ለአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የቀረበው ኤች አር 6600 የተሰኘ ረቂቅ ‹‹የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ እንዲሁም ዲሞክራሲዋን ለማፅናት የወጣ ሕግ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በቅርቡ ከመፅደቅ እንዲዘገይ ሆኗል የተባለው ይሕ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ግጭቶች እንዲቆሙ ይጠይቃል።
በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውና በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ናቸው የተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲያበቁ ብሎም ጥሰቶች የፈፀሙ ሁሉ ተጠያቂ እንዲደረጉም ይጠይቃል። ሰላማዊት ዲሞክራሲም የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁሉን አካታች ውይይት እንዲደረግ ረቂቅ ሕጉ ይጠይቃል። ይሕ ካልሆነ በአንፃሩ የአሜሪካ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በሕጉ በዝርዝር ተጠቅሷል።
የኤች አር 6600 እና የኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን በሚመለከት ሃሳባቸውን የሚያጋሩ ምሁርንም በአንጻሩ፤ ‹‹ረቂቅ ሕጉ የኢትዮጵያን ህልውናና ነጻነት የሚዳፈር ብቻ ሳይሆን ማዕከላዊው መንግስት እንዲዳከምና ኢትዮጵያ የሊቢያን መንገድ እንድትከተል ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ አደገኛ ነው›› ይሉታል። ረቂቅ ሕጎቹ ተቀባይነት አግኝተው ተፈጻሚ የሚሆኑ ከሆነም ኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ ተጽዕኖን ሊያስከትሉ እንደሚችል እየገለፁ ናቸው።
የኤች አር 6600 ሕግ በረቂቁ ኢትዮጵያን የሚያዳክምና በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋትና ቀውስ እንዲፈጠር የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር በፋይናንሱ ዘርፍ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የብድር፣ ዕርዳታና መሰል ጥቅማ ጥቅሞች ማስቀረትን ያለመ መሆኑ ያመላክታሉ።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደኅንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆም እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና የገንዘብ ምንጮች (አይ ኤም ኤፍና የዓለም ባንክን ጨምሮ) ገንዘብ እንዳታገኝ እስከ ማድረግ የሚደርስ ዕርምጃም ተካቶበታል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽኖች ጋር ያላትን ግንኙነት በማገድ ኢንቨስትመንቶችንና የገንዘብ ልውውጦችን የማስቆም አቅም አለው። ረቂቅ ሕጉ መሰረታዊ መብቶችንም ያግዳል።
‹‹ይህ ሕግ ከጸደቀ የአገሪቱ ኢኮኖሚን በከፍተኛ መልኩ በማድቀቅ በእያንዳንዱ ዜጋ ኑሮ ላይ ከባድ ጫና በማድረስ እጅግ አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ነው›› ይላሉ። ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የውጪ የፋይናንስ ድጋፎችን እንደምትቀበል የሚገልጹት የምጣኔ ሃብት ምሁራንም፤ በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ ግንባታ ዙሪያ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማስቀጠል ብድር ያስፈልጋል። ይህ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ መሠረተ ልማት ግንባታዋን እንዳታስቀጥል እክል የሚፈጥር ከሆነ ተጎጂው መንግሥት ሳይሆን ተራው ዜጋ ነው›› ይላሉ።
በአሁን ወቅትም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ የአሸባሪው ቡድን ትሕነግ ደጋፊዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቀመሩት ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሕጎች እንዲጸድቁና የሚፈልጉት እንዲሆን ተግተው እየሰሩ ናቸው።
