ኢትዮጵያ ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮ እየተወደደ፤ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል:: ትናንት የተገዛ ዛሬ፣ጧት የገዛነው ከሰዓት ዋጋው መጨመሩም በርካቶች የሚያስጨንቅ ጉዳይ ከሆነም ዋል አደር ብሏል::
ቸርቻሪው ስለ ዋጋው መጨመር ሲጠየቅ ‹‹የለም ከማለት እንጂ እኔም በውድ ገዝቼ ነው››ያመጣሁት ሲል ይደመጣል::አከፋፋዩ ሲጠየቅ ‹‹አምራቹ ነው የጨመረው››ይላል:: አምራቹ ደግሞ ‹‹ጥሬ ዕቃ የለም፣ጥሬ ዕቃው የሚገባው ከውጭ ነው፣ መንግሥት ደግሞ ዶላር ሊሰጠን አልቻለም››ሲል ይደመጣል::
አንዳንድ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችም በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን ያስረዳሉ።የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ከመሠረታዊ ፍጆታዎች ፍላጎት ማደግ ጋር የሚመጣጠን ምርትና ምርታማነት አለማደግ፣በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለመኖር፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረትና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም በዋነኛ ምክንያትነት ያነሳሉ::
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሸቀጦች ዋጋ መናር፣የሰላም መታጣት፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ኃብት መዋቅሮች አለመስተካከል፣በአገር አቀፍ ደረጃ ለታየው የኑሮ ውድነት ተጨማሪ ምክንያቶች ተብለው ይዘረዘራሉ::
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና የራሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያትም በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች በቂ ምርት አለመመረቱና መንግሥትም ለኢኮኖሚ ወይም ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ድጎማ የሚውል ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ለዋጋ ንረቱ መባባባስ ሁነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቁማሉ::
በአገሪቱ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል የተፈጠረው አለመጣጣም ለዋጋ ንረቱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤በግጭቶችና በድርቅ ምክንያት የተረጂ ቁጥር ማሻቀቡን ተደምሮ የኑሮ ወድነቱን ይበልጥ እንዳባባሰውም ያነሳሉ::
የዋጋ ንረት በበርካታ የአገሪቱ ዜጎች ኑሮ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ቢኖረውም በተለይም ገቢያቸው ውስን የሆኑ ሠራተኞች፣ጡረተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች ላይ የከፋ ጫና አሳድሯል:: የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ፤‹‹አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።በተለይም ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ላይ የኑሮ ጫናው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ››ይላሉ::
ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ለሠራተኞች የሚከፍሉት ደመወዝ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ ካሣሁን፤እነዚህ ሠራተኞች በሚከፈላቸው ደመወዝ ሕይወታቸውን መምራት አዳጋች እንደሆነባቸውም ይገልጻሉ::
በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ መሠረት ዝቅተኛውን የደመወዝ ወለል የሚወስን ደንብና የደመወዝ ቦርድ ተቋቁሞ እንደ አገር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መቀመጥ እንዳለበት የሚጠቁሙት ፕሬዚዳንቱ፤ አዋጁ የወጣው ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ደንቡ ወጥቶ ወደ ሥራ አለመግባቱም ይገልፃሉ:: ይህም ችግሩ መፍትሄ እንዲርቀው ማድረጉን ያሰምሩበታል::
ምሑራንም ምክንያቶቹን ከመዘርዘር ባሻገርም ችግሩ የሚገባውን ትኩረትና ፍቱን መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻለ በመግለፅ መንግሥትም ወጥ የሆነ ቁርጠኝነት አይስተዋልበትም ሲሉም ይተቻሉ:: በዚህ ወቅት ያለው ትልቁ ችግር የአቅርቦት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በገበያው ውስጥ የሰፈነው ሥርዓት አልበኝነት እንደሆነ አጽአኖት ይሠጣሉ::
