እርግጥ ነው ታሪክን ወደ ኋላ፣ በተለይም በጣም ወደ ኋላ ሄድ ብሎ ላገናዘበ ብቸኛው የፈጠራ መፍለቂያ ስፍራ ትምህርት ቤቶችና ዘመናዊ ትምህርት ነው ብሎ መደምደም ያስቸግር ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረበትና የሰውን ልጅ እስከ ዛሬ ድረስ ይዘውት የዘለቁት ሰው ሰራሽ ቅርሶች፣ መሳሪያዎች ወዘተ የተፈጠሩበት ዘመን የትና የት ልዩነት ስላለው ነው። እንደውም እንደ አንዳንድ ጥናቶች፣ በተለይም አርኪዮሎጂስቶች አካባቢ የተሰሩት እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ የተራቀቀው ዛሬ ሳይሆን ያኔ፤ ድሮ ነው። ዛሬማ ያንን እንኳን ደግሞ መስራት አልተቻለም።
እንደ ባለ ሙያዎች ጥናታዊ ድርሳን ከሆነም እራሱ “ሥራ ፈጠራ” የሚለውም፣ ሰማይና ምድር ከተዘረጉበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰላ፣ እድሜው ገና ለጋ ሲሆን፣ ከ”ሥራ ፈጠራ (ኢንተርፕረነርሺፕ)” ማሰልጠኛ ማኗል ላይ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው “የሥራ ፈጠራ ጽንሰ ሀሳብ የተጀመረው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይህ ቢዝነስ አስተሳሰብ ሲቀነቀን እስከ አሁን፣ እስካለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ደርሷል። ብዙዎች ይህንን ጽንሰ ሃሳብ ከግል ሥራ ፈጠራ (በግል ሥራ መጀመር) ጋር የሚያያይዙት ሲሆን፤ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ደግሞ ከዚህ ባለፈ ተጨማሪ ትርጉም እና ትንታኔ ይሠጡታል።” (ሥራ ፈጠራ ወይም ኢንተርፕረነር “አዲስና የተለየ የቢዝነስ ሃሳብ ወይም ዘዴ ይዞ የተነሣ” የሚል ብያኔን የያዘ መሰረተ ሀሳብ መሆኑንም ልብ ይሏል።)
አሁን አሁን “ለመንደሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጨው ኢትዮጵያዊ ተማሪ” (በደቡብ ኢትዮጵያ ቦረና ዞን፣ በቱላ ድር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ አዳን ሁሴን)፣ “የራሱን አውሮፕላን ለመስራት ያለመው ኢትዮጵያዊው መምህር” (የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር አማኑኤል ባልቻ)፣ “ተራኪ የተባለ የመጻሕፍት ትረካ መተግበሪያ ፈጠሩ” (ናሆም እና አቤል)፣ “ከባቄላ እና ገብስ ለሕፃናት አልሚ ብስኩት ያዘጋጁት ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች” (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ4ተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪዎችና በአንድ ዶርም ውስጥ የሚኖሩ አራት (ናኦል አዱኛ፣ ኪሩቤል እንግዳወርቅ፣ ሙሴ አብርሃም እና ዮሴፍ ታሪኩ) ተማሪዎች)፣ “በቆሎን ወደ ቢራ የቀየረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ” (በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ኤርሚያስ ዋቅሹማ)፣ “በኢትዮጵያ የተሰራ መኪና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚታትረው ወጣት” (የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ሺሃብ ሱሌይማን)፣ “የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለማቅለል ዘመናዊ ጎተራ የሠራችው ወጣት” (ደራርቱ ደረጀ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የባዮ ሜዲካል ትምህርት ክፍል መምህርት)፣ “በኤሮስፔስ ዘርፍ አሻራዋን