በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ግሽበት ይታያል፡፡ ሰሞኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አሰራር የቃልኪዳን ሰነድ የተፈራረሙ ፓርቲዎች ቁጥር 107 መድረሱን ስንመለከት እውን ይህ ሁሉ ፓርቲ በትክክል ለህዝብ ለመስራት የተፈጠረ ነው የሚል ጥያቄን ማጫሩ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል የፓርቲ ንግድ ተጀመረ የሚል ጥያቄንም ያጭራል፡፡ ይህ ካልሆነ ስንት አይነት አስተሳሰብ ኖሮ ነው እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች ልዩነትን የሚያራምዱት? ወይስ ፓርቲ ለመመስረት ልዩነት የግድ አይደለም? የሚል ሙግት ያስነሳል፡፡
በርግጥ በኛ አገር አብዛኞቹ ፓርቲዎች ብሄራዊ ማንነት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ብሄር እንኳን ፓርቲ ቢኖረው አገራችን ከ80 በላይ ብሄር ስለሌላት እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎችን መመስረት አያስፈልግም፡፡ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ እንመስርት ቢባል ደግሞ ይህንን ያህል የተዘበራረቀ ሃሳብ መፍጠር አይቻልም፡፡ ታዲያ ፓርቲዎቻችን ከየት መጡ? እውን ፓርቲዎቻችን የተመሰረቱት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መሰረት አድርገው ነው? በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ልዩነት ያራምዳሉ ወይ ብሎ ለሚጠይቅም በቂ መልስ ላያገኝ ይችላል፡፡
ምክንያቱም በዓለም ላይ ያለው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ከአራት ግፋ ቢል ደግሞ ከአምስት የዘለለ አይደለም፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች የዜጎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች የመመለስ ብቃት እንዳላቸውም ሳይንስ ያረጋግጣል፡፡ ታዲያ ይህ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ግሽበት እንዴት ተከሰተ ብለን ስንጠይቅ ፓርቲ ስንመሰርት በእውቀት ላይ ሳይሆን በስሜት ላይ ተመስርተን እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሁለት ወራት በፊት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት በአገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ ፓርቲዎች ውህደት ፈጥረው ቢጠናከሩ የተሻለ እንደሚሆን መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት ጠንካራ ፓርቲ ተፈጥሮ በውድድሩ ለህዝብ የተሻለ አማራጭ ያለው ፓርቲ ይፈጠር የሚል ትርጉም ያለው በመሆኑ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው ሃሳብ ነው፡፡ ፓርቲዎችም በዚህ ደረጃ ተጠናክሮ ለመውጣት አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ነገር ግን አሁን የሚታየው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የተበጣጠሱና የተበታተነ ሃሳብ ይዘው የተሰለፉ በርካታ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ለህዝብ የሚጠቅም አማራጭ ሃሳብ የያዘ የፖለቲካ ፓርቲን ለመለየት አዳጋች ያደርገዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሃብት አላግባብ እንዲባክንና ለአገር የሚጠቅሙ ፓርቲዎች ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡
በሌላ በኩል ለስም ብቻ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ፓርቲዎች ለአገራዊ እድገትና በጅግጅጋ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፤ ይህ ትንሽ ቆይቶ በጎንደርም ተደግሟል። በአጠቃላይ በነዚህ ወቅታዊ ግጭቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩትም ህይወታቸውን አጥተዋል። በርካታ ማህበራዊ ቀውሶችም ተፈጥረዋል። ከሰሞኑ አዲስ የተቀረጸልን አጀንዳ ደግሞ “አዲስ አበባ የማን ናት?” የሚል ነው።
