እንደ መግቢያ
ጉዳዩ፣ አቶ ሳሙኤል ጣሰው እና በቀለ ገብረሕይወት የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በይዞታ ይገባኛል ላይ ለዓመታት የተከራከሩበትና በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ብይኖች የተሰጠበት ነው። ዳሩ ግን አንዱ ሲፈረድለት ሌላው ፍርድ ሲጓደልበት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ሲረታ ሌላው ሲረታ ጠመዝማዛ መንገዶች የበዙበትን የክርክር ሂደትን የሚያሳይ ነው።
አቶ ሳሙኤል እንደሚሉት፣ “አቶ በቀለ ገብረሕይወት የእኔን ይዞታ የራሳቸው አስመስለው ለማቅረብና በተጭበረበረ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ፈልገዋል፤” ሲሉ ይከሳሉ።
አቶ በቀለ በበኩላቸው፤ “አቶ ሳሙኤል ከህግ አግባብ ውጭ የታገደ ካርታ በመጠቀም ብሎም የመከነ ካርታ ህጋዊ አስመስሎ በመጠቀም የማይገባውን ጥቅም የሚፈልግ ይልቁንም የእኔን መብት የሚጋፋ ግለሰብ ነው” ሲሉ ይኮንናሉ። በዚህ መልኩ እንደ መግቢያ ያነሳነውን የእሰጥ አገባ ሃሳብ ዘርዘር አድርገን እንመልከተው፡-
አቶ በቀለ እንደሚሉት፤
አቶ በቀለ ገብረሕይወት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ስሙ ወረዳ 25 ቀበሌ 05 በአሁኑ መጠሪያው ወረዳ 10 የቤት ቁጥር 081 ባለይዞታና ነዋሪ ናቸው። አቶ በቀለ ለዝግጅት ክፍላችን ይዘውት በመጡት ቅሬታ፣ በማን አለብኝነትና ህግን ባልጠበቀ አካሄድ በህጋዊ መንገድ በሚያስተዳድሩት የይዞታ ቤታቸው ላይ ድርብ ካርታ እንደወጣባቸውና ካርታውም በፍርድ ቤትና በከተማው ከንቲባ ቢሮ ትዕዛዝ እንዲመክን መደረጉን ያስረዳሉ።
ይሁንና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማና በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 የሚገኙ ህግ አስፈጻሚዎች የፍርድ ቤቱንና የከንቲባ ቢሮውን ትዕዛዝ ወደ ጎን በመተውና ትዕዛዙን ሊፈፅሙ እንዳልቻሉና በዚህም ምክንያት ለእንግልት መዳረጋቸው ይገልፃሉ። የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማና ወረዳ 10 የህግ አስፈጻሚ አካላት የፈጸሙብኝን በደል ‹‹ሕዝብ አይቶ ይፍረደኝ!›› ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለው ነበር።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አመራሮች፣ ግለሰቦችና የሰነዶችን በመመርመር ያገኘውን ውጤት ለሕዝብ መፍረድ እንዲያችል ጉዳዩን ለሕዝብ አቅርቦ ነበር። አቶ በቀለ ገብረሕይወት በኮልፌ ለምለም የህብረት ሥራ ማህበር በ1997 ዓ.ም ከ500 ሰዎች በላይ በወቅቱ በነበረው መንግስት በመደራጀት ቦታው ተከፋፍሎ ሁሉም የማህበሩ አባል በራሳቸው ፕላን መሰረት ቪላ ቤት በመስራት መኖር መጀመራቸውን ያወሳሉ።
‹‹ከወይዘሮ ታየች አጎናፍር በ1986 ዓ.ም 340 ካሬ ሜትር ይዞታ ገዝቼ በካርታ ቁጥር ኮ/ቀ/የማ/ን/መ/122/17448/00 በቀን 23/9/1997 ዓ.ም በስሜ የተመዘገበ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቶኛል፤ እኔም ዲዛይን በማሰራት ቤት ሰርቼ እየኖርኩኝ ባለበት ሁኔታ የእኔ አጎራባች የነበረው አቶ ሳሙኤል ጣሰው የተባለ ግለሰብ አጣና ሲሸጥበት የነበረው ሙሉ በሙሉ በመንገድ ልማት ምክንያት ሲነሳ፣ ከእኔም ሁለት ሜትር በመንገዱ ምክንያት ተነስቷል። ይሁንና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ባሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የመሬት የይዞታ ኃላፊዎች በሙስና በመመሳጠር በይዞታ ካርታዬ ላይ ደርበው ለአቶ ሳሙኤል ካርታ ሰጥተዋል›› ይላሉ።
ግለሰቡ ‹‹በግድግዳዬ ላይ በአጣና፣ ብረት፣ በብሎኬት በመስራትና እንዲሁም ሸራና ላስቲክ በመወጠር በአካባቢው የማይታወቁ ሰዎችን በማከራየት ታይዋን በሚል ስም የተለያዩ የንግድ ሥራ እየሠራ እየተጠቀመ ይገኛል›› ይላሉ። ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ግንባታና ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት፣ ለግለሰቡ በቀን 7/8/2006 ዓ.ም በቁጥር 1230/2006 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤም የተሰጠ እድሳት ፈቃድን እንዲመክን መወሰኑን ዋቢ ያደርጋሉ።
ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ግንባታና ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ኃላፊው በአቶ ገረመው ንጉሴ የተፈረመ ደብዳቤ፤ ‹‹አቶ ሳሙኤል ጣሰው የተባሉት ግለሰብ በወረዳ 10 ቀበሌ 05 የቤት ቁጥር 434 የሆነውን ቤት እድሳት ፈቃድ መውሰዳቸውን ይታወቃል፤ ይሁንና የወሰዱት የእድሳት ፈቃድ በአጎራባች በኩል የድንበር ክርክር ስለተነሳ የተሰጠው የእድሳት ፈቃድ ይዞታነቱ የእርሶ መሆኑ ተረጋግጦና አሁን ባለው ይዞታ መሰረት ካርታው ተስተካክሎ እስኪቀርብልን ድረስ የተሰጠው የዕድሳት ፈቃድ እንደማያገለግል እናሳውቃልን›› የሚል ደብዳቤም ከመንግስት አካላት ተፅፎ ነበር።
ከዚህ በኋላም ደረጃ በደረጃ እስከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀድሞ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ድረስ አቤቱታ ማቅረባቸውና ከንቲባውም በአስቸኳይ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን የሚያስታውሱት አቶ በቀለ፤ ከተቋቋመው ኮሚቴ መካከልም የወቅቱ የቅሬታ ሰሚ ኃላፊ ወይዘሮ ሃይማኖት ወልደ ገብርኤልና የመሃንዲስ ኃላፊው አቶ ጌቱ ዘውዴ የተባሉ ግለሰብ ይገኙበት እንደነበር ይጠቅሳሉ።
በወቅቱም እነዚህም ኮሚቴዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ግራ ቀኙን በማጣራት ለከንቲባው በካርታዬ ላይ ድርብ ካርታ የተሰራ እንደሆነ ሪፖርት አቅርበዋል፤ በዚህ መስረት በ24/4/2009 ዓ.ም በነበረው ነባር ካርታዬ መሠረት እንዲስተካከልና በይዞታዬ ላይ ያለ ማንኛውም ግንባታ በማንሳት በአምስት ቀን ውስጥ ፈፅማችሁን ሪፖርት እንድታደርጉ የሚል የፅሁፍ ትዕዛዝ ከከንቲባው ፅህፈት ቤት ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሰጠቱንም ይገልፃሉ። ይሁንና ትዕዛዙ የተሰጣቸው አካላት ከግለሰቡ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት ጉዳዩን ለመፈፀም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል›› ሲሉ ነበር ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ቅሬታ ያቀረቡት።
