በየአካባቢው የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቂምና በቀልን አራግፎ እርቅና ሰላምን የሚያወርድበት የየራሱ ቱባ ባህላዊ እሴት አለው። ኦሮሞው፣ አማራው፣ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ትግሬው፣ ሲዳማው፣ ጋሞው፣ ጋምቤላው ወዘተ እርስ በእርሱና ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በሚፈጥራቸው ጊዜያዊ ግጭቶች ባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ሥርዓቶችን እያከናወነ አብሮነቱን ሲያስቀጥል ኖሯል። አሁንም እያስቀጠለ ነው።
ኢትዮጵያ ስለዴሞክራሲ፣ ስለመልካም አስተዳደር፣ ስለእርቅና ሰላም ከየትኛውም አገር ሳትበደር ጥቅም ላይ ልታውላቸው የሚገቡ ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ማግኘት የምትችልባቸው ባህላዊ እሴቶች አሏት። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የጋሞ አባቶች የሽምግልና ሥርዓት /ዱቡሻ/ ነው።
በጋሞ ምድር ጠብና አለማግባባት፤ ቂምና ቁርሾ የሚወገዱባቸው ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች አሉ። የጋሞ ብሄረሰቦች ችግሮችን በባህላዊ መንገድ የመፍታት የቆየ ልምዳቸውን ጥቅም ላይ እያዋሉ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን አጠናክረው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ልጆቻቸው ከማህበረሰቡ እሴቶች እንዳያፈነግጡ በአባቶች ምክርና ተግሳጽ ተኮትኩተው ስለሚያድጉ ለባህላዊ እሴቶች ተገዢዎች ናቸው፤ ታላላቆቻቸውንና አባቶቻቸውን ያከብራሉ፤ የሽማግሌዎችን ቃል ያደምጣሉ።
በጋሞ ምድር ማህበራዊ ግጭቶች በ‹‹ዱቡሻ›› እየታከሙ አፋጣኝ ፈውስ እንዲያገኙ ስለሚደረግ ለጸብ የተመዘዙ ሰይፎች ወደ አፎታቸው ለመግባት አይዘገዩም። እሳት በጭብጥ ለምለም ሳር ይጠፋል። የበደለና የማህበረሰቡን ወግና ሥርዓት የጣሰ በሽማግሌዎች ይወቀሳል። የተበደለ ይካሳል። አሻፈረኝ ብሎ ከማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች ያፈነገጠም ይገለላል።
የጋሞ ማህብረሰብ ለማህበራዊ እሴቶቹ ያለውን ታማኝነት በተግባር ያሳየባቸውን አጋጣሚዎች ብናስታውስ፤ ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም በቡራዩ ከተማ በጋሞ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተወሰኑ ወጣቶች በቂም ተነሳስተው በአርባምንጭ ከተማ በሌሎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ በተነሱ ጊዜ የሀገር ሽማግሌዎች እንደ ባህላቸው በእጃቸው እርጥብ ሳር ጨብጠው እየተማጸኑ ማስቆሟቸው የሚረሳ አይደለም።
ጋሞዎች ሁልጊዜም ከአምባጓሮ ይልቅ ችግሮችን በንግግርና በውይይት የመፍታት ልምድ ያላቸው መሆኑን የማህበረሰቡ ነዋሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ።
በዛሬው የሀገርኛ አምዳችን ‹‹መተዳደሪያ የእርሻ መሬታችሁ ለልማት ስለሚፈለግ እንድትለቁ›› በመባላቸው ምክንያት ቅሬታ የገባቸው የአርባ ምንጭ አካባቢ አርሶ አደሮችን አቤቱታ ለፌዴራል መንግሥት ለማሰማት አዲስ አበባ ከመጡ የጋሞ አባቶች ጋር ቆይታ አድርገናል። ትኩረታችን ይዘው ስለመጡት አቤቱታ ሳይሆን ችግሮችን በሀገር ወግና ባህል መሰረት ለመፍታት በሚያደርጉት ጥረት ላይ ነውና በዚሁ ዙሪያ ከእነሱ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ሽማግሌዎቹ በአካባቢው መስተዳድርና በአርሶ አደር ልጆች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ መጥፎ ሁኔታ እንዳያመራ በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመምከር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አስበው የመጡ ናቸው። የጋሞ አባቶች ሁልጊዜ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚያስገድዳቸው ባህላዊ እሴታቸው ነው። አሁን ኢትዮጵያ አገራዊ ምክክርና መግባባት ለማደረግ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ሰዓት ከጋሞ አባቶች ምን ተሞክሮ ልትወስድ እንደሚገባት ጽሁፉን ካነበብን በኋላ የምናገኘው ቁም ነገር ይኖራል።
አቶ ካዎ ሙሉጌታ ከጋሞ አባቶቸ አንዱ ናቸው። በተለያዩ ሽምግልናዎች ላይ ተሳትፈው በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን ፈትተዋል። በአንድ ወቅት በቡራዩ ከተማ በሚኖሩ የጋሞ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች የበቀል ጥቃት ለመፈጸም ሲሞክሩ እንደማህበረሰቡ ባህል እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው የወጣቶቹን ቁጣ ካቀዘቀዙት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ናቸው። ዛሬም ለሽምግልና አዲስ አበባ መጥተው አግኝተናቸዋል።
የጋሞ ማህበረሰብ እና ሽማግሌዎቻቸው ሰምና ወርቅ ናቸው፤ መደማመጥና መከባበር የማህበረሰቡ መገለጫ ነው ይላሉ። በተለይም ወጣቶች ለሽማግሌዎች ቃልና ለባህላዊ እሴታቸው ታማኝ ናቸው። በሽማግሌዎች ምክርና በማህበረሰቡ ወግና ሥርዓት ተኮትኩተው ስለሚያድጉ ከባህላዊው ወግና ሥርዓት አያፈነግጡም። ስለሆነም ለጥፋት ሊዘረጉ የሚሞክሩ የጋሞ ማህበረሰብ እጆች በሽማግሌዎች ተግሳጽ በፍጥነት ይሰበሰባሉ ይላሉ አቶ ካዎ።
ይህን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምሳሌ የሆነ ገድል የፈጸሙ የጋሞ አባቶችም በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም የደቡብ ዞኖች እየተገኙ ልምዳቸውን አካፍለዋል። አቶ ካዎም የጋሞ አባቶችን በመወከል በተለያዩ ክልሎች እየተጋበዙ ስለጋሞ አባቶች ልምድና ተሞክሮ አካፍለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት የጋሞ ብሄረሰብ የራሱ ባህልና ማንነት አለው ። ሰው ወዳድና አቃፊ ነው። እርስ በእርስም ይሁን ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ግጭቶች ሲፈጠሩ ጸብ የሚያበርድባቸው ባህላዊ ሥርዓቶች አሉት። በብሄረሰቡ ዘንድ እርጥብ ሳር፣ ጋሻና ጦር ትርጉም አላቸው። ሰዎች ሲጣሉ ሽማግሌዎች እርጥብ ሳር ይዘው መሃል ይገባሉ፤ ጸቡ ደም የፈሰሰበት ወይም ህይወት የጠፋበት ከሆነም ጋሻና ጦር ይዘው በመንበርከክ ጸቡ እንዲቆምና ደም እንዳይፈስ ይማጸናሉ። እናቶችም ተንበርክከው ጡታቸውን በማውጣት በጠባችሁት ጡት እያሉ ጸብ እንዲበርድ ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት ማንም ሰው ለጸብ መጋበዝ የለበትም። ሁሉም በያለበት ይቆማል።
በድንበር ምክንያት በብሄረሰብና በጎሳዎች መካከል ቡድናዊ ግጭት ሲፈጠር /ኦገትሳ/ የሚባል መልእክተኛ ይላካል። ኦገትሳው /መልእክተኛው/ ህብረተሰቡን ያገለግላል ተብሎ ከሚታመን ቤተሰብ የሚመረጥ ነው። ግጭት ከመከሰቱ በፊት ሁኔታው በውይይት እንዲፈታ በዳይና ተበዳዮች ችግሩን እንዲፈቱ ያቀራርባል። ጉዳዩን የሚመለከቱ ሽማግሌዎች ከዚህም ከዚያም ወገን ተውጣጥተው ይሰየማሉ። ሽማግሌዎች በባህሉ መሰረት የበዳይና የተበዳይን ሀሳቦች አዳምጠው ተገቢውን ፍርድ ይሰጣሉ። የተበደለ ይካሳል የበደለም ይወቀሳል ወይም ይቀጣል።
