ግጥም ስሜትን ልዩ በሆነ መልክ ያመላክታል፤ የውስጥ ሀሳብን በተለየ መልክ ይገልፃል። ማህበረሰብን ለማነፅ ሰበብ ይሆናል ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይን ለማሄስ ብሎም ለማረቅ ግጥም ያለው ቦታ ከፍተኛ ነው። እንዲህ ቢሆን አልያም እንደዚህ መሆን አልነበረበትም ወይም ደግሞ እየሆነ ነው በተራ ቋንቋ ከመግጠም ባለፈ ጉዳዩ በግጥም ተዋዝቶ ሲነገር ድምፀቱ ይጎላል። ሀሳብን ልዩ በሆነ መልኩ አስውቦ በተመረጡና ቁጥብ ቃላት በተመጠነ ቀለም ተሳክቶና ዜማ እንዲላበስ ተሰናስሎ ይቀርባል።
ሀሳብን በጎላ መልኩ ከሚገልፁ የግጥም መፅሀፍት ውስጥ አንዱ መርጠን ከመሀሉ ደግሞ የሀሳብ ግዝፈቱ የጎላውን ልናስመለክታችሁ ስለወደድን ነው፤ ግጥምን መግለጥ የተያያዝነው። የዛሬ ቅኝታችን በአሌክስ አብረሀም አንፈርስም አንታደስም የግጥም መድብል ውስጥ ያገኘነው አንድ ግጥም በሀሳብ ትልቀቱ ከፍ ያለ ሆኖ አግኝተን መርጠነዋል።
በተባ ብዕሩ በአዲስ የአተራረክና ታሪክ ነገራ ስልት ብቅ ብሎ ብዕርህ አይንጠፍ ያልነው ወጣቱ ደራሲ አሌክስ አብረሀ በ2009 በታተመው “አንፈርስም አንታደስም” በተሰኘ የግጥም መድበሉ ውስጥ ያካተተውን “እግዜርን እሰሩት” የተሰኘ ግጥሙን በዚህ ፅሁፌ ውስጥ በራሴ አተያይ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ።
አሌክስ በዚህ ግጥሙ፡- ማህበረሰባዊ ልማድ፣ ፖለቲካዊ ሽሙጥ በአጠቃላይ የማህበረሰባችን እና የመንግስት አስተዳደር ባህሪና አጠቃላይ ገፅታ አጉልቶ በሚያሳዩ ልዩ አገላለፅ፣የቃላት አጠቃቀም ማህበራዊ ሂስና ትችት ጥልቅ በሆነ እይታ ይዘረዝራል።
አሌክስ በ “እግዜርን እሰሩት” በተሰኘው ግጥሙ በተመጠኑ ቃላት ገላጭ በሆኑ ውብ ስደራ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ዘይቤዎች ይጠበባል።እኔም የአሌክስ አብረሀምን ምልከታ የዚህ ወቅት አጠቃላይ ማህበራዊ ገፅታችን በትክክል ያሳያልና እንማርበትም በስነፅሁፉም እንዝናናበት ብዬ በዚህ መልክ እሱ ያሳየኝን ወደማሳየት ገባሁ።
አሌክስ አብረሀም “እግዜርን እሰሩት” በተሰኘ ግጥሙ ማህበረሰባዊ የበዙ ጉዳዮች በተለይም ለየት ያለ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በራሱ መነፅር አጉልቶ ለማሳየት ይሞክሯል። በግጥሙ የተገለፁት በተለይም ፖለቲካዊ ባህሪያትን በሚዘረዝር ምልከታው የአምባገነንነት ጥጉ ምንነት የእብሪተኝነት ልኬት መገለጫው የተበላሸ ስርዓትና አስተዳደር ባህሪው አቅም ያላቸው ቃላት በመጠቀም ይገልፃል።
ግጥሙ እጅግ በጣም ረጅምና እያንዳንዱ የግጥሙ ርዕሰ ጉዳይ ክፍሎች የተለያዩ ትልልቅ ጉዳዮችን አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ ግጥሙን አንድ ላይ ከመተንተን ይልቅ ሀሳቡ በግጥሙ መሀል እየገባው ለመግለፅ እሞክራለሁ። አንባቢው ይህንን ፅሁፌን ሲያነብ ግጥሙ አንድ ወጥ መሆኑን እንዲገነዘብና እኔ ሀሳቡን በገባኝ ልክ ለማብራራት ብዬ መሀሉ እየገባሁ እንደቆራረጥከት እንዲያውቅልኝ መግለፅ እወዳለሁ።