ለማሳረፍ እየሰራች ያለችው ኢትዮጵያዊት ወጣት” (ቤተልሄም ግርማ)፤ “በአውሮፕላንና ድሮን ፈጠራ ላይ የተሰማራው ወጣት” (ወጣት ብሩክ በቀለ) እና ሌሎች በርካቶች ለህዝብ የተገለፁበትና ስራዎቻቸውም ለእይታ የቀረቡበት ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል። የዚህ ጽሑፍ አላማም ይኸው አይነት የወጣት ተማሪዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እራሳቸውና አገራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ይኖር ዘንድ ግንዛቤን መፍጠር ነው።
ከላይ የጠቀስነው ማሰልጠኛ ማኗል ላይ እንደሰፈረው ከሆነ ከፈጠራ ሥራ አኳያ የመንግስታት ሚና ከፍተኛ ነው። “በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በመሰረታዊነት በአንድ ነገር ላይ ይስማማሉ፤ አንድ አገር ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ እንዲሁም በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲያስብ ሁነኛው መንገድ የሥራ ፈጠራ ነው። አዳዲስ እና ጀማሪ የሥራ ዘርፎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በገቢ እድገት እንዲሁም በድህነት ቅነሳ በኩል ለአገራት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስታት ለእነዚህ አዳዲስ የሥራ ዘርፎች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።”
እዚህ ላይ “ፈጠራ” የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ስንጠቀምና እሱን ይዘን ዳር ለመድረስ ስንጣጣር መሰረታችን ከሚመለከተው አካል የተገኘው፤ “የአንድ ሰው አእምሮ እንቅስቃሴ ውጤት፣ የምርት እና የጉልበት ብቃትን የሚጨምር መሆኑ የሚታመንበት” የሚለውና “ሥራ ፈጠራ ማለት አዲስ እሴት የመፍጠር ሂደት ሲሆን ስጋትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ግለሰብ ወይም የሆኑ የግለሰቦች ጥምረት በአግባቡ ያልተፈቱ ችግሮችን አዲስ ነገር በመፍጠር ወይም ባሉ ነገሮች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ለገበያው ፍላጎት ምላሽ መስጠት ነው። በዚህ ፍቺ ውስጥ አራት ትልልቅ ሀሳቦችን ማየት እንችላለን። “እሴት መፍጠር”፣ “ስጋትን መቀበል”፣ “አዲስ ነገር መፈጠር” እና “ሂደት” የሚሉት ሲሆኑ፤ ማንኛውም የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ከእነዚህ አምዶች አንፃር መቃኘት ይገባዋል።” የሚለው የጽንሰ ሀሳቡ ብያኔ ነው። አንባቢም ጽሑፋችንን ከዚሁ አኳያ እንዲረዳልንና እያወዛገበ (የተገለበጠ ሁሉ ፈጠራ፤ ገልባጩም ፈጣሪ ነው የሚል) ባለው አተያይ እንዳይረዳን ማሳሰብ እንፈልጋለን።
“መንግሥት አዳዲስ አይነት ፖሊሲዎችና አዲስ አይነት ማበረታቻዎችን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ እየሰራ ነው። በዚህ ዘርፍ በጣም በርካታ እድሎችና አማራጮች አሉ” የሚለውን ተከትሎ “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ባሉባት ኢትዮጵያ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ያሉና በርካቶችን ሊያሳትፉ ከሚችሉ የሥራ ዘርፎች” ተብለው በባለሙያዎች ከተዘረዘሩት መካከል የቱሪዝም ዘርፍ፣ የግብርና ዘርፍ፣ የዲጂታልና የአይሲቲ ዘርፍ፣ የማዕድን ዘርፍ፣ የሎጂስቲክስና የንግድ መጋዘን አገልግሎት እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በመሆኑም ወጣቶቻችንም ሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ወይንም የፈጠራ ሰዎች ከወዲሁ በእነዚህ ላይ አተኩረው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይታወቃልና እነዚህን መስኮች ልብ ማለት ያሻል ማለት ነው።
