የኢትዮጵያን እርሻ በዘላቂነትና በመዋቅራዊ መልክ መለወጥ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል። ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ፣ የኢትዮጵያን ግብርና እመርታ ውስጥ የሚያስገቡ የፖሊሲና የቴክኖሎጂ ለውጥ አምጪ ሃሳቦች በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ ጀምረዋል። ከእነዚህ መካከል የበጋ ስንዴ የመስኖ ልማት ይጠቀሳል። በዚህ ውስጥ የእርሻ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት ማዳረስም ትኩረት ይሻል። ከሕገ መንግሥቱ ጋርም በማይጋጭ መልኩ የመሬት የንብረት ባለቤትነትን ጥያቄ የመፍታት፣ የገጠር ብድር አገልግሎትንም ማስፋፋት ለዘርፉ ለውጥ ወሳኝ ከሆኑት መካከል መጥቀስ ይቻላል።
የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሥርዓቱ ዙሪያ በዓለም አቀፍ የተባበሩት መንግሥታት ያገለገሉትና አሁን የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍን በማማከር በማገልገል ላይ የሚገኙት ከዶክተር ጌታቸው ድሪባ ጋር በነበረን ቆይታ በተጠቀሱትና በተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት አድርገን የተነጋገርነውን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ወቅታዊ ሁኔታ
የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሥርዓት የቆየ፤ የስልጣኔ ምንጭ እንደነበረ መገንዘብ ያስፈልጋል። በዘመኑ አዝርዕቶች ተገኝተዋል። ከብቶች ተላምደዋል። የእርሻ መሳሪያዎች ተፈጥረዋል። የእርሻ ሥርዓቱ እስከዛሬ ድረስ ይዞ ያለው በዛን ዘመን የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ብቻ ነው።
ለተከታታይ ዘመናት ዕድገቶች እንዲታዩ፤ ውጤቶች እንዲኖሩ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ምርጥ ዘሮችን፣ ማዳበሪያን፣ የትራክተር እርሻን የማስተዋወቁ ሥራ በሰፊው በዘመቻ ደረጃ የተካሄደበት ጊዜ ነበረ። በተለያዩ መንግሥታትም ከፍተኛ ዕድገት እንዲመጣ ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን የተደረገው ጥረትና የደረስንባቸው ውጤቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ከደረሰበት የሕዝብ ዕድገት የምግብ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም አልሆነም።
እንደሚታወቀው ስንዴ፣ ሩዝና የምግብ ዝርያዎች ከወተት ተዋጽኦ ጀምሮ በአብዛኛው በከፍተኛ ዋጋ ወደ አገር እያስገባን ነው። ይህ ደግሞ ባለፉት 20፣ 30 እና 40 ዓመታት እያደገ መጥቶ ከፍተኛውን የአገርን የውጭ ምንዛሪ እየወሰደ ይገኛል። በጥቅሉ መመዘኛ የሚሆነው ዕድገት አለ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ እንዳላሳካ መመልከት ይቻላል።
ለዚህም ሁለት ነጥቦችን መመልከት አስፈላጊ ሲሆን ቀዳሚው አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚፈልጉ ሕዝቦች ቁጥር መጨመር ነው። በተለይ በከብት ማርባት የሚተዳደሩ አርብቶ አደሮች ከፍተኛ የምግብ ዋስትና መቃወስን በአንድ በኩል መመልከት እንችላለን። በሶማሌ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በቦረና አካባቢ በድርቅ ምክንያት የተከሰተውን መመልከት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ምግብ ነክ ነገሮችን ከውጭ ማስገባቷ ከሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ባሻገር የዓለም ፖለቲካ አሰላለፍ የዩክሬንና የራሺያ ጦርነት የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና በከፍተኛ ደረጃ እይታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ጦርነቱ የራቀ ቢሆንም የዓለም ሕዝብ ኒዩክሌር ቦንብ እንዳይፈጠር ቢያሳስበውም ለኢትዮጵያ ግን በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀን የምግብ ዋስትናው እንደኒዩክሌር ቦንብ ሆኖ እያሰጋ ነው።
ዩክሬንና ራሺያ በድምሩ በዓለም ንግድ ገበያ ያቀርቡት የነበረው የ25 በመቶ የዓለም ንግድ ድርሻ ሲገታ በዓለም ላይ የምግብ ዋጋ ንረቱ እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። መንግሥት በድጎማ ቢይዘውም በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ መናርም ከማጓጓዣ ሰንሰለቱ ጋር ስለሚያያዝ ከፍተኛ ችግር እንደሚያመጣ መመልከት ይቻላል። የማዳበሪያ ዋጋም ከእጥፍ በላይ እየናረ ይገኛል።
የዩክሬንና የራሺያ ግጭት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ብለን አቻችለን እንኖር የነበረውን በማዛባት ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ የመኖር ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና በተገለጹት ነጥቦች ያጠነጥናል።
የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር እንዴት ማለፍ ይቻላል?