በግጭቱ ወቅት የሰው ህይወት ቢጠፋ እንኳ እርቅ ከተፈጸመ በኋላ ጉዳዩ ዳግም አይነሳም። ሰዎች ያለፈውን በደል እረስተው በሰላም እንዲኖሩ ይደረጋል። የማህበረሰቡን ደንብና ሥርዓት መተላለፍና የሽማግሌዎችን ሀሳብ አለመቀበል በትውልድ ላይ የሚያስከትለው ርግማንና ቁጣ እንዳለ ስለሚታመን ሁሉም ለሥርዓቱ ይገዛል። ከሽማግሌ ዳኝነት ወጥቶ በራሱ ስልጣን ርምጃ ሊወስድ የሚነሳ ሰው ቢኖር እንኳ የራሱ የቅርብ ዘመዶች በሽማግሌ ርግማን ዘራችንን ታስጨርሳለህ በሚል ሀሳቡን አይቀበሉትም። ከዚህም ባሻገር ከአካባቢው ማህበረሰብ ውግዘት ስለሚደረስበት ይገለላል ይላሉ እንግዶቻችን።
ባለፈው በቡራዩ የጋሞ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመበቀል የተደረገውን ሙከራ ማስቆም የተቻለውም ወጣቱ የአባቶቹን ምክርና ተግሳጽ ስለሚሰማና የሥርዓቱ ተገዢ ስለሆነ ነው።
የጋሞ ማህበረሰብ ጥብቅ ባህል እንዳለው የሚናገሩት አቶ ካዎ፤ ለእርቅና ለሰላም የተዘጋጀ ሥነልቦና የገነባ ነው ይላሉ። እርስ በእርስ በመገፋፋትና በመጠላላት ሀገር ሊያድግ አይችልም፤ ኢትዮጵያ ማደግ የምትችለው ልጆች የአባቶቻቸውን ቃል እየሰሙ ከጥፋት መንገድ ሲታቀቡና ሰላም በማስፈን ሰርተው መኖር ሲችሉ ነው።
ባህላዊ እሴቶቻችን የሀገርን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር ከዩኒቨርሲቲዎች ያልተናነሰ ትውልድን የመገንባት አቅም አላቸው። የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ እንደሚባለው ወጣቱ ሀገሩን ከጠላት ለመከላከል ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምት ሁሉ የአባቶቹን ባህላዊ እሴቶችን በማክበርም ሰላሙን አስፍኖ ሀገሩን ከውድቀት መታደግ ይኖርበታል ብለዋል።
የጋሞ አካባቢ ወጣቶች ለባህላቸው ተገዢ መሆናቸው የአካባቢው ሰላም እንዳይደፈርስ አድርጓል፤ ሌሎችም ከዚህ ተምረው በየአካባቢያቸው የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር ቢቀበሉ የኢትዮጵያን ሰላም ማረጋገጥ ይችላሉ። ሰላም ከሌለ አርሶ መብላት፣ አግብቶ መውለድ፣ መማርና መበልጸግ አይኖርም ያሉት አቶ ካዎ፤ እንደ ጋሞ ህዝብ በፍቅር፣ በሰላምና በመከባበር የሚኖር ማህበረሰብ መገንባት ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በየብሄረሰቡ ጠቃሚ እሴቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ካዎ፤ ሁሉም ተሞክሮዎቻቸውን ቢለዋወጡ ለሀገር ሰላምና ግንባታ ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል። አቶ ካዎ ከሌሎች የጋሞ አባቶች ጋር በመሆን ቡራዩ ድረስ በመሄድ እርቅና ሰላም እንዲወርድ አድርገዋል፤ በአማራ ክልል ጎጃምና ጎንደር በመሄድ ልምድና ተሞክሯቸውን አስተዋውቀዋል። በጉጂና ቡርጂ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር ቦታው ድረስ በመሄድ አስታርቀዋል። ከየአካባቢው የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በጋሞ ባህልና ሥርዓት ላይ ኮንፈረንስ አካሂደው ጠቃሚ ልምዶችን አግኝተዋል። የሀገር ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶችም የጋሞን ማህበረሰብ የመከባበር ባህል ቀረብ ብለው ቢጎበኙ በርካታ ትምህርቶችን ሊያገኙበት ይችላሉ ብለዋል።
በጋሞ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች እርስ በእርሳቸው ጸያፍ ስድቦችን ሲሰዳደቡ ቢሰሙ የአምስት መቶ ብር (500) ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል። መሰዳደብ ባህላችን እንዳልሆነ እንነግራቸዋለን። ወጣቶች በሥነምግባር እንዲታነጹ ሁሉም ቦታ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱ የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ ጥቅም አለው።