አቶ በቀለ እንደሚገልጹትም፤ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ግንባታና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ ፀረ ሙስና እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ጥቆማ ተሰጥቶታል። ኮሚሽኑም በቀረበለት ጥቆማ መሰረት ቦታው ድረስ በመሄድ ጉዳዩን መርምሮ አጥርቷል። ከዚህ በኋላም ከእርሳቸው ካርታ ላይ የተደረበ ካርታ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል። የግለሰቡ ድርብ ካርታ መሆኑን በማረጋገጥ ከክፍለ ከተማው ሥራ አስፈፃሚ ጋር በመሆን የተደረበው የግለሰቡ ካርታ እንዲመክን ተደርጓል ይላሉ።
የአቶ ሳሙኤል ምላሽ
አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ ጉዳዩ አቶ በቀለ ገብረሕይወት እንደሚሉት ሳይሆን እውነታው ሌላ ነው ይላሉ። በአሁኑ ወቅት ክርክር የተነሳበትን ቦታ እርሳቸው መጋቢት 3 ቀን 1996 ዓ.ም ከሌላ ግለሰብ በግዥ ያገኙት ንብረት ስለመሆኑ ይናገራሉ። ለዚህም ማስረጃ ይሆኑ ዘንድ ግዥ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ህጋዊ መስፈርቶች ያሟላ ሲሆን ዕዳ እገዳ የሌለበት፤ የሌላ ግለሰብን ንብረት ወይንም ድንበር የማይነካ ስለመሆኑም ያስረዳሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ይዞታው ከአቶ በቀለ አቻ የሚሆን ሲሆን በመነገድ መሰረተ ልማት እንደፈረሰባቸው ይናገራሉ። ዳሩ ግን ምትክ ሌላ ቦታ ስላልተሰጣቸው በቀረው ቦታ ላይ ግንባታ አካሂደው ሥራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ። ታዲያ አቶ በቀለ ገብረሕይወትም የራሳቸው የሆነ ይዞታ ያላቸው ሲሆን፤ ከጉርብትና ውጭ የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ ያስረዳሉ።
አካባቢው የመንገድ መሰረት ልማት እየተሰራ ሲመጣ አስፋልት መንገድ የእኔ ቤት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ፈረሰ። ነገር ግን የቀረው ቦታ ከ75 ካሬ የማያንስ በመሆኑና በዚያው ቦታ መኖር ስለሚቻል ሕይወት ቀጠለ ይላሉ። በቀረው ቦታ ሥራ መሥራት ከመጀመራቸው ባሻገር ከቤታቸው በአንዱ አቅጣጫ ትርፍ ቦታ የነበረ ሲሆን ይህ ቦታ ደግሞ በሊዝ ከመንግስት አካላት ወደ ይዞታቸው ማካተታቸውንና ለዚህም ህጋዊ መረጃ እንዳላቸው ያስረዳሉ።
ታዲያ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ አቶ በቀለ ገብረሕይወት ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ ነጋ ጠባ ግጭት መፍጠር ጀመሩ። ነገሩ እየከረረ ሄዶ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤትም እንዳመራ ይናገራሉ። ዳሩ ግን በተለያዩ ፍርድ ቤቶችም ክርክር ቢያደርጉም በለስ አልቀናቸውም፤ ተሸነፉ። ይህን ሽንፈታውን ግን አሜን ብሎ ከመቀበል ይልቅ በርካታ ምክንያቶችን እየደረደሩ ወረዳ፤ ክፍለ ከተማ፤ ከተማ አስተዳደር እያሉ ያንገላቱኝ ጀመር። ይህም ሆኖ በህጋዊ መንገድ ማሸነፍ ባለመቻላቸው በአስተዳደራዊ ጉዳይ እንዲታይ አሊያም ሌላ መንገድ እፈልጋለሁ እያሉ ዓመታትን በእሰጣ እገባ መጓዛቸውን ያስታውሳሉ። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን አቶ በቀለ የተዛነፈ ፍትህ እንዲሰፍን ለፍተዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።
ሰነዶች ምን ያሳያሉ?