ይህ ጥያቄ አከራካሪ አይመስለኝም። አዲስ አበባ የማን ናት የሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያ የማን ናት፣ መቀሌ የማን ናት፣ ባርዳር የማን ናት፣ አዳማ የማን ናት፣ ሃዋሳ የማን ናት፣ ወዘተ ከሚለው ጥያቄ የተለየ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሁሉም የኛው የኢትዮጵያውያን ናቸውና። ለመሆኑ በህገመንግስቱም ቢሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሁሉም አካባቢ ተዘዋውሮ የመስራትም ሆነ ሃብት የማፍራት መብቱ የተጠበቀ አይደለምን? አንድ አማራ በኦሮሚያ ክልል፣ አንድ ትግራይ በአማራ ክልል፣ ወላይታው በትግራይ ክልል፣ ወዘተ የመኖር መብትስ የለውም? በኔ እምነትም ሆነ በህገ መንግስቱ መሰረት እነዚህ መብቶች የተከበሩ ናቸው።
ታዲያ ጥያቄው ከምን የመነጨ ነው? ከተማዋን ለማስተዳደር ነው? ከማስተዳደር በስተጀርባስ ምን አለ? እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ አለ። አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል ውስጥ የምትገኝ የአገሪቱ ዋና ከተማ ናት። በሁሉም አቅጣጫ ወጣ ቢባል የምናገኘው ኦሮሚያን ነው። በየእለቱም በርካታ የኦሮሚያ ነዋሪዎች አዲስ አበባ ውለው ይመለሳሉ። በተቃራኒውም ኦሮሚያ ውሎ የሚገባው የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህ ደግሞ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስር ያሳያል።
ይህ ደግሞ የቋንቋ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። በአዲስ አበባ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ምክንያት ሊሆን ይችላል። ጥያቄው ከዚህ አንጻር ከታየ ደግሞ መልስ ማግኘት ያለበት የመብት ጥያቄ በመሆኑ ጤናማ ነው። ለመሆኑ አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዳይሆን ምን የሚያግደው ነገር ይኖራል? በዓለም ላይ ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋ ያላቸው አገራት ቁጥር ቀላል አይደለምና ምኑ ላይ ነው የከበደን።
በሌላ በኩል ጥያቄ የምናቀርበውም ቢሆን የእኔነትን የምንገልፅበት መንገድ መስተካከል ያለበት ይመስለኛል። በዓለም ላይ 57 አገራት ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋ እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ያሳያሉ። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ከዚህ አንጻር ትልቅ ምሳሌ መሆን ትችላለች። ምክንያቱም በደቡብ አፍሪካ 11 የሚሆኑ ቋንቋዎች በመንግስት ተቋማት አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ በተጨማሪ 41 አገራት ሁለት ቋንቋ፣ 12 አገራት ሶስት ቋንቋ እንዲሁም 3 አገራት አራት ቋንቋዎችን በስራ ቋንቋነት ይጠቀማሉ።
በጎረቤት አገራት ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ ጅቡቲ፣ኤርትራ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ሁለት ሁለት ቋንቋዎችን በይፋ በስራ ቋንቋነት እንደሚጠቁሙ መረጃዎቹ ያሳያሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን እኮ የውጭ አገር ቋንቋ እየተማርን እንገኛለን። በርካታ የባለስልጣንና የባለሃብት ልጆች እኮ ከአማርኛ ቋንቋ ይልቅ እንግሊዚኛ ቋንቋ ይቀላቸዋል። ይህ ለምን ሆነ ስንል ለእንግሊዝኛውና ለአማርኛው የምንሰጠው ቦታ መለያየት ነው። በሁሉም አካባቢ ያለው ቦታ የኢትዮጵያ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ቦታን ለአንድ ማህበረሰብ ብቻ መስጠት የፖለቲካ ቁማር ካልሆነ በስተቀር ትርጉሙ አይገባኝም።
