ኢትዮጵያውያን መልካችን፣ ቋንቋችንና ሃይ ማኖታችን ዥጉርጉር ቢሆንም የተገነባንባቸው ማሕበራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ተወራራሽና ተቀራራቢ በመሆናቸው ተመሳሳይ ሰብእና ያለን ሕዝቦች ነን።
አብዛኛዎቻችን እንደየ ሃይማኖታችን አስተምህሮ የፈጣሪያችንን ቃል ለመፈጸም የተዘጋጀ ሥነ ልቦና ያለን ነን።ዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳንለይ እርስ በእርሳችን እንዋደዳለን፤ እንከባበራለን፤ በፍቅር ተሸናንፈን ብሄር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይገድቡን እየተጋባን በደምና በአጥንት እንተሳሰራለን።
በዚህም የአንድ ቤተሰብ አባላት ግማሹ ሙስሊም ግማሹ ክርስቲያን እስከመሆን ደርሷል።ይህ ትስስር ታዲያ በሕዝቦች መካከል ሰላማዊ መስተጋብር እንዲፈጠርና የአብሮነታችን ማገር እንዲጠብቅ አስችሏል።
ኢትዮጵያ በክርስትናና በእስልምና ቅዱሳት መጻህፍት ስማቸው ከተጠቀሱ ጥቂት የዓለማችን አገራት አንዷ ናት።እንደ መካ መዲና ወይም እንደ እየሩስዓለም ዓለምን ያስደነቁ መሲሆች ወይም ተአምር የፈጸሙ ነብዮች ሳይፈጠሩባት በሁለቱም ሃይማኖቶች ውስጥ ቦታ ተሰጥቷታል።
የተወሰነውን ብናስታውስ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች›› በሚል ስትጠቀስ ነብዩ መሃመድ ኡላማዎቻቸው ወከባና እንግልት ሲፈጸምባቸው ባዩ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ፤ በዚያ ፍትህ የሚያውቅ ንጉስ አለ። ብለው እንደጠቀሷት ይታወቃል፡፡
ሙስሊሙና ክርስቲያኑ በነበራቸው ማሕበራዊ ሕይወት ደስታቸውንና ኀዘናቸውን እየተጋሩ ረዥም ዘመናትን አሳልፈዋል፤ አንድ ወንዝ እየቀዱ፣ አንድ ገበታ እየተቋደሱ አንዳንዴም በአንድ ጣራ ሥር እየኖሩ እዚህ ደርሰዋል።
ተወዳጁ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ካንጎራጎረው ዜማ ቀንጨብ አድርገን የወሰድነው አንጓ ጉዳዩን ፍንትው አድርጎ ሊያሳይ ይችላል።
ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ፣
ተዘነጋሽ እንዴ ኢትዮጵያ መሆኑ?
አንቺም ባ’ይማኖትሽ እኔም ባ’ይማኖቴ፣
መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ልዩነት ሳንፈጥር አብሮነታችንን አጠናክረን የኖርን ሕዝቦች ስለ መሆናችን ከስንኞቹ በላይ ያደግንባቸው ወይም የኖርንባቸው አካባቢዎች ምስክሮቻችን ናቸው።ያም ሆኖ ስንኞቹ የሙስሊሙና የክርስቲያኑ ጥምረት ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው።
ሃይማታዊ እሴቶቻችን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከክፋት ይልቅ ርህራሄን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከእብሪት ይልቅ ትእግስትን፣ ከመንፈግ ይልቅ መስጠትን ወዘተ የሚያስተምሩን በመሆኑ በሰብእናችንና በኢትዮጵያዊ ማንነታችን ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በዛሬው የአገርኛ አምድ ዝግጅታችን ተዋዶ፣ ተከባብሮና ተዛዝኖ የመኖር ሃይማኖታዊ አስተምህሯችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን ምን አስተዋጽኦ አለው? በተማርነውና በተለማመድነው እሴት ልክ እየኖርን ነው? እየጾምን ባለነው የሁዳዴና የረመዳን ጾም በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ የሃይማኖት አባቶችን አስተያየት ለማጠናቀር ሞክረናል፤ እንደሚከተለውም አቅርበነዋል።
ሊቀ ህሩያን ሰርጸ አበበ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ሃላፊ እንደሚናገሩት፤ የወንጌል ትምህርት ማዕከል የሚያደርገው ፍቅር ላይ ነው።ፍቅር በቃላት ብቻ ሳይሆን በሕይወት /በመኖር/ የሚገለጽ ነው። ፍቅር ሰው ለሆነ ፍጡር ብቻ ሳይሆን ለአንስሳትም ሆነ ለማንኛውም ሥነ ፍጥረት ዋጋ መሥጠትን ያጠቃልላል።