አቶ በቀለ ገብረሕይወት፣ በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ሐሳቦች መካከል “የመከነ ካርታ መጠቀም እና የታገደ ካርታ ጥቅም ላይ የዋለ በማስመሰል ያልተገባ ጥቅም መፈለግና የእኔን መብት መጋፋት ነው” ሲሉ ይከሳሉ። አቶ ሳሙኤል ጣሰው ግን “ይህ ወቀሳ ውሃ የማይቋጥር ይልቁንም ደግሞ በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ነው” በማለት፤ ከዕግድ ነፃ የሆነና ያልመከነ ካርታ እንዳላቸው ህጋዊ መረጃዎችን አሉኝ በማለት ይከራከራሉ። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ቤት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በንግድ ፈቃድ ቁጥር 09/1/4/02156/96 የንግድ ፈቃድ ሲሆን፤ ከ10/08/ 1991 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እያሳደሱ ሲሠሩ መቆየታውን የሚናገሩበትን መረጃ ይዘዋል።
ከዕግድ ነፃ የሆነው ካርታ
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት በቀን 10/11/2010 ዓ.ም በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የይ/አስ/የሽ/ጊ/አገ/ፕ/ፅህፈት ቤት 168/2010 ለሰባት መንግስት ተቋማት በግልባጭ እንዳሳወቀውና ለአቶ ሳሙኤል ጣሰው በፃፈው ደብዳቤ መሰረት ‹‹ጉዳዩ፡- ታግዶ የነበረው በሴሪ ቁጥር 058762 በካርታ ቁጥር 10/46/1/10527 የተመዘገበው ካርታ እግዱ የተነሳ መሆኑን ማሳወቅን ይመለከታል በሚለው ደብዳቤ እንዲህ ያትታል።
አድራሻው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በቀድሞ አደረጃጀት ወረዳ 25 ቀበሌ 05 በቤት ቁጥር 434 ለተመዘገበው ይዞታ ወይንም ቤት ተሰጥቷችሁ የነበረው በሴሪ ቁጥር 058762፤ በካርታ ቁጥር 10/46/1/10527 የተመዘገበው ነባር ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳዳር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በቀን 24/04/ 09 ዓ.ም በቁጥር ይመስ/1223/09 በተፃፈ ደብዳቤ አቶ በቀለ ገብረሕይወት ለክቡር ከንቲባ ያቀረቡትን አቤቱታ አስመልክቶ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የፀደቀ ስለሆነ በውሳኔ መሰረት ተፈፃሚ እንዲደረግ ያሳወቀንን መነሻ በማድረግ በቀን 23/02/2009 ዓ.ም ለክቡር ከንቲባ ቀርቦ በጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ለመፈፀም ይቻል ዘንድ በቀን 13/10/10 ዓ.ም በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የይ/አስ/የሽ/ጊ/አገ/ኘ/ፅህፈት ቤት/19838/10 በተፃፈ ደብዳቤ ካርታው መታገዱን ያሳውቅናችሁ መሆኑ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ለአቶ በቀለ ገብረሕይወት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ለክቡር ከንቲባ ያቀረቡትን ቅሬታ በከንቲባ ጽህፈት ቤት በተቋቋመ ኮሚቴ በተደረገ ማጣራት በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ያቀረባችሁት ቅሬታ ተገቢነት ያለው ስለሆነ አስፈላጊው ማስተካከያ እንዲደረግ በማለት የመሬት ልማትና ማናጅመንት ቢሮ ያሳወቀውን መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽ/ጊ/አገ/ፕ/ ፅህፈት ቤት በቀን 15/10/2010 ዓ.ም በቁጥር ይአስ/3038/10 በተፃፈ ደብዳቤ በኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት አስፈላጊው እንዲፈፀም በማለት አሳስቦናል።
