በሰሜን ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገዋል። በተለይ ከትግራይ ክልል በርካታ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ፍለጋ ወደ አዋሳኝ አማራ ክልል እየጎረፉ ናቸው፡፡
ይሕን ያስተዋለው የፌዴራል መንግሥትም በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግና እንግልታቸውን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው አሳውቋል፡፡ ለሰብዓዊነት ሲባልም ከሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ. ም.ከሰዓት ጀምሮ ግጭት የማቆም ውሳኔ አስተላልፏል።
ውሳኔው ከተወሰነበት ቀን አንስቶም በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረውን የአየር በረራ በየቀኑ እንዲደረግ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ተቋማት ፍቃድ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ ገንዘብና አልሚ ምግቦችን ረጂ ድርጅቶች በቻሉት መጠን በአየር ትራንስፖርት መጓጓዝ ጀምረዋል፡፡
ይህ የመንግሥት ጥረት እና ቁርጠኝነት የሰብዓዊ ሁኔታውን በማሻሻል ረገድ የሚኖረው ስኬት የሚረጋገጠው በሌላኛው ወገን የሚገኘው አካል በተመሳሳይ ለዚህ ዓላማ በሚኖረው ቁርጠኝነት ልክ መሆኑን ያስገነዘበው የፌዴራል መንግሥት፣ ውሳኔው የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲችል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከማንኛውም የጥቃት እንቅስቃሴ እንዲታቀብ እና በጉልበት ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣም ጠይቋል።
ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በፌዴራል መንግሥቱ ውሳኔ መደሰቱን በተለያየ መንገድ ገልጿል፡፡ የአውሮፓ ሕብረት ጉዳዩን አስመልክቶ በማሕበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ፣ የኢትዮጵያን የመንግሥት ውሳኔ እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡ ሕብረቱ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በፍጥነት ለማድረስ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።
የተለያዩ አገራትም ውሳኔውን አወድሰውታል፡፡ ውሳኔው ይፋ መደረጉን ተከትሎ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጡት መካከል የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ መንግሥታት ይገኙበታል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭት ለማቆም መወሰኑ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር ለመስራት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ውሳኔው ድጋፍ ለሚሹ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት ለማቅረብ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስም፣ ለአገሪቱ ደህንነትና ብልጽግና ሁሉን አካታች የሆነ ፖለቲካዊ ሂደት ለማስጀመር መሠረት እንደሚሆንም አሳውቃለች፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ለሰብዓዊ አቅርቦት ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰነው ውሳኔ አጥብቀን እንደግፋለን›› ብለዋል። ቪኪ ፎርድ ፣ የትግራይ ባለሥልጣናት ተኩስ በማቆምና ከአፋር በመውጣት ምላሽ መስጠት አለባቸው” ብለዋል። ቱርክም ውሳኔውን አድንቃ ‹‹ለግጭቱ መፍትሔ ለማፈላለግ ትክክለኛ እርምጃ›› ብላዋለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንደሚያደንቁ አውስተው፣ አሁን የታዩት አዎንታዊ ለውጦች በፍጥነት ወደ መሬት ወርደው መተርጎም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ሁሉም አካላት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በሙሉ ሰብአዊ እርዳታዎች ያለመስተጓጎል እንዲገባ እንዲያመቻቹም አጽእኖት ሰጥተውታል፡፡
ከውሳኔው በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም እርዳታውን ለማቅረብ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባ ቢሆንም ይሁንና የሌላኛውን ወገን ቅን ትብብር ማግኘት አልቻለም፡፡
