እስካሁን የምሽት መብራት አልተገጠመለትም። ከዚህ በተጨማሪ ቀድሞም ሜዳውን የሚንከባከበው ቋሚ ድርጅት አለመኖሩ ለእገዳው ዋና መነሻ ቢሆንም ይህ ችግርም አሁንም ድረስ አልተቀረፈም።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ስታዲየሞችም ከመብራት ውጪ የመጫወቻ ሜዳቸው እና የመልበሻ ክፍሎቻቸው በጣም በአሳፋሪ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በቤትኪንግ ፕርሚየር ሊግ ጨዋታዎች እንዲሁም በሃምሳ አንደኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ወቅት ለመታዘብ ተችሏል። ትንሽ ተስፋ ሊጣልበት የሚችለው የባህርዳር ስቴድየም ቀጣዩን የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ጨዋታዎች የሚያስተናግድ ከመሆኑና ጨዋታዎቹንም ዲኤስ ቲቪ በቀጥታ የሚያስተላልፍ በመሆኑ የመብራት ጉዳይ ሊስተካከል ይችል ይሆናል። ነገር ግን ካፍ የግምገማ ቡድኑን ከመላኩ አስቀድሞ የሜዳውም ይሁን የመብራቱና ሌሎች መስተካከል ይገባቸዋል የተባሉ ክፍተቶች ባሉት ጥቂት ቀናት እስካልተስተካከሉ እገዳው የማይቀር ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ዋልያዎቹ በመጪው ሰኔ ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚና ጠንካራ የሆነችውን ግብጽን በሜዳቸው እንደሚገጥሙ ይጠበቃል። ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማቅናት በሜዳቸው የሚያከናውኗቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ነጥቦችን ለማሳካት ትልቅ እድል እንዳላቸው ካለፉት ተሞክሮዎች መረዳት ይቻላል።
ይሁን እንጂ ዋልያዎቹ በሜዳቸው መጫወት የሚገባቸውን ወሳኝ ፍልሚያ በሌላ አገር ለማድረግ ከተገደዱ ትንሹን የማሸነፍ እድላቸውን ለተጋጣሚያቸው አሳልፈው እንደመስጠት እንደሚቆጠር ግልጽ ነው። በበርካታ አጋጣሚዎች ለመታዘብ እንደተቻለው የምእራብና ሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሲጫወቱ አየር ንብረቱ ይከብዳቸዋል። ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ ኮትዲቯርን የመሳሰሉ ትልልቅ ቡድኖች ጭምር አሸንፈው ወሳኝ ነጥቦችን በመሰብሰብ መሳተፍ የቻሉትም በእንዲህ አይነት ምክንያቶች ጭምር ነው።
አሁንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም ጋር በመሆን የስቴድየሞችን ችግር ካልቀረፉ የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ጉዳይ እግር ኳሳዊ ባልሆኑ ችግሮች ጭምር ሊከሽፍ የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014