ሌላው የሰሞኑ የውዝግብ ምንጭ ደግሞ በቅርቡ የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ እንደነበር እናስታውሳለን። በርግጥ የዚህ ችግር ዋነኛ ተጠያቂዎች ቀደም ሲል የነበሩ አመራሮች መሆናቸውን መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም ፕሮግራሙ በራሱ ከተመሰረተበት ዓላማ ውጪ የተካሄደ ነውና። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መልሶ ማልማት በሚል የጀመረው ፕሮግራም አላማ አንድም የከተማዋን ገጽታ ሊለውጥ የሚችል ግንባታ ማካሄድ ሲሆን በሌላ በኩል ለነዋሪዎቹ ምቹ የመኖሪያ ስፍራን መፍጠር ነበር። በዚህም መሰረት አዲስ አበባ ወደላይ እንጂ ወደጎን ማደግ የለባትም በሚል ተደጋጋሚ ስብከቶችን ከባለስልጣት ስንሰማ ኖረናል።
ነገር ግን ከዚህ በዘለለ መልኩ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች እያፈናቀለ ከከተማ ውጪ በሚገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት ሲሰጥ ቆይቷል። ይህ ደግሞ አብዛኛው ነዋሪ ሲያማርር የቆየ ነው። በርግጥ በመኖሪያ ቤት እጥረት እና በቤት ኪራይ የተማረረ ዜጋ በዚህ መልኩ ከከተማ ውጭም ቢሆን ሂድ ሲባል አልፈልግም የማለት ድፍረትም ሆነ መብት አልነበረውም። ይህ ማለት ግን ቀደም ሲል በዚህ መልኩ ከከተማ ውጪ ወደሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገባ የነበረው በፍላጎቱ ነበር ለማለት አያስደፍርም። አብዛኞቹ ወጣቶች በዚያ መልኩ ከከተማ ውጪ በተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች ከመግባት ይልቅ ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው በነበሩበት አካባቢ ቀርተዋል። አንዳንዱቹም የጎዳና ኑሮን መርጠዋል።
ነገር ግን አዲስ አበባ በአንድ በኩል በግብታዊነት በፈረሱ ሰፈሮች የባሰ የቆሸሸችበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። በሌላ በኩል ደግሞ በልማት ስም በርካታ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበትና ከተወለዱበት ስፍራ ተፈናቅለው ከከተማ ውጪ እንዲወጡ ተደርጓል። ነገር ግን የፈረሱ ሰፈሮችን ማልማት ሲቻል ለምን በዚህ መልኩ ከከተማ ወጥቶ ቤት መገንባት አስፈለገ የሚለው ጥያቄ ለአመታት ሳይመለስ የቆየ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶቹ በተለይ በቅርቡ የተላለፉት የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከአስተዳደሩ ውጪ በሚገኝ የኦሮሚያ ክልል አካባቢ የተገነቡ ናቸው መባሉ አጠቃላይ የቤት ልማት ፕሮግራሙ ዓላማውን መሳቱን አመላካች ነው? በከተማዋ መልሶ መልማትን የሚፈልጉ በርካታ መንደሮች የቆሻሻ ክምር ሆነው እያለ ከከተማ ውጪ አርሶ አደሩን እያፈናቀሉ በዚያ ሁኔታ ሰፊ ግንባታ ማካሄድ ለሁሉም ያልጠቀመ ኪሳራ ነው።
ሰፊ ቦታን የሚሸፍኑትና ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉት የወንዝ ዳርቻዎቻችንም ቢለሙ ምን ያልህ የከተማዋን ውበት እንደሚጨምሩ መገመት አያዳግትም። በየመንደሩ በልማት ስም ፈርሰው መልሰው ያልተገነቡትና የሌባ መናኸሪያ የሆኑት መንደሮችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ታጥረው ለበርካታ አመታት የልማት ያለህ እያሉ የከረሙት ሰፈሮችና ቦታዎችም እንኳስ ለቤት አጥ ለሌላም የሚተርፉ ናቸው። ታዲያ ይህንን ትቶ ሌላ መሻት ምን ይሉታል። ጉዳዩ በእጁ ላይ ዳቦ ይዞ ሌላ ዳቦ ፍለጋ እንደሚሮጥ ህጻን አልጠግብ ባይነት ይመስለኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ በዚያ አይነት ሁኔታ በርካታ ገንዘብና ጉልበት ፈሶባቸው የተገነቡ ቤቶች በቅርቡ ለቤት ፈላጊዎች ሲተላለፉ ይህ የኔ ቦታ ነውና በዚህ መልኩ መሰራቱ ትክክል አይደለም ብሎ ወደ ሙግት መግባቱም በራሱ ሌላ ችግር ነው። እጣው የደረሳቸው አካላት መንግስትን አምነው ለአመታት ከኑሯቸው ላይ ቀንሰው ሲቆጥቡ የነበሩ ዜጎች ናቸው። መንግስት ደግሞ ቆጥቡ እያለ ሲያበረታታ እንደነበር የሚታወቅ ነው።በሁለቱ ወገን ያለ መንግስት ደግሞ አንድ ነው።ከአንድ ፓርቲ የወጣ ነው።