ፈጠራን ከመማር-ማስተማር ሂደት፣ ወይም ከትምህርት ተቋማት አኳያ ስንመለከት በዋናነት የሚከተሉት የፈጠራ አይነቶች ትኩረት ሲደረግባቸው የምንመለከት ሲሆን፤ እነሱም “ሳይንሳዊ ፈጠራ” (የመጨረሻው ምርት እውቀት ነው)፤ “የቴክኒክ ፈጠራ” (ቴክኒካዊ ወይም የቴክኖሎጂ እድገት ሲሆን፤ የመጨረሻው ምርት ማሽን ወይም ዲዛይን ነው፤ “አርቲስቲክ ፈጠራ” (ለዓለም ውበት መጨነቅ ሆኖ፣ ውበት የመፈለግ ፍላጎትና ተግባር ሲሆን፤ የመጨረሻው ምርቱም የሥነ-ጥበብ (ግጥም፣ ሥዕል፣ ቅርፅ) ነው)፤ እና “የጋራ ፈጠራ” (የሥነ ጥበብ ስራዎች፣ ትርጓሜያቸውን … ይመለከታል)፤ ስነ-ልቦናዊ ፈጠራ (ዕውቀት የማስተማር ልዩ ስልት ሆኖ፣ ቀዳሚ ዓላማው አዲስ ነገር ማስተማር ነው)።
ትምህርት ሚኒስቴርም “የተማሪዎችን የፈጠራ ውጤቶች በአግባቡ መምራት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ” በሚል ርእስ በድረ-ገፁ ላይ ባስነበበው ዜና “በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በጥበብና ሂሳብ ዘርፍ የሚቀርቡትን የተማሪዎችን የፈጠራ ሥራዎች ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ረቂቅ መመሪያ” አዘጋጅቻለሁ ማለቱ ከላይ ካቀረብነው አንቀፅ ጋር ሲተያይ ተደጋጋፊ እንጂ የተለየ ሆኖ አይገኝም። በተደጋጋሚም “ተማሪዎች በመማሪያ ክፍል የቀሰሙትን እውቀት ወደ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤት ለመቀየር በትኩረት መሰራት እንደሚገባ”ው አፅንኦት ሰጥቶ ሲናገር መሰማቱም (መሬት ላይ ያለውን ባናውቅም) ተስፋ ሰጪ ነው።
እነዚህ የፈጠራ አይነቶች ናቸው እንግዲህ ፈጠራን ከትምህርት ተቋማት ጋር አያይዘን እንድናነሳ ያደረጉን። በእነዚሁ ተቋማትም ሲዘወተሩ የሚታዩትም በዋናነት እነዚሁ ናቸው። ለምሳሌ ያህልም የሂሳብና የሳይንስ ትምህርት ፈጠራዎችን በቴክኖሎጂ አሰራር በመደገፍ ለተማሪዎች ፍላጎትና ዝንባሌ አጽንኦት የሚሰጡ መሆናቸው በእኛው አገር ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል።
እንደ አገርም “ጀነሬሽን አንሊሚትድ የተሰኘ ድርጅት ከኢትዮጵያ የሥራ ክሂሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ አምስት ከተሞችን የሚያሳትፍ የሥራ ፈጠራ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ። […] ጥምረቱ በዓለም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎች የሚያዳብሩበት ክህሎታቸውን በመገንባት፣ ከተለያዩ የሥራ ዕድሎች ጋር በማገናኘት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማድረግ ትልቁ ዕቅዱ መሆኑን ሚስ ኢቭ ተናግረዋል። የተለያዩ የንግድ ሥራ ሐሳብ ላላቸው ወጣቶች ከውድድሩ በኋላ ሥራ ማስጀመሪያ የገንዘብ ድጋፍ እስከ 100ሺህ ብር ይሰጣቸዋል።” የተባለውንም ማስታወሱ ተገቢ ሲሆን፤ “ውድድሩ በአለም አቀፍ ደረጃ መሆኑን፣ ከ35 በላይ በሚሆኑ አገሮች እንደሚካሄድ፣ በኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ዘላቂ የልማት ግቦችን ስኬታማነት የሚያፋጥኑ ሐሳቦችን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችላቸው ነው።” መባሉንም አለመርሳት ተገቢ ነው። “በኢትዮጵያ አሁን አሁን ወጣቶች የተለያዩ አስደናቂ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ሲያቀርቡ ይታያል። ያም ሆኖ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ብዙዎቹ ወደ ተግባር ሲሸጋገሩ አይታይም።” የሚለውም ቁልፉ ጉዳይና አስቸኳይ መፍትሄን የሚሻ ነው።