“እግዜርን እሰሩት” የተሰኘው ግጥም ፖለቲካዊ ይዘት የተላበሰ ሲሆን ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን በማንሳት የአስተዳደር ስርዓቶች ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ የአምባገነንነት ጥጉ የእብሪተኝነት ልኬት፣ የተበላሸ ስርዓትና አስተዳደር ባህሪው እምቅ ቃላት በመጠቀም ለመግለፅ ይሞክራል።
ስለ ግጥሙ ርዕሱ
የግጥሙ ርዕስ ገና ከጅምሩ ብዙ ስለ ግጥሙ ይነግራል። የእግዜር ሀያልነት ከማንም የተሰወረ አይደለም የአምላክ አዛዥነት ከፀሀፊውም ሆነ ከአንባቢው ፈጽሞ የራቀ አይደለም ግን እንዲህ ብሎ ጀመረ “እግዜርን እሰሩት” ብሎ የሚያዝ የትኛው ሀያል አካል ነው? አምላክን እሰሩት ብሎ የሚል ከየት የተገኘ የአምላክ የበላይነትን የናቀ ወይም ካህዲ ሊሆን ይችላል። ምን ሊሆን ይችላል? አምላክን እሰሩት ብሎ የሚያዝ ደፋር ብሎ ማንነቱን ለመረዳት መሞከር ይገደዳል። የግጥሙ ርዕስ ሳቢና ለማንበብ የሚጋብዝ ነውና አንባቢው ገና ከጅምሩ የግጥሙን ርዕስ አይቶ ግጥሙን ለማንበብ እራሱን ይጋብዛል።
ስለዚህ ለግጥም “ርዕስ” መረጣ ወሳኝ መሆኑን የተገነዘበ ይመስላል ደራሲው። ርዕስ ሲመረጥ አንባቢ ሊጋብዝ የሚችል ሊያመራምርና መልስ ለመፈለግ የሚጋብዝ መሆን ይገባዋልና ይህ ርዕሱን የተዋጣለት
አድርጎታል። እኔም በግጥሙ ውስጥ ያለው እግዜርን እሰሩት ያለው ደፋር ማንነቱን ለማረጋገጥ ግጥሙን ለመመርመር ገባሁ። ይሄው…
እግዜርን እሰሩት
ከስሩ ታድሞ…ትውልድ ይማከራል..
“እና ምፅ” እያለ፣
ቁረጡት ያን ዝግባ- ምናባቱ ቆርጦት…
ለህዝብ ጥላ ጣለ!?
ወንበር ሲገረሰስ-ላገር ጣይ ሊያወጣ…
ጥላው ስር ተቀምጦ… ህዝብ ከመከረ፤
ዝግባ አሸባሪ ነው..በግንደ ልቦናው
ሳጥናዔል ያደረ!
……..“
ዝግባ የታላቅነት ምልክት ነው። የአጋር አድባር የሂነ ሰውን ሽምግልና ይወከላል። ግጥሙ በጥሬ ትርጉሙ ሰዎች በዝግባ ጥላ ስር ሆነው መክረው አመፅ ያስነሳሉና የሚጠለሉበት ባለ ጥላው ዝግባ ይቆረጥ የሚል ይመስላል። ግን ፈፅሞ ትርጓሜው የተለየ ነው። በሀገሩ ላይ ያሉ እድሜ ጠገቦች ታላላቆች የሀገር አድባሮች። መልካሙን በመምከር እኩዩን በመኮነን በማረቅ ከዕድሜ ያገኙትን ለሌላ በመልካምነት የሚያወርሱ ታላላቅ ሰዎችን ይወክላል። እነዚያ ሰዎች ሸፍጥን በቀላሉ ይለያሉ፤ተንኮልን በእድሜያቸው ያወቁታልና ህዝባቸው እንዳይጎዳ ይህ መልካም የሆነ ነው ብለው ይነግራሉ። ያን የማይወድ ደግሞ እነዚያ የአገር አድባሮች መጥፋታቸውን እጅጉን ይገልጹታል። በግጥሙም የተጠቀሰው ሚስጥራዊ ቅኔ ይህንን ያመላክታል።
“………
እሰሩት!!