ምንም እንኳን የመንግሥት ውሳኔን ተከትሎ አሸባሪው ሕወሓት ባወጣው መግለጫ ለዚሁ የግጭት አቁም እርምጃ ተባባሪ መሆኑን ቢያሳውቅም፣ ከሕወሓት በኩል አስፈላጊው ትብብር ባለመኖሩ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ቀናት በየብስ አማራጭ ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ማድረስ አልተቻለም፡፡
የአሸባሪው የሕወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ መንገድ በመዝጋት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ የሚያደርጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የትግራይ ሕዝብ የእርዳታ አቅርቦት ስላላገኘ በረሃብ አደጋ ላይ ነው በማለት ክስ ሲያሰሙም ይደመጣሉ፡፡
ከቀናት በፊትም የሽብር ቡድኑ በተለይ በበራህሌ፤ ኮነባና አብአላ አካባቢዎች ተኩስ በመክፈቱም ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ሰመራ ከተማ ለመቆም ተገደውም ነበር፡፡ የአፋር ክልል አመራሮችም መጋቢት 22 ቀን 2014 ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እርዳታው እክል እንደገጠመው አረጋግጠዋል፡፡
የአፋር ክልል ኪልበቱ ረሲ ዞን /ዞን ሁለት/ የሎጂስቲክስ አስተባባሪ አቶ አብዱ መሃመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹትም፤ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል ወረራ በመፈጸም በራህሌ፤ ኮነባና አብአላ አካባቢዎች ተኩስ ከፍቷል። ‹፣ይህ የጥፋት ድርጊቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ሊገቡ የነበሩ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሯል። በዚህ የተነሳ ዕርዳታ የጫኑ 20 ከባድ ተሽከርካሪዎች በሰመራ ከተማ ቆመዋል›› ብለዋል፡፡
‹‹አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት የተነሳ በርካታ የአፋር ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል›› ያሉት አቶ አብዱ፤ ይሁንና የትግራይ ሕዝብም የኢትዮጵያ አካል ነው በሚል ሕብረተሰቡ የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲያልፉ ትብብር ቢያደርግም የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት የተነሳ ተሽከርካሪዎቹ አብዓላ እንኳን መድረስ አልቻሉም›› ብለዋል።
‹‹አሸባሪ ቡድኑ ግን የእራሱን ጥፋት ለመሸፋፈን መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ አድርጓል የሚል ክስ በተደጋጋሚ ማቅረቡ ቡድኑ ውሸትን እንደ አንድ የማደናገሪያ ስልት የሚጠቀምበት መሆኑን ያረጋገጠ ነውም›› ብለውታል፡፡
‹‹አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል የሚያደርገውን ጦርነትና ግጭት አባባሽ ድርጊቶች የሚያቆም ከሆነ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለምንም ችግር ወደትግራይ ክልል መግባት ይችላሉ›› ያሉት አቶ አብዱ፤ ለዚህም መላው የአፋር ሕዝብና መንግሥት በቀናነት ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል ወረራ በመፈፀም አምስት ወረዳዎችንና አንድ የከተማ አስተዳደርን ይዟል፡፡ በወረራው 600 ሺህ ሰዎች ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በተለይ ከዞን ሁለት 480 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
የአፋር ክልል የብልጽግና ፓርቲ አፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን እንደሚገልጹት ከሆነ ግን፣ የአፋር ሕዝብ በሽብር ቡድን የተነሳ ጉዳት እየደረሰበት ቢሆንም የትግራይ ሕዝብም እንደኛው ችግር ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ ነው በሚል ስሜት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎች እንዲያልፉ ትብብር እያደረገ ይገኛል፡፡