ኢትዮጵያውያን ሃይማኖትና ብሄር ሳይለየን ከመላው ሕዝብ ጋር አብሮ ለመኖር ያለን እሴት ከኢትዮጵያ አልፎ ሌላውን ዓለም የሚያስደንቅ ነው ይላሉ ሊቀ ህሩያን ሰርጸ። በብሄርና በሃይማኖት መለያየት እንኳን ቢኖር ሁላችንም የዘር ሀረጋችን ወደ ኋላ ቢቆጠር ርቀን ሳንሄድ ግንዳችን አንድ ሆኖ የሚገኝ ሕዝቦች ነን ይላሉ።
እንደ ሊቀ ህሩያን አባባል ሃይማኖት የግል ስለሆነ ሰው የራሱን ሃይማኖት ይዞ ሊቀጥል ይችላል።በሌላ በኩል መረዳዳት፣ መፈቃቀር፣ የአንተ ችግር ከእኔ ይብሳል መባባል ሃይማኖታዊ እሴት እንደሆነ ይገልጻሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ለሰው ሁሉ በጎ ነገር አድርጉ›› ተብሏል ያሉት ሊቀ ህሩያን የእስልምና እምነት ተከታዮች በነብዩ መሃመድ ምክር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በወቅቱ የነበሩ የክርስትና እምነት አባቶች በሃይማኖታቸው ላይ ችግር ይፈጥራል ብለው ቢያምኑ ኖሮ ባልተቀበሏቸው ነበር። ግን በፍቅር ተቀብለዋቸው፤ እየተመካከሩና እየተረዳዱም በሰላም ለመኖር በቅተዋል ብለዋል።
መተሳሰቡና መቀራረቡ የማንንም ሃይማኖት የሚጫን ሳይሆን ይልቁንም እንደፈጣሪ ቃል ለማደር የሚረዳ ነው።እነዚህን ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችሉ ነባር እሴቶቻችንን በወጉ ይዘናቸው በነበር ሰዓት ፍቅርና በረከት በዝቶልን አይተናል።
ሃይማኖት ግላዊ ምርጫ ነው የሚሉት ሊቀ ህሩያን ሙስሊም የነበረ ክርስቲያን፤ ክርስቲያን የነበረም ሙስሊም የሚሆንበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል።እስከ አሁን የመጣንበት አብሮነት ለአገራችን ሰላምና ለማሕበራዊ ሕይወታችን ማማር ከፍተኛ ጥቅም ነበረው ይላሉ።
አሁን አሁን ጊዜንና ወቅትን እየጠበቀ በሚመጣ በሽታ አብረን የቆይንባቸው እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ ተግባራት ሲፈጸሙ ይታያል።የሃይማኖት ተከታዮች እና ሃይማኖት ተቋማት ጥቃት ሲደርስባቸው ታዝበናል።ሁሉም ሃይማኖቶች እንዲህ አይነቱን ተግባር የማይደግፉት መሆኑ ይታመናል።መፍትሄ የሚሆነው በአንድ ድምጽ ማውገዝና ምዕመኑ ነባሩን እሴት አጠንክሮ አንድነቱን እንዲያስጠብቅ ማድረግ ነው።
በውይይት ሊፈቱ የሚገባቸውና እዚህ ግቡ የማይባሉ ምክንያቶችን ለጠብ መንስኤ አድርጎ ህዝብን የሚያለያይ ሥራ ሲሰራ የሃይማት አባቶች ዝም ማለት እንደሌለባቸው ሊቀ ህሩያን ይመክራሉ ።
እንደ ሊቀ ህሩያን አስተያየት ሃይማኖት የሰዎችን ስሜት በቀላሉ ሊኮረኩር የሚችል ስስ ጉዳይ በመሆኑ አንዳዴ በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካዊ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የሚጥሩ አካላት ሰርገው በመግባት አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ሲሞክሩ አባቶች ሀይ ሊሏቸው ይገባል።
ባለንበት ወቅት እንደ አገርም ይሁን እንደ ሕዝብ ዋጋ ያስከፈሉን በርካታ ጉዳዮች ተከስተዋል።ሰዎች ለሃይማኖታዊ እሴቶች ተገዢ ቢሆኑ ኖሮ በአገር እና በሕዝብ ላይ ጉዳት ባልደረሰና ስጋቶችም ባልኖሩ ነበር። የየትኛውም ሃይማኖት ማጠንጠኛው ሰላም፣
ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ መተዛዘን፣ መከባበር፤ በአጠቃላይ መልካም ነገር መሥራት ነው።ሁሉም ሰው እንደየሃይማኖቱ ሰማያዊ ጸጋን ያጎናጽፉኛል ብሎ የሚጠብቃቸው እነዚህ እሴቶቹ ለምድራዊ ህይወቱም እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡
ለበርካታ ዓመታት የቋንቋ፣ የብሄር፣ የሃይማኖት ልዩነት ችግር ሳይሆንብን ተዛዝነንና ተከባብረን የምንኖር ሕዝቦች ሆነን ሳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጸማሉ ተብለው የማይታሰቡ ግፎችና ጭካኔዎች ሲፈጸሙ ማየታችን በእጅጉ የሚያሳፍር ነው።ይህ የጭካኔ ተግባር የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅብንን ሥራ አለመስራታችንን የሚሳይ ነው ሲሉ ሊቀ ህሩያን ገልጸዋል።
እንደሃይማኖታዊ አስተምህሮ መንጋውን የሚጠብቅ እረኛ ነው።መንጋው መረን የሚወጣው እረኛ ሳይኖረው ሲቀር ነው።መንጋዎችን ማሰማራት፣ ከተኩላና ከቀበሮ ጠብቆ ወደ ማደሪያቸው ማስገባት ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው።የሃይማኖት አባቶች ልጆቻቸው ፈጣሪ የሚወደውን ሥራ እንዲሰሩ በተግሳጽም፣ በምክርም፣ በትምህርትም ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው ተፈናቅለው ላሉ ሰዎች፣ ለጠፋው ነፍስ፣ ለወደመው ንብረት ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን በሚፈለገው ደረጃ በሕብረተሰቡ ዘንድ አለመስረጻቸው አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ስለዚህ እንደ እስልምና እና ክርስትና አስተምህሮ የሁለቱም ሃይማኖት አባቶች ተወቃሽ ናቸው።በዚህም በዚያም ሃይማኖት ውስጥ የነበሩ አባቶች አገርን እንደአገር አቁመው ለልጆቻቸው ያስተላለፉት አብሮነትን የሚያጠናክሩ ቅርርቦችን በመፍጠራቸው ነው።የሚፈለገውን ያህል አይሁን እንጂ ዛሬም የአባቶቹን እሴት ጠብቆ የሚሄድ ትውልድ አልጠፋም፡፡
በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የደረሰው መከራ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በመፈጸም አንድነትን ለማጠናከር የሚረዳ አጋጣሚ ሲሆን ተመልክተናል። የሃይማኖት አባቶች ይህንን በተግባር አሳይተውናል።ዘርና ሃይማኖትን ሳይለዩ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል።ኢትዮጵያውያን ከአባቶቻችን የወረስነው ማንነትም ይህ ነው።
አሁን ያለንበት ወቅት ሙስሊሙ የረመዳን ጾም ክርስቲያኑ የሁዳዴን ጾም እየጾመ ያለበት ነው።በኑሮ ወድነትና በሰላም መደፍረስ ምክንያት በርካታ የተቸገሩ ሰዎች አሉ።በጾም ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜም ቢሆን የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት የየሃይማኖቶቹ ጥብቅ አስተምህሮ ነው።ሃይማታዊ እሴቶቻችን የሚያስተምሩን ከተረፈን ላይ ሳይሆን ካለን ላይ እንድናካፍል ነው።
የእለት ጉርስና ልብስ ያጡ ወገኖችን የመርዳት ሃይማኖታዊ ግዴታ አለብን። ፈጣሪ የተራቡ፣ የተጠ ሙና የታረዙ ምስኪኖችን እንዲታገዙ ይፈልጋል። ይህ በክርስትናው ብቻ ሳይሆን በእስልምናውም ያለ አስተምህሮ ነው። በተለይም በጾም ወቅት እንዲህ
አይነቱ የበጎ አድራጎት ተግባር ይበረታታል።
እግዚአብሄር እኛን ሊታዘበን ያመጣብን ፈተና እንደሆነ አስበን የተቸገሩ ወገኖቻችንን መርዳት ይኖርብናል።ሙስሊሙም ክርስቲያኑም እንደ አንድ ሕዝብ ቆመን የመስጠትና አቅመ ደካሞችን የማገልገል ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን አጠናክረን በመቀጠል ለተቸገሩ ደራሽነታችንን በተግባር ማስመስከር ይኖርብናል ብለዋል።
ሼህ ኑሪ ሁሴን በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ነዋሪ ናቸው።ከትውልድ አካባቢያቸው መጥተው አዲስ አበባ መኖር ከጀመሩ ስልሳ አምስት ዓመታትን አስቆጥረዋል።በኖሩባቸው ዓመታት የአካባቢያቸው ነዋሪዎች የሃይማኖት ልዩነት ሳይፈጥሩ ማሕበራዊ ሕይወታቸውን ሲመሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ።እስላምና ክርስቲያን በችግር፣ በኀዘንና በደስታ ወቅት እየተረዳዱ የኖሩ ናቸው።ሌላው ቀርቶ ጋብቻ መስርተው ልጆችን እስከ መውለድ የደረሱ ሙስሊምና ክርስቲያን አባወራዎችና እማወራዎች በየመንደራችን መኖራቸውን ተናግረዋል።