ይጨፍጨፍ ባህር ዛፍ
ምን ቅብጥ አድርጎት
ማገዶ እየሆነ እንጀራ አበሰለ፣
ስንቴ እየገደልነው የሞተ ግንዱ ላይ
ሌላ ነፍስ ፀደቀ..እልፍ ሆኖ በቀለ?
እንጀራ በወጡን በልቶ እየጠገበ
“ስራ ፈት ሰልፈኛ” መንገድ ካጣበበ
እዚህ ስነኝ ላይ የላቀ ምልከታ ማህበራዊ እይታ የተለየ ሽሙጥ በእኛ በእያንዳንዳችን በዛሬዎቹ ላይ ተነስቷል። ለአገር ዋልታ ለወገን ጥላ የሆኑ መልካም ነገሮቻችን ሁሉ በእንቢታ መገፍተራችን ለእኛ የሚበጁ ለህዝብ የሚጠቅሙ እሴቶቻችን ማህበረሰባዊ እውቀትና ልማዶችን ሁሉ መቃረናችን የሚበጁንን አይበጁንም ብለን መኮነናችን ያነሳል።
“… ሽብር ነው ባህር ዛፍ ፅድና ግራሩ
ከየበቀሉበት እየተለቀሙ
የዛፍ ዘር በሙሉ ከ’ሳት ይወርወሩ
ስሩ እየተማሰ ቅጠላ ቅጠሉ እየተበጠሰ
ለሕዝብ ጤና ሰጠ፤
በማህበር ስናብድ ጤነኛ በቅሎብን
መንጋው ተናወጠ
ከዚህ በላይ ሽብር ከዚህ በላይ ረብሻ፣
አላፊ አግዳሚውን..ስለምን ይንከሰው…’
እውነት’ እንደውሻ…”
በየጉዳዮቻችን ላይ በማህበር በደቦና በአንድነት መላ ቅጡ እንደጠፋብን ሁሉ የምነሆነውን በእብደት ስሎ የእውነት ተግባርና ሁኔታችን ሁሉ የእብድ መሆኑ ያመላክታል። እንደግለሰብ ትክክለኛ መስመርና አቋም መያዝ ሲያስወቅስ፤ በጎ ነገር ላይ መቆማችን በህብረት ስያስወግዘን ተመለከተና በጋራ ማበዳችን በጎ
እንደሆነ አድርጎ በአሽሙር ያወግዘናል።
ማን አብዶ ማን ሊቀር… አናብድም ”ምትሉ?
አርፋችሁ እበዱ “ሽብርተኞች” ሁሉ!
መንጥሩት ቅጠሉ ከተቀበረበት ስራስር ይመዘዝ፣
“መድሀኒት ነኝ” የሚል ይወገር
ይሰቀል በደቦ ይወገዝ!
……”
በእያንዳንዱ አገራዊና ማህበረሰባዊ ጉዳይ ላይ የምንሄድበት የምናይበትና የምንቆምበት ጉዳይ ሁሉ መስተካከል እንዳለበት ለእኛ በጎ የተባለ ለመኖራችን ወሳኝ የሆነ ለህልውናችን እጅጉን አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ መተዋችን በአንድነት እብደት ላይ መገኘታችን ያመላክታል። በእርግጥ ዛሬ እርጋታ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን። በእርግጥም አሌክስ አብረሀም ያየበት መነፅሩ እኛን በትክክል ያየበት መሆኑ ማመሳከሪያው ዛሬ ላይ የምንሆነውና የሆነው ትልቅ ማስረጃ ነው። ግጥሙ ቀጠለ…
“የታባቱ!
እሰሩት በሬውን! እኛ ሳንፈቅድለት
ምድር እያረሰ፣
ሥጋውን ጀብቶ …ጥሬውን ከብስል…
ህዝብ እያጋበሰ
ህዝበ በላተኛ…በየ በረንዳው ላይ …
በሚስለው ቢላ፣
ይበላው ያጣ ቀን እኛን እንዳይበላ
ራብን ይጥገባት…ከዳቦ በስተቀር…
እንዳያስብ ሌላ
ሳሩን እጨዱና በሬውን እሰሩት፣
መደለብ ሽብር ነው የደለበን ቀንዳም
ጮማውን ትታችሁ…እርሻውን ትታችሁ..ውጊያውን አግንኑት!”
እርግጥ ለኛ የሚገባው ስር ነቀል ለውጥ፤ አስተማማኝ በራሳችን የሚያቆመን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሆኖ ሳለ እንደማህበረሰብ ዋንኛ ፍላጎታችን የሚያስፈልገንን አርቆ የማያስፈልገን ላይ ትኩረት ማድረጋችን በዚህ ስንኝ ማሳየቱን ቀጥሏል። ማህበረሰባዊ ዝንፈታችን የማይበጀንን መስመርና ሂደት ላይ መሆናችንን ማሳየቱን ግጥሙ አላቆመም። ለእኛ የተሻለው የቱ እንደነበር ነገር ግን ምርጫችን ምን እንደሆነ ያሣየናል። በእርግጥ ግጥሙ የታተመው ስንኙ የተቋጠረው ዛሬ ባይሆንም ለአሌክስ ግን ትናንት ጥበብ አሻግሮ ዛሬን እንዲያይ አድርጎት ነበርና ያኔ ያየው ዛሬ ከቆምንበት ጋር ገጠመ። እናም በዚህ ግጥም የዛሬ ሁኔታችንን ተመለከትን።
“እሰሩት!!
ንፋሱን እሰሩት ማንን አስፈቅዶ
እንዳሻው ነፈሰ፣
ህዝቡስ ካለ ፍቃድ ለምን ተነፈሰ?
እሰሩት አየሩ መታፈን ነው ደጉ፣
የታፈነ ትውልድ… ጩኸት አያበዛም…በየጥጋጥጉ!
“ሺ ዓመት ንገስ” የሚል ምድሩ ይፈንጭበት፣
“ለምን” ባዩ መቶ…
”እንዴት”ባዩ ‘በጥባጭ’
ይቆምበት ይጣ… ‘ቅድስት’ ምድራችን
እሳት ይሁንበት!!
ሰቅዞ ይዞናል…የራሳችን ድግስ…
የራሳችን ተስካር
መድረሻህን ፈልግ -’ሰላማዊ ስካር’
እዚህ ስንኝ ላይ በወቅቱ የነበረውን አገራዊ ገፅታችን በጊዜው የነበረውን ፖለቲካዊ ገጽታ ቅልብጭ አድርጎ ያሳያል። በአገሪቱ በነበረው ፖለቲካዊ ስርዓት መበደልና ጭቆና ያንገሸገሻቸው ስርዓቱን ሲቃወሙ ይደርስባቸው የነበረው እስራት እንዲሁም ተገቢ ያል ሆነ የመብት መገፋት አጉልቶ ያሳያል።
እሰሩት!
እ…ዛ ላይ…
ድንገት ሳይደፋብን የአብዮት ዝናብ…
የብጥብጥ መና፣
ከሰማይ ሰማይ…ተገፎ ይታጎር…
ይቀፍደድ ደመና
በዚች ‘ቅድስት’ አገር እንኳን
ያመፅ ጥሪ እንዳይኖር ትንታ
ከስር ያመለጠች የዝናብ ዘለላ-የውሀ ኮለልታ፣
እንጦሮጦስ ትውረድ በፍኝ ተጠራቅማ…
በፎሌ ተሞልታ
ድንጋይ ትበሳለች…ላይን አትሞላም
ብለን የናቅናት ጠብታ!
ትታሰር!!
ግጥሙ የወጣበት እና ከዚያ በፊት የነበረው አገራዊ ሁኔታ ያሳያል። የወቅቱን ስርዓት (ኢህአዴግ) ይቃወማል አልያም ስርዓቱን ይፈታተናል ያለው ሁሉ በየ ምክንያቱ ያስር ነበርና ደመናውም ሳር ቅጠሉ ሁሉ ይታሰር ምክንያቱም በጣም ተቃዋሚ ነውና ብሎ በሽሙጥ የስርዓቱን ስራ ይኮንናል።ታቃዋሚ የተባለ ሁሉ ይደርስበት የነበረው መከራ፤ አመፅና የህዝብ ተቃውሞ እንዳይነሳ ለማድረግ ይደረጉ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ይዘረዝራል።
…….
