የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሊሰጥ ነው፡፡
የጎንደር የኒቨርሲቲ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል የሚሰጠው ‹‹ከማሰተር ካርድ ፋውንዴሽን›› ጋር በመተባበር ነው፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተወካይ ወይዘሮ ይዳኙ ማንደፍሮ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት ይተገበራል፡፡
ዓላማውም የተሻለ ውጤት እና የመማር ፍላጎት ኑሯቸው በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የመማር እድል የተነፈጋቸው አፍሪካውያን አካል ጉዳተኞች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከ2010 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ ትወልደ ኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር 20 ተማሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
በዚህ ዓመትም ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ 40 ተማሪዎችን ተቀብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ አስሩ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ መሆኑ ታውቋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ይዳኙ ገለፃ መርሃ ግብሩ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከኤርትራ፣ከሱዳን፣ከኬንያ፣ከሶማሊያና ከጅቡቲ የሚመለመሉ 450 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡
እንደ አብመድ ዘገባ የተማሪዎቹ ሙሉ ወጭ በፕሮግራሙ የሚሸፈን ሲሆን ለዚህም 24 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል፡፡