የእጅ ቦርሳ ሴት ልጅ ሊኖሯት ይገባል ተብለው ከሚታሰቡ ቁሳቁስ መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሴት ልጅ በምትንቀሳቀስበት ጊዜ ከእጇ ልታጣቸው የማይገቡ አንዳንድ መሠረታዊ ግብአቶች በመኖራቸው እና እነዚያን ነገሮች በአንድ ላይ ለመያዝ ቦርሳው አስፈላጊ ስለሆነ ነው።
ከዚህም ያለፈ ፋይዳ አለው። የእጅ ቦርሳ ለሴት ልጅ ውበት መጉላት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ የፋሽን ቁሳቁስ መካከልም አንዱ ነው። ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ሴቶች ቦርሳ ለመያዝ የሚያበቃ ምክንያት ባይኖራቸውም እንኳ እንዲሁ ባዶ ቦርሳውን አንጠልጥለው ይወጣሉ የሚባሉት። የሆነ ሆኖ የእጅ ቦርሳ ለሴት ልጅ አስፈላጊ ነው።
ይህን ሀቅ ከያዝን በኋላ በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ ያለው የእጅ ቦርሳ ገበያ ምን ላይ ነው እኛስ እንደ አገር ምን ልንጠቀም እንችላለን የሚለውን መቃኘት የዛሬው ርእሳችን ይሆናል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የእጅ ቦርሳ ገበያ በቢሊየኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በአመት የሚንቀሳቀስበት ገበያ ነው። ፎርቹን ቢዝነስ ኢንሳይድ የተባለ ድረ ገጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ባሰፈረው መረጃ መሠረት የእጅ ቦርሳ ገበያ በፈረንጆቹ 2020 ብቻ 47 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘበት ገበያ ነው። ይህ ገቢ ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መቀነስ አጋጥሞት የነበረ ሲሆን፣ ይህን የገበያ መቀነስ በቁጥር ሲያስቀምጡትም የእጅ ቦርሳ ገበያ በዓለም ደረጃ እስከ 25 በመቶ ማሽቆልቆል አጋጥሞት እንደነበር ይገልጻሉ። ብዙዎች ከቤት እንዳይወጡ መከልከላቸው ነው ለገበያ ማሽቆልቆሉ መንስኤው።
ከወረርሽኙ መቀነስ በኋላ ግን አሁን ላይ የቦርሳ ገበያው መልሶ መነቃቃት ማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ እድገትም እየተመዘገበበት ነው። ድረ ገጽ ትንበያዎችን አመሳክሮ እንደገለጸው ከሆነ ከ2021 እስከ 2028 ባሉት 7 አመታት የእጅ ቦርሳ ገበያ በአመት 6 ነጥብ 7 በመቶ ገደማ እድገት በማስመዝገብ በ2028 እ.ኤ.አ በአመት 78 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ይሆናል። ይህም በ2019 እ.ኤ.አ ብቻ በዓለም ደረጃ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ከሚያስገባው እና ከ300 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ከፈጠረው እና አሁንም ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ያለው የፋሽን ዘርፍ አካል ነው።
ለመሆኑ የእጅ ቦርሳ ገበያ እንዲህ እንዲጦፍ ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው የተባለ እንደሆነ ዋነኛው ምክንያት ሴቶች ከቤት እመቤትነት ወደ ቢሮ ሠራተኝነት እየተቀየሩ መምጣታቸው ነው። መረጃዎቹ እንደሚሉት፤ በአህጉር ከአገር አገር ቁጥሩ ቢለያይም የሴቶች የትምህርት ተደራሽነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ80 በመቶ ልቋል። የዓለም ሥራ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ደግሞ በ2018 እ.ኤ.አ ብቻ ከጠቅላላው ሴቶች 48 በመቶው ከቤት እመቤትነት ወጥተው ሠራተኛ ሆነዋል። የዓለም ሴቶች በ2019 እ.ኤ.አ ብቻ አመታዊ ወጪያቸው ወደ 31 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ደርሷል።
