ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የአገረ መንግስት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሔረሰቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ተጋምደው የሚኖሩባት አገር መሆኗ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው። ሕዝቦቿ ለአይን ማራኪ፣ ጆሮ ገብና ተወዳጅ የሆኑ እሴቶች ባለቤት፤ ባህልና ወጋቸው ለባዳው የሚያስቀና ለወዳጅ ሃሴትን የሚፈጥር ጭምር ነው። ጠላትን በአንድነት መክተው ድባቅ የሚመቱ ለሉዓላዊነታቸው መከበር በጋራ ዘብ የሚቆሙ ቆራጦች ጭምር ናቸው። ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቁና የመጡበትን ማህበረሰብ ባህልና ማንነት ሳይሸራርፉ አብረው የመኖር የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤትም ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት የእነዚህን ሕዝቦች አንድነት የሚፈታተኑ አያሌ አጋጣሚዎች ነበሩ። ይሁንና በጠንካራው አብሮነትና የተጋድሎ ወኔ ችግሮቹን በጣጥሰው በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
ዛሬም ይህን መሰል አጋጣሚ በኢትዮጵያውያን ላይ የተከሰተ ይመስላል። ላለፉት 30 ዓመታት ዘርን መሰረት አድርጎ ተዋልደውና ተዛምደው የሚኖሩ ሕዝቦች መሃል ጥርጣሬንና መከፋፈልን የሚፈጥሩ አጀንዳዎች ይራገባሉ። ይሁንና የጋራ ማንነትና ያላቸው ሕዝቦች ንፋስ ያመጣውን ወጀብ ለዘመናት በገነቡት የአብሮነት ባህላዊ እሴት ለመመከት ተዘጋጅተዋል። ከሁሉም በላይ ግን የሕዝቦች የጋራ ባህላዊ እሴቶችን አሁን ካለው በእጅጉ በላቀ ማጠንከርና ማጎልበት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ለመሆኑ “ኢትዮጵያውያን የጋራ ባህላዊ እሴቶች አሏቸው። እነርሱን ማልማትና ማጠናከር ላይ መስራት ያስፈልጋል” ሲባል ምን ማለት ይሆን?
ደስታ ሎሬንሶ በአንትሮፖሎጂ የትምህርት መስክ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ያሉና በባህል ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በርካታ የጥናት ውጤቶችን ይፋ ያደረጉ ምሁር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን (ብሔር ብሔረሰቦች) እምቅ የባህል ሃብት አላቸው። እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሏቸው የባህል እሴቶች ትልቅ ሃብት ነው። ማልማትና ማሳደግ ያስፈልጋል። ከዚህ ባሻገር ግን እንደ አገር የጋራ የሆኑና የሚያስተሳስሩ እሴቶችን ከማጎልበትና ከማበልፀግ አንፃር ብዙ ይቀራል። ይህ ባለመሆኑ ባለፉት ጊዜያት እርስ በእርስ ያለመተማመን፣ መጠላላትና አንዱ አንዱን የመግፋት ችግሮች እየተስተዋለ ነው።
“እንደ አንድ አንትሮፖሎጂስት ለአገር የትኛው ይጠቅማል የሚለውን ለማሰላሰል ስሞክር የጋራ ባህላዊ እሴቶች ላይ ለማተኮር ወስኛለሁ” የሚሉት አንትሮፖሎጂስቱ ደስታ፤ በዚህ ዘርፍ ላይ ሳይንሳዊ ምርምር በሚያደርጉበት ወቅት ኢትዮጵያውያን የጋራ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች፣ የተሳሰረ ማንነትና አንዱ በአንደኛው ውስጥ የተጋመደ አብሮ የመኖር እሴት እንዳለው ማረጋገጥ መቻላቸውን ይጠቅሳሉ። በመሆኑን እነዚህን ባህላዊ እሴቶች ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።
የጋራ ባህላዊ እሴቶቻችን የትኞቹ ናቸው?