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የኢትዮጵያ ወዳጆችም በሌላ በኩል ፊርማዎችን በማሰባሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ ሕጉን የሚደግፉ የኮንግረሱን አባላት በማነጋገርና ተቃውሞዎችን በማሰማት ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ተጠምደዋል። በተለያዩ ከተሞች ታላላቅ የተቃውሞ ሰልፎችን በማካሄድ ረቂቅ ሕጉ ለአሜሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም መሆኑንም በህብረት አስተጋብተዋል።
በአሁን ወቅት ረቂቅ ሕጎቹ ከነበሩበት የ8ተኛ ደረጃ አጀንዳነት ወደ 335ተኛ ወርደዋል። እንዲዘገዩ መደረጉም በኢትዮጵያ በኩል ደስታን ፈጥሯል። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴ፣ ረቂቅ ሕጎቹ ለጊዜው ባሉበት እንዲቆዩ የሚል ሃሳብ መንፀባረቁ የኢትዮጵያውያን ብርቱ ርብርብ ውጤት ስለመሆኑ ይመሰክራሉ። ይሑንና ባሉበት እንዲቆዩ ተደርገዋል ማለት ፋይላቸው ተዘግቷል ማለት እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ እንዳለ ሁሉ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ ምሁራንም ‹‹ረቂቅ ሕጎቹ ባሉበት እንዲቆዩ መደረጉ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ስኬት ነው። ይሑንና ረቂቅ ሕጉ እንዲቆይ መደረጉ በራሱ ሙሉ ድል አይደለም። እንዲቆይ መደረጉም ብቻውን ጥቅም የለውም።›› ይላሉ።
‹‹አንድ መታወቅ ያለበት አብይ ጉዳይ ቢኖርም ረቂቅ ሕጎቹ ተራዘሙ ማለት ተሰረዙ ማለት አይደለም፤ ረቂቅ ሕጎቹ የተጠመዱና ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲፈነዱ የተደረጉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፣ ደጋግሞ መቃወም የግድ ነው። መዘናጋት ፈፅሞ ሊታሰብ አይገባም›› ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። አንዳንዶች በአንፃሩ ረቂቅ ሕጎቹ እስካልተሰረዙ ድረሰ ጠረጴዛችን ስር ናቸው እንዲህ ካላደረጋችሁ እንዲህ እናደርጋለን በሚል ማስፈራሪያ እጅ ለመጠምዘዝ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ እንደሆኑም ያስገነዝባሉ።
ሕጎቹን በሚመለከት አንዳንዶች፣ ሕጎቹ ኢትዮጵያ ላይ ሳይሆን የጊዜው መንግሥት ላይ ጫና ማሳደርን አላማ ያደረጉ ናቸው በሚል ሙጉት ሲገጥሙ ይስተዋላል። ይሕን እሳቤ የሚደግፉት እንዳሉ ሁሉ በርካቶች ይቃወሙታል። አንዳንዶች በአንፃሩ እሳቤው ፍፁም ስህተት መሆኑን በማስረገጥ አምርረው ይቃወሙታል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ዳይሬከተር አቶ ወንድወሰን ግርማ፣ አንድ መጽሐፋ በሽፋኑ ወይንም በርእሱ ሳይሆን በይዘቱና ውስጡ ባለው ትሩፋት እንደሚመዘን ሁሉ፣ ይህን ሕግ ጠንቅቆ ለመረዳት ውጪውን ሳይሆን ውስጡን መፈተሸ የግድ ስለመሆኑ አጽእኖት ይሰጡታል።
‹‹እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በውጭ ሽፋናቸው ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና መረጋጋት የሚያስቡ ይምሰሉ እንጂ ውስጣቸው ሲገለጥና ይዘታቸው ሲፈተሽ በጣም አደገኛ፣ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑና አገሪቱን በእጅጉ የሚያዳክሙ ብሎም የሚጎዱ ናቸው››ይላል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴ፣ ረቂቅ ሕጉ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት፣ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ›› በሚል ሽፋን በዜጎች ብርቱ ትግል የወደቀውን የሽብር ቡድን እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ አገሪቱን የመከፋፈል አጀንዳ የያዘ ነው›› ይላሉ።
የረቂቅ ሕግ መነሻ አይን ያወጣ የቅኝ ልግዛህ ወይንም የኒዎኮሎኒያሊዝም አስተሳሰብ በመሆኑ አዋጁን የሚያዘጋጀው ቡድን በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንድነት እንዳይኖና ሕዝቦቿን የመከፋፈል አጀንዳ የነገበ ስለመሆኑን ይጠቁማሉ።
‹‹እነዚህ ሕጎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሆን ተብለው የተቀመሩ ሴራዎች መሆናቸውን የሚያስገነዝቡ ምሁራን፤ ሕጎቹ እንዲፀድቁ እድል መስጠት የሚጎዳው ፖለቲካውን፣ መንግሥትን ወይም ባለስልጣንን ሳይሆን አገርና ሕዝብን ነው››ይላሉ።
መንግሥትና በአመራር ላይ የሚገኝ ግለሰብን አዳክማለሁ በሚል አገርን ለጥፋት የመዳረግ ግዙፍ ስህተት መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግም አፅእኖት ይሰጡታል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የአሜሪካ ማዕቀብ የሚጎዳው በድህነትና በግጭት የቆየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ስለመሆኑ ያሰምሩበታል።
መንግሥታት በየጊዜው ቢቀያየሩም አገር ግን እንደማትቀየር እና በውጭ ጣልቃ ገብነትና ሴራ ደካማ መንግሥት ተፈጥሮ ጠንካራ አገር እንደማይኖር ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝቡት ምሁራኑ፤ የሕጎቹ መሰረዝ ሕዝብና አገር ላይ ከሚያስከትለው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንፃር የሕጉቹ እንዲዘገዩ መደረግ ሳይሆን መሰረዝ የግድ መሆኑን ያሰምሩበታል።
አንዳንዶች በአንጻሩ ለሕጎቹ መሰረዝ መንግሥትም የራሱን የቤት ሥራ መወጣት እንዳለበት አጽእኖት ይሰጡታል። በተለይ ሰብአዊ መብትን በማክበር እና በማስከበር ረገድ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። የሕግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን ሃይሌ ይሕን እሳቤ ከሚጋሩት መካከል አንዱ ናቸው።
ኢትዮጵያ በረቂቅ ሕጉ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የተፈራረመች አገር መሆኗን የሚጠቁሙት አቶ ካሳሁን፤ ‹‹ይሕ እንደመሆኑም ሕጎች ተጥሰው ከተገኙ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ወስዶ ማሳየት ይገባል›› ይላሉ፡›፡
ይሑንና ረቂቅ ሕጎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ እንሰራለን ከሚሉ ታላላቅ ተቋማት በኩል ሳይሆን በአሜሪካ መርቀቁ በራሱ ፍላጎቱ ሌላ ስለመሆኑ በቂ ፍንጭ የሚሰጥ ነው ሲሉ የሚተቹት በርካቶች ናቸው።
ምንም እንኳን ስቴት ሪፖርቲንግ (state reporting) የሚባል አቤቱታ አቀራረብ ቢኖርም የአሜሪካ አቤቱታ ግን ከመስፈርቱ ጀምሮ ሚዛናዊና እውነትን መሰረት ያደረገ እንዳልሆነም የሚያስረዱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በተለይም በአሸባሪው የህወሐት ቡድን በኩል የከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ እየታወቀ አሜሪካ ያረቀቀችው ረቂቅ ሕግ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገና የሕግ ተጠያቂነት ለማስፈፀም የሚታትር መሆኑም ከጀርባ ስላለው ፍላጎት ግልፅ ጥቆማን የሚሰጥ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የረቂቅ ሕጉ ይዘት ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚጎዳና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላገናዘበና አገሪቱ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ ከግንዛቤ ያላስገባ›› ሲሉ ይተቹታል። ረቂቅ ሕጉ በይዘት ደረጃ ሲታይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ቀድሞውኑ በኢትዮጵያ መንግሥት የተመለሱ ስለመሆናቸውንም ያስገነዝባሉ።
ሰነዱ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት እንዲኖርና አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት፣ እዚህ ሶስቱም እንኳር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ችግር እንደሌለበትና ጥያቄዎቹም እንደተመለሱም ይጠቁማሉ። ይህ እስከሆነም፣ ‹‹ጉዳዩ አሜሪካ እንደምትለው ስለ ሰብአዊ መብት አያያዝና አከባባር የሚጨነቅ ሳይሆን ፖለቲካዊ ፍላጎትን የተሸከመ ነው››ይላሉ።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሚያጋሩ ምሁራን፣ረቂቅ ሕጎቹ ለጊዜው ከመፅደቅ እንዲዘገዩ ተደርጓል ቢባልም ሰበብ ፈልጋ አሜሪካ አንድ ቀን እንደገና እንዳትመዘውና ሕግ አድርጋ እንዳታፀድቀው መደረግ ስላለበትም የሚሉት አላቸው። በተለይ በአሁን ወቅት የዳያስፖራው ማሕበረሰብ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር መንግሥት ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለበት ይታመናል።