ይሁንና አሸባሪው ሕወሓት በአብዓላና በተለያዩ የአፋር አካባቢዎች በከፈተው ጦርነት የተነሳ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ገብተው የጫኑትን እርዳታ ማድረስ አልቻሉም ያሉት አቶ መሐመድ፣ የቡድኑ እኩይ ተግባርም እርባና ቢስ የፖለቲካ ቁማር ስለመሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ በወቅቱ የአብኣላ የዕርዳታ ማስተላለፊያ መንገድ በሕወሓት ታጣቂዎች በመዘጋቱ የተነሳ 43 የጭነት መኪና የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ሊገቡ እንዳልቻሉ ገልፆ በተለይም 20 የጭነት መኪናዎች የእርዳታ እህሉን እንደጫኑ በአፋር ክልል በሠመራ ከተማ መቆማቸውንም አረጋግጦም ነበር፡፡
ይሁንና ከቀናት በኋላ በዓለም ምግብ ድርጅት አማካኝነት 21 ከባድ የጭነት መኪናዎች የእርዳታ እህል በመጫን በአፋር ክልል በአብኣላ መንገድ የሰብአዊ እርዳታ በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ መጀመራቸውን አሳውቋል፡፡
ጉዳዩን በሚመለከት አስተያየት የሚሰጡ አካላት በአንፃሩ፣ ይህን መንገድ የመክፈትና የመዝጋት የፖለቲካ ጨዋታ አዋጭ አለመሆኑን በማስረገጥ በተለይ ፌዴራል መንግሥት ይፋ ያደረገው ውሳኔ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲችል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከማንኛውም የጥቃት እንቅስቃሴ መታቀብ እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ካጋሩን መካከልም የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማሕበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ አንዱ ናቸው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በ2013 ዓ ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ሃምሳ አለቃው፣ የትግራይ ሕዝብም ዋነኛ የቀውሱ ሰለባ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልል ሕዝቡን ካለበት ትልቅ ቀውስ በተለይም ከረሃብ ለመታደግ መውሰድ ያለበትን እርምጃ እየወሰደ ነው›› የሚሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ አስፈላጊውን መስዋትነትና ዋጋ በመክፈል በተለይም ሕዝብን ከረሃብ ለመታደግ እርዳታ እንዲገባ እየደረገ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ባገኘው አጋጣሚ በመጠቀም፣ በተለይ ለረሃብ ለተጋለጠው ሕዝብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ታላቅነትን የሚመሰክር ነው›› ይላሉ፡፡
ይሁንና የመንግሥት ሃሳብና አቋም ባለመደገፍ እርባና ቢስ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ ሰብአዊ እርዳታዎች ተደራሽ እንዳይሆኑ መከልከል እጅግ ከፍተኛ ወንጀል ስለመሆኑ የሚያሰምሩበትት ሃምሳ አለቃው፣ በዚህ አይነት ተግባርም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚጎዳው ሕዝብ ስለመሆኑ አጽእኖት ይሰጡታል፡፡
ችግር ላይ ለሚገኝ ሕዝብ መፍትሄ መሆንና በፍጥነት መድረስና አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል እርዳታ እና ድጋፍ የሚደርስለትን መንገድ ማመቻችት እንጂ በተለያየ መንገድ እንቅፋት መፍጠር ኪሳራ እንጂ አንድም ትርፍ እንደሌለውም አፅእኖት ይሰጡታል፡፡ ተግባሩንም በራስ ላይ ከመጫወት ጋር ያነፃፅሩታል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የአሸባሪው የሕወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ መንገድ በመዝጋት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ የሚያደርጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የትግራይ ሕዝብ የእርዳታ አቅርቦት ስላላገኘ በረሃብ አደጋ ላይ ነው በማለት ክስ ያሰማሉ›› የዚህ ጨዋታ ግብ ምን ይሆን የሚለው ታዲያ የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡
ሃምሳ አለቃ ብርሃኑም፣ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ሁለት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እንደ ሃምሳ አለቃ ገለፃም፣ በመሰል ቀውስ ወቅት የእርዳታ ድርጅቶች እና የአገራት መንግሥታት የሰጡትም ሆነ ለመስጠት ያቀዱት እርዳታ በተገቢው መንገድ ለሕዝብ እንዲደርስ ይፈልጋሉ፡፡ ማንኛውም እርዳታ በተገቢው መልኩ መድረስ ካልቻለም፣ ለምን የሚል ጥያቄና ጫና ይፈጥራል፡፡
ይህ እንደመሆኑ ለትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እንቅፋት የመፍጠሩ ተግባር አንደኛው ዓላማ፣ ‹‹መንግሥት በተገቢው መንገድ እርዳታ እንዲደርስ እያደረገ አይደለም›› የሚል ብርቱ ጫና ከእርዳታ ድርጅቶች፣ ከአገራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደርስበት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