ደስታ ሎሬንሶ እንደሚገልፁት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ “የየአገራቱ የጋራ ባህላዊ እሴቶች ምን ምንድን ናቸው” በሚል በዘርፉ ምሁራን ይጠናል። ወደ ኢትዮጵያ በሚመጣበት ወቅት እጅግ በርካታ የጋራ እሴቶች ማግኘት ይቻላል። የጥናት ውጤታቸው ላይ ተመርኩዘውም በምሳሌነት “የዓድዋ ድል” መነሻ በማድረግ ብቻ ኢትዮጵያውያን በጋራ ለመሰረቷት አገር ቀናኢ፣ በሉዓላዊነታቸው ላይ የማይደራደሩና በአገር ጉዳይ በጋራ የመቆም ባህላዊ እሴት ያላቸው እንደሆኑ ያነሳሉ።
“የኢትዮጵያን በጀግንነት በአገር ላይ ጠላት ሲመጣ የሚመክቱበት እሴት በሌላው ዓለም ላይ የሌለና ብቸኛው የማንነታቸው መሰረት ነው” የሚሉት ደስታ፤ ከዚህ ባለፈ ፍቅር፣ ብሔርን ሳይሆን ሰውነትን ያስቀደመ መተሳሰብና ትብብር የኢትዮጵያውያን መገለጫና የጋራ ባህላዊ እሴት እንደሆነ ይናገራሉ። በዚያ የድል ወቅት መላው ብሔረሰቦች ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው ከሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ብዙ ከሺ በላይ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩበት ዋነኛ ምክንያትም የጋራ እሴቶች ስላሏቸው እንደሆነ ነው የሚያስረግጡት። ይህንን በወጣቱ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ማሳደግና እሴቶቹን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ነው የሚያስረዱት። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ሌሎቹ አገራት ሁሉ መረዳዳት፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት እና ሌሎችም መሰል ማንነቶች የኢትዮጵያዊነት መገለጫና የጋራ እሴት መሆኑን ያስረዳሉ።
ከመሪዎች ምን ይጠበቃል?
“የጋራ ባህላዊ እሴቶችን ማጉላትና ማሳደግ ተገቢ ነው” የሚል ምክረ ሃሳብ በሚነሳበት ወቅት የመንግስት አመራሮችና ፖሊሲ አውጪዎች ሚና ቁልፉን ድርሻ እንደሚወስድ ይነገራል። በዚህ በኩል አንትሮፖሎጂስቱ ደስታ ሎሬንሶ ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ግልፅ የሆነ የጋራ ባህላዊ እሴቶችን ለማበልፀግ የሚያስችል ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ተቋምም ሆነ የተደራጀ ጥናት አለመኖሩን ይገልፃሉ።
“ሁሉም ሰው ስለ ጋራ እሴት ሊያወራ ይችላል። ይሁን እንጂ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ተጠንቶና ታትሞ ለትውልድም ሆነ ለትምህርት ተቋማት እየተላለፈ አይደለም” የሚሉት አንትሮፖሎጂስቱ ደስታ፤ በተለይ በመንግስት ስር ያሉ በባህልና በብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ እንደ ባህል ሚኒስትርና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት በተደራጀ መንገድ በስትራቴጂ ተደግፈው የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት እየሰሩ እንዳልሆነ ነው የሚያምኑት። ከዚህ በመነሳትም “የኢትዮጵያውያን የጋራ ባህላዊ እሴት ግንባታና ጥናትና ምርምር ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል” የሚል ጠንካራ አቋም ያራምዳሉ። ይህንን ኃላፊነት መንግስት ሊወጣና በፖሊሲ፣ ህግና በተግባር መሬት ላይ የሚተረጎምበት መንገድ መፈለግ እንዳለበትም ይናገራሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚቀነቀኑ “መደመርን”ና “ወንድማማችነት” የመሰሉ የጋራ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ሃሳቦች ከቃላት ባለፈ መሬት ላይ ወርደው በጥናት፣ ፖሊሲ ተቀይረው ማህበረሰቡን ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡ በማድረግ የባህል አብዮት ሊያመጡ በሚችሉበት መንገድ ላይ ሊሰራ ይገባል የሚል ጠንከር ያለ መልእክት ያስተላልፋሉ።