መንግሥት በድጎማ የሚያመጣቸውን መሠረታዊ ሸቀጦች ሳይቀር በአግባቡ ለሸማቹ እየደረሱ ስለመሆናቸው ከላይ እስከ ታች መከታተልና መቆጣጠር እንዳልቻለ የሚጠቁሙት ምሑራኑ፣ምርቱን ማስገባት ብቻ መፍትሔ አለመሆኑን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የታየ ችግር እንደሆነ ያነሳሉ::
በየቀኑ የሸቀጥ ዋጋ እየጨመረ በነፃ ገበያ ስም
ሕዝቡ እየተበዘበዘ፣ ጥቂቶች እየበለፀጉ መሆኑን የሚገለጹት ምሑራኑ፣ነጋዴው በነፃ ገበያ ስም ሕዝቡ ላይ እንዳገኘ ዋጋ እየጨመረ የሚሄድበት አሠራር ከልካይ እንደሚያስልገውም ያስገነዝባሉ::
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል። በእለቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነቱን ያባብሳሉ ተብለው በተጠረጠሩ 104 ሺሕ የሚጠጉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ በየደረጃው በተዋቀረ የዋጋ ማረጋጋት፣ ሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል በተደረገ ክትትል ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን ለፓርላማው ገልጸዋል::
አቶ ገብረ መስቀል የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ በሕገወጦች ላይ በተደረገው ክትትል ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት መደረጉን ቢገልጹም፣የፓርላማ አባላቱ በአንጻሩ፣‹‹የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ሕገወጦች ላይ ተገቢው እርምጃ አልተወሰደም፤ በዚህም የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ መቆጣጠር አልተቻለም›› በሚል በሚኒስቴሩ ላይ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።
ሥልጣኑ በእጃችሁ እስካለ ድረስ ሕገወጦች ላይ አስተማሪ እርምጃ ለምን መውሰድ ተሳናችሁ? ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባላቱ፤ ሕገ ወጦቹ ተለይተውም አስተማሪ እርምጃ ሲወሰድባቸው የማናያቸው ለምንድ ነው ሲሉም ጠይቀዋል::
ሌላው ቀርቶ በድጎማ የሚገቡ ምርቶች ሳይቀር በአግባቡ ለኅብረተሰቡ እየተዳረሱ እንዳልሆነ በመግለፅ፣ ይህም የሆነው ተጠያቂነት ስለሌለና የግብይት ሥርዓቱን የሚመራ አሠራርና አደረጃጀት ባለመኖሩ እንደሆነ አንስተዋል::
የዋጋ ንረቱን ያባባሰው የመንግሥት የላላ ቁጥጥር እንደሆነም በርካቶች ይስማሙበታል::ምርት ደብቆ ወይም ከገበያ ዋጋ በላይ ሲሸጥ የተገኘ ነጋዴ የሚወሰድበት እርምጃ ምናልባት እስካሁን የምንሰማው ተወረሰ የሚል ዜና ነው::ማንም ነጋዴ እንዲህ በማድረጉ በፍትሕ ተጠይቆ ሲቀርብ ወይም ሲፈረድበት አይሰማም::ይኼ ደግሞ ሕገወጥነት እንዲስፋፋና እንዲበራከት አጋጣሚ ፈጥራል::
ይሕን እሳቤ የሕግ ባለሙያዎችም የሚጋሩት ነው::አቶ ኪያ ፀጋዬም እሳቤውን አጥብቀው ከሚጋሩ መካከል አንዱ ናቸው::‹‹ሌላው ቀርቶ በሕገ ወጥ መልኩ የተደበቀ የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር ዋለ ሲባል በዜና እንሰማለን፣ እናያለን፣ ይሑንና የደበቀው ማነው፣ፍርድ ቤት መቼ ቀረበ፣ ክስ ተመስርቶበትስ ምን ውሳኔ ተላለፈበት›› የሚል ዜና አንሰማም፣ አናይም፣ ባለፉት ዓመታት አንድም ለፍርድ የቀረበና የተፈረደበት ሕገ ወጥና ስግብግብ ነጋዴ አላየንም›› ይላሉ::
የሕግ ባለሙያው መንግሥት የኑሮ ውድነትን እና የጋራ ንረትን ፈር በማስያዝ ረገድ ሕግን በአግባቡ ለመተግበርና ለማስፈፀም ቁርጠኛ ከሆነ መሰል አስተማሪ የሕግ ውሳኔዎችንም በአደባባይ ሊያሳውቅ እንደሚገባም ያሰምሩበታል::
መጋቢት 29 ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት በተዘጋጀው አዲስ ወግ መድረክም የኑሮ ውድነትን አብይ ጉዳይ ሆኖ ውይይት ተደርጎበታል:: ‹‹የኑሮ ውድነት መንስኤዎቹ እና የመፍትሔ እርምጃዎች›› በሚል ርዕስ በተካሄደው በዚሁ ውይይትም ምሑራን ለችግሩ መንስኤ እና መፍትሔ የሚሉትን አቅርበዋል::
በዚሁ መድረክ ላይም በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ይርጋለም እንየው፣የኢትዮጵያ የግብይት ሰንሰለት የሚስተዋለው ርዝማኔ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ነው ያስገነዘቡት:: ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራዎች እየተከወኑና የኅብረት ሥራ ማኅበራትና በርካታ የሸማቾች ማኅበራት ቢኖሩም እሴት የማይጨምሩ ሕገወጥ የግብይት ተዋናዮች መኖራቸው ተገቢው የዋጋ ተመን እንዳይኖር አድርጓል ነው››ያሉት።