አሁን የተፈጠሩ ችግሮች መፈታት አለባቸው። የኑሮ ግሽበቱ እና የዋጋ ንረቱ እያንዳንዱ ተመጋቢ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጫና ያሳድራል። ስለዚህ ፈጣን የአጭር ጊዜ መፍትሔ ያስፈልጋል። መንግሥት በዘመቻ መልክ አሁን እያደረገ ያለው የበጋ ስንዴ የመስኖ ልማትን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ ማምረቱ ጥሩ ነው።
ትግበራውን ከዘመቻ ሥራ ወደ ወትሮና ዘለቄታዊ ትግበራ ማዞር ያስፈልጋል። ተግባሩንም የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያን አካባቢዎች እንዲያካትት አድርጎ መቀጠል ያስፈልጋል። በአጭር ጊዜ ሲታሰብ አሁን የተያዘው የመስኖ እርሻ በተለይም በበጋ ማምረቱን የማስፋት፣ ኅብረተሰቡ ጋር የማድረስ፣ ከፍተኛ እገዛ ማድረግ ግድ ይላል።
በርካታ ዜጎች በምግብ እና በማኅበራዊ ደህንነት ርዳታ ውስጥ ናቸው። አሁን የዳቦ ጥያቄ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እያደገም እንደሚመጣ መታሰብ ይኖርበታል። በመሆኑም የማኅበራዊ ድጎማ ማድረግ ግድ ይላል። በተለይ የገቢ ደረጃቸው በአነስተኛና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላሉት በዳቦ ላይ የሚደረገው የዋጋ ጫና ሁሉን አቀፍ ማድረግ ባይቻልም በኑሮ ደረጃቸው ተመዝነው እገዛ የሚደረግበት መንገድ መታሰብ አለበት። መደበቅ የማንችልበት ዘመን መሆኑን የኢትዮጵያ መሪዎች፣ ገበሬው፣ ባለሃብቱ፣ ነጋዴው በጥሞና ማየት አለባቸው።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ምን መሠራት አለበት?
መንገድ የሚያሻግሩና የዘለቄታ ትልም የሚያመጡ የዘላቂ የልማት ግቦች ወይንም 2030 አጀንዳ ተብለው ኢትዮጵያም የገባችበት ቃል ኪዳን ላይ በርካታ ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያም የምግብ ሥርዓት ብላ ከተባበሩት መንግሥታትና ከሌሎችም አጋሮቿ ጋር በመተባበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ችግር ሊፈቱ ይችላሉ የተባሉ 22 የመፍትሔ ሃሳቦች ይዘው ቀርበዋል። እነዚህ የመፍትሔ ሃሳቦች ሰፋ ያሉ ቢሆኑም በዚህ ዓምድ ስር ስድስቱን መመልከት እንችላለን።
እነዚህ ጉዳዮች የኢትዮጵያን እርሻ በዘላቂነትና በመዋቅራዊ መልክ ሊለውጡ የሚችሉ፣ አሁንም ሆነ ለወደፊቱ ኢትዮጵያን እመርታ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ተብለው የሚታሰቡ የፖሊሲና የቴክኖሎጂ ለውጥ የሚያመጡ ሃሳቦች ናቸው። ሥራውም በግብርና እና በጤና ሚኒስቴር እየተመራ ይገኛል።
የመሬት የንብረት ባለቤትነት ጥያቄ እንዴት ይፈታ?
