ቅን ልቦና እና አስተሳሰብ ቅን መንገድን ይመራል፤ ቸርነትና ለጋስነት በተሰጠን ሀብት ብቻ ሳይሆን በተሰጠን ልብ የሚወሰን ነው፡፡ ቸርና ሩህ ሩህ ሰዎች ካላቸው ላይ አካፍለው ይኖራሉ፤ ባይኖራቸው እንኳ ከሌሎች ላይ ወስደው ለተቸገሩ ሰዎች ይለግሳሉ፡፡
በዛሬው የሀገርኛ አምዳችን ከጎዳና ሕይወት ወጥቶ ትምህርቱን በመማር ላይ ያለ አንድ ወጣት በአዳማ ከተማ ጓደኞቹን በማስተባበር እያደረገ ስላለው የበጎ አድራጎት ሥራ የሚያስቃኝ ይሆናል፡፡ ወጣቱ ለጥቂት ዓመታት የጎዳና ሕይወትን ሲመራ በነበረበት ጊዜ የተመለከታቸው ነገሮች ወደ በጎ አድራጎት ሥራ እንዲገባ አድርገውታል። እኛም የወጣቱ ተነሳሽነት ለሌሎች አስተማሪ ይሆናል በሚል የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርገው ወደናል፡፡
ጆን ማሙሽ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን፣ ኢተያ ከተማ ሲሆን በልጅነቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቹ እያፈነገጠ ጥቂት ጊዜም ቢሆን በአዳማ ከተማና በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ የጎዳና ሕይወትን ቀምሷል፡፡ በጎዳና ሕይወት ውስጥ በነበረባቸው ጥቂት ዓመታት አስቸጋሪ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፡፡ ዞር ብሎ የሚያያቸው ወላጅና ዘመድ አዝማድ አጥተው ጎዳና ላይ የወጡ በርካታ ጓደኞቹን ተዋውቋል፤ የተዋወቃቸው አብዛኛዎቹ ጓደኞቹ ከቤት እየኮበለሉ ለጓዳና ሕይወት የተጋለጡበት ምክንያት ቢለያይም ወላጆቻቸው ስለሞቱባቸው ወይም እናትና አባታቸው ስለተለያዩ መሆኑን እንዳጫወቱት ነግሮናል፡፡
እርሱም ጎዳና ለመውጣት ምክንያት የሆነው ከወላጅ አባቱና እናቱ ጋር ስለማይኖር በትንሽ በትልቁ ጉዳይ ይከፋው ስለነበር ነው፡፡ እናቱ አረብ አገር በመሄዷ ምክንያት ጆን የሚኖረው አንዳንዴ አክስቱ፣ አንዳንዴም ከአጎቱ ጋር ነበር፡፡ በልጅነቱ አስቸጋሪ ባህሪ ስለነበረው (ከ)ማንም ሰው ጋር ተረጋግቶ የመቀመጥ ፍላጎት አልነበረውም፡፡ በዚህ የተነሳ ትንሽ በከፋው ቁጥር ወደ ጎዳና ይወጣ ነበር፡፡ ቢያንስ ከአራት ጊዜ በላይ እየጠፋ ከጎዳና ልጆች ጋር ለመኖር ሞክሯል፡፡ እየጠፋ ወደ ጎዳና በወጣ ቁጥር አደራ የተጣለባቸው አክስቱና አጎቱ እየፈለጉት ወደ ቤት ቢያስገቡትም እርሱ ልምዱ አልለቀው ብሎ ጭራሽ ወደ አዲስ አበባ ይሄዳል ፡፡
አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ መጥቶ መኖር ከጀመረ በኋላ ግን የጎዳና ሕይወት ምርር ይለዋል። በተለይም በጨቅላ እድሜያቸው በሱስ የተለከፉ ጓደኞቹን ሲያይና የእርሱም እጣፈንታ ከዚህ ውጭ እንደማይሆን ሲያስብ ይፈራ ነበር፡፡ ክፉና ደጉን መለየት ባልቻለበት በዚያ እድሜው በአዳማም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ሕይወትን በመራባቸው ወቅቶች የሱስ ተጋላጭ እንዳይሆን ይጠነቀቅ ነበር፡፡ ጫት መቃም፣ ማስቲሽ መሳብ፣ ሲጋራ ማጨስን አልሞከራቸውም። እንደውም ጓደኞቹ እነዚህን ነገሮች እንዳያደርጉ ይመክራቸው ነበር፡፡
ጆን የአዲስ አበባ የጎዳና ሕይወት ምርር ሲለው አንድቀን አዳማ ከተማ ወደ’ምትገኘው አክስቱ ዘንድ አስደውሎ እንድትወስደው ይጠይቃታል፡፡ አድራሻው ጠፍቶባት ስትፈላልገው የነበረችው አክስቱም ማመን አቅቷት ልክ እንዳስደወለላት ሳትውል ሳታድር በርራ መጥታ ይዛው ወደ አዳማ ትሔዳለች፡፡