አቶ ቦኖ ቦሻ የአርሶ አደሮችን ቅሬታ ለማሰማት ለሚመከተው አካል ለማሳወቅ የመጡ ሌላው የጋሞ አባት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ቅሬታን በንግግር መፍታት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላቸው ነው። በጋሞ ባህል የወላጆቹንና የሽማግሌዎችን ምክር የማይቀበል ልጅ እንደልጅ አይታይም።
ወጣቶች ወደ ጥፋት እንዳይገቡ የሚያደርጋቸው የሽማግሌዎችን ቃል ስለሚሰሙ ነው። ማህበረሰቡ በ‹‹ዱቡሻ›› ሥርዓት እየተገራ ስለሚኖር መልካም እንጂ መጥፎ ነገርን ለማድረግ አይነሳሳም። “የጋሞ ባህል ከወንጌል ቃል ጋር ይቀራረባል” የሚሉት አቶ ቦኖ፤ ሰዎች ቂም ይዘው እንዲያድሩ አይፈለግም፤ የተኮራረፉ ሰዎች ካሉም ውለው ሳያድሩ እንዲታረቁ ይደረጋል ይላሉ።
አባቶች ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያስተምራሉ፤ ይመክራሉ። ልጆችን የሚያስተምሩት ባህልን ከወንጌል ቃል ጋር እያስተሳሰሩ ስለሆነ ክፉ ነገር ለመሥራት የሚነሳሳ ሰው አይኖርም።
የጋሞ አባቶች በልጆቻቻው ኩራት የሚሰማቸው ናቸው፤ ወጣቶች ከቃላቸው አይወጡም፤ የሚሏቸውን ሰምተው ይተገብራሉ። ወጣቶች የሽማግሌዎችን ቃል በመስማታቸው እራሳቸውን ከጥፋት ታድገው ለአባቶቻቸው ሞገስ ሆነዋቸዋል። በተለያዩ መድረኮች የጋሞ አባቶች መልካም ሥራ እየተባለ ለመነገር የበቃው ማህበረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎችን ቃል ስላከበረ ነው።
ሁሉም ብሄረሰብ በየአካባቢው ጥሩ ጥሩ ባህሎችና ባህሉን የሚያስፈጽሙ የሀገር ሽማግሌዎች አሉት። መኖሩ ብቻውን ትርጉም ላይኖረው ይችላል፤ ዋናው ቁም ነገር እሴቱን እንደ አስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ማዋል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስለጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች ገድል በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያነሱ ይሰማል። የጋሞ አባቶች ሊወደሱ የቻሉት በትውልድና በባህል መካከል ክፍተት እንዳይፈጠር አስቀድመው በመሥራታቸው ምክንያት የሚታዘዛቸው ወጣት ስላገኙ ነው።
ሁሉም ማህበረሰብ በየአካባቢው በአዲሱ ትውልድና በባህል መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ወጣቱ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቱን እንዲጠብቅ ማድረግ ይኖርበታል። ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
መንግሥትም እንዲህ አይነት እሴቶች እንዲጎለብቱ እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል። እንዲህ አይነቶቹ እሴቶቻችን የታሰበውን ሀገራዊ ምክክርና መግባባት እውን ለማድረግ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው። ወደ ሰላም ጎዳና የሚያመጡንን ባህሎቻችንን ማጎልበትና በሀገራዊ ምክክሩና ማግባባቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ያስፈልጋል።
‹‹ዱቡሻ›› የጋሞ ብሄረሰብ የእርቅና የሰላም ባህልም ሊካሄድ በታሰበው አገራዊ የምክክርና የመግባባት መድረክ ላይ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት የጋሞ አባቶችን ወደ መድረኩ መጋበዝ ያስፈልጋል። የጋሞ ባህልን የጋሞ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያውያን ቢጠቀሙበት ሰላምና ፍቅርን ያተርፉበታል እንጂ አይጎዱበትም።
ቱባው ባህላዊ እሴቶቻችን የሆነው ዱቡሻ ለዘለአለምይኑር። አሜን!!!
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2014 ዓ.ም