የአድዋ ድል ተዋንያን ፣ ሁነቶች፣ መስዋዕቶች ፣ ታሪካዊ ቦታዎች ፣ ውርሶችና (legacies) ሰብዕናዎች በእኩልነት በአንድ ማዕቀፍ ሊታዩ ይገባል። አንዱ ሁነት ከሌላው ሊያንስም፣ ሊበልጥም አይገባም። የውጫሌ ውል የተፈረመበት ይስማ ንጉሥም ሆነ ፤ ስለ አይቀሬው ጦርነት የተመከረበት፣ የተዘከረበት ታላቁ የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ፤ ክተት የታወጀበት አዲስ አበባ ፤ ከአራቱ ማዕዘናት ጦሩ የከተተበት ወረ ኢሉ ፣ ንጉሡ የጦር ስትራቴጂያቸውን የነደፉበት ማይጨው፣ የጦርነቱን ማርሽ የቀየረው የአምባ ‘ላጌ፣ የመቀሌውን የወራሪ ጠንካራ ምሸግ ከሁለት ሳምንት በኋላ በውሃ ጥም የሰበረው ፣ ጦር የፈታው የእቴጌይቱ የጦር ስልት ፤ የንጉሡ ፣ የንግስቲቱ ፣ የጦር ባለሟሎች ፣ የመላ ሕዝቡ በመጨረሻም የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሆነው የኢትዮጵያውያን ፣ የጥቁር ሕዝቦች ከሁሉም በላይ የሰው ልጆች ሁሉ ድል የሆነው ዓድዋ እውን የሆነባቸው የዓድዋ ተራሮች እኩል ሊታዩ ሲገባ የታሪክ የእናትና የእጀራ ልጅ እያስተዋልን ነው።
ይህን ስል የዓድዋ ድል በሁሉም ኢትዮጵያውን ደምና አጥንት የታተመ ፤ መደምደሚያ ፣ ከፍታ ፣ ጉልላት መሆኑን ዘንግቸው አይደለም። የዓድዋ ድል እውን ሊሆን የቻለው ከክተት አዋጁ ጀምሮ በቅደም ተከተል የተከወኑ ሁነቶች ፣ የተነደፉ ስልቶች፣ አውደ ውጊያቸው፣ ወዘተ . አንዱ በአንዱ ላይ ተደምረው ፣ ተንሰላስለው፣ ተቀጣጥለው ፣ ሕብር ፈጥረው ፣ ተለስነው ምክንያትና ውጤት ሆነው እንጂ እንደ መና ደርሶ ዓድዋ ላይ ወርዶ አይደለም። ዓድዋን ለብቻው አግዝፎ ከማሳየት ፅንፍ በተቃራኒው ደግሞ ድሉን የማይቀበሉ ፣ የሚያጣጥሉ ፣ የሚያናንቁ ወገኖች መኖራቸው ታሪካችን ገና ያልተሻገራቸው ብዙ ወለፈንዲ ገደሎች መኖራቸውን ያሳያል። እዚህ ላይ የራሴን ገጠመኝ ላውሳ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የአፍሪካ ታሪክ ፕሮፌሰሬ ከክፍላቸው በአንዱ ቀን የዓድዋ ድል በአጋጣሚ ፣ በዕድል የተገኘ ፣ እንደ መና ከሰማይ የወረደ ነው ብለው የአብዛኞቻችንን እንጥል በድንጋጤ ዱብ ያደርጉታል።
ፕሮፌሰሬ የዓድዋ ድል በአጋጣሚ የተገኘ ነው ሲሉ የሰማውን ጀሮዬን ለማመን ስቸገር ይባስ ብለው ሲደጋግሙት ፤ በስሜት በተማሪ ፊት የዓድዋ ድል በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን በታላቅ መስዋዕትነትና ተጋድሎ የተገኘ ነው ብዬ አስቆምኋቸው ፤ ይህን እንደ ድፍረት ቆጥረውብኝ ከክፍል አስወጡኝ፣ ዳግም እንዳልገባም ከለከሉኝ መጨረሻ ላይ ግሬድ ስላልሰጡኝ ኮርሱን ደግሜ እንድወስድ አደረጉኝ። የሚያሳዝነው እኝሁ ፕሮፌሰር ዓይናቸውን በጥሬ ጨው ታጥበው ከአንድ ዓመት በኋላ በዩኒቨርሲቲው በተከበረው የዓድዋ 100ኛ ድል በዓል አከባበር ዝግጅት ኮሚቴ አባል ሆነው ብቅ ማለታቸው ነው።