እነዚህ ቁጥሮች በሙሉ የሚያመለክቱት ነገር ቢኖር የእጅ ቦርሳ ገበያ ገና እየጦፈ እንደሚሄድ ነው። ይህንን የተረዱ አገራትም ከዚህ ገበያ የድርሻቸውን ለመውሰድ ከፍተኛ ርብርብ እያካሄዱ እና አዳዲስ ፈጠራዎችን እየጨመሩ ነው። ከፈጠራዎቹ መካከል ቦርሳዎቹ የስልክ ቻርጀር እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ውሀን መቋቋም እንዲችሉ ማድረግ እና መሰል ፈጠራዎች እየተጨመሩ ሄደዋል። በእጅ ቦርሳ ገበያው ላይ በተለይ ዋነኞቹ የቦርሳ ዓይነቶች ካርመን ቶቴ፤ ክላች እና ሳቸል የሚባሉ ሲሆን የመጀመሪዎቹ ሁለቱ በተለይ በሴቶች እጅጉን የሚዘወተሩ ናቸው።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ የእጅ ቦርሳም እንደሌሎች ግብአቶች በአብዛኛው ከውጭ በሸመታ የሚመጣ ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከሚፈታተኑ በርካታ የቅንጦት ግብይቶች መካከል ዋነኛው እንዲሆን ያደርገዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቆዳ ምርት ጸጋ ያላት አገር ከመሆኗ አንጻር በዚህ ዘርፍ ብትሠራ ብዙ ልታተርፍ የምትችል አገር ነበረች። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ ምልክቶች አሉ።
ኢቢሲ በአንድ ወቅት ይዞት የወጣ መረጃ እንደሚያመልከተው፣ ከሁለት አመት በፊት ውቅሮ የሚገኘው ሼባ ሌዘር ኢንዱስትሪ የሴቶች የእጅ ቦርሳን አምርቶ ወደ አሜሪካ ገበያ መላክ ጀምሮ ነበር። በዚህም በአመት 3 ሚሊዮን ዶላር በመጀመሪያው አመት ለማግኘት ችሎ ነበር። እንደ አገር ያኔ በነበረው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአምስት አመት ውስጥ ከቆዳ እና ሌጦ ዘርፉ ከ700 ሚሊዮን እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከቦርሳ እና መሰል ንግድ ማግኘት የተቻለው ግን ከ2 ሚሊዮን ዶላር በታች ብቻ ነበር።
አንድ ፋብሪካ ግን ለብቻው በቀን 300 መቶ በአመት ደግሞ ወደ መቶ ሺ ገደማ በማምረት 3 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዝግጅቱን ጨርሶ ነበር። ይህን ገቢም በ5ኛው አመት ወደ 1 ሚሊዮን ቦርሳ ምርት አሳድጎ 25 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ነበር የታለመው።
ይህ የሚያመለክተው ዘርፉ ከተሠራበት በዓለም ደረጃ የገበያ እጥረት እንደሌለ እና አማራጭ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ስልት እንደሚሆን ነው። አሁን ያለነው ገና እአአ 2022 ላይ ነው። በዚህ ወቅት የእጅ ቦርሳ ገበያው በዓለም ደረጃ አመታዊ ገቢው ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር የተጠጋ ነው። ይህ አሀዝ በቀጣይ የት እንደሚደርስ ቀደም ብለን በጠቀስናቸው የቁጥር ማስረጃዎች ላይ ተመልክተናል። ስለዚህም ገበያው ከፊታችን ነው። ጥሬ ዕቃውም በእጃችን ነው። ከእኛ የሚጠበቀው ዓለምአቀፉን የጥራት ደረጃ በሚመጥን መልኩ made in Ethiopia የሆኑ ቦርሳዎችን አምርቶ መግባት ብቻ ነው። ያን ለማድረግ ማን ይከለክለናል?
ለማንኛውም የዛሬውን ጽሒፋችንን ዝነኛው ተዋናይ ቢሊ ኮነሊ ስለ ሴቶች እና ቦርሳዎች በሰጠው አስተያየት እናጠቃልላለን፡-«የሴት ልጅ አእምሮ እንደ እጅ ቦርሳዋ ውስብስብ ነው። የቦርሳዋ የመጨረሻ ወለል ላይ ደርሰህ እንኳ አንድ የሆነ የሚያስገርም ነገር ማግኘትህ አይቀርም» ከዚህም ቦርሳ ለሴቶች የግድ መሆኑን ያስረዳል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014