ድሮ ድሮ ሕፃናት እያለን ሌሎች ትልልቅዬ መሠሎቻችን ነበሩ ሁለታችንንም አጥበው የሚያሠማምሩን። ያኔ ሁለታችንም እንመሳሰልና ቆንጅዬዎች እንደነበርን አስታውሳለሁ። እንደዛሬው ነገር ተቀይሮ አንዳችን ተመራጭ መሆን ሳንጀምር በፊት ነው ይሄ ሁሉ። አሁን ላይ ዓይቻቸው የማን እንደሆኑ የማለያቸው ታላላቅ ሸካራ መዳፎች ያኔ እኔንም እህቴንም እኩል እጥብ፣ ቅብትብት አርገው ያሽሞነሙኑን ነበር።
ያው እንግዲህ ማደግ አይቀርምና ከፍ እያልን ስንሄድ ራሣችንን እንድንችል ጣል ጣል እንደረግ ጀመር። እህቴን እወዳታለሁ። ለዚያም በደንብ አሣምራታለሁ። እስዋም በተራዋ ታሳምረኛለች። ያኔ እንቅስቃሴያችን፣ ሁሉ ነገራችን አንድ ዓይነት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ መጡ፣ የነገሮች ሁሉ ጫና እኔ ላይ እየተቆለለ ይሄድ ጀመር። እስዋ ከምትሠራበት የማትሠራበት ጊዜ ይበልጣል። ብትሠራም ደግሞ ምንም ጥራት ያለው ሥራ አትሠራም። ቢያንስ ቢያንስ ሌሎች እጆች ለሠላምታ ሲዘረጉ እንኳን የማስተናገዱ ሥራ የኔ ብቻ፤ የኔ የቀኝ እጅ ብቻ ነው።
ዕቃ ቢወድቅ የማነሣው እኔ፤ እስክሪቢቶና እርሳስ የምጨብጠው እኔ፤ የምቆርጠው የምፈልጠው እኔ። ይሄ ያናድደኛል። የኔና የግራ እጅ እኩል ሥራ የሚሆነው አንድ ጉዳይ ቢኖር ማጨብጨብ ብቻ ነው። እሱም እንደሚመስለኝ እኔን መምታት ስለሆነ ይሆናል የተቻላት፣ ማን ያውቃል?
ሌሎች መሠሎቻችን የኔ ምሬት ይሠማቸው እንደሆን ለማወቅ ሁሌ እጠይቃለሁ። አልፎ አልፎ በተቃራኒ የኔ ዳፋ ከገጠማቸው ጥቂት ግራ እጆች በቀር፤ አብዛኛዎቹ ቀኝ እጆች እንደኔው ሲማረሩ እሰማለሁ። «እንዴ በዛ! ፈጣሪ እኩል አድርጎ፣ በአንድ አምሣል ፈጥሮን እያለ እንዲህ ዓይነት በደልና ጭቆና ለኔ ተለይቶ መሰጠቱ እንቆቅልሽ አይሆንም?»
ከምንም ከምንም ግን የሚያናድደኝ እኔ እንዲህ እየፈጋሁ፤ ሁሌ የምታምረው እስዋ ግራ እጅ መሆንዋ ነው። ድሮ አንድ ዓይነት የነበርን እጆች ዛሬ ላይ እስዋ ለግለግ ያሉ ጣቶች፣ የተዋቡና የተስተካከሉ ጥፍሮች፤ ለስላሣ ቆዳ ሲኖራት፤ የኔ ጣቶች ከዕለት ወደዕለት እየወፈሩ፣ ጥፍሮቼ እየዶለዶሙና ቆዳዬና መዳፌም እንደ ድብዳብ እየሻከሩ መሄዳቸው ምርር ያደርገኛል።
እኔ እስዋን ተጨንቄ ሳሳምራት ማራኪ ሳደርጋት፤ እስዋ ግን ጥፍሮቼን እንኳን አስተካክላ ለመሞረድ ይሣናታል። ይሄንን ሳጣራ ግን አንዳንዶቹ መሰሎቼ ሁለቱም እኩል በባለሙያ እንክባካቤ እንደሚደረግላቸው ሰምቻለሁ። የታደሉ፣ ካለው የተወለድ… ምናምን የሚባለው ይሄው አይደል?
በፊት በፊት ሆን ብላ ከኔ በልጣ ለመታየት የምትሠራው ተንኮል እየመሠለኝ እበሳጭባት ነበር። በኋላ በኋላ ስረዳ ግን እንደኔ በቅልጥፍና መሥራት አለመቻልዋን አወኩ። ለተንኮል እየለገመች ሳይሆን የኔን ያህል ችሎታ እንደሌላት ስረዳ አዘንኩላት። የሚገርመኝ ግን የሰዎች ዕይታ ነው። ከኔ አስበልጠው የሚወዱት እስዋን ነው። ሌላው ቢቀር እንኩዋን እኔን 24 ሠዓት እያስፈጋች እንዳስጠላና እንዳያምርብኝ ያረገችኝ እመቤቴ ራስዋ ሁሌ የምትወደውና የምትስመው እስዋን ነው። ሌሎች እንዲስሙላት፣ ቀለበት እንዲያጠልቁላትና እንዲደባብሱላት የምትጋብዘውም የግራ እጅን ጣቶች እንጂ የኔን አይደለም።
ሁሌ የምታዘበውና እርር የሚያደርገኝም ይሄ ጉዳይ ነው። ይህን ያህል ስፈጋላት እየኖርኩ ለውለታዬ እንኳ አንድ ቀን ወዳኝ አታውቅም። አንድ ምርር ብዬ የተከፋሁበት ቀንማ መቼም አይረሣኝም። አንድ ዶፍ እየወረደ በነበረበት ጭጋጋማ የሐምሌ ቀን ነበር። ብርዱ በቃል የሚገልጹት ዓይነት አይደለም። እመቤታችን በደረበችው ጥቁር ወፍራም የክረምት ካፖርት እንዳይበርደን ግራ እጅን በግራ፣ እኔን ደግሞ በቀኝ ኪስዋ ከታ ደስ የሚል ሙቀት እየለገሰችን ነበር። ወደኪሶቿ ከመግባታችን በፊት እርስ በርስ እንድንሟሟቅ ስታፋትገን ብትቆይም ስላልቻለች ነበር ወደ ኪሶቿ ያስገባችን። ታድያ በዚያ ብርድ ደህና ሞቆኝ ተጠቅልዬለሽ ባልኩበት ድንገት የሆነ ሠው መጥቶ ቆፈን ያቆራመተው እጁን ለሠላምታ ቢዘረጋላት ከተኛሁበት ተቀስቅሼ የተዘረጋው ወዳጄን አስተናገድኩ።
አቤት ከዛ ስወጣ የተሰማኝ ቅዝቃዜ! ወድያው ወደቦታዬ በመመለሴ አረፍ አልኩ። ነገር ግን እንደገባሁ አልቀረሁም፤ ሌላ ወዳጅ ይሁን ጠላት ያለየሁት አንድ ሰው የደወለውን ስልክ አንስቼ ወደ ጆሮ እንድወስድ ትዕዛዝ ተላለፈልኝ። ይሄኔ ደም ዕንባ የሚያስለቅስ ምሬት ተሠማኝ። ደሞ የወሬው እርዝመት! ቆፈኑ ከቆዳዬ አልፎ ውስጤ ገብቶ ያንዘረዝረኝ ጀመር። ጩሂ ጩሂ፣ የሞባይሉን ቀይ ቁልፍ ተጫኚ ተጫኚ፣ ስልኩን ወርውሪ ወርውሪ አሠኘኝ። ግን ከእመቤቴ ትዕዛዝ ውጪ አንዲት ተግባር የማልፈጽም ታማኝ በመሆኔ ምሬቴን ውጬ፣ ብርዱን ጠጥቼ፣ ጣቶቼ መንቀሣቀስ እስኪያቅታቸው ደንዝዤ ግዳጄን ተወጣሁ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግራ እጅ ካለችበት የምቾት ዓለም ያስታወሣትም ሆነ የቀሰቀሳት አልነበረም። ይቺን ቀን መቼም አልረሣትም።
አንድዕለት ደግሞ፣ አቤት አቤት የሠራሁት ተንኮል፣ ውይ ክፋቴ! እመቤቲቱ ባዘዘችን መሠረት ምግብ እየተጋገዝን እያበሰልን ነበር። ታድያ እየተጋገዝን ቢሆንም የግራ እጅ ሥራ ግን ይህን ያህልም አልነበረም። አልፎ አልፎ ዕቃ ከማያያዝና ውሃ ከማፍሰስ በቀር ብዙውን ጊዜ እኔ ወድያ ወዲህ ስል እስዋ ባብዛኛው የእመቤቴ ወገብ ላይ ቁጭ ብላ ማየት ነበር ሥራዋ።