የመጀመሪያው ብዙ ወጪም የማያስወጣ ከሕገ መንግስቱ ጋርም በማይጋጭ መልኩ የመሬት የንብረት ባለቤትነትን ጥያቄ የመፍታት ጉዳይ ነው። ገጠሩንና ከተማውን ወጥ የሆነ የፖሊሲ ምንጭ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥቱም ይህንን ይፈቅዳል።
የመሬትን ሥርዓት የሚያስተዳድር እርስ በእርስ የሚናበብ ሁሉን ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያደርግ፣ ተዘዋውሮ የመኖር፣ ሃብት የማፍራት ጉዳይ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
የመሬት ጉዳይ ከ1967 ዓ.ም መሠረታዊ ለውጥ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ቢደረጉበትም የሕዝብ ዕድገቱና የግብርና ዘርፉ ፍላጎት ጋር ሊሄድ አልቻለም። በገጠር የሚገኘው ሕዝብ እየተዋለደና እየኖረ በከተማ ደረጃ የተወሰነ ፍልሰት ቢኖርም አሁንም በዛው እርሻ ላይ ይገኛል።
ይህ የመሬት መበጣጠስን በማስከተል የአንድ ሄክታር አንድ አስረኛ በሆነ መሬት ላይ ኑሮውን የሚመራው የቤተሰብ ብዛት አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ነው። 12 ሚሊዮን የሚሆኑ ገበሬዎች ደግሞ የሚተዳደሩት ከግማሽ ሄክታርና ከዛም በታች በሆነ መሬት ነው። በዚህ ላይ ብዙ ለውጥ ማምጣትም ብዙ ማምረትም አይቻልም። በነፍስ ወከፍ ምርታማነትን ማምጣት አይቻልም።
የምርት ዕድገት መጥቷል ተብሎ ቢገለጽም የምርት እድገት የመሬቱ የምርታማነት መጨመር፣ በተወሰኑ አርሶ አደሮች ከጎረቤት አገራት ሊወዳደር የሚችል የመሬት ምርታማነት ሊኖር እንደሚችል ያሳያል። ነገር ግን እያንዳንዱ ገበሬ ምርታማነቱ አናሳ ነው።
በአንድ አስረኛ ሄክታር ላይ የሚመረት ምርት ሊያሳድግ፣ የኢኮኖሚ ውጤትን፣ የማኅበራዊ ደኅንነትን፣ የምግብ ዋስትና ምን ያህል ሊያመጣ ይችላል? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል። ስለዚህ የመሬት ጥያቄን ሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ብሎ አስቀምጦታል። በዛው ድንጋጌ ውስጥ ደግሞ የመሬት ባለቤትነትን በአንቀጽ 40 ገበሬው የሊዝ መብት ተሰጥቶት መሬቱን አስይዞ መበደር፣ በገጠር የእርሻ ዘርፍ የመሬት ጉዳይ በሕጋዊ መንገድ ማስተላለፍ የሚችልበትን መንገድ በጥናት በመመሥረት ኪሳራ በማያስከትል ሁኔታ መፈታት ይችላል። ይህም ለመሪዎች ቀርቦ ውሳኔ ሊያሰጥ በሚችል ደረጃ ላይ ነው።
በተበጣጠሰ መሬት ቴክኖሎጂን እና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከባድ እንደሆነ መንግሥትም ገብቶታል። የኩታ ገጠም እርሻ ለማስፋፋትም ያዳግታል። አንድና ሁለት ዓመት ምርታማነት ያድጋል። በዛ ጊዜ የሚገኘው ዕድገት የተወሰኑ ሰዎችን ሊጠቅም ይችላል። ነገር ግን አርሶ አደሩ ሃብት ማፍራትና መሸጋገር ካልቻለ ጊዜያዊ ዕድገት ቢገኝ የዘለቄታ እድገት አይሆንም።
የገጠር ፋይናንስና የብድር አገልግሎት
ሌላው ሊነሳ የሚገባው ነጥብ እስከዛሬ ድረስ ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ ያለው በርካታ የኢትዮጵያ የፖሊሲ አውጭዎች በቅርበት ያላዩት በሩቅ ብቻ የሚመለከቱት የብድር ወይም የእርሻና የገጠር የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቅርበት፣ በስፋት አነስተኛ አርሶ አደሮችን ሊያግዝ፣ ካፒታላቸውን ሊያሳድግ የሚችልና የእነርሱን ሕይወትና ህልውና ያማከለ የፋይናንስና የብድር አገልግሎት አለመኖር ነው።
