‹ዝናቡ..አንተ ዝናቡ? እማማ ሸጌ ተጣሩ። እጃቸውን በአዳፋ ቀሚሳቸው እየጠራረጉ።
‹እማማ ሸጌ! ዝናቡ አይበሉኝ..ስሜ ሸጋው ነው..እርሶ ትልቅ ሰው አይደሉ? ባኮረፈ ድምጽ።
‹ምን እኔ ላይ ዘራፍ ትላለህ! ያወጡልህ ጓደኞችህን እነሱን ሀይ አትልም ነበር›።
‹በቃ አይናገሩኝ..ሁለተኛ ዝናቡ ካሉኝ ግን..› ብሎ ዝም አለ። ፊቱ ላይ እየመጣ የሚሄድ ለቅሶ ይታያል።
‹ሁለተኛ ዝናቡ ብልህ ምን ልትሆን? ወገኛ..ወገኛ ነህ›። እንዳውም ዝናቡ ነው የምልህ የምታመጣውን አያለሁ..›።
‹እንዳይሉኝ! ስሜ ሸጋው ነው ሸጋው›። እንባ እየተናነቀው..ትቷቸው ሄደ። ቤት ደርሶ..‹እማዬ..አንቺ እማዬ?
‹ጉድህ አያልቅ! ምን ሆንክ ዛሬ ደግሞ?
‹እማማ ሸጌ ዝናቡ እያሉኝ አይደል..! ለምንድነው ዝናቡ የሚሉኝ? ከእንግዲህ ዝናቡ ካሉኝ ግን..
‹ከእንግዲህ ዝናቡ ካሉህ ምን ልትሆን? ትልቅ ሰው እኮ ናቸው። ትልቅ ሰው ምንም ቢልህ ማክበር እንጂ እንደነዛ ጓደኞችህ መሳደብም ሆነ ድንጋይ መወርወር የለብህም› አለችው።
የእናቱ ንግግር ከእማማ ሸጌ ባሰበት። እናቱ እማማ ሸጌን መሰለችው፤ እሳቸውም እንዲህ ነበር ያሉት። በዚህ ንዴት ውስጥ እያለ ከርቀት ‹ዝናቡ..ክረምቱ..ዶፉ› የሚል ድምጽ ሰማ። ጥርሱን እንደነከሰ ድምጹን ወደሰማበት አቅጣጫ ሮጠ።
ከርቀት ናሆምን አየው። እዛ ሁሌ የሚጫወቱበት የተበላሸችው መኪና ጋ። እንደ ሹፌር መሪዋን ወደዚያና ወደዚህ እየጠመዘዘ፣ በእግሩ የዛገውን ማርሽ እየጠበጠበ። አላየውም.፤ ልቡ የሚነዳው አሮጌ መኪና ላይ ነበር። በአፉ የዝናቡን ስም እየተጣራ..በእጁ መሪውን እየመዘወረ አንዳንዴም እንደ መኪና ድምጽ ባፉ እየተጫወተ እንደዚህ።
ቀስ ብሎ እያደባ ተጠጋው። ከእሱና ከእማማ ሸጌ በቀር ዝናቡ ብሎ የሚጠራው የለም። በትዕግስት፣ በመቻል ማሸነፍ አይችልበትም። አብዛኞቹን ጓደኞቹን እያደባ በማጥቃት፣ እያደባ በመፈንከት፣ እያደባ በመንከስ፣ እያደባ በመቧጨር፣ እያደባ በማነቅ፣ እያደባ በማስደንገጥ ከዝናቡ ወደ ሸጋው መልሷቸዋል። ናሆምን ግን አልቻለውም.፤ በጉልበትም በእድሜም ስለሚበልጠው ሊያስቆመው አልቻለም።
በእሱ አማካኝነት ስሙን የረሱት ጓደኞቹ እንዳይመለሱ ይፈራል። የሚያደርገውን አድርጎ ከናሆም አፍ ላይ፣ ከናሆም ልብ ላይ ያን የማይወደውን ዝናቡ የሚል ስሙን መሰረዝ አለበት። ዛሬ ደግሞ በእማማ ሸጌና በእናቱ እንደተበሳጨ ነው ናሆምን ምን እንደሚያደርገው ሲያስብ የሆነ ክፉ ሀሳብ መጣለት።
ወርውሮ በማይስት እጁ ከመሬት ሁለት መጠነኛ ድንጋዮችን አነሳ። እንደ ዳዊት መሆን አማረው፤ አዎ ይህ ቀን እንደ ዳዊት ከምንምነት የሚነሳበት ነው። ሀያሉን ጎልያድ በወንጭፉ ጥሎ ከፍ የሚልበት። ናሆም ለእሱ እንደ ጎልያድ ነው። በሀይሉ፣ በጉልበቱ የሚታበይ። ብዙዎችን አሸንፎ ናሆምን ግን ታግሎ መጣል አልቻለም። ዛሬ የሚያሸንፈው ይመስለዋል፤ ዛሬ ካላሸነፈው መቼም አያሸንፈውም።
እያደባ ተጠጋው..አሮጌ መኪናዋ ላይ ተሰቅሎ ሁሌ እንደሚሉት አፉን እንደሞተር ኡ..ኡ እያደረገ አየው። ስሙ ይሰማዋል ‹ዝናቡ..ክረምቱ..ዶፉ›። እንደ ጎልያድ የገዘፈበትን ይሄን ጓደኛውን ወርውሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጀግንነቱን ያሳየዋል።
