ሴቶች ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የማስቀጠል ፀጋ የተጎናፀፉ ድንቅ ፍጡሮች ናቸው። ነገ ልምላሜ ሕይወት ያለው ተስፋ የሚሰጥ፣ ዓለምን የሚያገለግል፣ ለሕዝብ የሚቆም “ሰው” የሚባል፤ በጣም ክቡር የሆነ ፍጡር በሴቶች አማካኝነት ነው ዓለምን የሚቀላቀላት። በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች እነዚህ እናቶች በወሊድ ወቅት በደም መፍሰስ፣ በፌስቱላና በሌሎች የጤና ችግሮች ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳያጡ፤ ፅንሱም በአጭር እንዳይቀር እጅግ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋሉ።
የዛሬ እንግዳችን ሲስተር እታለማሁ ገብረዮሐንስ ይህንኑ የተቀደሰ ተግባር ሲያከናውኑ ከቆዩ የጤና ባለሙያዎች አንዷ ናቸው። በሙያቸው አዋላጅ ናቸው። ከባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ከሥራ ገበታቸው በጡረታ ቢገለሉም 40 ዓመታትን ሕይወትን በሚያስቀጥል ሙያ አገልግለዋል። ከአራት አሥርቱ ዓመታት የሥራ ዘመናቸው ስድስት ዓመታቱን በሻኪሶ ሆስፒታል ነው ያገለገለገሉት።
ሁለቱን ዓመታት ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሰርተዋል። ቀሪዎቹን 32 ዓመታት በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በመሥራት ነው ሙያዊ አገልግሎታቸውን ያጠናቀቁት። ወደ እናቶች የማዋለድ ሕክምና ሙያ የገቡት በ20 ዓመታቸው ሙያዊ ስልጠና በመውሰድ ነበር። በሙያው ያላቸው የትምህርት ዝግጅት ከታች ከመለስተኛ ጤና ረዳት ይጀምራል። ከመለስተኛ ጤና ረዳት ወደ ጤና ረዳት ለማደግ የሚያስችል ትምህርት ተከታትለውም የትምህርት ደረጃቸውን አሻሽለዋል። የማዋለድ ሙያቸውን ስለሚወዱት በሙያው ከዲፕሎማ አስከ ዲግሪ ለመዝለቅ በቅተዋል።
‹‹ሙያዬ በየጊዜው ባሻሻልኩት ትምህርት መታገዙ የ40 ዓመት አገልግሎቴን ስኬታማ አድርጎልኛል›› የሚሉት ሲስተር እታለማሁ በዚህ ጊዜ ውስጥ ካዋለዷቸው በሺህ የሚቆጠሩ እናቶች መካከል የአንዲትም እናት ሕይወት እንዳልጠፋባቸውም በኩራት ይናገራሉ። በተለይ 32ቱን ዓመታት እንዳገለገሉበት የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ብዙ ስፔሻሊስቶች ስላሉና የተለያዩ የትድግና እርብርቦች ስለሚደረጉ የእናቶች ሞት ብዙም እንዳልነበረ ይገልፃሉ። በሆስፒታሉ ባለሙያ ሲያዋልዳት በዓመት አንድ እናት ከሞተች ሰራተኛው በሙሉ ከቤተሰብ ባልተናነሰ ሁኔታ ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ይወድቅ እንደነበርም ያወሳሉ። ‹‹በዓመት አንድ እናት የምትሞትብን ከአቅም በላይ ስለሚሆንብንና ከአምላክ የመጣን ሞት መከላከል ስለማንችል ነበር›› ሲሉም ያብራራሉ።
‹‹አጅግ ያሳዘነኝ እና አንድ ጊዜ የገጠመኝ ከውርጃ ጋር ተያይዞ ነበር›› የሚሉት ሲስተር እታለማሁ እንዳከሉልን ሟቿ ውርጃውን እቤት ውስጥ ሞክራ ነበር ወደ ሆስፒታሉ የመጣችው። ስትመጣ እጅግ ብዙ ደም ይፈሳት ነበር። ደም ብዙ ወሰደች። ሕይወቷን ከሞት ለመታደግ ብዙ ርብርቦች የታከሉበት ሙከራ ተደረገላት። ስፔሻሊስት ሐኪሞችም ያለ የሌለ አቅማቸውን አሟጠው ጨረሱ። ‹‹ሆኖም ልናተርፋት አልቻልንም።
በዚህች ሀገሯም ቤተሰቧም ብዙ በሚጠብቅባት ወጣት እናት ሞት ምክንያት በጣም ያለቀስኩበትና ያዘንኩበት ጊዜ አጋጥሞኝ አያውቅም። እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች ሠራተኞችም በዚህ የተነሳ በሆስፒታሉ ውለን ምግብ ሳንቀምስ ነው ያደርነው›› ሲሉም ባለሙያው በተገልገጋዩ ጉዳት የሚሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀውልናል።
ሲስተር እታለማሁ በተለይ ከደም መፍሰስ ጋር ተያይዞ የእናቶችን ሕይወት ለመታደግ በሆስፒታሉ ያለውን ተሞክሮ አስመልክተው እንዳከሉልን ሆስፒታሉ በወሊድ ጊዜ በሚገጥማቸው ከፍተኛ የደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ሕይወት ለመታደግ ደም የሚያዘጋጅበት ጊዜ አለ።
እንደ ዕድል ሆኖ ያኔ የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በቅርቡ ወደ ጤና ሚኒስትር ከሄደው ከደም ባንክ ጋር ጎረቤት ነበር። በመሆኑም አንዲት ወላድ እናት ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ከመግባቷ በፊት ወይም በወሊድ ወቅት ደም የሚፈሳት ከሆነ ደም የሚዘጋጅበት ሁኔታ አለ። በፊት በፊት ታዲያ ከዚህ ከደም ባንክ ከመጣ ወይም ሆስፒታሉ ካዘጋጀው ደም ይሰጣትና በኋላ ላይ ቤተሰቦች እንዲተኩ የሚደረግበት አሰራር ነበር።
እንደ ሲስተር እታለማሁ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለይም አሁን ላይ ግን እናቶችን ከሞት ለመታደግ ሲባል ይህ አሰራር ቀርቷል። ለየትኛዋም እናት ደም ቤተሰብ አይጠየቅም። ለእናቶች ደም በነፃ ነው የሚሰጠው። ደም ከደም ባንክ ይመጣል። በዚህ ላይ በበጎ ፈቃድ ተነሳስተው ደም የሚለግሱ የማሕበረሰብ ክፍሎች አሉ። በመሆኑም እንደ ሲስተሯ በየትኛውም የጤና ተቋም እናቶች በአብዛኛው ለሞት የሚዳረጉት በወሊድ ወቅት ከፍተኛ ደም ስለሚፈሳቸውና በፈሰሳቸው ደም ልክ ተተኪ ደም በማጣት በመሆኑ የአሁን እናቶች ዕድለኞች ናቸው።
ሲስተሯ አሁንና ቀድሞ በጤና ተቋማት የነበረውን ሁኔታ እያነፃፀሩ እንዳጫወቱን ‹‹የያኔ የአገልግሎቱ አቅርቦት በዚያው ዘመን ልክ ፍላጎት የተሟላ ነበር። አንቡላንስን ጨምሮ የሕክምና መሳሪያዎች ነበሩ። አብዛኞቹ አስፈላጊ ነገሮች ስለነበሩ እናቶች በቂ አገልግሎት ያገኙ ነበር። ሆኖም በሰው ኃይል በኩል የነበረው እንደ አሁኑ በበቂ ሁኔታ የተሟላ አልነበረም። በሕክምና ሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘቱም አስቸጋሪ ነበር። በአብዛኛው በተለይ በማዋለድ በኩል በልምድ ይሰራ የነበረበት ሁኔታ ጭምር ነበር። በመሆኑም ያኔ የሥራ ጫናው ይወድቅ የነበረው ባለሙያው ላይ ነው። በትንሽ ባለሙያ ብዙ አገልግሎት መስጠት ግድ ይል ነበር። ጥቂት ከማይባሉ ዓመታቶች ጀምሮ ግን እግዚአብሄር ይመስገን መንግስት በዘረጋው አሰራር ባለሙያም ከየትምህርት ተቋሙ እየተማረ እየወጣ ወደ ሕክምና ሙያው መግባት በመጀመሩ በቀደምቱ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ የነበረው ጫና ሊቃለል ችሏል። እናቶችም ባለሙያው ከነበረበት የሥራ ጫና የተነሳ በመጠኑም ቢሆን ከሚዘገይ የጤና አገልግሎት መላቀቅ ችለዋል።››
ሲስተሯ ስለ ነፍስ ጡር ሴት የሚሰማቸውን ስሜት አስመልክተው ‹‹እርጉዝ እናት ሳይ ደስ ይለኛል። ልቤ ርህራሄ ይሰማዋል። ይሄ ስሜት የኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም እንደሆነ አስባለሁ። ምክንያቱም አንድም የሁላችንም አመጣጥ በዚህ መንገድ ነው። ሁለትም ከእግዚአብሄር በታች በፈቃዱ ሕይወትን ምታስቀጥል ብቸኛ መንገድ እንደሆነች እንረዳለን›› ይላሉ።
ለዘጠኝ ረጅም ወራቶች ስትጨነቅ የነበረችበትን ሸክሟን ጨምሮ ከባዱን የምጥ ወቅት ጭንቋን መጋራትና መረዳት እንደሚገባ ይመክራሉ። ትዕግስተኝነትም በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነም ያሰምሩበታል። በሰላም ለመገላገሏ በባለሙያ የሚሰጣት እያንዳንዱ አገልግሎት አስተዋጾ እንዳለውም ያሳስባሉ።
‹‹እኔ እያለሁ አንድም እናት ቤት አትወልድም›› የሚሉት ሲስተር እታለማሁ እናቶች ልጆቻቸውን መውለድ ያለባቸው በጤና ባለሙያዎች በመታገዝ በሆስፒታል ውስጥ መሆን እንደሚገባውም አበክረው ይመክራሉ። ሲስተሯ እንደሚናገሩት በጤና ተቋም መውለዳቸው የእናቶችንም ሆነ የህፃናትን ሞት በመቀነሱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ አለው። ሆኖም በ40 ዓመት የማዋለድ አገልግሎታቸው እንደታዘቡት፣ በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች በአብዛኛው እናቶች ልጆቻቸውን በቤታቸው ውስጥ ነበር የሚወልዱት። ይህ ደግሞ የእናቶች ሞት ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።
በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም እሳቸው ይሰሩበት በነበረው ሻኪሶ ሆስፒታል አካባቢ ያሉ የሻኪሶ ገጠር አካባቢ አንዳንድ እናቶች ምጣቸው ሲመጣ በፍጥነት ወደ ጫካ ሄደው በአስገራሚ ሁኔታ ልጆቻቸውን በጫካ ውስጥ የሚወልዱበት ሁኔታ ጭምር መኖሩን በወሬ ደረጃ ይሰሙ እንደነበርም ይጠቅሳሉ። በእርግጥ ወደ ጤና ተቋም እየመጡ የማዋለድ አገልግሎት ያገኙ የነበሩት እናቶች ከተማ ውስጥ የሚኖሩ እንደነበሩ እርሳቸውም ያስታውሳሉ። ልጆችን በቤት ውስጥ የመውለድ ሁኔታ በተለይ በገጠሩ የሀገሪቱ አካባቢ እንደ ፊቱ አይብዛ እንጂ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አለመቀረፉንም ይናገራሉ። ዛሬም በሀገራችን የገጠሪቱ አካባቢዎች ልጆቻቸውን በቤታቸው ውስጥ የሚወልዱ እናቶች እንዳሉም አበክረው ይገልፃሉ።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር በሕክምና አገልግሎት ዘመናቸው በተለይም ሻኪሶ በነበሩበት ጊዜ ወላድ እናቶች ወደ ጤና ተቋሙ ባይመጡም እሳቸውም ሆኑ ሌሎች ባልደረቦቻቸው እናቶቹ ወዳሉበት ገጠር አካባቢ እየሄዱ ቤት ለቤት ጭምር በመዝለቅ ለገጠር ወላድ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጡ መቆየታቸውንም ይናገራሉ። በዚህም እናቶች ወደ ጤና ተቋም እየመጡ እስከ መውለድ የደረሰ የተወሰነ ለውጥ መታየት መቻሉንም ያስታውሳሉ።
‹‹እኔ እያለሁ አንድም እናት ቤት አትወልድም›› በሚል የግል መርህ የሚመሩት ሲስተር እታለማሁ በሥራ ዘመናቸው ከሚሰሩበት ተቋም አልፈው በሚኖሩበት አካባቢና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እናቶች ልጆቻቸውን በጤና ተቋማት ውስጥ በሰለጠነ ባለሙያ በመታገዝ እንዲወልዱ ግንዛቤ ሲፈጥሩ መቆየታቸውንም አንዳንድ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው ነግረውናል። በተለይ የጤና ረዳት አፀደ ወልዴ እንደነገሩን ሲስተሯ ወላድ እናቶችን ከሞት ለመታደግ ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ መንገድ ላይ የሚያገኟቸውን ነፍሰ ጡሮች ሳይቀር እያስቆሙ ክትትል ማድረግና አለማድረጋቸውን ከመጠየቅ ጀምሮ ልጆቻቸውን በአቅራቢያቸው ባለ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ሳያሰልሱ ምክር ይሰጡ ሁሉ ነበር። ሲስተር እታለማሁ እንዳወጉን እሳቸውም በጾታቸው ሕይወት የማስቀጠል ፀጋ ከፈጣሪ የተሰጣቸው እንስት እንደመሆናቸው ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ልጅ ወልደዋል። ሁለቱን ልጆቻቸውን ቀደም ብለው ይሰሩበት በነበረው ሻኪሶ ሆስፒታል አንዱን ልጃቸውን የወለዱት ደግሞ ለ32 ዓመታት አገልግለው በቅርቡ በጡረታ በተሸኙበት ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ነው።
ሲስተር እንዳወጉን በተለይ ለአዋላጅ ባለሙያ ሴቶች በሚሰሩበት ተቋም መውለድ ትልቅ ዕድል ነው። እንክብካቤው ለሌሎች ተገልጋይ እናቶች ከሚሰጠው አገልግሎት የተለየ ባይሆንም አገልጋይ የነበረችው በተራዋ ስትገለገል ማየቱና ዕድሉን ማግኘቷ በራሱ ከፍተኛ ደስታን ይሰጣል።
እኛም የሲስተር እታለማሁን የ40 ዓመታት ተሞክሮ ስንቋጭ ደስታ ለማግኘት ደስታውን ለዘለቄታው ለማጣጣም የጤና ባለሙያ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ወላድ እናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ አለባቸው እንላለን። በተለይ በቅርቡ እንዲህ እንደ ሲስተር እታለማሁ ለረጅም ጊዜ እናቶችን ሲያገለግሉ የቆዩ የጤና ባለሙያዎች በጡረታ በተሸኙበት መድረክ ተገኝተው በሕክምናው