ታድያ ስጋ እንድንከትፍ ታዘዝንና እስዋ ስጋውን እየያዘችልኝ እኔ ቢለዋውን ይዤ መክተፍ ጀመርኩ። እመቤታችን ከላይ ሆና ትመለከተናለች። ነገር ግን ትኩረትዋ ሁሉ ግራ እጅ ላይ እና ስጋው ላይ ነበር። እስዋ ስጋውን ብቻ ነው የያዘችው። ቢለዋውን ይዤ ስጠጋ ወደ ሁዋላ እያለች ስጋውን ለኔ ከማስጠጋት በቀር የምታደርገው ነገር አልነበረም።
እመቤቴ ግን ሙሉ ትኩረትዋን እስዋ ላይ አርጋ በውበትዋ ተመስጣለች። የምታስበው ስለሷ ውበት እንጂ ስለኔ አሠራር አለመሆኑን ሳውቅማ ደሜ ፈላ፣ መሥራት ሁሉ አስጠላኝ። አውቄ ልለግም ስል እንኳን የኔ መድከም ሳይሆን የሚታየው ቢለዋው ነው የሚሳለው። እኔ ሥራዬን ለአፍታ አቁሜ ግራ ቀኝ ወዝወዝ ከመደረግ በቀር። ይሄን ሳይ ታድያ አንድ የተንኮል ሃሣብ ውል አለኝ። ጊዜ ማጥፋት አልፈለኩም፤ እመቤቴ እኔን በማታስተውልበት ፍጥነት ቢለዋውን ከስጋው አሳልፌ የግራ እጅ ሌባ ጣት ላይ አሳረፍኩት። ሸረከትክዋት።
አቤ…ት! የተፈጠረው ትርምስ! ቢለዋውን ከኔ ምን እንዳወናጨፈው በዚያ ግርግር ትዝ አይለኝም። ጫጫታ እና ጩኸት ሆነ። ያንን ሸር ስሠራ ያላገናዘብኩት አንድ ነገር ግን ነበረ፤ ጫና ራሴ ላይ ማብዛቴን። ግራ እጅን የማከሙ ሥራም የኔው ኃላፊነት ሆኖ ቀረ። ሆን ብዬ ያደረኩት አልመሠላቸውም። እንዲህ ታስባለች ብለው ሊገምቱም አይችሉማ። በእህቴ ላይ!
ከዚያ በኋላ ስጋውን ማን ከትፎ እንደጨረሰው ባላውቅም፤ ወጡ ተሠርቶ እስኪያልቅ ግን ደህና የምትረዳኝን ግራ እጅ ጎድቼ፣ ራሴው ውኃ አፍሣሽ፣ ራሴው እሳት ቆስቋሽ ሆኜ ቀረሁ። ግን ደስ ያለኝ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን በፋሻ ተጠቅልላ ውበትዋ ስለጎደለ ነው። ያኔ እኔ ከስዋ ቆንጆ እንኳን ሆኜ መታየት ቢያቅተኝ እስዋን አስቀያሚ በማድረጌ ደስ አለኝ። የታባትዋ! ይሄ ተንኮሌ ራሴኑ መልሶ ያስቀኛል። ቆይ ግን ምን እጠቀማለሁ? ሆሆይ ሸር! ሠዎች ምቀኝነት የሚሉት ይሄንኑ ነው አይደል? እኔ ግን ምቀኛ አይደለሁም!
ደግሞ የራስዋ የግራ እጅ ቀሽምነት ይገርመኛል። እኩል ተፈጥረን፣ አብረን አድገን ፣ለምን እስዋ ልፍስፍስ እንደሆነች አታውቀውም። እኔ ግን በደንብ አውቀዋለሁ። እኔ ሥራ ስሠራ እሷ ስለምትዘፈዘፍ ነው። ያኔ ገና ጢኒጥዬ ሆነን እስዋ ነበረች ቀደም ቀደም የምትለው። እስዋ ሠሪ፣ እስዋ ቀዳሚ፣ እንደው ፈጠን ፈጠን ሲያደርጋት ሞራልዋን ነክተዋት መሠለኝ… ይሄው ያኔ በቆመችበት አለች። እስክሪቢቶ እንኳን መጨበጥ ሞትዋ እኮ ነው። ብትጨብጥ ራሱ ጣቶችዋን አንቀሣቅሣ የሚነበብ ነገር መሥራት ያቅታታል። ያኔ እኔን ሲያሰለጥኑ እስዋንም አሠልጥነው ቢሆን ዛሬን ከኔ እኩል ትሆን ነበር። ለነገሩ አሁንስ ምን ጎደላት? እነሱ እንደሆነ ለማየትም ለመዳበስም ለመሣምም የሚመርጡት እስዋን አይደል? መልኳን ስላሳመረች ወዳጅዋ፣ ተንከባካቢዋ መብዛቱ። እሷኮ ራስዋን መንከባከብ እንኳን አትችልም፤ ግን ለዕይታ ተመራጭ አሷ ናት። አያናድድም?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ
ስመኝ ታደሰ