ክረምቱን ቀድሞ መሬቱን የሚያረሰርሰውና የሰው ልጅን ከሀሩር ፀሐይ በረድ የሚያደርገው ይህ አሁን የምንገኝበት በልግ እየተባለ የሚጠራው ወቅት ነው።ይህ ሰሞኑን እየዘነበ ያለው ዝናብ ለከተሜውና በገጠር ለሚኖረው ማህበረሰብ የተለያየ ትርጉም ነው የሚሰጠው።ከተሜው በፀሐይ ኃይል የነደደው አናቱ ቀዝቀዝ ማለቱን ነው የሚያየው። ብዙዎችም በአየሩ ቀዝቀዝ ማለት የደስታ ስሜታቸውን ሲገልጹ ይሰማል።
በገጠሩ ግን ዝናባማ የሆነው የአየር ፀባይ ለውጥ ሞቃታማውን አየር ከማቀዝቀዝ በላይ ለግብርና ሥራው ምቹ መሆኑ ላይ ነው ትኩረት የሚሰጠው። በኢትዮጵያ ዋነኛው የዝናብ ወቅት ከሰኔ እስከ መስከረም የሚቆየው የክረምት ጊዜ ሲሆን፣ የግብርናውን ሥራም በስፋት ማከናወን የተለመደውም በእነዚህ አራት ወራቶች ነው። ይህ ወቅት ለሰብል ልማት (እድገት) ተመራጭ ቢሆንም በዚህ ወቅት መዝነቡም በልግ አብቃይ ለሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ወቅታዊው ዝናብ ይጠበቃል።
ይህ ወቅት የሚጠበቅና የተለመደ ቢሆንም የአየር ፀባዩ ከአመት አመት የተለያየ ስለሚሆን ወቅታዊው የአየር ፀባይ ለግብርና ሥራው ተስማሚ ስለመሆኑ ወቅቱን ተከትሎ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረጃ አደራጅቶ ዘርፉን ለሚመራውና ግብርናውን ለሚያከናውነው መረጃውን ማድረስ ይጠበቃል።
በበልጉ በሚከናወነው የግብርና ሥራም በሰብል የሚሸፈነው መሬትና አስፈላጊው ዝግጅት ቀድሞ መከናወን ያለባቸው ተግባራት ናቸው። እኛም ወቅታዊውን የአየርፀባይና በበልግ ታርሶ በዘር የሚሸፈነውን መሬትና ሊሰበሰብ የታቀደውን የምርት መጠንና አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በተመለከተ እንደሚከተለው ቃኝተናል።
ወቅታዊውን የአየር ፀባይ መረጃ ሰብስቦና ተንትኖ ለሚመለከተው አካል በማሰራጨት ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ያለውን የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃን ነው ያስቀደምነው። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ኃይለማርያም እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተውናል። እርሳቸው እንዳሉት የበልግ ወቅት የሚባለው ከየካቲት እስከ ግንቦት ወራቶች ያሉት ጊዜያቶች ናቸው።
በእነዚህ ወቅቶች በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የበልግ ዝናብ የሚያገኙበት ዋነኛው ወቅታቸው ነው። የዘንድሮ የበልግ ወቅት ዘግይቶ ካለፈው ሳምንት ነው ዝናቡ የጀመረው። ይህም ሆኖ ግን የዝናብ ስርጭቱ አብዛኛውን የአገሪቱን አካባቢዎች የሸፈነ መሆኑን ነው የኤጀንሲው ትንበያዎች የሚያመለክቱት። ቀሪው የበልግ ወቅት አልፎ አልፎ ዝናብ ቢኖረውም ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና የተቆራረጠ ሊሆን እንደሚችል ተተንብዮዋል።
መዘናጋት ሳይኖር በመረጃው የተገኘውን እርጥበት በመያዝ በአግባቡ ለግብርና ሥራው መጠቀም ያስፈልጋል። በተሰጠው ትንበያ መሠረት ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ከመደበኛው ያደላ የዝናብ መጠን እንደሚያገኙም እንዲሁ ተተንብዮዋል። በሰሜን ምሥራቅ የበልግ ተጠቃሚዎችም ወደ መደበኛ የተጠጋ ዝናብ ያገኛሉ። በምዕራብ አጋማሽ ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ ነው በትንበያው ማረጋገጥ የተቻለው።