ፈጣሪ ሰውን ሲፈጥር አስቀድሞ የፈጠረው አዳምና ሄዋን ነው ያሉት ሼህ ኑሪ እስላምም ይሁን ክርስቲያን መነሻው አንድ ነው ብለዋል።ሁለቱም በተረዱት መጠን የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ ለመፈ ጸም የሚጥሩ ናቸው። አስተምህሯቸው ሰዎች ፈጣሪያቸውን እንዲፈሩ፣ እርስ በእርሳቸው በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ ስለሚያደርጋቸው ሁል ጊዜ መልካም ነገሮችን ለማድረግ የሚዘጋጁ ናቸው። በጉርብትና ቡና እየተጣጡ፣ በእድር ኀዘናቸውን እየተከፋፈሉ፣ በእቁብ እየተጋገዙ፣ ሌላው ቀርቶ በጋብቻ እየተሳሰሩ የኖሩ ናቸው።የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ አንድ ላይ ዘምተዋል፤ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ ተሰውተውም በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል።
ሼህ ኑሪ በድሮ ጊዜ ተደረገ ስለተባለ አንድ ጉዳይ ከወላጆቻቸው የሰሙትን እንዲህ ይናገራሉ። ‹‹ሙስሊምና ክርስቲያን በአንድ ጉዳይ ለመምከር ሸንጎ ይቀመጣሉ።በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግረው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በመጨረሻ መተማመናቸውን፣ አብሮነታቸውንና ፍቅራቸውን ለመግለጽ ሲሉ ሁለቱም የሃይማኖታቸው ሥርዓት በሚያዘው መሰረት የባረኩትን የየራሳቸውን የከብት ስጋ አስረው በአንድ እቃ ከቀቀሉ በኋላ ተመግበዋል ይባላል።በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት አባቶች ሰው ልዩነቱን አቻቻሎ መኖር እንደሚችል ያሳዩበት ምሳሌ ነው።‹‹ሙስሊሙ ቢስሚላሂ›› ብሎ ሲባርክ ክርስቲያኑ ‹‹በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቁዱስ አሃዱ አምላክ›› ይላል።ይህን መሰረታዊ ልዩነት ሊሆን ይችላል።ዞሮ ዞሮ አቅጣጫና አንድምታው ግን አንድ ነው።
ሁለቱም ባርከው ያረዱትን ከብት እንዳይቀላቀል አድርገው በአንድ እቃ ሲቀቅሉት ፈሳሹ ሁሉንም እንደሚያዳርሰው ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም።ነገር ግን በዋና ዋና ሃይማኖታዊ መርሆዎች ቢለያዩም በበርካታ ጉዳዮች የማይለያዩ መሆኑን ለማሳየት ነው።አንዳቸው ከአንዳቸው ተገልለው የማይኖሩ እንደሆነ የተረዱበት ምሳሌ ነው›› ይላሉ።
የሃይማኖት ልዩነት መለያየትንና መራራቅን አይፈጥርም። ቅዱስ ቁርዓን ከሰው ጋር በፍቅር ኑሩ፣ ተዋደዱ ይላል እንጂ ተለያዩ አይልም።ዘመናትን የተሻገረው የሙስሊምና የክርስቲያን አብሮነት በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም።ከክርስትና ወደ እስልምና ከእስልምና ወደ ክርስትና ሃይማኖትን እስከማስለወጥ የሚደርስ ማሕበራዊ ትስስር ያለን ነን።
በዚህም በዚያም ሃይማኖት ውስጥ ለተቸገረ ስጥ ስለሚል ሙስሊሙ ለክርስቲያኑ ክርስቲኑም ለሙስሊሙ ይለግሳል።ሙስሊም በጾም ወቅት በዓመት ካገኘው ነገር ለምስኪኖች መስጠት ሃይማታዊ ግዴታ አለበት።ካለው ነገር ላይ ለተቸገረ ያካፍላል።
ባለንበት ወቅት ሰው በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ነው። በእርስ በእርስ ግጭትና ድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችን አሉ።እነርሱንም መርዳት ይጠበቅብናል። ትናንት የነበረው አብሮነታችን ዛሬም አለ፤ ወደፊትም ተጠብቆ ይኖራል ብለዋል። እኛም በዚሁ ሼህ ኑሪ ሃሳብ የዛሬውን ዝግጅታችንን እናጠቃልላለን።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 /2014