የኢህአዴግ አመራር ነው።ታዲያ ከዛሬ ነገ ቤት ይደርሰኛል እያሉ በተስፋ የኖሩ ዜጎችን ጭላንጭል ተስፋ ካሳዩ በኋላ መልሶ ተስፋ ማሳጣት ምን ይባላል? እነዚህ ዜጎችስ ኢትዮጵያውያን አይደሉምን? እነዚህ ዜጎች በየትም የአገሪቷ ክፍል ሃብት የማፍራትም ሆነ የመኖር መብትስ የላቸውምን? በኔ እምነት የኮዬ ፈጬ ጉዳይ በዚህ መልኩ መነሳቱ የተሰራብን የጥፋት አጀንዳ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ያመላክተኛል። በአንድ አገር ውስጥ እየኖርን ቦታና ወሰን እየለካን በዚህ መልኩ መነታረካችን የምን ውጤት እንደሆነም መገመት አያዳግትም። አዲስ አበባም ሆነ ኦሮሚያ የኢትዮጵያ አካላት ናቸው።
በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖር ቤተሰብ የሌለው የአዲስ አበባ ነዋሪ አለ ማለት ይከብዳል። ባይኖርም ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ ነው ማለት ነውር አይደለም። ከኦሮሚያ አዲስ አበባ ለመኖር የማይመጣ አለ? ታዲያ አዲስ አበባ የጋራችን አይደለችም? የአዲስ አበባ መጎዳትስ የሁላችንም መጎዳት አይደለምን? አዲስ አበባ እኮ ዘር የላትም፤ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ የሌላውም ዓለም ህዝብ የሚኖርባት የጋራ ከተማ ናት። ታዲያ በዚህ መልኩ የጋራችን የሆነን ቦታ እንዴት ነው ይህ አይገባችሁም እያልን ልዩነት የምንፈጥረው። ለኔ አልገባኝም።
ይህ ማለት ግን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ይፈናቀሉ፣ እነሱ ተባረው ሌላው በአካባቢው ላይ ይኑር የሚል አመለካከት ይዤ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ። አሁን ባለው ሁኔታ እውነት እንኳንስ የክልል ወሰንን ቀርቶ በኢትዮጵያና በጎረቤት አገራትስ መካከል በትክክል የሚታወቅ ወሰን ወይም ድንበር የታለ? ድንበሮቻችን በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት “አርተፊሻል ድንበሮች” ናቸው። በክልሎች መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰንም ተመሳሳይ ነው። በጥቂቱ ወደ ኋላ መለስ ብለን በደርግ ዘመን የነበረውን የአገራችንን አስተዳደራዊ ወሰን ስንመለከት የአገራችን የክልል አወቃቀር በክፍለሃገር እንደነበር ይታወቃል።
ይህ በሆነበት ሁኔታ አሁን በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ያለው ብሄራዊ ማንነትን መሰረት ያደረገው አደረጃጀት ነው። ነገር ግን ይህ ለአስተዳደር እና ለህዝቡ ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ ካልሆነ በስተቀር የባለቤትነት ጥያቄን ለማረጋገጥ አልነበረም። በዚህ ሁኔታ ይህ አካባቢ የኔ ነው። ያንተ አይደለም በሚል አተካራ ለመግጠም የሚያስችል ምን አይነት መነሻ ይኖረናል። በርግጥ የፌዴራል ስርዓቱን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጠቃሚ መሆኑ እውን ነው። ምክንያቱም ዜጎች ማንነታቸውን አውቀው፣ በማንነታቸው ኮርተው ራሳቸውን ሲያከብሩ አገራቸውን ሊያከብሩ ይችላሉ።
ይህ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህርይ ነው። ሰው በቅድሚያ ራሱን መውደዱ፣ ከዚያም ቤተሰቡን፣ ቀጥሎም አካባቢውን እያለ አገር መውደድ ይከተላል። ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን የማይወድ ሰው አገሩን ሊወድ አይችልምና። ፌዴራሊዝም ተመሳሳይ ገጽታ ያለው ይመስለኛል። ነገር ግን ፌዴራሊዝምን የተረዳንበትም ሆነ ተግባራዊ የምናደርግበት አካሄድ በተሳሳተ አቅጣጫ ከተመራ የሚያስከትለው ቀውስ ከባድ ነው። ሰሞኑን የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያ መጥተው የላሊበላን ቅርስ ለማደስ ቃል ሲገቡ ስናይ የምንገኝበት ደረጃ ላይ ጥያቄ የምናነሳበት እንደሚሆን እገምታለሁ።