በዚህ የበልግ ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለሚከናወነው የግብርና ሥራ ኤጀንሲው የሚኖረው ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል አቶ ክንፈ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የበልግ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት ጥር ወር መጨረሻ ላይ ኤጀንሲው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝቶ ያለውን ወቅታዊ የአየር ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።የጽሑፍ ሰነድም አሰራጭቷል።
ኤጀንሲው የአራቱን ወራት አጠቃላይ የአየርፀባይ መረጃ ከማሳወቅ በተጨማሪ በየአስር ቀኑ፣ የወቅት አጋማሽ ላይ እና በአጭር ጊዜ ደግሞ በየ24 ሰዓት ኤጀንሲው የራሱን ድረ ገጽ ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ወቅታዊውን መረጃ በማሰራጨት የግብርና ሥራውን በማገዝ ኃላፊነቱን ይወጣል። የመረጃው ዋና ተጠቃሚ ለሆኑ የዘርፉ አካላት ደግሞ ግምገማና ትንበያ የያዘ መረጃ በየአስር ቀኑ በደብዳቤ ያሳውቃል።
ከወቅታዊ የአየርፀባይ መረጃ ጋር በተያያዘ ከሚሰጡ ማስጠንቀቂያዎች አንዱ ጎርፍ ነው።በዚህ የበልግ ወቅት እንዲህ ያሉ ስጋቶችን ቀድሞ መረጃ በመስጠት ላይ ስላለው ነባራዊ ሁኔታም አቶ ክንፈ እንደገለጹት፤ በበልግ ወቅት በስጋት ሊገለጽ የሚችል ጎርፍ አይጠበቅም።ነገር ግን በአንድ ቀንም ሆነ በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ጠንካራ የሆነ ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ከአስር ቀን በታች በአጭር ጊዜ በሚሰጥ ትንበያ መረጃ ይገለጻል።አጠቃላይ ግን ልክ እንደ በልግ ሲተነበይ ወቅታዊው የዝናብ ሁኔታ በአብዛኛው ወደ መደበኛ የተጠጋጋ ስለሆነ የተለየ ጎርፍ አልተተነበየም።
በዘርፉ ላይ የሚገኙት አካላት ከኤጀንሲው ጋር ሊኖራቸው ስለሚችለው ቅርበትም እንደተናገሩት፤ ኤጀንሲው ከግብርና፣ ከጤና፣ከትምህርትና ከሌሎችም አስፈጻሚ ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሠራ ሲሆን፣ ባሉት አስራአንድ ማዕከላት ነው አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኘው። የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መደበኛ፣ ወደ መደበኛ የተጠጋ፣ አልፎ አልፎም ከመደበኛ በታች የሆነውን ወቅታዊ መረጃ መሠረት በማድረግ በወቅቶቹ የተገኙትን እርጥበቶች ውሃ በማቆርና በተለያየ ዘዴ በመያዝ ለግብርና ሥራው በማዋል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲጠቀሙበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚሰጠውን ወቅታዊ የአየር ሁኔታ መረጃና ትንተና ከሚጠቀሙት አስፈጻሚ ተቋማት ቀዳሚ የሆነው የግብርና ሚኒስቴር መረጃውን መሠረት አድርጎ የበልግ ወቅት የግብርና ሥራውን እንዴት እየመራ እንደሆነና በልጉ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተከናወኑ ሥራዎችና የሚጠበቁ ውጤቶችን በተመለከተ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ እንደሚከተለው ገልጸውልናል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የንቅናቄ መድረክ ሥራዎችን፣ በበልግ ወቅት አምራች በሆኑ እንደ ደቡብ ክልል ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ስልጠና በመስጠት ጭምር ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ነው የበልግ የግብርና ሥራው ላይ እገዛ ያደረገው። በዚህ የበልግ ወቅት ወሳኝና የበልግ ተጠቃሚ የሆኑት የደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሆኑ አካባቢዎች ሲሆኑ ለግብርና ሥራ ከሚውለው መሬታቸው ውስጥ 50 በመቶውን በማረስ በተለያየ ሰብል የሚሸፍኑት በዚህ የበልግ ወቅት ነው። በመሆኑም የበልግ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ነው።
ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የበልግ ተጠቃሚ ተብለው ከሚታወቁት ደግሞ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ናቸው። በኦሮሚያ እስከ አንድ ሚሊዮን ሄክታር፣ አማራ ክልል እስከ ሦስት መቶ ሺህ ሄክታር የሚደርስ መሬት በማረስ በተለያየ ሰብል ይሸፍናል። በአጠቃላይ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በበልግ የግብርና ሥራ በሰብል ልማት ለመሸፈን የተዘጋጀውና በዕቅድ የተያዘው መሬት ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ይሆናል።
ከዚህም 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ነው በቅድመ እቅድ ዝግጅት ላይ የተቀመጠው። በበልግ የግብርና ሥራው ከተጀመረ ደግሞ ይህ መረጃ እስከተጠናከበት ጊዜ ድረስ ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል። ከታረሰው መሬት ውስጥ ደግሞ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ወደ ሁለት መቶ ሺህ በተለያየ ሰብል በዘር ተሸፍኗል።
የበልግ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ሳይሆን ዘግይቶ በመግባቱ በአብዛኛው የበልግ የግብርና ሥራ በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመረው በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም መጨረሻ ነው። በዚህ የበልግ የግብርና ሥራ የሚመረተው ምርትም በቆሎ፣ ማሽላ፣ አንዳንድ የጥራጥሬ የሰብል ዓይነቶች ሲሆኑ፣ በተጨማሪም እንደየአካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ወይንም ስራ ስሮችን ለምግብነት በማዋል በሚጠቀሙ አካባቢዎች የተለያዩ የስራስር ተክሎች ልማት ይከናወናል።ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስካሁን የተከናወነው የበልግ የግብርና ሥራ ግምገማ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ነግረውናል።
እንደ ዩሪያ ዳፕ ያለው የአፈር ማዳበሪያና ምርጥዘር ያለው የግብአት አቅርቦትን በተመለከተም ዳይሬክተሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ እንዳስረዱት፤ ለበልግ የግብርና ሥራ ተብሎ ለብቻ የሚቀርብ ግብአት የለም። የመኸር፣ የመስኖና የበልግ ተብሎ አንዴ በሚገባው ግብአት ነው ልማቱ የሚከናወነው። በመሆኑም ሚያዝያ ወር ላይ የዘር ሥራ የሚያከናውኑ እንደ ሲዳማ ካሉት አካባቢዎች በስተቀር ከመኸሩ የግብርና ሥራ የተረፈው ግብአት ነው ለመስኖና ለበልግ የግብርና ሥራዎች የሚውለው። በዚህ መልኩ አብዛኞቹ አካባቢዎች እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ወቅታዊው ዝናብና አጠቃላይ የአየር ፀባይ ለበልጉ የግብርና ሥራ ተስማሚ ስለመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ስላለው ግምገማም ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ ዝናቡ ዘግይቶ በመግባቱ የዘር ወቅቱም ገፋ ብሏል። ይህም መሬቱ በዘር መሸፈን ከነበረበት ወቅት ዘግይቷል።መዘግየቱ ቢኖርም የዝናቡ መምጣት እንደ አንድ ዕድል ስለሚወሰድ በበጎ ነው የሚታየው።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት በመቀስቀስ ለአንድ አመት ጦርነቱ እንዲዘልቅ በማድረግ የግብርና ሥራውን ያስተጓጎለው አሸባሪው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ትህነግ) የ2013/ 2014 ዓ.ም የመኸር የግብርና ሥራ እንዳይካሄድ ክረምቱ ላይ ጠባጫሪነቱን መጀመሩ ይታወሳል። በዚህም በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ አብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች የግብርና ሥራ አለመካሄዱ ይታወቃል። ምንም እንኳን አሁን ላይ ጦርነቱ እንደስጋት የሚነሳና አንፃራዊ ሰላምም መገኘቱ እየተነገረ ቢሆንም እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ስጋታቸውን የሚገልጹ አካላት አሉ።