ጆን የጎዳና ሕይወትን እርግፍ አድርጎ በመተው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ይጀምራል፡፡ ጭምት የቤት ልጅ ሆኖ ትምህርቱንም ቀጠለ፡ የትምህርት ደረጃው እያደገ ሲሄድና ነገሮችን ማመዛዘን ሲጀምር ያሳለፈው ሕይወት ተገቢ እንዳልነበር፤ የቤተሰቦቹን ምክርና ተግሳጽ አለመስማቱ ትክክል እንዳልሆነ እየተሰማው ይጸጸት ነበር፡፡
በጎዳና ሕይወቱ የብዙ ጓደኞቹን ብሶት ያዳምጥ ነበር፡፡ የቤት ልጅ ሆኖ ትምህርት መማር በጀመረ ሰዓት የእነዚህ ጨቅላ ጓደኞቹ ብሶትና ሮሮ በህሊናው እየተመላለሰ ሰላም ይነሳው ነበር፡፡ በአይኑ ላይ የሚመላለሱትን እነዚያን ጓደኞቹን እንዴት አድርጎ ከጎዳና ሕይወት ማውጣት እንዳለበት እና እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል ያስብ ነበር፡፡
ጆን ያቋረጠውን ትምህርት በመቀጠል መማር ከጀመረ አንስቶ ሁል ጊዜ በጎዳና ላይ ስለተዋወቃቸው ችግረኛ ልጆች ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ ያጫውታቸው ነበር፡፡ የገቢ ምንጭ ቢኖረው እነርሱን የመርዳት ፍላጎት እንዳለው ይነግራቸዋል፡፡ የክፍል ጓደኞቹም በሚነግራቸው ነገር እየተደመሙ ከጎዳና ሕይወት ወጥቶ አብሯቸው የሚማረውን ጓደኛቸውን ሀሳብ የመደገፍ ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ የበሰለ ምግብ ይዘው በመምጣት የጎዳና ልጆችን እንጠይቅ ማለት ይጀምራሉ፡፡ በጓደኞቹ ቅን ትብብር በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ተግባራትን ይፈጽማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ምግብ፣ አንዳንዶቹ አልባሳት፣ አንዳንዶቹም ገንዘብ እያሰባሰቡ በተወሰነ ጊዜ እየሄዱ የጎዳና ልጆችን ይረዳሉ፡፡
አንድ ቀን የጆን አጎት ከኢተያ ሊጠይቀው መጥቶ ጫማ ልግዛልህ ይለውና ይዞት ወደ ሱቅ ይሄዳል፡፡ ሱቅ እየዞሩ ጫማ ሊያስመርጠው ሲሞክር ጆን ብሩን እንዲሰጠውና እራሱ የሚፈለገውን መግዛት እንደሚፈለግ ይነግረዋል፡፡ አጎቱም አምስት መቶ ብሩን በእጁ ይሰጠዋል፡፡ ጆን ብሩን ይዞ ወደ ትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ይሄድና ለጊዜው ጫማ ስላልቸገረው ገንዘቡን ለጎዳና ልጆች ምግብ ሊገዛላቸው እንደሚፈልግ ይገልጽላቸዋል፡፡ ከዚያም ከአርባ በላይ የሚሆኑ የጎዳና ልጆችን ሰብስቦ ሽሮ ቤት በመውሰድ በተሰጠው ገንዘብ ይጋብዛቸዋል፡፡ ኋላም ያደረገውን ነገር አብራው ለምትኖረው አክስቱ ይነግራታል፡፡ የሠራው ሥራ መልካም ነገር መሆኑን ብታምንም ቤተሰብን ሳያስፈቅድ በራሱ ፈቃድ የፈጸመው ነገር ጥሩ አለመሆኑን ትነግረዋለች፡፡
ጆን በተለያዩ ምክንያቶች ከአክስቱ ጋር መግባባት ባለመቻሉ እንደገና ወደ ኢተያ ይመለሳል፡፡ በዚህን ጊዜ ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር የነበረው ግንኙነትም ይቋረጣል፡፡ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወላጅ እናቱ ከአረብ አገር መጥታ አብረው መኖር ይጀምራሉ፡፡ ጆንና እናቱ ከኢተያ ለቀው ኑሯቸውን በአዳማ ያደርጋሉ፡፡
ወደ አዳማ ሲመለስ ከቀደምት የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ይገናኝና የጎዳና ልጆችን ለመረዳት የሚታደርጉትን እንቅስቃሴ በአዲስ መልክ ማጠናከር እንዳለባቸው ይነጋገራሉ፡፡ በተለይም አደም ከሚባለው ጓደኛው ጋር ስለ ጉዳዩ በደንብ ያወራሉ፡፡ ጆንና አደም ሀሳባቸውን ለማሳካት በአንድ ትምህርት ቤት እየተማሩ ጎን ለጎን የበጎ አድራጎት ሥራውን ለማስተባበር ቢስማሙም አደም የሚማርበት ትምህርት ቤቱ ቦታ በመጨረሱ ምክንያት ጆን በቁጥር ሶስት ትምህርት ቤት ተመዝግቦ ለመማር ይገደዳል፡፡
ሁለቱም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ የጎዳና ልጆችን ለመደገፍ ተማሪዎችን ማስተባበራቸውን ቀጠሉ።
በዚሁ መሰረት ጆን በራሱ በኩል ቁጥራቸው ስልሳ የሚደርስና ፍላጎት ያላቸው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በሳምንት አምስት ብር እንዲያዋጡ ያሳምናቸዋል፡፡ አደምም በሚማርበት ቦሰት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አሳምኖ በሳምንት ሁለት ብር ለማዋጣት ይስማማሉ፡፡ ሁለቱም በያሉበት ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ መስራት ጀመሩ፡፡
ጆን ከዚያም አልፎ ትኬት በማሳተም ጭምር ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በሽያጭ ያቀርባል። ትምህርት ቤቱም የተነሱበትን ቅዱስ ዓላማ በማየት እንደ ማህተም (ለህጋዊነታቸው)ና የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይፈቅድላቸዋል፡፡ እንቅስቃሴያቸውም የ”ማህበር” ቅርፅና ይዘትን እየያዘ መጣ።
አንድ ቀን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ መምህራን በተገኙበት ከሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች የምሳ ግብዣ ያዘጋጃሉ፡፡ ከምሳ ግብዣው በኋላ የትምህርት ቤቱ የስነ ልቦና መምህር ወጣቶች ከጎዳና ሕይወት እንዴት ሊወጡ እንደሚችሉና የሱስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ማድረግ የሚያስችል የምክር አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡ በመጨረሻም ተማሪዎች ያሰባሰቡትን አላባሳት ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ አድለው ያሰናብቷቸዋል፡፡
የ”ማህበሩ” ጸሐፊ ሰብሳቢና ሌሎች የኮሚቴ አባላት ተመርጠው ገቢያቸውንና ወጪያቸውን በመረጃ በመያዝ የከፋ ችግር ያለባቸውን የጎዳና ተዳዳሪዎች መርዳት ይጀምራሉ፡፡ አንዳንዶቹን እየመከሩ የትራንስፖርት ገንዘብ በመስጠት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡
በአንድ ወቅት አቡዱራዛቅ የሚባል ታዳጊ የአራት ዓመት ወንድሙን ይዞ ሲለምን ያገኙትና ወላጆቻቸው የት እንዳሉ ይጠይቁታል፡፡ አብዱራዛቅ መኖሪያ ቤታቸው በላያቸው ላይ ፈርሶባቸው መጠለያ ቦታ እንዳጡና እናታቸውም ታማሚ መሆኗን ይነግራቸዋል። የ”ማህበሩ” አባላት በቀጥታ የእነአብዱራዛቅ እናት ወዳሉበት ሄደው ቤቱን ሊጠግኑላቸው እንደሚፈልጉ ያሳውቋቸዋል፡፡ ለአናጺና ለቆርቆሮ አራት ሺህ ብር ብቻ አውጥተው እራሳቸው ጭቃ አብኩተው በመለጠፍ በአጭር ጊዜ ቤቱን ሠርተው ያስረክቧቸዋል፡፡ ለልጆቹም ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ገዝተው በመስጠት እንዲማሩ ያደርጋሉ፡፡
በሌላም ጊዜ እንዲሁ አንዲት እናት ህጻን ልጅ ይዛ እየለመነች ያገኟታል፡፡ ሴትይቱ ወገቧን ስለሚያማት የጉልበት ሥራ መሥራት የማትችል ነች፡፡ ቀለል ያለ ሥራ እየሠራች እንድትኖር ማህበሩ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግላትና ቆሎ እየቆላች መሸጥ ትጀምራለች፤ አሁን ካፒታሏን አሳድጋ ጉልት እየሸጠች በመኖር ላይ ነች። ልጇም ትምህርቱን እየተማረ በትርፍ ሰዓቱ ጋራዥ ውስጥ እየሰራ ይገኛል፡፡ ጆንና ጓደኞቹ ከጎዳና ህይወት እንዲወጡ የሚደግፏቸውን ሰዎች ሥራ አስጀምረው አይተዋቸውም፤ ሁል ጊዜም ለውጣቸውን እየገመገሙ ሀሳብ ይሰጧቸዋል፡፡