ባለፉት 20 ዓመታት የፋይናንስ ሴክተሩ በተለይም የግልና የመንግሥት ባንኮች በስፋት መጥተዋል። ይህ በጎ ነው። የንግድ ባንኮች የግሉም ሆነ የመንግሥት የሚያበድሩበት፣ የሚመሩበት የብድር ሥርዓታቸው ከግብርናው ዘርፍ ጋር የሚጣጣም፣ የሚደጋገፍና የሚገናኝ አይደለም። ግብርና አደጋን ያማከለ፣ በተፈጥሮው በእሳት፣ በጎርፍ፣ የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ባለመዝነብ፣ በድርቅ፣ በአዝዕርት ተባዮች በሽታዎችና በተለያዩ ችግሮች እያለፈ የሚሄድ ዘርፍ ነው።
የመንግሥትና የግል የፋይናንስ ዘርፉ እያበደረ ያለው በሚታወቅ አንድ አካባቢ ላይ ተበትኖ ባለው ወይንም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ነው። ይህንን ዘርፍ በቀላሉ መምራት ይቻላል። የግብርና ዘርፉ ግን ሰፊ ነው። ግለሰቦች በትናንሽ ቦታዎች ላይ በተለያዩ የስጋት ቀጠናዎች የሚኖሩ ናቸው። በመሆኑም የግብርናው ዘርፍ የተለየ የፋይናንስና የብድር አገልግሎቶች ሊፈቀድለት ይገባል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ፣ በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ በደቡብ የፋይናንስ ዘርፎች ተብለው በቅርብ ጊዜ ተፈጥረዋል። እነርሱ እያደጉ ናቸው። በተቻላቸው መጠን ለግብርናው ዘርፍ የተቻላቸውን ያህል በማበርከት አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ ድርጅቶች ናቸው። ጥሩ ነው። ግን የኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ከሚፈልገው ጋር የሚጣጣም ዕድገት አይደለም።
የግል የንግድ ባንኮች ከግብርናው ጋር የሚያገናኛቸው በጣም ውስን ነው። እነርሱ ደግሞ የመሬት ጥያቄው በዋስትና መሬትን ማስያዝ አይቻልም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአንድ ገበሬ ብድር መስጠት የሚችለው 30 ሄክታርና ከእዛ በላይ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ 30 እና ከእዛ በላይ ሄክታር መሬት የአነስተኛ ገበሬ ዘርፍ አንድም የለም። ስለዚህ ብድር እሰጣለሁ የሚለው በሌለው ዓለም ውስጥ ነው።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ብድር እሰጣለሁ የሚለው ከፍተኛ ሄክታር 20 ሺህ እና ከዛ በላይ ላላቸው ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ የሚኖረው በግማሽ ሄክታር፣ አንድ ሄክታር ውስጥ ነው። የብድር አገልግሎት ለማግኘት የሚችልበት አይደለም። ይህም ከፍተኛ የሆነ ማነቆ፣ ከድህነት ወደ ድህነት፣ ከችግር ወደ ችግር እየሄደ ያለ የኅብረተሰብ ክፍል የሚዳረስ የፋይናንስ አገልግት አለመኖሩን ያሳያል።
የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ብንወስድ የእርሻ አብዮት ከገጠሩና የእርሻ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን የዓለም የእርሻ ታሪክ ያሳያል። ኢትዮጵያም ወደ እዛ መግባት አለባት። በቅርብ ዘመን ቻይና በ15 ዓመታት ውስጥ የግብርናውን ዘርፍ በገንዘብ በመደገፍ የእርሻ አብዮት ካካሄዱ አገራት አንዷ ናት። የተለያዩ የግብርና ዘርፍ ባንኮች የተለያዩ የብድር አገልግሎቶች በከፍተኛ ደረጃ ያሳደገች አገር ናት።
ከምዕራባውያን በተለይም ከእንግሊዝ፣ ከመካከለኛው አውሮፓ ከ17ኛው እና 18ኛው ከኢንደስትሪ አብዮቱ ጋር ተያይዞ እርሻን ለማሳደግ የተጠቀሙበት የብድርና የገጠር ልማት ፋይናንሲንግ እንደምሳሌ መጠቀም እንችላለን። እንደሁኔታውም በኢትዮጵያም እያንዳንዱ አይነት የብድር አገልግሎት የሚገኝበት ራሱን የቻለ ተቋም ይዞ መሄድ ያስፈልጋል።
የእርሻ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት ማዳረስና ፈጠራ
እርሻ በኢትዮጵያ ያረጀ ያፈጀ ግን የስልጣኔ ምንጭ ነው። ዓለም ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የገባበት መድረስ ቀርቶ ኋላ ቀር ነው። በመሆኑም አሁን የሚጠበቀው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት ማዳረስ ያስፈልጋል። የብድር አገልግሎቱ ገበሬዎች የሚሳተፉበት ሁኔታን በምስጢር መልኩ ከተዘረጋ በኋላ ቴክኖሎጂዎች በስፋት እንዲዳረሱና እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል። የተወሰኑትን ብንጠቅስ ትራክተር፣ መሰብሰቢያ ማሽን፣ ኮምባይነር በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል። እነዚህን ለማስተዋወቅ በ1960ዎቹ በስዊድኖች የአርሲ የገጠር ልማት ድርጅት፣ የወላይታ ሶዶ፣ የቆቦ አላማጣ የሚባሉ የእርሻ ተቋማት ነበሩ። በተለያዩ ምክንያቶች ፕሮጀክቶቹ አልቀጠሉም። ግን የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የነበሩ አካባቢዎች እንደ ባሌ፣ አርሲ፣ ከፊል ሸዋ እነዚህን የእርሻ መሳሪያዎች በስፋት ተጠቃሚዎች ናቸው።
የባሌና የአርሲ የስንዴና የገብስ ቤት ተብለው የሚጠሩት እነዚህን ተገን አድርገው በመሥራታቸው ነው። አብዛኛው ተረፈ ምርት ከጤፍ ውጭ የሚመጣው ከእነዚህ ሁለት አካባቢዎች ነው። ኢትዮጵያ በታሰበና በታቀደ አንዱ ሌላውን እየደገፈ በሚሄድበት ሁኔታ እነዚህን ቴክኖሎጂዎችን ማምጣት ያስፈልጋል። በአንድ ወቅት የእርሻ መሣሪያዎችን የመገጣጠም ሥራ ተጀምሮ ነበር። ነገር ግን በሙስና ችግር ምክንያት ሥራው ለመሬቱ የማይሆን የብረት አይነት ባለመቅረቡ ምክንያት ተስተጓጉሏል። ለኢትዮጵያ የአፈር አይነት የመሬት ይዞታ ታሳቢ ያደረገ የእርሻ ትራክተሮች፣ ኮምባይነር፣ ኸርቨስተሮች፣ መከስከሻዎችን በጥልቀት ተመልክቶ ከሌሎች ጋር አጋርነት ፈጥሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገጣጠምበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
የማዳበሪያ ጉዳይም ወሳኝ ነው። የዩክሬን ጦርነት የነበረንን ችግር አባብሶታል። የማዳበሪያ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። አሁን ተጽዕኖው ባይታይም ጊዜው ደርሶ ማዳበሪያ ተገዝቶ ለአርሶ አደሩ በሚከፋፈልበት ጊዜ ድሮም ዋጋው ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የመንግሥት ፖሊሲ አውጭዎች በዚህ ጉዳይ ሊያስቡበት ይገባል።
በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች በመኖራቸው ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ማምረት ትችላለች። አፋር ላይ ከፍተኛ የፖታሽ ሃብት አለ። ይህን መሠረት በማድረግ የተወሰኑ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን የማቋቋም ሃሳብ በተቀናጀ መልኩ ሊተገበር ይገባል።
የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማምጣት፣ ከብቶችን የማዳቀል ሥራ በከፍተኛ ደረጃ የሚታሰብበትና የኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት የሚሠራቸውን እንደየአካባቢዎቹ ሊመረጡ በሚችሉበት ዙሪያ አገልግሎት መስጠት አለበት። ትግበራውንም በቅንጅት በመሥራት ለሕዝብ ማዳረስ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ትግበራው በቴክኖሎጂና ፈጠራ የኢትዮጵያን ግብርና ማዘመን አካል ነው።
ያለፉት 10 እና 15 ዓመታት ግምገማ ሲታይ ለስንዴና የእህል ውጤቶች በአማካኝ የሚወጣው አንድ ቢሊዮን ዶላር ነው። የገቢ ምርትን ሊያስቀር የሚችል ምርታማነትን መፍጠር ሲቻል ይህንን ካፒታል ኢንቨስትመንት ውስጥ ማዋል ይቻላል። የውጭ ርዳታ ውስጥ ሳንገባ ባለው ሃብት ወደ ዘለቄታ መፍትሄ መምጣት ይቻላል።
የመሬትና የተፈጥሮ ሃብት መመናመን
ከመሬት መበጣጠስ፣ የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ጋር አሁን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንኳን በመኪና በትራክተር ገብቶ ለማረስ ድንበር የሌለበት ሁሉም ሰው መሬቱን እያንዳንዱን ኢንች በከፍተኛ ደረጃ እየተከታተለ ነው። በአንድ በኩል ጦርነትና ግጭት ያስከተለ ሁኔታ ይታይበታል። ስለዚህ የገጠር እርሻ ውስጥ መንገዶችን ማውጣት፣ የትኛው ቦታ ለከብት ርባታ፣ ለከተማ መስፋፋት እንደሚውል ለይቶ ማጥናት ይገባል። ከተማ እየተስፋፋ በጣም ምርታማ የሆኑ መሬቶችን ቀይሯል። ይህ ለዘለቄታው አያዋጣም፣ በትውልድም ነቀፌታን ስለሚያስከትል የመሬት አጠቃቀም እቅድን በከፍተኛ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
መሬት ደግሞ እርሻ እየተስፋፋ በመሄዱ ያሉ የተፈጥሮ ደኖች፣ የተፈጥሮ ምንጮችና የተፈጥሮ ሃብቶች እየደረቁ ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ መሪነት በአረንጓዴ አሻራ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎች መተከላቸው እሰየው ቢያስብልም የመሬት አጠቃቀም ጉዳይ እርሻ በየትኛው ቦታ መኖር እንደሌለበት የሚደነግግ ሕግ ባለመኖሩ የተበላሸ አሠራር ወንዞች፣ ኩሬዎችና ሐይቆች ሳይቀሩ እየደረቁ ይገኛሉ። የዚህ የመሬት አጠቃቀም በከፍተኛ ደረጃ የሚታሰብበት መሆን አለበት።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለገጠሩ ማኅበረሰብ
ኅብረተሰቡ ማገዶ አንድዶ ለማክሰል፣ ለመብራት ጥቅም ላይ የሚያውለው የተፈጥሮ ሀብትን አመናምኖ እንጨት ቆርጦ ነው። የኤሌክትሪክ አገልግሎት በስፋት እየደረሰ አይደለም። በርካቶች የከተማ ነዋሪ በበቂ ደረጃ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስለማያገኝና የመቆራረጥ ችግር በመኖሩ በእንጨትና በከሰል የመጠቀም ሁኔታ አለ።