ጉዳዩን በተናጠል፣ ማለትም ከተማሪዎችና መምህራን አኳያ መመልከቱ እያልን ያለነውን ምሉእ አያደርገውም። ምሉእ ይሆን ዘንድ ከግለሰብ ፈጣሪዎችም ባለፈ እንደ ተቋም በተቋም ደረጃ የፈጠራ ባለቤት መሆን ይቻላል፤ መፍጠርም እንደዛው። ለዚህ ደግሞ “የደብረ ብርሃን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የገብስና ስንዴ መውቂያ ማሽን አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን፣ ከአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንፃር የአርሶ አደሮችን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ ነው። መሣሪያውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብና አርሶ አደሮች በማሽኑ እንዲገለገሉ በማድረግ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት አዘጋጆቹ ገልጸዋል።” የሚለው የወቅቱ መረጃና ፈጠራው ምን ያህል የአካባቢውን አርሶ አደሮች ችግር እንደፈታ ሲነገር የነበረ መሆኑ ነው። ይህንንና የመሳሰሉትን ስናይ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ መሆኑን እንረዳለንና፣ ይህ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል።
እንደwhat-is-entrepreneurial-ability ማብራሪያ አንድ ጥሩ ሥራ ፈጣሪም ይሁን የፈጠራ ሰው የሚከተሉትን መሆንና ማድረግ እንዳለበት ይመከራል። እነሱም፣ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ገለልተኛ፣ ታታሪ፣ በራስ የመተማመን፣ አፍቃሪ ሰው፣ ሥነ ምግባራዊ፤ ጠንካራ ፍላጎት፣ የተረጋጋ ስሜት ባለቤት፣ የአመራር ባሕሪያትን የተላበሰ፤ ደንበኛ-ተኮር፤ ከሰዎች ጋር መግባባት የሚችል፣ ቡድን መምረጥ፣ ሌሎችን ለቡድን ስራ ማነሳሳት፣ የቡድን ሥራን መቆጣጠር (መምራት)፤ ለፈጠራ፣ ለአዳዲስ ሀሳቦች እና ለአቀራረብ ክፍት መሆን፤ የሌሎችን አስተያየት ማዳመጥ፣ ለጉዳዩ ፍላጎቶች፣ ለቡድን ሲባል የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ዝግጁ መሆን፤ መተንተን፣ ማቀድ፣ መተንበይ መቻል፤ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ መኖር፤ እንደ ደንበኛ (ገዢ) ማሰብ መቻል፤ በሕጋዊ ጉዳዮች ላይ እውቀት ያለው ሆኖ መገኘት።
ባጠቃላይ፣ ከላይ በወፍ በረር እንደ ተመለከትነው ፈጠራ ለአለማችን እዚህ መድረስ የአንበሳውን ድርሻ እንደ ተጫወተው ሁሉ ወደ ፊት ስለ መገስገሷም ወሳኙ እሱው ነው። በተለይ ለእንደኛ አይነት አገራት የ”ፈጠራ”ም እንበለው የ”ሥራ ፈጠራ” የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነውና ፋታ የሚሰጥ አይደለም። በኋላ ቀር አሰራርና እጅ እግር በሌለው ችግር እግር ከወርች ታስሮና ይሄንን ሁሉ ሥራ አጥ ወጣት ይዞ ሥራ ፈጠራን ችላ ማለት የጤና አይደለምና እዳው ገብስ አይደለም። ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር “የኢትዮጵያን የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳ መምራት” የሚለውና “እስከ 2022 20 ሚሊዮን የሥራ እድሎች” በማለት ያስቀመጠው ግብ ይሳካ ዘንድም የሁሉም ወገን ርብርብ ያስፈልጋል እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014