አያቶቻችን የሰሩትን ግንብ ለማደስ እንኳ የማንችልበት ደረጃ ላይ የደረስነው ለምንድነው ብለን እንድናስብም ያስገድደናል። ከጥንቱ ስልጣኔ ልቀን መሄድ እንኳ ቢያቅተን የያዝነውን አስጠብቀን መቆየት ለምን ተሳነን ማለትን ይጠይቃል። አሁን የምንራኮተው በተሳሳተ አጀንዳ ውስጥ መሆኑን ግልፅ አድርጎም ያሳየናል። ዛሬ ከኛ የሚጠበቀው እንዴት ተባብረን እንደግ መሆን ሲገባው ለመነጣጠልና ለመናቆር፣ ያለችውንም ለማጥፋት ከሆነ ቀጣዩ ትውልድ የመኖር ህልውናው አደጋ ውስጥ ይወድቃልና ሁላችንም እናስብበት። ለህዝቦች እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉና ትክክለኛ የህዝብ ጥያቄን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችንም ሞራልና ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ድጋፍ ያላቸውና ለህዝባቸው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ለአመታት የታገሉ ፓርቲዎች በየመንደሩ በጥቂት ደጋፊዎችና ቡድኖች ተፈጥረውና የጠራ አላማ ሳይኖራቸው እንታገላለን ከሚሉ የስም ፓርቲዎች ጋር እኩል በአንድ መድረክ መሰለፋቸውም የሞራል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፓርቲን የገንዘብ ማግኛና መተዳደሪያ ያደረጉ አካላት መኖራቸው የፓርቲዎች ህልውና ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ ያሳርፋል፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ለህዝብ ታግለው ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ከመንግስትና ከጥቂት ደጋፊዎቻቸው በሚሰፈርላቸው ቀለብ ህልውናቸውን ለማቆየት ይጥራሉ፡፡
ይህ ደግሞ ለህዝብ ተገቢውን አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ አድርባይ እንዲሆኑና ለመንግስትና ድጎማ ለሚያደርግላቸው አካል ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ሰላምና ብልፅግናን ነው፡፡ ህዝባችን ለዘመናት ወደኋላ ያስቀረውና በአለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር መዘባበቻ ያደረገው ድህነትና ኋላቀርነት ተወግዶ እንደበለፀጉት አገራት የተሻለ ኑሮ መኖርን ይመኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ ሰላምን የሚያረጋግጥለት፣ በእኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያስተዳድረው፤ ለዚህም የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ የሚሰራለት መሪን ይፈልጋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት፣ ሁሉንም ያማከለ ፍትሃዊ አስተዳደር እና ከአድልዎ የፀዳ አስተዳደራዊ መንግስት እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ልማቱን ለማረጋገጥ ጠንክሮ ለመስራትም ሆነ ሰላሙን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አይልም፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታም በቅርቡ ለመጣው ለውጥ የህዝቡ አስተዋፅኦ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ መሪዎቻቸው ደጋግመው ሊያስቡና ከፓርቲ ህልውና ይልቅ የሃገር ህልውናና እድገት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ መረዳት አለባቸው፡፡ ከሚመሩት ፓርቲ ይልቅ የአገር ህልውና እንደሚበልጥም ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
አሁን እንደሚታየው አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች የፓርቲ ቁጥር ሲያንስ ወይም ጥምረት ሲፈጠር የመሪነት ሚናዬን አጣለሁ ከሚል መንፈስ ወጥተው መሪም ሳይሆኑ ለአገራቸው ጠቃሚ ስራ መስራት እንደሚችሉ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፓርቲዎቻችን ከልዩነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ለጋራ እድገትና ብልፅግና መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሲሆን ህዝቡም የሚበጀውን ለመለየት አይቸገርም፤ የአገር ሃብትም አይባክንም፤ የምንፈልገው እድገትም ይከተላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011