ኮቪድ-19 በተከሰተ ጊዜ በርካታ ሰዎች በራቸውን ዘግተው ተቀምጠው ስለነበር ለእነዚህ ሰዎች “ማህበሩ” ዘርፈ ብዙ እገዛዎችን አድርጓል፡፡ ህብረተሰቡ እራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች እየተገኙ እጅ ከማስታጠብ ጀምሮ የተለያዩ ግንዛቤዎችን እያስጨበጡ፤ ለአቅመ ደካሞችም አስቤዛ እየገዙ ቤታቸው ድረስ ይወስዱላቸው ነበር፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የአባላቱ ቁጥር እየበዛ ሲሄድና የ”ማህበሩ” አስፈላጊነት በተግባር እየታየ ሲመጣ መደበኛ አደረጃጀት እንዲይዝ ይደረጋል፡፡ በዚሁ መሰረት ‹‹ይቻላል የበጎ አድራጎት ማህበር›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ከትምህርት ቤት ውጭ ያሉ ሌሎች ሰዎችም ተካተውበት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል። ማህበሩ ከሲቪል ማህበራት ማደራጃ ባለስልጣን ፍቃድ ያገኝ ዘንድም ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ መሆናቸውን ጆን ይናገራል።
ማህበሩ እስከ አሁን ድረስ ገቢው የተመሰረተው ከአባላቱ በሚያገኘው መዋጮ ብቻ ነው፡፡ የማህበሩ አባላት ቀደም ሲል የሚሰባሰቡት ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ አሁን ግን አንዳንዶቹ ትምህርታቸውን በመጨረሳቸው ምክንያት በየአስራ አምስት ቀኑ የሚሰባሰቡት በአዳማ ፖስታ ቤት በር ላይ ነው፡፡ ሁሌም በስብሰባቸው ቀን አባላቱ ከቤታቸው የበሰለ ምግብ በፌስታል እየቋጠሩ በመምጣት ለጎዳና ተዳዳሪዎች ከሰጡ በኋላ በቀጣይ ስለሚሠሩት ሥራ ተነጋገረው ይለያያሉ፡፡
በተለይም በለጋ እድሜ ውስጥ ሆነው ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ልጆችን እየተከታተሉ ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ትኩረታቸው ነው፡፡ ወላጅ አልባ ለሆኑትም እስከ ሁለት ሺህ ብር የሚገመት ሸቀጥ ማለትም ሶፍት፣ ማስቲካ ሞባይል ካርድ፣ የታሸጉ ምግቦችን ወዘተ ገዝቶ በመስጠት እየነገዱ እራሳቸውን እንዲረዱ ያደርጓቸዋል፡፡
ይቻላል የበጎ አድራጎት ድርጅት ወደፊት ትልቅ ማእከል ገንብቶ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመርዳት እቅድ እንዳለው የማህበሩ ሰብሳቢ ጆን ይናገራል፡፡ በተለይም በለጋ እድሜያቸው ለጎዳና ሕይወት የሚጋለጡ ህጻናት ላይ በማተኮር በሱስ ከመጋለጣቸውና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት የተሻለውን አማራጭ እንዲከተሉ በስነ ልቦና ምሁራን የታገዘ ድጋፍ የማድረግ ዓላማ አላቸው፡፡
ለዚህም የሚመለከተው የመንግሥት አካል የቦታ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር መቀነስ የሚቻልበት አንዱ መንገድ እንዲህ አይነት ሥራዎችን መሥራት ሲቻል በመሆኑ መንግሥት በዚህ ዘርፍ ለሚሰማሩና ለሚሰሩ ድርጅቶች (ግለሰቦችም ጭምር) እገዛ ቢያደርግ ችግሩን መቀነስ እንደሚቻል ጆን ይናገራል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም የወጣቶቹ ቅን አስተሳሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያገኝ የተለያዩና ውስብስብ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅምን በመገንባት የማህበረሰብ አለኝታ ይሆናል የሚል እምነት ያለን መሆኑን በመጠቆም ዝግጅቱን እናጠናቅቃለን፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም