ቀዩ አውራ ዶሮ እንደልማዱ ማልዶ ተነስቷል። በእርሻ ማሳው ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደም ድምፁን ከፍ አድርጎ ኩ…ኩ…ኩሉ…እያለ መጮሹን ቀጠለ። ደግሞ ጎንበስ ብሎ እያቅራራ በዝናብ የረሰረሰውን መሬት ጫር ጫር አደረገ። «መሬቱ ጥሩ ነው፤ ዝናብ ገብቶታል የበልጉ ምርት ጎተራ እንዲሞላ ጠንክሮ መሥራት አለብን።» ሲል ከአጎነበሰበት ቀና ብሎ አኩተመተመ። «በልግ ቀረ መጣ ብለን በጉጉት ስንጠብቀው የነበረውን ዝናብ የሰጠን ፈጣሪ ይክበር ይመስገን» ሲል አመሰገነ። አሁንም ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ፤ በሃሳብ ውጣ ውረድ ድልድይ እየተሻገረ መደበኛ ሥራውን አላቆመም። ደጋግሞ ይላል ኩ…ኩ…ኩሉ።
ደጋግሞ የሚያሰማው ድምፅ የሰፈሩን ዶሮዎች አላስተኛ ቢላቸው አንድ ሁለት… እያሉ ድምፁን ወደሰሙበት ማሳ አመሩ። ገብስማው ዶሮ ፈጠን ብሎ «ምነው ጌታው! እንዳው በሰንበት እንኳን አላስተኛ አልከን» ሲል ቅሬታ አዘል ጥያቄ አቀረበ። ቀዩ ዶሮ አንገቱን ተክሎ የሚጭረውን እርሻ እንዲያይለት በመፍቀድ ስፍራውን እየለቀቀ «አሁን ጊዜው የበልግ እርሻ የሚታረስበት ነው። ገበሬ ዝናብ ካገኘ ለምን ይተኛል፤ ማልጄ በመነሳቴ ይኸው የሠራሁት» እያለ በኩራት መናገሩን ቀጠለ። ገብስማው ዶሮው ያስጨነቀው ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር …አለማግኘቱ መሆኑን አጫወተው። «አንተ ከየት አገኘህ ወዳጄ» ሲልም ጠየቀው። መለሰለት ቀዩ ዶሮ «ተው እንጂ እኛ እኮ ጥሩ ልምድ አለን። ባህላዊ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንጠቀማለን።
ያለፉት ወራት ሁሉ ይሄንኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ስናዘጋጅ አይደል የቆየነው፤ ደግሞም እኮ ከግብርና ልማት ባለሙያው የተነገረን የተፈጥሮ ማዳበሪያንም ሳንተው እንደአስፈላጊነቱ ዘመናዊውንም መጠቀም እንዳለብንም አይደል? ባለፈው ዓመት በሠራነው ሥራ በአንድ በኩል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሌላ ማሳ በኬሚካል ማዳበሪያ ተጠቅሜ ያገኘሁትን ምርት አላየህም? ውጤቱ መሳ ለመሳ ነው።» እያለ አስረዳው። ይሄን ያዳመጠው ገብስማው ዶሮ የራሱን ስንፍና ረግሞ፤ ጎበዙንና ዘዴኛውን ጓደኛውን በማድነቅ ጭንቅላቱን ነቀነቀ።
«ይህን ጊዜ ፈጥኜ ማሳዬን ላዘጋጅ ከህብረት ሥራ ማህበሩ ሰሞኑን የሚሰራጨውን ማዳበሪያም ገዝቼ የበልጉ ወቅት ሳያልፍ እዘራለሁ» ሲል ተናገረ። «እውንተ ብለሀል፤ ገበሬ ዝናብ ጠብ ካለ ሌላ ምን ሊሠራ ብለህ፤ለእርሻው አንተም ታውቅበታለህ፣ አስቀድመህ ዳፕ፣ ዩሪያ… አልቀረበም እያልክ ብቻ ሳትጠብቅ በራስህ የተፈጥሮ ማዳበሪያም በማዘጋጀት የእርሻ መሬትህን አዘጋጅተህ መሥራት እንዳለብህ አትዘንጋ። አሁንም ቢሆን ጎን ለጎን የጓሮ አትክልትህን ቦታ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተህ በመርጨት ተጠቀም።» ሲል ዳግም አሳሰበው። በሃሳቡ መስማማቱን ራሱን በመነቅነቅ ገለጸ። የሁለቱን አውራ ዶሮ ውይይት ስታደምጥ የነበረችው ሴት ዶሮ መሀል ገብታ
«ውይይታችሁን አደመጥኩ፤እኔም ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፤የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቀደም ሲልም አባት አያቶቻችን መሬቱ ለምነቱን እንዳያጣ፣ ምርትም እንዲሰጥ ሲጠቀሙበት ነበረ። አሁን ዘመናዊው ሲመጣ ሙሉ ለሙሉ መተዋችን ተገቢ አይደለም። ይሄንንም ባለሙያዎቹ ደጋግመው ነግረውናል። መጠቀም የሚገባን መሬቱ እንደሚፈልገው የማዳበሪያ ዓይነት እንጂ ለሁሉ የተፈጥሮ ወይም ለሁሉም የኬሚካል ማዳበሪያ አይደለም። መሬቱ ምን ይስማማዋል የሚለው ከባለሙያ ምክር ጠይቆ መጠቀሙ ለሁላችንም ይጠቅማል።
ሰሞኑን ደግሞ ማዳበሪያ በየመሸጫዎቹ እየተከፋፈለ መሆኑን ሰምቻለሁ። የዘር ጊዜው ሳያልፍብን ተሸጦም ሳያልቅ ሄደን እንግዛ። የማዳበሪያው ዋጋም የትየለሌም አይደል» እያለች እፊት እፊት መምራት ቀጠለች። «ኧረ ሌሎች የግብርና ግብአቶችም አስቀድመን ገዝተን ለመጪውም ክረምት መዘጋጀት አለብን» ስትልም ሁሉም አስቀድመው እንዲያስቡበት አደራዋን አስከተለች። ቀዩ ዶሮም በሃሳቡ መስማመቱን እንደለመደው ኩ…ኩ..ኩሉ… በማለት አረጋገጠ። ይህ የሚያሳው የሃገራችን አርሶ አደር ባህላዊ ዕውቀትና ዘመናዊነት አጣምሮ በመያዝ ምርታማነቱን ማሳደግ እንዳለበት ነው፡፡ ወቅቱ የመኸር ወቅት የግብርና ዝግጅት የሚካሄድበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብአት አቅርቦት ወሳኝ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃም ለ2011/2012 ምርት ዘመን ለመኸርና በልግ ወቅት የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎች እንዲሁም ሌሎች የግብርና ግብአቶችን ገዝቶ በማሰራጨት ላይ ነው።
ስለሆነም አርሶ አደሩ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል ምርታማነትን ለማሳደግ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ከከሚካል ማዳበሪያዎች በተጨማሪም ባህላዊ ማዳበሪያንም መጠቀም አለበት፡፡ ለዚህ ሁሉ ቀድሞ ዝግጀት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሀገር አቀፍ የማዳበሪያ አቅርቦት አንድ ሚሊዮን 125 ሺ ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በሚያደርገው ድልድል መሰረት ለህብረት ሥራ ዩኒየኖች ይከፋፈላል። ኮርፖሬሽኑም ባሉት የሽያጭ አውታሮቹ መሰረት ሽያጭ ያከናውናል። በዚሁ መሰረት እስከአሁን 542 ሺ 166 ኩንታል ማዳበሪያ በብር 702 ሚሊዮን 402 ሺ 12 ሽያጭ ተከናውኗል። በቀጣዮቹ ወቅቶችም ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
አርሶ አደሩ ከባለሙያ በሚያገኘው ምክር ታግዞ ለመሬቱ ባህሪ የሚስማማውን የኬሚካል ሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በወቅቱና በተገቢው ቦታ፣ ተገቢውን መጠን በመጠቀም ለምርትና ምርታማነቱ ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። ባህላዊ ዕውቀትን ከዘመናዊው ጋር አጣምሮ በመጠቀምም ምርታማነቱን ማረጋገጥ አለበት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011