ችግሩን ለመሻገር ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአቅርቦት ክፍተትን መሙላት፣ የአምራችና የኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን አሠራር ማዘመን እና ሕገ ወጥ የግብይት ተዋናዮችን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግም አጽእኖት ሰጥተውታል::
ምሑራንም፣በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ ከቀጠለ አገሪቷን አስቸጋሪ የምጣኔ ኃብት ቅርቃር ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል ይስማሙበታል::ይህ እንዳይሆን ምን ይደረግ ለሚለውም መፍትሔ የሚሉት አላቸው::ከሁሉ በላይ መንግሥት የገበያ ሥርዓት ማስከበር፣ ሕገወጥ የገበያ ሰንሰለቱን መበጣጠስ እንዳለበት አጽእኖት ይሰጡታል::
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግሥት የአጭር የጊዜና የረዥም ጊዜ ተከታታይነት ያላቸውን ሥልቶች መቀየስ እንደሚጠበቅበት የሚያስገነዝቡት ምሑራኑ፣‹‹በአጭር ጊዜ መፍትሔዎች መንግሥት ጣልቃ በመግባት ምርቶቹን ከአምራቹ ወይም ከውጭ በማስመጣት ወደ ተጠቃሚው በቀጥታ እንዲደርሱ ማድረግ ይኖርበታል››ይላሉ::
‹‹ዘይትና ስኳር በመሳሰሉ የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የያዙና በምርት ሒደት ላይ ያሉ ድርጅቶችን፣ በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ፤የዋጋ ንረት እየፈጠሩ ያሉ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግና ሱቆችን ከማሸግ ጀምሮ፣የንግድ ፈቃድ እስከ መቀማት አስፈላጊን የሕግ እርምጃ መወሰዱንም በግልጽ ማመልከት፣በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተተገበረው የቀረጥ ቅነሳ በሌሎችም ላይ ማድረግ የግድ ነውም›› ይላሉ::
የገንዘብ ሚኒስቴርም መሠረታዊ የምግብ ሽቀጦች የሆኑት ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የሕጻናት ወተትና ሩዝ ያለምንም የውጭ ምንዛሪ ፍቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በቀጥታ እንዲገቡ ሚያዚያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም መወሰኑን አሳውቋል::መንግስት የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንዲቻልና በርካታ የውጭ አገር የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ እያቀረቡ በመሆኑ መወሰኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል::
ቀረጥና ታክስን በሚመለከት በገንዘብ ሚኒስቴር በ22/3/2013 ዓ.ም በቁጥር ማአ.30/7/51 በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት እንዲፈጸም፤አፈጻጸሙን በተመለከተ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግበት ወስኗል::
ይሑንና ምሑራኑ፣ከመሰል እርምጃዎች ባሻገር የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ከሁሉ በላይ ማክሮ ኢኮኖሚውን (macro Economic policy) ውን መፈተሽ ያስፈልጋል››ይላሉ::ይሕን እሳቤ የምጣኔ ሃብት ምሑሩ ዘመዴነህ ንጋቱ ይጋሩታል::አቶ ዘመዴነህ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመግታትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ፈትሾ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ያሰምሩበታል::ይህን እሳቤ በመንግሥት በኩልም ታምኖበታል::
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተዛባውን የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስተካከል የሶስት ዓመት እቅድ መዘጋጀቱን አሳውቋል::ከዚህ ቀደም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱ ምንጭ አገሪቷ አይኗን ጨፍና የተበደረቻቸው ውድ ብድሮች ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተው አገሪቱን የከፋ ሁኔታ ውስጥ መክተቱ ያስታወሱት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣አሁን ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የገጠመው የበጀት እጥረት የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት ምንጭ ሆኗል ነው ››ያሉት::
ሚኒስትሯ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣በበጀት በኩል የሚመጣ መዛባትን ለመከላከል ፕሮጀክትን በሚገባ ማስተዳደርና ወጪን መቆጠብ በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸው ሥራዎች መሆናቸውን ነው ያመላከቱት::