ሌላኛው እና ዋነኛው የቀመሩ ዓላማም ‹‹የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንዳይገባ ከልክሏል›› የሚል አጀንዳ በመንገር ሕዝብ ብስጩ እንዲሆንና ይበልጡን ለተቃውሞ እንዲነሳሳ ብሎም ለጦርነት እንዲመቻች ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ‹‹የቀመሩ ድምር ውጤትም ኢትዮጵያን ይበልጥ ቀውስ ውስጥ መክተት ነው›› ይላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም መንግሥት መሰል ሰብአዊነት ውሳኔ በማስተላለፍና የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ በሰኔ 2013 ዓ.ም.መጨረሻ ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክፍል ለቅቆ እንዲወጣ ሲያደርግ ሕወሓት ሰብዓዊ እርዳታ ተባባሪ ከመሆን በተቃራኒ ጦርነቱን እንደገፋበት ይታወሳል፡፡
አሸባሪው ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በኩል ባካሄደው ጦርነት መጠነ ሰፊ ጥቃትና መጠነ ሰፊ ጉዳትን ያደረሰ ሲሆን፣ ከወራት ጉዞ በኋላም በኢትዮጵያ ልጆች ብርቱ ትብርብና ክንድ ተደቁሶ ወደ መጣበት መመለሱም ይታወሳል፡፡
ይህን ዋቢ የሚያደርጉም፣ ይህ ታሪክ እንዳይደገም ከወትሮው በተለየ የቤት ስራን መስራት ያስፈልጋል የሚል ፅኑ አቋም አላቸው፡፡ ሃምሳ አለቃ ብርሃኑም ቢሆን ይህን እሳቤ ይጋሩታል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ተክለ ቁመና በእጅጉ ማደራጀት የግድ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል፡፡
መከላከያው ይበልጥ ከተጠናከረና በተገቢው ውሃ ልክ ላይ ከተቀመጠ ማንኛውም ሃይል በቀላሉ ተነስቶ የማይተነኩሰው፣ የማይደፍረውና በተገቢው መንድ የሚደመጥ እንደሚሆን የሚያስገነዝቡት ሃምሳ አለቃው፣ መከላከያ ሰራዊት ተክለ ቁመናን ማጠናከር ማለት ግን ለጦርነት እጅ መስብሰብ ማለት እንዳልሆነ አፅእኖት ይሰጡታል፡፡
ይልቁንስ አሸባሪው የሕወሓት ቡድንም ሆነ ማናቸውም ሃይሎች እድልና አጋጣሚዎች በመጠቀም ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያና መከላከያዋናን ከመድፈር አስቀድመው ቆም ብለው እንዲያስቡ ማድረግ ታሳቢ ያረገ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የመንግሥት ሰብአዊ ውሳኔ ግቡን እንዲመታ ጥረቱን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት የሚያስገነዝቡት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ በማንኛውም መንገድ፣ መድረክና ሁኔታ ሰላማዊ ግኑኙነትን እየፈጠረ ሕዝብ ጋር መድረስ እንዳለበትና በተረጋጋና በሰከነ መልኩ ሕዝብ ዘንድ መድረሻ በሮቹን እያስከፈተ መዝለቅ እንዳለበት ነው ያስረዱት፡፡
የሰላም አየር ለመተንፈስ ከሁሉ በላይ መንግሥት ለሰላም ሆደ ሰፊ መሆን እንዳለበት የሚጠቁሙት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ኢትዮጵያውያንም አንዳቸው ከሌላቸው በሁሉ ረገድ የተሳሰሩና ውህድ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች እንደመሆናቸው በአገራቸው የተነሳውን እሳት ለማጥፋትና ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ በስክነት፣ በትብብርና በፍቅር መትጋት ብሎም መወያየት እንዳለባቸውም ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
የሰብአዊነት የግጭት አቁም ውሳኔው ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በተሳለጠ ሁኔታ መድረስ እንዲችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ፣ ዓለም አቀፉ የለጋሾች ማሕበረሰብ እያቀረበ ያለውን ድጋፍ እና እርዳታ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
አሸባሪው ቡድንም ልዩ ልዩ ምክንያቶች ከመደርደርና የተዛቡ መረጃዎችን ከማሠራጨት በመቆጠብ የእርዳታ አቅርቦት ከሚተላለፍባቸውና በጉልበት ከያዙዋቸው የአፋርና የአማራ ክልል ወረዳዎች መውጣት እንዳለበት አፅእኖት የሠጠው የፌዴራል መንግሥት፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጫና እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014