ከያዛቸው እኩያ ድንጋዮች አንዱን መረጠ። ጥርሱን እንደነከሰ ነው። እንደ ዳዊት ወንጭፉ ላይ ሳይሆን በግራ እጁ መዳፍ ላይ አስቀምጦ፣ በአምስት ጣቶቹ ደግፎ ወደ ፊት አሽቀነጠረው። ወርውሮ የሳተበት ጊዜ የለም። አይወርውር እንጂ ከወረወረ ግዳዩን ይጥላል። ምን አይነት እጅ ነው ያለው? የዳዊት ሞገስ፣ የዳዊት ሀይል በእሱ ግራ እጅ ላይ ያለ ይመስል ጠጠሮቹ ዝንፍ አይሉም።
የኦሪቱ ዳዊት በግ ጠባቂ ነበር፣ በእግዚአብሄር የሚያምን፤ እሱ ግን በማን እንደሚያምን አያውቀውም። እናቱ ነበረች ትልቅ ሰው አትስደብ፣ ትልቅ ሰው አይሰደብም እያለች ብኩርናውን ሽራበታለች። አሁን የሚያምነው በራሱ ነው እና በግራ እጁ እና ደግሞ በሚያወናጭፋቸው ጠጠሮች።፡
የወረወረው ድንጋይ ኢላማውን ሳይስት መሪ የጨበጠ ናሆም ክርን ላይ አረፈ። ያን ቦታ ለምን መርጦ እንዳለመበት እሱ ብቻ ነው የሚያውቀው። ባለው የውርወራ ልምድ መሰረት የትኞቹ የሰውነት አካላቶች እንደሚያሙና እንደሚያንፈራፍሩ ያውቃል። ለዛም ሲል ነው የናሆም ጀርባና፣ ጭንቅላት ለመመታት እንዲያመች ሆኖ ፊቱ ተጋርጦ እያለ ክርኑን የመረጠው።
ወርውሮ ማንፈርፈር እንጂ ማድማት አይፈልግም። ስስ ብልት እየመረጠ ነው የሚተኩሰው። አብዛኞቹ ጓደኞቹ ክርናቸውና ቁርጭምጭሚታቸው የተመታ ነው። እዛ ቦታ ላይ ስለመታቸው ይመስለዋል ዛሬም ድረስ ዝናቡ የሚለውን ስሙን የተጸየፉት። ይሄም ጓደኛው ስሙን እንዲጸየፈው ይፈልጋል።
እሱ ስርዐት ከያዘ እማማ ሸጌ ናቸው የሚቀሩት። እሳቸውን ደግሞ እንዴት አድርጎ ዝም እንደሚያሰኛቸው ያውቃል። አጥሚት እንደሚወዱ ያውቃል። አንድ ጊዜ እነሱ ቤት መጥተው ሙቅ መስሏቸው ሊጡን ሊጠጡት ሲሉ ታላቅ እህቱ ነበረች ያተረፈቻቸው። ዝናቡ ማለታቸውን ካልተው ሙቅ መስሏቸው ሊጥ የጠጡትን እያነሳ ሰፈሩ ውስጥ ያወራባቸዋል። ያኔ ለስማቸው ሲሉ ዝናቡ ማለትን እርግፍ አድርገው የሚተው ይመስለዋል። ያኔ እንደ ዳዊት ሆነ ማለት አይደል?
ናሆም ከመኪናዋ ላይ ወድቆ መሬት ተንፈራፈረ። ከመኪናዋ ላይ ወድቆ መሬት ሲንፈራፈር አጠገቡ ቆሞ ሲያላግጥበት ነበር። ‹ሁለተኛ ዝናቡ ብለህ ብትጠራኝ…እንዲህ ነው የማንፈራፍርህ› አለው ጥርሱን ነክሶ በጀግንነት ስሜት።
ናሆም የተመታ እጁን ባልተመታ እጁ ደግፎ መሬትን አሸሼ ገዳዎ አለባት። አፈር ከድሜ ደባለቃት።
‹ስማ! ስሜ ሸጋው ነው፤ ዝናቡ..ክረምቱ..ዶፉ ብትለኝ እንዲህ እንደ አሁኑ ሳታየኝ ነው ጉድ የምሰራህ› አለው።
ናሆም ምንም ሳይል ያደምጠዋል። አይኖቹ ወፋፍራም የእንባ ጽንስ አርግዘዋል። ከታች ወደ ላይ ሲያየው የሚያውቀው ዝናቡ አልመስልህ አለው። ፊልም ላይ እንደሚያያቸው ግብዳ ሰዎች አስፈሪ መስሎ ታየው። በእሱ ያልተመታው እሱ ብቻ ነበር ይሄው ዛሬ ምሱን ቀመሰ። የተመታ ክንዱን እንደያዘ ወደ ቤቱ ሄደ። ለአስራ አምስት ቀን ያህል አልተገናኙም። በአስራ ስድስተኛው ቀን ከእናቱ ጋር ቤተክርስቲያን ሄዶ ሊቆርብ ወረፋ ሲጠብቅ ነበር ናሆም ቆርቦ አፉን በነጠላው ይዞ ያየው።
‹ሸጋው? ናሆም ጠራው። በስሙ..ለመጀመሪያ ጊዜ።
‹ኧረ አንተ የቆረበ ሰው አያወራም..ሀጢዐት ነው›
ናሆም አፉን በነጠላውና በእጁ እንደ ሸፈነ ቀረበው። አንድ ጊዜ ማውራት ቢችል ‹ከዚህ በኋላ ዝናቡ አልልህም የሚለው ይመስለዋል። እዛው ነበር በልጅነት አንደበቱ ባለፈው ስለመታውህ ይቅርታ አድርግልኝ ያለው።
ከናሆም ጋር ወደ ቤት ሲሄዱ ‹ሸጋው..› የሚል አንድ ድምጽ ከኋላው ተሰማው። ሲዞር እማማ ሸጌን ነጭ በነጭ ለብሰው አሮጊት መላዕክት መስለው አያቸው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 /2014