የጋራ እሴትና የብሔር ፖለቲካ አደረጃጀት
ከ80 በላይ ብሔርና ብሔረሰቦች ባሉበት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ብሔርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ስርዓት ተዘርግቷል። አሁንም የመንግስት የአገር መምራት ማጠንጠኛ ነው። ይህ በመሆኑ ምክንያት የጋራ ባህላዊ እሴቶችን ለማበልፀግና ጠንካራ የማህበረሰብ ትስስር ለመፍጠር አዳጋች እንደሆነ የሚናገሩ አካላት ቢኖሩም በዚህ ሃሳብ ግን አንትሮፖሎጂስቱ ደስታ ሎሬንሶ አይስማሙም። እንደ እርሳቸው እይታ ሁለቱንም በማይጋጭ መንገድ ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻል ይናገራሉ።
“የብሔር ብሔረሰቦች ሀብት የሆነው ባህል፣ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ስነጥበብም ሆነ ኪነ ጥበብ ማደግ አለበት” የሚሉት አንትሮፖሎጂስቱ፣ የኦሮሞም ሆነ፣ የከምባታ፣ የአማራም ሆነ የሱማሌው፣ የአፋሩም ሆነ የሀረሪው … የማንነት መገለጫዎች እንዲያድጉ በመስራት ወደ ኢኮኖሚም ሆነ የቱሪዝም ሀብትነት መቀየር ያስፈልጋል ይላሉ። እዚህ ላይ ዋነኛው ችግር የሚሆነው ግን ይህን ማንነትና ባህላዊ እሴት ወደ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም በመውሰድ የስልጣን ማግኛና የመጫወቻ ካርድ ወደ ማድረጉ ከተለወጠ ነው። ይሄ ማድረግ ፈፅሞ ተገቢ አለመሆኑን ነው የሚያስረዱት። እያንዳንዱ ብሔረሰብ ባሉት ባህላዊ ማዕከላት ሆነ በሌሎች መሰል መንገዶች የማንነቱን መገለጫ እንዲያለማ መደረግ አለበት። ይሁንና የጋራና የአንድነት መሰረት የሆኑት ባህላዊ እሴቶችን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ በተመሳሳይ ያለምንም ተቃርኖ ኮትኩቶ ማሳደግ እንደሚቻል ይገልፃሉ። ይሁንና የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና የማንነት መገለጫዎች ለፖለቲካ ስልጣን ማግኛ መንገድ ወደላይ አምጥቶ መጠቀም የጋራ እሴቶች ግንባታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ያብራራሉ።
“እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ የራሱም ሆነ በጥቅል የሚጋራው እሴቶች አሉት። ተነጣጥሎ የሚኖሩበት የፖለቲካ ደሴት ባለመኖሩ አእምሯቸውን ከፈት አድርገው ማስተዋልና የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ለማበልፀግ መትጋት ያስፈልጋል” የሚል ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ። በተለይ የአንድን ማህበረሰብ የፍትህ፣ የእኩልነት እና መሰል ማህበራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የሚፈታበት መንገድ መቀየስ እንጂ ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ በማቀንቀን የስልጣን ጋሻ ማድረግ “የጋራ እሴቶቻችንን” የሚሸረሽርና ለግጭትና የሚዳርግ ነው ሲሉ ይናገራሉ ።
መውጫ ምክረ ሃሳብ
በመግቢያችን ላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያውያን ጠላትን በጋራ ድባቅ መትተው ሉዓላዊነትን ከማስከበር ጀምሮ በደስታም ሆነ በሃዘን አብሮ የመኖር፣ የመተባበር፣ የመረዳዳትና የፍቅር እሴቶችን ለዘመናት አዳብረው በአንድነት የኖሩ ሕዝቦች ናቸው። ይህን ልዩ ሃብታቸውን ደግሞ አሁንም ይበልጥ ባሳደግ የገጠማቸውን የውስጥም ሆነ የውጭ ፈተናዎች መጋፈጥ ይኖርባቸዋል።