ሰማይ ባዶ ይሁን
ከ’ኛ እግዜር በቀር ማንም እንዳይረግጠው
‘ፀሀይ የት ደረሰች ጨረቃ የት ገባች’
የሚል ጠያቂ ነፍስ …መቼም እንዳይገልጠው!
ይከደን ሰማዩ- ጨለማ ይዋጠው!
በጨለማ ሰማይ በድቅድቁ ህዋ የተጠራቀመ፣
ይታሰር ኮከቡ አንድ ባንድ በነቂስ እየተለቀመ!
መሬቱም ይታረስ አዳሜ ሚረግጠው፣
ሽብርተኛ ደም ነው ሲጠጣ የኖረው፣
አፈሩን ብትገልጠው
ይመስልሀል እንጂ የስጋጃ ምንጣፍ
ሸፍኖት ሳር ቅጠል ሸፍኖት አበባ፣
ነገ ቀን ሲከዳ በቁምህ የሚውጥ
ክፉ መቃብር ነው ካፈር የሚያስገባ
አፈሩ አፍ አውጥቶ አይናገርም፣ ምድሩ ልሳን አበጅቶ አያወራም፣ሰማዩ ሰው አይደለምና ምንም ቢሆን ተው አይልም እዚህ ላይ በተምሳሌታዊ ዘይቤ የሚጠቀሱት ሰዎች ናቸው ሰማይነትና መሬትነት ተላብሰው የሚተነፍሱና ምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች ናቸው። ነገር ግን ሳር ቅጠሉ ታዳኝ ነበርና አዳኙ ምንም እንደማይለይ በአንድነት ሁሉም ላይ ስቃይ እስርና ያመላክታል። ለተቃውሞና ለስርዓቱ ፈተና እንዳይሆን ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚሰራውን ተግባር በዘይቤ ይወርፋል።
እሰረው!!
እንደውም… ሰማዩ ይታረስ …
ተጠቅልሎ ይግባ እንደ ሰሌን ምንጣፍ፣
ቀና እንዳይል ህዝቡ-የነጻነት ምኞት-በላዩ እንዳፃፈ! ሰማይ ሸቤ ይውረድ…
እግዜር ለዙፋኑ ቦታ ሲቸግረው፣
ይወድቃል ከጃችን…በደረቅ እንጨት
ላይ ግራ ቀኝ ቸንክረው!
በቃ! ምድርን ከቀፈደድክ… እግዜርን ካሰርከው፣
ህዝብና ህዝቤን…”ኢትዮጵያ እጆችዋን”
እያልክ ስበከው
የታሰረች አገር…ወዳሰርነው አምላክ-እጇን ብትዘረጋም፣
ይህን ሁሉ ደክመን… ያቆምነው ጨለማ…በቀላሉ አይነጋም!!
……../… /……
እዚህ ላይ የማያደርጉትን ሀያል ተግባር የማይሟገቱትን ትልቁን ዙፋን አምላክነት በሰውኛ ልኬት ተለክቶ መታሰር የታወጀበት መሆኑ ሲታይ እንዴት ይባል ይሆናል። ነገር ግን ህልውናው ለሚጠራጠር እሱን ማሰር ይቀለዋልና ከሱ በላይ ነኝ ብሎ ለሚያስብ አልያም በአምላክነቱ ለማይቀበለው አምላክ ለሱ ምኑም ነውና የናከውን ትዕዛዙ ያልተገበርከውን ምንም አድርግ እንደማለት ።
በመጨረሻም መራር እውነት ነግሮ ዝንኙን ይቋጫል። በዚህ ሁሉ ተግባር ውስጥ ታልፎ በዚህ ሁሉ እኩይ ተግባር ውስጥ ተቆይቶ መልካም ነገር ላይ ለመድረስ እንደሚያስቸግር ነግሮ ያበቃል። በጎነት ካልቀረበ መሄጃውና አካሄዱ ካላማረ መድረሻው ይቸግራልና የወቅቱን ሁነት ከባድነት ዛሬ ላይ ተገልጦ እንደታየ ሁሉ በመጠቆም ምግባር ውስጥ የበለጠ መጥፎነት ጎልቶ ይወጣልና ተግባሩ ይቁም ካልሆነ ግን ይከፋል ብሎ አበቃ። እኔም አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014