እንደ ሮማውያኑ ጣኦት ጃኑስ Janus ባለ ሁለት ተቃራኒ ፊት የሆነውን የፕሮፌሰርን ማንነት በመቃወም ለ “ጦቢያ “ ጋዜጣ የላክሁት አርቲክል ታትሞ ሳይ አንድ የፕሮፍን ገመና በማጋለጤ ሁለት ጦቢያን በሚያክል ጋዜጣ የመጀመሪያ አርቲክሌ በመታተሟ ከዶርም ጓደኞቼ ጋር በደስታ የፈነድቅሁበትን አጋጣሚም ትላንት የሆነ ያህል ይታወሰኛል። ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና፤ ከዓድዋ ድል በፊት የነበሩ ሁነቶች ለጦርነቱ መቀስቀስም ሆነ በኋላ ላይ ለተገኘው አንፀባራቂ ፣ ታሪካዊ ፣ ታላቅ ድል የነበራቸውን አበርክቶ በስሱ እንደቅደም ተከተላቸው ላውሳ፦ ☞ የውጫሌ ውል፦ የውጫሌ ስምምነት ከሀገራችን አበይት የታሪክ ሁነቶችና መታጠፊያዎች ቀዳሚው ነው።
የሀገሪቱን መፃኢ ዕድልና ዕጣ ፋንታ የወሰነ ክስተት ስለሆነ ትውልድ ሲቀባበለው ይኖራል። ታላቁ የኢትዮጵያውያን ገድል የሆነው ዓድዋ በተወሳ ቁጥር የውጫሌ ውል በተለይ አንቀፅ 17 አብሮ ይነሳል። በጣሊያኑ መልዕክተኛ ፔትሮ ኢንቶኔል ወትዋችነትና አግባቢነት በሚያዝያ ወር መጨረሻ ከአፄ ምኒልክ ጋር በ1881 ዓ.ም በተፈረመው ውል የሰፈረው ይህ አወዛጋቢ የጣሊያነኛ አንቀፅ ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን በጣሊያን በኩል እንድታደርግ የሚያስገድድ እና ሀገሪቱም በጣሊያን ሞግዚትነት የምትተዳደር መሆኗን የሚደነግግ ነው። በዚህ የተነሳ በሀገራቱ መካከል ያለው አለመግባባት በከፍተኛ ደረጃ ተካሮ በዓድዋ ጦርነት ተደመደመ። ዳሩ ግን የውጫሌ ውል ለጦርነቱ መቀስቀስ ቀዳሚው ምክንያት ቢሆንም፤ በታሪክ ተገቢውን ገፅ አላገኘም። ☞
ወረ ኢሉ፦ የንጉሠ ነገሥት ምኒልክን የክተት አዋጅ ተከትሎ፤ ከመላ ሀገሪቱ ኢትዮጵያውያን ጠመንጃ ያለው ጠመንጃውን ፣ ጎራዴ ያለው ጎራዴውን ፣ ጦር ያለው ጦሩን ይዞ ፣ ስንቁን ቋጥሮ መሪውን ተከትሎ የከተተው በወሎዋ ወረ ኢሉ ነበር። ወረ ኢሉ ለዓድዋ ድል የሚያበቃው የጦር ስትራቴጂ የተነደፈባትና ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸው ወደ ጎን ትተው የሀገራቸውን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ቃል የገቡባት ፣ ኪዳን ያሰሩባት የቃል ኪዳን ምድር ብትሆንም እንደ ውጫሌ ውል በታሪክ ተገቢ ስፍራ አልተሰጣትም። ☞ አምባ ‘ላጌ፦ የአፄ ምኒልክ የመጨረሻ የእንደራደር ጥያቄ በእብሪተኛው የጣሊያን ወራሪ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ፤ በወርሀ መስከረም መጨረሻ 1887 ዓ.