አንትሮፖሎጂስቱ ደስታ ሎሬንሶም በዚህ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ። በጉዳዩ ላይ ሳይንሳዊ ጥናት በመስራትም ከላይ ካነሱት የጉዳዩ ዋንኛ ማጠንጠኛዎች በተጨማሪ የሚከተለውን ጥቅል መደምደሚያ በምክረ ሃሳብ ሰንዝረው ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
እንደ አንትሮፖሎጂስቱ የጥናት ውጤት ጥቅል ሃሳብ “በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊነት ፈተና ላይ ነው” በማለት የጋራ ባህላዊ እሴቶች ከተዳከሙ መሆኑን ያስረዳሉ። የጋራ ባህላዊ እሴቶችና አገር ግንባታ የሚነጣጠሉ አለመሆናቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ እና የአገሪቱ ታሪክ የተገነባው በጋራ ባህላዊ እሴቶች መሆኑንም በማስረጃነት ያስቀምጣሉ፡፡ አሁን አገሪቷ ከደረሰችበት የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲሁም ለውጥ አኳያ በጋራ ባህላዊ እሴቶቻችን ላይ መስራት ለብልጽግና እና መደመር መርሆዎች መሳካት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም ይናገራሉ፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ሕዝቦች ወይም ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸው ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ያላቸው ናቸው” በማለትም እነዚህን ማንነቶች በግል ወይም በተናጠል ማሳደግ ወይም በትይዩ (parallel) የጋራ እሴቶቻችን ማስተሳሰር፣ መገንባት እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት ወይም አገራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት የወቅቱ ትልቁ የአገሪቱ አጀንዳ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ በዚህ አገራዊ ማንነት ላይ መሰረት ጥለን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ብልጽግና በተባበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማረጋገጥ ይቻላል ይላሉ፡፡
“የጋራ ባህላዊ ትስስር የኢኮኖሚ ማህበራዊ ትስስር፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ዋስትና ይሰጣል” የሚሉት አንትሮፖሎጂስቱ፤ ከዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ መስተጋብር እና የንግድ ልውውጥ (shared values) እንደሚፈጥር ያስገነዝባሉ፡፡ ጠንካራ አገር በጋራ እሴት ውስጥ እንደሚገነባም እንደዚያው ያስረዳሉ፡፡
በዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሳይንሳዊ ምርምር እንዳደረገ ምሁር፤ ሕዝቦች ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱት የጋራ እሴቶቻቸውን ለይተው ትኩረት ሲሰጡት መሆኑን ነው የሚያምኑት፡፡ የአገር ውስጥ ማህበራዊ ትስስር እና የጋራ እሴቶች ሲላሉ ለእርስ በእርስ ግጭት (civil war) መነሻ እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡ ይህ እሴት የማይዳብር ከሆነ ሕዝቦች አገርን አናውቅም፣ ትስስር የለንም ማለታቸው እንደማይቀር ነው የሚያስረዱት፡፡ በዚህ ምክንያትም ጥላቻ ይሰፍናል፣ ኢኮኖሚ ይወድማል፣ የአገር ጸጥታ ይናጋል፡፡ ሕዝቦች በስጋት ይኖራሉ፣ የሕዝቦች ጥርጣሬ እና አለመተማመን ጎልቶ ይወጣል፡፡ የጋራ ባህላዊ እሴት መገንባት አገሪቷን ቀደምት ታሪኮች የጀግንነት፣ የሉዓላዊነት፣ የመተባበር፣ የመረዳዳት እሴቶች ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ አገር ደግሞም የብዙ ሕዝቦች የጀግንነት እና ሉዓላዊነት ውጤት ነች በማለት ሃሳባቸውን አካፍለውናል ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም