ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር የጋራ ሕግና መተዳዳሪያ ደንብ አርቅቀን ጥቅም ላይ ከማዋላችን በፊት እንደየማህበረሰባችን ባህላዊ ዳራ ዲሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ አብሮነትን፣ እርቅን፣ ፍቅርና መቻቻልን ወዘተ ከእሴቶቻችን ተምረናል፤ ወርሰናልም። ባህላዊ እሴቶቻችን በየአካባቢው የሚኖረው ማህበረሰብ እርስ በእርሱም ይሁን ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ጥሩ መስተጋብር ፈጥሮ እንዲኖር አስችለዋል። እንደ ጉዲፈቻ፣ ሞጋሳ፣ የጡት አባት፣ የአይን አባት የመሳሰሉት እሴቶች ማህበራዊ ትስስሩንና ስንስሉን የሚያጠብቅባቸው ገመዶቹ ናቸው። ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ እዚህ እንድትደርስ ያስቻላትም በየጊዜው በባህላዊ ወግና ሥርዓት የተገራ፣ የአባቶቹን ምክርና ተግሳጽ የሚሰማ፤ የማህበረሰቡን ወግና ባህል የሚያከብር ትውልድ ስለሚፈጠር የወረሰውን ትውፊትም አጠናክሮ ስለሚያስቀጥል ነው።
ኢትዮጵያዊያን በባህላችን መሰረት ሽማግሌዎቻችንን እናከብራለን፤ ፈጣሪያችንን እንፈራለን፤ እንግዳ እንቀበላለን፤ እንረዳዳለን፤ እርቅና ሰላምን እንወዳለን፤ ነውር የሆነ ድርጊትን፣ ግፍና በደልን እንጸየፋለን። ይህ ትናንት የነበረ፤ ዛሬም ያለ፤ ወደፊትም የሚኖር ማህበረ-ባህላዊ እሴታችን ያጎናጸፈን ታላቅ ጸጋ ነው።
በዛሬው የሀገርኛ አምዳችን ቅኝት ያደረግነው በሀዲያ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች ላይ ነው። በዋናነትም ማህበረሰቡ እርቅና ሰላምን ለማውረድ የሚጠቀምባቸው ባህላዊ ሥርዓቶች ጥልቅና ዝርዝር አፈጻጻሞች ያሉት ነው። እኛ ግን በወፍ በረር ምልከታ የፍትህና የእርቅ ስርዓቱን ለመዳሰስ ሞክረናል። በዚሁ መሰረት ከሰውና ከሰነድ የተገኘ መረጃ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።
‹‹ገራድ አድል ገብረ ኪዳን ቀልበጎ›› በሀዲያ ባህላዊ ሥርዓት ከአያት ቅድመ አያታቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ስልጣን እንዲይዙ ማህበረሰቡ ሃላፊነት የሰጣቸው አባት ናቸው። ‹‹ገራድ አድል›› የሚለው የማዕረግ ስም ሲሆን የሀዲያ ብሄረሰብን በኃላፊነት ለሚመራ ሰው የሚሰጥ የክብር ስም ነው። ‹‹ገራድ›› ‹‹ገሩ አዶ›› ከሚሉት ቃላት ጥምረት የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም “የረጋ ወተት” ወይም “የበሰለ ሰው” ማለት ነው። ‹‹አድል›› የሚለውም “የፍትህ መሪ” ወይም “የፍትህ ንጉስ” እንደ ማለት ነው።
ገራድ አድል ገብረኪዳን ቀልበጎ የተወለዱት በሀዲያ ዞን አመካ ወረዳ፤ አንጃማ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ነው። አንጃማ ማለት የአንድ ባህላዊ መሪ መቀመጫ ቦታ እንደ ማለት ነው። በወቅቱ ቦታው የአያታቸው መቀመጫ ስለነበር ይህን ስያሜ እንዳገኘና ቀበሌውም አንጃማ ተብሎ ለመጠራት እንደበቃ ገራድ አድል ገብረኪዳ ይገልፃሉ።