ከሕጎቹ አደገኛነታቸው አንፃር እንዳይፀድቁ ለማድረግ ምን ይደረግ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ የረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚጎዱ በመሆናቸው ተቀባይነት እንዳያገኙ ከዚህም በላይ መቃወም እንደሚያስፈልግ አፅእኖት ሰጥተውታል። ይሕን የማድረግ ጊዜው ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆን አለበት የሚለውም የጋራ ሃሳባቸው ሆኗል።
ሕጎቹ ‹‹ኢትዮጵያን ለማድቀቅ የተቀመሩ በመሆናቸው አምርረን እንድንቃወም ያደርጉናል። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ አደገኛ ጥቃት ካላሰባሰበን፣ ሌላ ምንም ሊያሰባስበን አይችልም›› የሚሉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ተቃውሟቸውን እንዲያጠናክሩ ነው አፅእኖት የሰጡት።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል አገሪቱ ገጥሟት የነበረውን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም ዳያስፖራው ያስመለከተው ተጋድሎ፤ እነዚህ ረቂቅ ሕጎችም እንዳይፀድቁ ከምንጊዜውም በላይ በተቀናጀ በአንድነት ዘመቻ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስምረውበታል።
ምሁራን ረቂቅ ሕጉ እንዳይፀድቅ የማድረጊያው መንገድ በየት በኩል ነው የሚለውን ጥያቄም ሲመልሱ፤ እውነታውን ለማስገንዘብና ለማሳመን ጉዳዩ አሁን ባለበት የተቃውሞ ግለት ይበልጥ መቀጣጠል እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥና ማሻሻያዎች እንዲሁም እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ ማስገንዝበን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በማካሄድ ረቂቅ ሕጎቹ እንዲሰረዙ በማድረግ ረገድ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ብልሃት የተሞላበት ዲፕሎማሲ መከተል እንዳለበት ያስገነዘቡት ምሁራኑ፤ ‹‹የምንፈለገው የእድገት ደረጃ እስክንደርስ ዓለም አቀፍ ግንኙነታችንና የዲፕሎማሲ ሥራችንን በእልህ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በእውቀት ላይ የተመረኮዘ መሆን መቻል አለበትም።›› ነው ያሉት። በተለይም የሁለቱን አገራት ከመቶ አመት በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት በሚያውክ መልኩ መሆን እንደሌለበትም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
የሕግ ባለሙያው አቶ ካሳሁን በበኩላቸው፤ መንግሥትም ቢሆን እውነታነት አላቸው የሚባሉ ጥሰቶች ከተገኙም ፈጣን የእርምት መውሰድና ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት ካሉም እርምጃን መውሰድ እንዳለበት ነው ያሰመሩበት።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው ፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ ረቂቅ ሕጉ ላይ ትግሉንና ተቃውሞውን መቀጠል እንዳለበትና ይህን ረቂቅ ሕግ የሚያዘጋጅ አካል ከኢትዮጵያውያን ላይ እጁን እንዲያነሳ አበክሮ መታገል እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።
መንግሥት በዲፕሎማቶቹ በኩል ለመላው አፍሪካውያንና ወዳጅ አገራት አሜሪካ አፍሪካን በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት የምታደርገውን እንቅስቃሴና የዚህን ረቂቅ ሕግ አደገኝነት ግልፅ በማድረግ ትግል ማድረግ እንደሚገባ ነው ያመላከቱት። አይሆንምን ትቶ ይሆናልን እያሰቡ ቅድመ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግም ነው ያሰመሩበት።
መገናኛ ብዙሃንም በዚህ ረቂቅ ሕጉ ዙሪያ ለማሕበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ከመስጠትም በላይ ይህ ሕግ እስከ መጨረሻው ድረስ ተቀባይነት እንዳይኖረውና ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም። ሕጎቹ እንዲዘገዩ ሳይሆን እንዲቀሩ ማድረግ የግድ ነው የሚለውም የአስተያየት ሰጪዎች የጋራ እሳቤ ሆኗል። የፌደራል መንግሥትም በአገርም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ የኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ሕጎቹ እንዲሰረዙ የጀመሩትን ጥረት እንዲያስቀጥሉ ሲል ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 /2014