ም በራስ መኮነን ፣ በልዑል መንገሻና በአሉላ አባ ነጋ የተመራው ጦር በቆራጥነትና በጀግንነት ለሰዓታት ተፋልሞ በከፍተኛ መስዋዕትነት የሻለቃ ቶሌሲን ጦር አይቀጡ ቅጣት ቀጡት። አምባ ‘ላጌንም ተቆጣጠሩ፤ ብዙዎች ይሄን ድል፦ ታሪክ፣ ማርሽ ቀያሪ ውሎ ሲሉ ያሞካሹታል። ሌሎች የታላቁ የዓድዋ ድል አይቀሬነት አበክሮ ያበሰረ ፣ ያወጀ ፋና ወጊ ፣ አብሪ ድል ይሉታል።
☞ የመቀሌው ጦርነት፦ ጣሊያን ቀድሞ ቦታውን ስለተቆጣጠረ ጠንካራ ምሽግ ገንብቶ ነበር፤ የድርድሩን መክሸፍ ተከትሎ፤ የራስ መኮንን ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራ ጦራቸውን አስደንጋጭ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። እሳቸውንም በሀገር መክዳት እስከ መወንጀል አድርሷቸዋል፤ አፄ ምኒልክና እቴጌይቱ ብዙ ሰው በመጎዳቱ ክፉኛ አዝነው ነበር ፤ ራስ መኮንንም ለንጉሣቸው ታማኝ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንደገና የማጥቃት ሙከራ አደረጉ፤ የወራሪው ጦር ጠንካራ ምሽግ ይዞ ይዋጋ ስለነበር ከፍተኛ ጉዳት አደረሰባቸው የአሉላ ጦር ደርሶ ባይታደጋቸው ኖሮ ጉዳቱ የከፋ ይሆን ነበር፤ በተደጋጋሚ የጠላትን ምሽግ ለመስበር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን የታዘቡት መለኛዋ እቴጌ ጣይቱ የጠላት ጦር ይጠቀምባቸው የነበሩ ምንጮችን የመቆጣጠርን ጉዳይ በመላነት አቀረቡ።
ንጉሡም እንደ ሁል ጊዜው ሃሳባቸውን ተቀብለው እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጡ። ሁለቱ ምንጮች በተያዙ በቀናት ልዩነት የጠላት ጦር በውሃ ጥም ተፈታ። ተደራድሮ ምሽጉን ለቆ ወጣ። ስንቁ በከፍተኛ ፍጥነት እየተመናመነበት ለነበረው የንጉሡ ጦሩ የመቀሌ መያዝ ድርብ ድል ነበር። ለዓድዋው ድልም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። የውጫሌ ውል ፣ በወረ ኢሉ መክተት፣ የማይጨው ስትራቴጂ ፣ የአምባ ‘ላጌ ማርሽ ቀያሪ ድል፣ የመቀሌ ምሽግና እዚህ ያላነሳኋቸው ሁነቶችና ሰብዕናዎች በኋላ ለተመዘገበው ታላቁ የዓድዋ ጦርነትም ሆነ ድል የየራሳቸው የማይተካ ሚና ነበራቸው። ስለሆነም በታሪክ ገፅም ሆነ በሚደረግ ዝክር የሚገባቸውን ቦታና ትኩረት ማግኘት ሲገባቸው፤ በተንሸዋረረ የፖለቲካ ብያኔ የተነሳ እየሆነ ያለው ለየቅል ነው። ይህን ተከትሎም የውርስ ፣ የውለታ ሽሚያ፣ ሸመታ ገብያው ደርቷል።
ይህን ለማለት የተገደድሁበት ለዓድዋና ለሌሎች የታሪክ ክፋዮች የተሰጠው ትኩረት ፍትሐዊ ሆኖ ስላላገኘሁት ነው። በየትኛውም መመዘኛ የአንድ ታሪክ አንጓ፣ አጥቅ የበላይና የበታች፤ ትልቅና ትንሽ የለውም። ከብልቶቻችን አንዱን ከሌላው እንደማናበላልጠው ሁሉ ፤በዓድዋ የፓን አፍሪካኒዝም ዩኒቨርሲቲንና ሙዚየም ለመገንባት የተሄደበት ርቀት ከፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ተሻግሮ አህጉርን እስከ ማሳተፍ የሚደርስ ሰፊ ዓለምአቀፍ ቅስቀሳ ፣ ንቅናቄ ከማካሄድ አንስቶ ከፌዴራል ግምጃ ቤት 200 ሚሊዮን ብር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10 ሚሊዮን፣ ወዘተ.፤ “ በእርሾነት“ ተችሮታል። ቃል ተገብቶለታል። ዩኒቨርሲቲው የሚገነባበት ክልል መረጣ ላይ መነጋገር፣ መወያየት መከራከር፣ መሟገት ይገባ ነበር። ይህ አልሆነም። ይህ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ መዲና ለሆነችው፤ ክተት ለታወጀባት፤ የሁሉም ኢትዮጵያውን መዲና ለሆነችው፤ የነገስታቱ መናገሻ ለሆነችው፤ አዲስ አበባ አይቀርብም …!? ከሚለው መከራከሪያ ጀምሮ፤ በተከፈለ የሕይወት መስዋዕትነት፤ በፈሰስ ደም፤ በተከሰከሰ አጥንት የታሪክ ሒሳብ ይወራረድ ከተባለ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ለባህር ዳር አልያም ለአዳማ
አይገባም ነበር !? ሌላው የዚህ ጦርነት መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት ውጫሌ ከተማ የሚገኘው ይስማ ንጉሥ በተባለው ታሪካዊ ቦታ ላይ ሙዚየም ለመገንባት የክልሉ መንግሥት ሲነሳ የፌዴራል መንግሥት ድንቡሎ እንኳ ካለማጋጨቱ በሻገር በትዝብት እስክንመለከተው ይሉኝታውን ሽጦ ፤ ለፓን አፍሪካኒዝም ዩኒቨርሲቲ አደግድጎ ፣ በአጭር ታጥቆ ጠብ እርግፍ፣ ሽርጉድ፣ ያለውን ያህል ባይሆንም ለይስማ ንጉሥም ሆነ ለወረ ኢሉና ለሌሎች የዓድዋ አሻራዎች ትንፍሽ ሳይል መባጀቱ ዛሬ በፍትሐዊነት ሚዛን፤ ነገ በታሪክ ገፅ ስለሚኖረው ቦታ እንድናሰላስል አስገድዶናል። የሚያሳዝነው የታሪክ ምህራን፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ከሁሉም በላይ የታሪኩ ሠሪና ባለቤት የሆነው ሕዝብ፤ ሚዛኑን ሲስት ዓይተው እንዳላዩ፤ ሰምተው እንዳልሰሙ ማለፋቸው ነው።
ይሁንና የክልሉ መንግሥት ስንት አንገብጋቢና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ የልማት ጥያቄዎች እያለበት ድንገት ባኖ “ትክሻ ለመለካካት” ይመስላል፤ በእልህ 25 ሚሊዮን ብር ለዚህ ፕሮጀክት በጅቷል። ቅርሱ በክልሉ ቢገኝም የሀገር መሆኑን ዘንግቶ ታሪክን ዘውጋዊ በማድረግ ወጥመድ ተጠልፏል። ከዚህ ይልቅ ለታሪካዊ መስህቦች የተሰጠው የፍትሐዊነት፣ የእኩልነት ጥያቄ ሙግት ሊቀድም ይገባ ነበር። ሆኖም ይህን ታሪካዊ መስህብ ጨምሮ የንጉሡም ሆነ የንግስቲቱ የትውልድ ቀዬ አንጎለላና ጎንደር፤ ከክልል አልፎ የፌዴራል መንግሥቱ እንዲሁም አህጉራዊና ዓለምአቀፍ ቅርስ፣ ታሪካዊ መስህብ መሆኑን ተገንዝቦ ለዓድዋው ዩኒቨርሲቲ እንዳደረገው ለእነዚህ ፕሮጀክቶችም “ፓን አፍሪካዊ !” ዕይታ ሊኖረው ይገባል።
የአፄ ምኒልክ ሀውልት እዚህ ፒያሳ አፍንጫው ስር ለዓመታት ፀሐይና ቁር እየተፈራረቀበት ዝጎ እያለ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በሃሳብም በአካልም ርቆን ለሚገኝ” ፓን አፍሪካኒዝም “ ዩኒቨርሲቲ ጭራውን የቆላውን ያህል፤ ለሌሎች የዓድዋ ቅርሶች ትንሽ እንኳ እንዴት አልገደደውም !? የእቴጌ ጣይቱን ( ብርሃነ ዘኢትዮጵያን ) ሐውልት ለመገንባት ገና ከመታሰቡ አቧራ በመነሳቱ መልሶ ባለበት እንዲቀዘቅዝ ተደርጓል። ለታላቁ የዓድዋ ድል መገኘት መሰረት የሆኑ እንደ ወረ ኢሉ፣ ውጫሌ፣ ማይጨው ፣ አምባ ‘ላጌ፣ …ላሉ የገድሉ አንጓዎች የረባ ሙዚየም ወይም መታሰቢያ አለመኖሩ፤ የሙዚቃ ሊቁ ቴዲ አፍሮ የፊቱ ከሌለ የኋላው አይኖርም ያለውን መልዕክት ልብ እንዳላለው ያሳጣል። ነገርን ነገር ያነሳዋልና፤ “ ጉዞ ዓድዋ”ም የዚህ የተሸዋረረ ትርክት ቅርሻ ነው ። የገድሉን አላባውያንና ተዋንያን ሚና፣ ዋጋ፣ ድርሻ ፣ ትርጉም በአንድ ቅርጫት የማስቀመጥ አባዜ ነው። ጉዞው በተለይ ለዓድዋ ( ጦርነቱ ለተቋጨበት ቦታ) ያደላ ነው። የሁሉም ጉዞዎች መዳረሻ ዓድዋ ነው። ይሁንና ጉዞው ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት ለሆነው ውጫሌ፤ ለዓድዋው ድል መገኘት ትልቅ ሚና ለነበራቸው የአምባ ‘ላጌና የመቀሌ ዓውደ