በመሆኑም ለካርታው መታገድ ምክንያት የነበረው ቀደም ሲል ለክቡር ከንቲባ በቀን 23/03/2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ድጋሚ በተዋቀረው ኮሚቴ በቀን 14/10/ 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ለክቡር ከንቲባው በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ የተሻረ ስለሆነ በቀን 13/10/2010 ዓ.ም በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የይ/አስ/የሽ/ጊ/አገ/ፕ/ፅህፈት ቤት/19838/10 በተፃፈ ደብዳቤ
ታግዶ የነበረው በሴሪ ቁጥር 058762፤ በካርታ ቁጥር 10/46/1/10527 የተመዘገበው ካርታ እግዱ የተነሳ መሆኑን እናሳውቃለን። የሚመለከታቸው ክፍሎችም እግዱ የተነሳ መሆኑን አውቀው አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በግልባጭ እንዲያውቁት ተድርጓል ሲል አቶ ሳሙኤልን ህጋዊነት ያረጋግጣል።
ያልመከነው ካርታ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በቀን 10/11/2010 ዓ.ም በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የይ/አስ/የሽ/ጊ/አገ/ፕ/ፅህፈት 167/2010 ለሰባት መንግስት ተቋማት በግልባጭ እንዳሳወቀውና ለአቶ ሳሙኤል ጣሰው በፃፈው ድብዳቤ መሰረት ‹‹መክኖ የነበረው በሴሪ ቁጥር 045220 በካርታ 10/46/1/10528 የተመዘገበው የሊዝ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ወደ ነበረበት የተመለሰ መሆኑን ማሳወቅን ይመለከታል›› በሚለው ደብዳቤ እንዲህ ያብራራል፡-
አድራሻው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በቀድሞው አደረጃጀት ወረዳ 25 ቀበሌ 05 በቤት ቁጥር 434 የተመዘገበው ይዞታ/ቤት በሴሪ ቁጥር 045220 በካርታ ቁጥር 10/46/1/10528 የተመዘገበው የሊዝ ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ በቀን 06/11/08ዓ.ም በቁጥር አ//ከ/81/ክ/የይ/አስ/የሽ/ጊዜ/አገ/ፕ/ጽ/ቤት/10412/08 በተፃፈ ደብዳቤ የመከነ ወይንም የተሰረዘ መሆኑ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በቀን 27/10/2010 ዓ.ም በቁጥር ይአስ/3173/10 እንዲሁም በቀን 04/11/2010 ዓ.ም በቁጥር ይአስ/3262/10 በተፃፉ ደብዳቤዎች የፍርድ ቤት ዕግድ የሌለው መሆኑ ታይቶ ካርታቸው ወደነበረበት እንዲመለስ በማለት ያሳወቀንን መነሻ በማድረግ ባደረግነው ማጣራት ይህ ደብዳቤ ወጭ እስኪደረግ ድረስ በማህደሩ ውስጥ የተያያዙ የፍርድ ቤት ዕግድ ሰነድ ያለመኖሩን አረጋግጠናል።
ስለሆነም አድራሻው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በቀድሞ አደረጃጀት ወረዳ 25 ቀበሌ 05 የቤት ቁጥር 434 ለተመዘገበው ቤት ወይንም ይዞታ በሴሪ ቁጥር 045220 በካርታ 10/46/1/10528 የተመዘገበው የሊዝ ይዞታ ካርታ በቀን 6/11/08 ዓ.