ገራድ አድል ገብረ ኪዳን ቀልበጎ በዚሁ አካባቢ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። በወቅቱ ወደ ስልጣን የመጣው የደርግ መንግሥት ቤተሰቦቻቸው ላይ ግፍና በደል ይፈጽምባቸዋል። የተወሰኑ ቤተሰቦቻቸው ይረሸናሉ፤ አባታቸውም ይታሠራሉ፤ እርሳቸውም በልጅነታቸው ወደ አዲስ አበባ ለመሰደድ ይበቃሉ። ስማቸውን ቀይረው አዲስ አበባ ጀነራል ዊንጌት አካባቢ ተቀምጠው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው ካጠናቀቁ በኋላ ለአራት ዓመት የቲዮሎጂ /የሥነመለኮት/ ትምህርት ተምረው ኬኒያና ኡጋንዳ እየተንቀሳቀሱ መንፈሳዊ ተግባራትን ይፈጽሙ ነበር። እግረ መንገዳቸውንም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተምረው ያጠናቅቃሉ።
ገራድ አድል ገብረ ኪዳን እንደሚናገሩት፤ ከኢጣሊያን ወረራ በኋላ አያት ቅድመ አያታቸው ሲመሩት የነበረው ባህላዊ ሥርዓት በአጼ ኃይለሥላሴ ከዚያም ወዲህ በደርግ መንግስት ጫና ተፈጥሮበት ከአባት ወደ ልጅ ይደረግ የነበረው የስልጣን ሽግግር ወደ አባታቸው ሳይተላለፍ ይቀራል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ግን ባህላዊ ሥርዓቱ እንዲቀጥል የገራድ አድል ገብረኪዳን አባት ማህበረሰቡን እንዲመሩት ይፈለጋል። እርሳቸው ግን በተለያዩ ምክንያቶች ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመሸከም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ።
የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ለባህላዊ እሴቶች ዋጋ መስጠቱን ተከትሎ የማህበረሰቡ ባህላዊ ሥርዓቶች እንደገና ማንሰራራት ይጀምራሉ።
የሀዲያን ማህበረሰብ ሲመሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል ማህበረሰቡን የሚመራ ሰው እንዲመረጥ ይደረጋል። በዚሁ መሰረት ገራድ አድል ገብረ ኪዳን ቀልባጎ እስከ አያታቸው ዘመን ድረስ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ሥርዓት እንዲያስቀጥሉ ለ‹‹አሸን ገራድ›› ይታጫሉ። ሥርዓተ ሹመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ‹‹ሄቦ… ሄቦ… አሸን ገራድ›› ተብሎ ስልጣናቸው ይታወጃል።
ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ አጠቃላይ የሃዲያ ገራድና የሌሎችም ብሔረሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ባለስልጣናት በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ ‹‹ገራድ አድል›› የሚለው ከፍተኛ ማእረግ ይሰጣቸዋል።
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ትኩረት ያደረግነው የገራዳዊ ሴራ ታሪካዊ አመጣጥና አወቃቀር ላይ ሳይሆን የሀዲያ ብሔረሰብ እርቅና ሰላምን ለማውረድ የሚጠቀምባቸው ማህበረ-ባህላዊ እሴቶች ላይ ነው።
ዘመናትን የተሻገረው የገራድ ማህበረ-ባህላዊ ሥርዓት የብሄረሰቡን ተወላጆች ብቻ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችንም ያቅፋል። የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የእርቅ፣ የሰላም የሀዘን፣ የደስታ ወዘተ ማህበራዊ መስተጋብሮች በባህሉ መሰረት እንዲከወኑ ያደርጋል።
ገራድ በሥሩ አምስት መዋቅሮች አሉት። መዋቅሩን ከታች ወደ ላይ ስንመለከተው ሚንዳና፣ ሞልዳና፣ ሱልዳና እና ጊችዳና ናቸው።
በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች ወይም ችግሮች እንደ ክብደትና ቅለታቸው መጠን በየደረጃው በተዋቀሩ ተወካዮች እንዲታዩ ይደረጋል። በቤተሰብ መካከል ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ጀምሮ አጠቃላይ የሀዲያ ብሔረሰብ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ግጭት ውስጥ ቢገባ ገራዶች እየመከሩ መፍትሄ ይሰጣሉ።
እንደ ገራድ አድል ገብረኪዳን አባባል የሀዲያ ሕዝብ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የሰላም እና የሌሎችንም ማህበራዊ ጉዳዮች ከአምስት መቶ አመት በፊት ጀምሮ በባህላዊ ሥርዓት ሲፈጽም የኖረ ነው። ሀዲያ ከእርሱ ጋር የሚኖሩ ሌሎች ብሄረሰቦችንም በባህላዊ ሥርዓቱ ያቅፋል። በባህሉ መሰረት ጡት መጣባት አለ። ጡት የተጣባ ሌላ ብሔረሰብ እንደ ወንድም ወይም እንደ ሀዲያ ብሔረሰብ አባል ይታያል። ለምሳሌ በሀዲያ ብሔረሰብ ስድስት ጎሳዎች /የዘር ግንዶች/ አሉ። የአማራ ተወላጆች ወደ ሥፍራው መጥተው መኖር ሲጀምሩ ሀዲያ እነዚህን አካላት እንደ ሰባተኛ ጎሳ አድርጎ ተቀበላቸው እንጂ አልገፋቸውም ይላሉ ገራድ አድል ገብረ ኪዳን። ጡት ተጣብተው በሀዲያ ብሄረሰብ ወግና ባህል መሰረት እየኖሩ ነው። ምርቃት ላይ ሰባተኛ ወንድም ተነስተህ መርቅ ይባላሉ።
የሀዲያን ቋንቋ ወግና ሥርዓት እያከበሩ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተስማምተው እየኖሩ ነው። ስለዚህ ሀዲያ ለራሱ ብሄረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ተገቢውን እውቅና ይሰጣል። አሁን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ሲፈጠሩ ሀዲያ ውስጥ ኮሽታ የሌለው ሌላውንም እንደራሱ አድርጎ ስለተቀበለ ነው። ይህ ታዲያ ሀዲያ ለዲሞክራሲ ሥርዓት አዲስ አለመሆኑን ያሳያል። የሀዲያ ሕዝብ ለዘመናት ሲያራምድ በነበረው ባህላዊ ሥርዓት የዲሞክራሲ፣ የፍትህና የእኩልነት አስተሳሰቦችን አዳብሯል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስለ ፍትህ ስለ ዲሞክራሲ የሚታገሉ ጎምቱ ፖለቲከኞችና የታሪክ ተመራማሪዎች ከዚህ ማህበረሰብ ወጥተዋል። እንደ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና እንደ ፕሮፌሰር ላፒሶ ጌ.ዴሌቦ የመሳሰሉትንና ሌሎች በርካቶችን መጥቀስ ይቻላል።