ውጊያዎች፤ ለንጉሠ ነገሥት ምኒልክና ለእቴጌይቱ ፤ ለጦር አበጋዞቻቸው፤ ከሁሉም በላይ ለዚህ ድል ላበቃው ሕዝብ ተገቢውን ቦታ አልሰጠም። ጉዞ ዓደዋ ለ6ኛ ጊዜ ተመሳሳይ ጉዞ አድርጓል። ከአዲስ አበባ ዓድዋ፤ 7ኛ ጉዞው ግን ሌሎችን የዓድዋ አንጓዎች ለማስተዋወቅ በሚያግዝ መልኩ እንደገና ሊቃኝ ይገባል። 124ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ከዓድዋ ውጪ ስለማክበር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። እንደ መውጫ ፦ የዚህን ታላቅ ድል ገድል ትርጉም አንድምታ በጥልቀት ‘ ከአሜን ባሻገር ‘ ስንመረምረው፤ የዓድዋ ውርስ legacy ፦ ፍቅር ፣ አንድነት ፣ ይቅር ባይነት ፣ እኩልነት ፣ ነፃነትና የአሸናፊነት መንፈስ ነው። ለዚህም ነው እነኝህን ውርሶችን ለመቀዳጀት ጉዞው ከራስ የሚጀምር መንፈሳዊ ጉዞ ፣ ንግደት ጭምር እንጅ እንደ ጉዞ ዓዳዋ አካላዊ ብቻ ሊሆን አይገባም የምለው። አዎ ! ጉዞው እንደ አባቶቻችን ሳይሆን ሀዲሳዊ ፣ ሃሳባዊ ሊሆን ይገባል ፤ ማለትም አካላዊ ሳይሆን ወደ አንድነት፣ ወደፍቅር፣ ወደ ይቅርባይነት የሚያደርስ ከራስ የሚጀምር፣ ጎረቤት የሚደርስ አዕምሮአዊ፣ ሃሳባዊ፣ መንፈሳዊ፣ አመለካከታዊ መሆንም አለበት። አባቶቻችን የከፈሉልን ዋጋ ለነፃነት፣ ለክብርና ለእኩልነት ስለሆነ ጉዞው ለተሰውበት፣ ለሞቱበት፣ ደም ላፈሰሱበት፣ አጥንት ለከሰከሱት መሬት ብቻ ሳይሆን ለዓላማውም ሊሆን ይገባል። የፌዴራል መንግሥት ለዚህ አኩሪ የአፍሪካ ፣ የጥቁር ሕዝቦች ከፍ ሲልም ለሰው ልጆች ነፃነት ፋና ወጊ ለሆነው የዓድዋ ድል ሕዝባቸውን በአንድነት ዳር እስከዳር ላነቃነቁት ለአፄ ምኒልክና ለእቴጌ ጣይቱ፤ ለጦር አበጋዞቻቸውም እደግመዋለሁ፤ ፍትሐዊ “ፓን አፍሪካዊ” ትኩረት፣ ዋጋና ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል።
የታላቁ የዓድዋ ድል ውርሶችን ማለትም የጥቁር ሕዝቦች ነፃነትን፣ አንድነትን፣ እንደ ፓን አፍሪካኒዝም፣ እንደ ብላክ ኮንሽየስ፣ እንደ ፀረ አፓርታይድና ሌሎች ዓይነት ውርሶችን ስንወሰድ ስማቸውን ብቻ ነጥለን ሳይሆን የተሸከሙትን ከቡድ ፅንሰ ሃሳብና ባህሪ ጭምር ካልሆነ የታሪክ ምፀት፣ ልግጫና ሽሙጥ ይሆናል። ከመንደርተኛ፣ ከጎጠኛ፣ ከቀዬኛ፣ ከወንዝ ልጅኛ፣ ከጎሰኛ፤ እስር፣ አዚም፣ የዞረ ድምር ( hangover ) ሳንላቀቅ ስለጥቁር ሕዝቦች ድል፣ ስለዓድዋ፤ ስለ ፓን አፍሪካኒዝም፤ ስለ አንድነት፤ ስለ ፍቅር፤ ስለ እኩልነት፤ ስለ ፍትሕ የማውራት የቅስም ልዕልና አይኖረንም። ታሪክ እንደ ትውልዱ የፍትሐዊነት ጥያቄን አንግቦ ግዘፍ ነስቶ ለተቃውሞ ጎዳና ባይወጣም በብራናው ከትቦ ነገ ይጠይቀናልና፤ በተከሳሽ ሳጥን ያቆመናል ከዚህ ተጠያቂነት ለመዳን የዓድዋን ድል ብልቶች አንዱን ከሌላው ሳናበላልጥ በፍትሐዊነት በማየት ኃላፊነታችንን እንወጣ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)