ም በቁጥር አ/ከ/ክ/የይ/አስ/የሽ/ጊዜ/አገ/ፕ/ጽ/ቤት/10412/08 በተፃፈ ደብዳቤ ተጥሎ የነበረው የይምከን ውሳኔ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕ/ጽ/ቤት ከላይ ቀንና ቁጥሩ በተጠቀሱት ደብዳቤዎች የመከነው ካርታቸው ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማለት በሰጠው ውሳኔ በይዞታ አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 12/2004 አንቀፅ 16 ንዑስ አንቀፅ 16.8 ድንጋጌ መሰረት የካርታ መምከኑ ቀርቶ ወደ ነበረበት የተመለሰ መሆኑን እናሳውቃለን። የሚመለከታቸው ክፍሎችም የካርታው መምከን ቀሪ የተደረገ ወይም ወደ አገልግሎት የተመለሰ መሆኑን በግልባጭ እንዲያውቀው ተደርጓል።
የመንግስት አካላት ምላሽ
የዝግጅት ክፍላችን ጉዳዩ በዋናነት ወደሚመለከተው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በማምራት ለማጣራት የሞከረ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ለሚጠይቃቸው መረጃዎች ለመተባበር ፈቃደኛ አልነበሩም። ይልቁንም የአቶ በቀለ እና የአቶ ሳሙኤል ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ያመራ ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ መስጠት የፍርድ ቤቶችን በነፃነት የመወሰን መብት ላይ ጫና ማሳደር ነው የሚል ነበር። ከዚህም በዘለለ የግለሰቦቹ ክርክር ከይዞታ ይገባኛል ይልቅ ከግንባታ ፈቃድ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እልባት ሊሰጠው እንደሚችልም ጠቁመው ነበር። ይህ ሆኖ ሳለ ግን የአቶ ሳሙኤል ንብረት እንዲወረስና እንዲፈርስ ተደርጓል። ጉዳዩ በህግ ሂደት ላይ ከሆነ ሰሞኑን የአቶ ሳሙኤል ቤት ንብረት መፍረሱና መወረሱ ስለምን አስፈላጊ ሆነ ለሚለው ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
በአንድ ራስ ሁለት ምላስ
የአቶ ሳሙኤል ጣሰው ይዞታ ህጋዊ ስለመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይዞታው ቀደም ሲል ከሌላ ግለሰብ በግዥ ያገኙት ነው። በአካባቢው የመንገድ መሠረተ ልማት ሲሠራ ቤታቸው ከእኩሌታው በላይ ያፈረሰባቸው ቢሆንም ይልቁንም ደግሞ ለዚህ ቦታ ምትክ ያልተሰጣቸው መሆኑ እየታወቀ የክፍለ ከተማው አስተዳደር በቀን 20/7/14 ዓ.ም የመከነ ካርታ ስለመሆኑ ደብዳቤ ፅፏል። ክፍለ ከተማው ይህን ደብዳቤ ይፃፍ እንጂ ቀደም ሲል ይህ የአቶ ሳሙኤል ይዞታ ህጋዊ ስለመሆኑ ለበርካታ ጊዜያት በሰጠው መረጃ እና ደብዳቤ አሳውቋል። ይህም ሁሉ ሆኖ ሳለ በቀን 20/7/14 ዓ.ም የተፃፈው ደብዳቤ ይዞታው ህጋዊ አይደለም ይፍረስ የሚል አልተካተተበትም። ግን ከመቅፅበት የአቶ ሳሙኤል ንብረት ወደፍርስራሽ ተቀይሯል።
ክፍለ ከተማው በቀን 20/7/14 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ፅህፈት ቤት፤ ‹‹ጉዳዩ፡- በካርታ ቁጥር 10/46/1/10/928 በሴሪ ቁጥር 045220 የተሰጠውን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማምከንን ይመለከታል›› በሚል ደብዳቤ በቀን 20/7/2014 ዓ.ም በቁጥር አከክከ/መልማት ፅ/ቤት 14-02-14፤ ለአቶ ሳሙኤል ጣሰው በጻፈው ደብዳቤ እና ለ10 ተቋማት በላከው ግልባጭ እንዲህ ሲል ያትታል፡-
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የካርታ ቁጥር 10/46/18/10528 የሴሪ ቁጥር 045220 የሆነ ካርታ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የቤት ቁጥር 434 ለሆነ ቤት ተሰጥቶት የነበረና ከአሁን በፊት 6/11/08 ዓ.ም በቁጥር አ/ከ/ክ/ከ/የይዞ/አስ/የሽ/ጊዜ/አገ/ፕ/ጽ/ቤት /0412/2008 በሆነ የመከነ መሆኑ ተገልፆልዎት ባቀረቡት አቤቱታ በድጋሚ በቁጥር 167/2011 በቀን 10/11/2010 ዓ.ም ወደነበረበት ተመልሶ ነበር።