በጦርነቱ የግብርና ሥራው የተስተጓጎለባቸው አካላት በዚህ የበልግ የግብርና ሥራ ወቅትም በተመሳሳይ ስጋት ይኖር እንደሆን ዳይሬክተሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በልግ አምራች የሆኑ አካባቢዎች በሙሉ በመካተታቸው በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ አካባቢዎች በልግ አምራች ከሆኑ ያመርታሉ። ከክልሎች ጋር መሠራት ያለበት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።በጦርነት ቀጣና ውስጥ በመሆናቸው በመኸሩ የግብርና ሥራ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎችን ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ያለው ለመስኖ ሥራ የሚያገለግለው ግድብ ወይንም የመስኖ አውታራቸው በጦርነቱ ያልፈረሰባቸውና በልግ አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ የግብርና ግብአት እንዲያገኙ በማድረግ እገዛና ክትትሉ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው። በቀጣዩ የመኸር የግብርና ሥራም የመኸር ግብርና ሥራ ለሚያከናውኑት በተመሳሳይ ቅድሚያ በመስጠት ድጋፉ ይጠናከራል። በአካባቢዎቹ የመስኖ አውታር የወደመባቸውን መልሶ የማቋቋም ሥራ በማከናወንም የግብርና ሥራውን የማስቀጠል ሥራ ይሠራል።
እንደአገር የመኸር፣ የመስኖና የበልግ እያለ የግብርና ሥራው ተጠናክሯል። በዚህ ውስጥ መዘንጋት የሌለበት በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ሥራ ማከናወን ነው። በዚህ ረገድ ስላለው እንቅስቃሴም ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ በባለሙያ የታገዘ የእርሻ ክትትል ሥራ ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ያለውን ክፍተትና ጠንካራ ጎን የመከታተል ሥራ በመስራት ጠንካራው ተግባር እንዲጎለብት፣ ክፍተቱ ደግሞ እንዲታረም ይደረጋል። ጎን ለጎንም ለመኸሩ የግብርና ሥራ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ይከናወናሉ።
የመኸሩ የግብርና ሥራ እንደተጠናቀቀ የተጀመረው የበጋ የመስኖ ልማት፣ አሁን ደግሞ የበልጉ ወቅት ተደምሮ እየተከናወነ ያለው የግብርና ሥራ አበረታች መሆኑን ከዳይሬክተሩ ጋር በነበረን ቆይታ ለመገንዘብ ችለናል። በበጋው የመስኖ ልማት የተዘራው ሰብል በተለይም የስንዴ ሰብል አጨዳም በመጀመሩ እንደአገር ያለው የሰብል ልማት ሥራ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግምገማዎች ያሳያሉ።
እንደአገር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እህል እራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት የሚቻለው ተፈጥሮ የለገሰችውን ፀጋ ከመጠቀም ጎን ለጎን አጋዥ የሆኑ ነገሮችንም በመጠቀም ከአምራቹ፣ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ደግሞ ከዘርፉ አስፈጻሚ የሚጠበቁ ተግባራት በመሆናቸው ለአገራዊ የልማት ዕድገት ሁሉም የየራሱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014