ኢኮኖሚው መሻገር ያልቻላቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በማንሳት ይህን ለማስተካከል ደግሞ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ ዝርዝር እቅድ በማስፈለጉ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ የተቀዳ እና አሁናዊነትን የተጎናጸፈ የሶስት ዓመት እቅድ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።‹፣በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት መተግበር የሚጀምረው እቅዱ ጥራት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማስመዝገብ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዋነኛ ምሰሶው ያደረገ ነው››ብለዋል::
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ባሻገር ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ወድነቱ አንዱ መንስኤ የሆነው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ዘመዴነህ፣ አላስፈላጊ ግዥዎችንና የውጭ ምንዛሪን የሚሻሙ ተግባራቶችን መግታት የግድ ስለመሆኑም አጽእኖት ሰጥተውታል::በተለይም‹‹ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለባት አገር 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መኪናዎችንና ውድ ሸቀጦች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መፍቀድ ተገቢ አይደለም››ይላሉ::
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ በጥቁር ገበያ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ጎን ለጎንም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በሕጋዊ መንገድ ገንዘባቸውን ሲልኩ የተሻለ ምንዛሪ የሚያገኙበትን የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ ጠቃሚ ስለመሆኑም ነው አፅእኖት የሠጡት::
የገበያ ሥርዓቱም ሥራ ላይ ያሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች በአመዛኙ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበሩ በመሆናቸውን አስታውሰው፤በዚህ ምክንያትም አስመጪና ላኪዎች በተወሰኑ ሰዎች የተያዘ በመሆኑ እንደሌሎች አገራት የሸቀጦችን ዋጋ የሚወስኑ ሸማቾች ሳይሆን እነዚህ ግለሰቦች መሆናቸውንም ይጠቁማሉ::በተለይ ሰው ሠራሽ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ምን ያህል ሸቀጦች እንደሚያመጡና በስንት ዋጋ እንደሚሸጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባም ነው ያመላከቱት::
በዓለም ላይ የሸቀጦች የዋጋ ንረት በቀጣዩ ወራቶች የመጨመር አዝማሚያ እንደሚኖረው ታሳቢ በማድረግ መንግሥት በተቻለው መጠን በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚያደርገውን ድጎማ ማጠናከር እንደሚኖርበትም ነው ያስገነዘቡት::
የዋጋ ንረትንና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የግብርና የኢንዱስትሪ ምርትና ምታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤በተለይ መንግሥት በበጋ ስንዴ የጀመረውን ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ በሌሎች ምርቶችም ማስፋት ለነገ የማይባል ጉዳይ እንዳልሆነም አስምረውበታል::
‹‹ኢትዮጵያ ያላትን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማልማት ከቻለች ዘይት ጨምሮ ለሌሎች አገራት የመላክ አቅም እያላት ከውጭ ዘይትና ስንዴ ማስገባቷ የሚያስቆጭ ነው››የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ትላልቅ መካናይዝ እርሻዎችን ማስፋት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑም ሳይጠቁሙም አላለፉም::፡
በሌሎች አገሮች ልምድ ኑሮ ውድነቱ ሲጨምር ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል እንዲሻሻል እንደሚደረግ የሚጠቁሙት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ፣ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መወሰኛ ደንብ በአፋጣኝ ወጥቶ ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል እንዲቀመጥ መደረግ እንዳለበት ሳያስገነዝቡ አላለፉም::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 /2014