ነገር ግን በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 245802 በቀን 29/08/2010 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ የካርታው መምከን አግባብ ነው የሚል ውሣኔ በመስጠቱ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ በቁጥር አአ/መልአቢ/212/3499/2014 በቀን 09/7/ 2014 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ካርታው በመከነው አግባብ እንዲፀና መክኖ የነበረው ካርታ ወደነበረበት ተመልሶ ከሆነም ደግሞ እንዲመክን እንዲደረግ ያሣወቅን በመሆኑ ከቢሮው በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በካርታ ቁጥር 10/46/1/10928 በሴሪ ቁጥር 045220 በቤት ቁጥር 434 ለሆነ ቤት ተሰጥዎት የነበረ ካርታ በይዞታ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 12/2004 መሠረት የመከነ መሆኑን እያሣወቅን ግልባጭ የተደረገላችሁ መስሪያ ቤቶች ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሣውቃለን ሲል በተደጋጋሚ ጊዜ የአቶ ሳሙኤል ካርታ አለመመክኑን እና አለመታገዱን በገለፀበት አንደበት መልሶ ለአቶ ሳሙኤል የተሰጠውን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መመከኑን ይገልፃል።
አቶ ሳሙኤል ይጠይቃሉ!
እነዚህ ሁሉ ህጋዊ ሂደቶች ታልፈው እንዲሁም ሁኔታዎች ሁሉ መረጃዎችን መሰረት አድርገው እየሄዱ እያሉ ስለምን ዱብ ዕዳ ወረደ? ሲሉ ይጠይቃሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በህግ አግባብ እንደሚታየውና ሁኔታዎችን መረዳት እንደሚቻለው ሰው ህጋዊ ይዞታው ስለምን እንዲቀማ ይወሰናል ይላሉ። ንብረት ማውደም ቤት ማፍረስ እና መቆራረጥስ ከምን የመነጨ ነው ሲሉም ይጠይቃሉ። እልባት ባላገኘ ጉዳይ ላይ የመንግስት አካላትም ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ የግለሰብን ንብረት ማፈረስና ማውደም ዓይን ያወጣ የመብት ጥሰት መፈጸም በየትኛው ህግ ይዳኝ ይሆን ይላሉ። ለመሆኑ መፍረስ ቢኖርበት እንኳን ግለሰቦች ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው አይገባምን፤ ንብረትስ በሥርዓት እንዲነሳ አይደረግም? በመንግስት አካላትና በተዋረድ በሚመለከታቸው ህጋዊ አካላት ምንም ሳይነገርና በደብዳቤ ሳያሳውቁ የግለሰብን ንብረት ከጥቅም ውጭ እንዴት ሊደረግ ይችላል ሲሉ ግራ በመጋባት ስሜት ይጠይቃሉ።
ከምንም በላይ ይዞታው ያልመከነ ካርታ እና በዚህ አግባብ እገዳ የሌለበት መሆኑን ማስረጃ እያለ መልሶ ራሱ ክፍለ ከተማው የሚጣረስ ተግባር ውስጥ ለምን እንደገባ ለማወቅ መቸገራቸውን ይናገራሉ። ይህም ሆኖ ሳለ አፍራሽ ግብረ ኃይሎች በድንገት መጥተው ማፍረሳቸው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት መፈፀማቸውንና ኃይል መጠቀማቸው በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ። ታዲያ ይህን መሰል ዓይን ያወጣ ድፍረትና የመብት ጥሰት ወደየት አቤት ማለት ይቻላል ሲሉ ፍትህ መጠማታቸውን ይናገራሉ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014