እንደ ገራድ አድል ገብረኪዳን እንደሚሉት እነዚህ ምሁራን የታሪክ፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የሰላም ወዘተ እውቀትን ከማህበረሱ ባህላዊ ሥርዓት እየተማሩ ያደጉና ከባህሉ የተቀዳ ማንነትን ያጎለበቱ ናቸው።
የኢህአዴግ እጩዎች ለበርካታ ጊዜ ከማይመረጡበት አካባቢ አንዱ ሀዲያ ነበር ያሉት ገራድ አድል ገብረ ኪዳን ይህ የሚያሳየን የሀዲያ ሕዝብ ለእውነተኛ ዲሞክራሲና ለሰው ልጆች መብት መከበር የቆመ መሆኑን ነው። የሀዲያ ሕዝብ በጎሰኝነት፣ በጎጠኝነት፣ በዘረኝነት … ፖለቲካ እንዳይጠላለፍና ፍትሃዊ እንዲሆን ያደረገው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ማህበረ-ባህላዊ እሴቱ ነው። በመሆኑም የሀዲያ ሕዝብ እሴት ለሌሎች አካባቢዎችም ምሳሌ መሆን የሚችል ሀብት ነው።
አሁን አሁን ይህንን ድንቅ ባህል ሊያደበዝዙ የሚሞክሩ አሠራሮች እየታዩ ስለሆነ ሊታረሙ እንደሚገባ መጠቆም ያስፈልጋል ይላሉ ገራድ አድል ገብረኪዳን።
እንደ ገራድ አድል ገብረኪዳን አባባል ባህላዊ ተቋማት ህጋዊ መሰረት ቢኖራቸው አሁን እየታየ ላለው አገራዊ ችግር መፍትሄ ማመንጨት በቻሉ ነበር። ከሰማኒያ አምስት በላይ የሚሆኑ ብሄረሰቦችን ባህልና እሴት ወደ ጎን ትቶ የውጭ አገር ልምድን መሰረት ባደረገ ሕገ መንግስት አገርን መምራት አስቸጋሪ ነው። አገራዊ እሴቶች እየተጠኑ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ ኢንስቲትዩት ሊኖር ይገባል። ‹‹ወፍ እንደአገሯ….›› እንዲሉ ለአገራዊ ችግሮቻችን አገራዊ መፍትሄዎችን ማስቀደም ያስፈልጋል።
ለምሳሌ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት፣ የሀዲያ ገራዳ ስርዓት፣ የጋሞ፣ የሲዳማ፣ የአማራ፣ የወላይታ ወዘተ እሴቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ቢውሉ ችግሮቻችንን መቅረፍ ያስችሉናል። ሽማግሌዎች የመንግሥት ፖለቲካዊ ጉዳይ አስፈጻሚ መሆናቸውን ትተው እንደ ባህሉ፣ ወግና ሥርዓቱ ሕዝባቸውን እየመሩ ተሰሚ መሆን ይገባቸዋል። የአገር ሽማግሌዎች የሚደመጡና የሚከበሩ እንዲሆኑ ከተፈለገ ከመንግሥት ተጽዕኖ መላቀቅ አለባቸው። በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመግባባት ቢፈጠር እንኳ ሽማግሌዎች ሕዝባቸውን ማረጋጋትና እሳት ማጥፋት የሚችሉት የሕዝብ ድጋፍ ሲኖራቸውና ከመንግሥት ተፅዕኖ ነጻ መሆናቸው ሲታመን ነው ብለዋል።