አሁን የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ምርት ላይ ነው። በተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ምርት እንደሚቀጥል እየተጠበቀ ነው። ይህ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ባሻገር ተፈጥሮንም ማዳን ነው። እንጨት ላይ ተመስርቶ ያለውን ኅብረተሰብ ኤሌክትሪክ እንዲጠቀም በማድረግ ተፈጥሮ ሀብትን እንዲጠብቅ የተመናመነውን መልሶ እንዲገነባ፣ ከአረንጓዴ አሻራ ሥራ ጋር የማቀናጀት ሥራን ይጠይቃል።
ከሕዳሴ ግድቡ የሚገኘው ኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገራት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ነው ቢባልም፤ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለኢትዮጵያ ገበሬና ለገጠር ሕዝብ እንዲዳረስ ማድረግ ነው። ከእነርሱ ከተረፈ የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት መታሰብ ያለበት። የፀሐይ ኃይልን ጥቅም ላይ ማዋልም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ኢንሹራንስ
እርሻ በተፈጥሮው ስጋት ያለበትና ለአደጋ የተጋለጠ የሥራ ዘርፍ ነው። የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ካለበት ደረጃ ለማሻገር ተገቢ ሥራ ቢተገበርም ተፈጥሮ አንዳንዴ ትቀጣናለች። በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ፣ በግጭትም የብዙ ጊዜ ኢንቨስትመንትም በአንድ ጊዜ ሊወድም ይችላል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ኢንሹራንስ ገብቶ በሙሉ ልቡ በኢንቨስትመንቱ እንዲሳተፍ ቢደረግ መልካም ነው።
መንግሥት ከመደበኛ በጀት ላይ ወስዶ ኅብረተሰቡን እየቀለበ ነው። ለወደፊቱ ግን ይሄ በዘለቄታነት መቀጠል አይችልም። ገበሬው ራሱን ኢንሹራንስ ገብቶ በተለይ የሕክምና አገልግሎት እያገኘ ነው። በተጨማሪም ለሚደረሰው አደጋ ኢንሹራንስ ገዝቶ እንዲጠቀም ማድረግ ይገባል።
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያን እርሻ ስራ ከነበረበት፣ አድጓል የሚባለው እውነታነት ቢኖረውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ እድገት ጋር አይናበብም፤ አቅርቦትና ፍላጎቱም አልተጣጣመም። አሁን ከቀውሱ እየተወጣ ነው።
ግብርናውን ለማዘመን አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር ፊቱን ወደ ኢኮኖሚው ማዞር፣ ኃይሉን የመጠቀምና የሚያስፈልጉ ከላይ የተመለከቱ ዐቢይ ጥያቄዎችን የሚመልስ አሰራርን መፍጠር ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያውያንም የንግዱን፣ የኢንዱስትሪውን ዘርፎች እርሻን የሚደግፍ በማድረግ እየተደጋገፈ የሚሄድ ማድረግ ይጠበቅብናል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014