ውስጥ ያለፉት ዶክተር ወዳጄነህ መሀረነ እንዳደረጉት ንግግር እናቶች በወሊድ ጊዜ ከደም መፍሰስ እና ፌስቱላን ጨምሮ ሌሎች ለሞት የሚያበቁ ውስብስብ ችግሮች ይገጥሟቸዋል። እናቶች ብቻ ሳይሆኑ ልጆች ሲወለዱ በሚገጥሙ አደጋዎች ሊታመሙ፣ አካል ጉዳተኛ ሊሆኑ እንዲሁም ሊሞቱና ብዙ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። ከወሊድ ጋር በተያያዘ አያሌ ቁጥር ያላቸው እናቶች ይሞታሉ። ለምሳሌ፦ የጋንዲ ሆስፒታል ባለሙያዎች ከስድስት አሥርት ዓመታት በላይ ለነፍሰ ጡር እናቶች ከእርግዝና ወራት ጀምሮ በወሊድ ወቅት ከፍተኛ ተከታታይነት ያለው የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በሰላም ልጆቻቸውን እንዲገላገሉ ሲያደርጉ የቆዩ ባለውለታዎች ናቸው። ሌሎች ነባርም ሆኑ አዳዲስ የጤና ተቋማት ባለሙያዎቹን አርአያቸው ሊያደርጓቸው ይገባል።
‹‹የማሕፀን ፅንስ በምንማርበት ጊዜ ዶክተሮቹ መምህሮቻችን ታካሚዋ ለክትትል መጥታ ከክትትል በኋላ ከአልጋ ስትወርድ ጫማዋን እንድናቀርብላት ያደርጉን ነበር›› ሲሉ የሕክምና ሙያ ትምህርት ተሞክሯቸውን የሚጠቅሱት ዶክተር ወዳጄነህ የአሁኖቹ የጤና ባለሙያዎች ከድሮዎቹ የጤና ባለሙያዎች ለተገልጋይ እናቶች ክብር መስጠትን ገንዘብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራሉ። እንደ ዶክተር ወዳጄነህ ይህች ነፍሰ ጡር የመጨረሻ ምስኪን ደሃ ብትሆንና የተበጠሰ ነጠላ ጫማ ብታደርግም ክብርና ክብካቤ መስጠት ለባለሙያው ግድ እንደነበር ያስታውሳሉ። እግሯ ላይ እብጠት መኖሩንና አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚደረገውም እጅግ ከፍተኛ አክብሮትና ጥንቃቄ የሞላበት እንደነበርነም ያወሳሉ።
ዶክተሩ እንደሚሉት እንደ እርጉዝ እናት የሚያምር ፍጡር የለም። ምክንያቱም ፍሬ እንደሚያፈራ እንደ ጎመራ ዛፍ ትመሰላለችና ነው። እርጉዝ እናት ከሰማይ በታች እጅግ በጣም የሚከበር ፍጡርን የምትሰጥ ስለሆነች ይህችን እናት የሚያገለግል ባለሙያ ደግሞ እጅግ በጣም ሊወደድና ሊከበር የሚገባ ነው። ውለታው በገንዘብና በቁስ አይለካም ፤ አይገመትም። ቢሆንም ለረጅም ጊዜ አገልግሎቱ ዕውቅና እና ክብር ሊሰጠው፤ ሊበረታታም ይገባል።
ማረሚያ
ሚያዝያ 4 ቀን 2014 አ.ም በዚሁ ገጽ፣ “ሴቶች” አምድ ላይ ባሰፈርነው ጽሑፍ “የባከነው ጊዜ” ደራሲ መጠነወርቅ ሳሙኤል አባታቸው አቶ ሳሙኤል “የፅዳት ሰራተኛ” ተብለው የተገለፁት የ”ሂሳብ ሰራተኛ”፤ መጠነወርቅ ሳሙኤል “በፀሐፊነት የተቀጠሩት የንግድ ሥራ ኮሌጅ” ሳይሆን አሁን “የመንገድ ሥራ ባለስልጣን” ያኔ “የአውራ ጎዳና ባለስልጣን”፤ ዘጠነኛና 10ኛ ክፍል የተማሩትም “ብርሃነ ኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት” ተብሎ እንዲስተካከል በጠየቁት መሰረት፤ ከይቅርታ ጋር በዚሁ መስተካከሉን እንገልፃለን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014