ገራድ አድል ገብረኪዳን ከፍትህ አንጻር የሀዲያ ብሔረሰብ ከመንግሥት የፍትህ ተቋም ይልቅ በባህላዊ የፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት አለው ይላሉ። ለምሳሌ በመንግሥት የፍትህ መዋቅር ዳኞች ተጨባጭ መረጃ ከሌላቸው ፍርድ አይሰጡም። በሀዲያ ማህበረሰብ እውነትን ገላልጦ በማውጣት በዳይን ለመውቀስ ተበዳይን ለመካስ የሚያስችል ባህላዊ የፍትህ ሥርዓት አለ። በተለይም ነፍስ ከጠፋና ወንጀሉን የፈጸመው ሰው ካልታወቀ ጥፋት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩት ሰዎች ጉዳዩን ስለመፈጸማቸውና አለመፈጸማቸው ቃለ መሃላ ያደርጋሉ። መሃላው ጥቁር መውጋት /ሄመቻ ቀስማ/ ይባላል።
ተጠርጣሪው ጥቁር ከብት እየወጋና ደሙን እያፈሰሰ አልገደልኩም፤ ከገደልኩ ደሜን እንደዚህ ያፍስሰው፤ በወንጀሉ እጄ ካለበት የተረገምኩ ልሁን፤ እያለ ቃለ መሃላ የሚፈጽበት ባህላዊ ሥርዓት ነው። በዚህ አያበቃም፤ ሳር የማያበቅል ገላጣ ቦታና የእንቧይ ዛፍ ወዳለበት ቦታ ይሄዳል። በብሔረሰቡ እምነት የእንቧይ ዛፍ ከዛፎች ሁሉ አጭሩና የተናቀ ነው፤ ለጣውላ፣ ለማገዶ፣ ለጥላ የማያገለግል እሾሃማ ነው። ስለዚህ ተጠርጣሪዎቹ በእንቧይ ላይ እንዲሸኑ ይደረጋል። ገራድ አድል ገብረኪዳን እንደሚያስረዱት “ወንጀሉን ከፈጸምነው ዘራችን እንደዚህ እንቧይ ለምንም የማይጠቅም ይሁን” የሚል አንድምታ አለው።
መሃላው ይደርሳል ተብሎ በጽኑ ስለሚታመን ሰዎች ሳይዋሹ እውነታውን ይናገራሉ። ተጠርጣሪው እውነታውን ለመሸሸግ አይደፍርም፤ እውነታው ከታወቀ በኋላ ተበዳይ ትክክለኛውን ፍትህ እንዲያገኝ ይደረጋል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ የተለያዩ ባህላዊ ሂደቶች ተከናውነው እርቅ ይደረጋል። የእርቅ ስርዓቱ “የጢግ ጉላ ሥነ ሥርዓት” ይባላል።
አለባቸው ኬዕሚሶ እና ሳሙኤል ሀንዳሞ እንዳጻፉት ‹‹በሀዲያ ማህበረሰብ ‹የጢግ ጉላ› ሥነ ሥርዓት የጥል፣ የበቀልና የጸጸት ስሜትን በማንጻት ወደ ሰላማዊና ጤናማ ግንኙነት የመመለስ ሥነ ሥርዓት ነው። የጢግ ጉላ ሥርዓት ለሟች ቤተሰብና ለገዳይ ቤተሰቦች የሥነ ልቦና ፈውስ ይሰጣል›› ይላሉ ።
የበዳይና የተበዳይ ቤተሰቦች ወንዝ ወርደው ወተትና ማር በአንድ እቃ እንዲጠጡ ይደረጋል። ተበዳይ ካሳ እንዲያገኝ ይደረጋል። ገዳይ የሟች ቤተሰብ ይሆንና መሬት ተሰጥቶት እያረሰ እንደ ልጅ የሟችን ቤተሰብ ያግዛል። ተበዳይም ቂሙን እርግፍ አድርጎ ይተዋል፤ ከዚያ በኋላ ሰላም ይሰፍናል ማለት ነው።
በሀዲያ ብሔረሰብ እንደመተውና እንደመስጠት በምድር ጸጋ የለም ተብሎ ስለሚታመን ሰዎች ቂማቸውን ይተዋሉ። ማህበረ-ባህላዊ እሴቱ ለዘመናት በሀዲያ ምድር ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ በመሆኑ ልምዱና ተሞክሮው በአገራዊ ምክክሩና መግባባቱ ተጠቃሽ ቢሆን ሌሎች ሊማሩበት ይችላሉ ብለዋል ገራድ አድል ገብረኪዳን ቀልበጎ።
ቅራኔዎችን በባህላዊ መንገድ የመፈታት ልምዳችን ቢዳብር የኢትዮጵያ ዛሬ ያንዣበበት አደጋ ባልኖረ ነበር። እኛም የሀዲያ ማህበረ-ባህላዊ የእርቅና ሰላም ሥነስርዓት ለአገራዊ ምክክርና መግባባት የራሱን ድርሻ ስለሚያበረክት ሊበረታታ ይገባል እያልን ተሰናበትን። ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2014