ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁነቶች መከናወናቸው ይታወቃል። መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሰራባቸው ሥራዎች መካከል የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚያስችል የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት አንዱ ነው። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እንዲለማ ሲሰራ መቆየቱም አገሪቷ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ አቅም መሸፈን እንድትችል ታሳቢ በማድረግ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከውጭ ለምታስገባው ስንዴ ከ710 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታደርጋለች። ታድያ ይህን ወጪ ከማስቀረት ባለፈ በምግብ እራስን መቻልና ለውጭ ገበያም ጭምር ማቅረብን ታሳቢ በማድረግ የበጋ መስኖ ስንዴ በስፋት እየለማ ይገኛል። ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከውጭ አገር ከሚገባው 34 በመቶ ያህሉን ያስቀራል ተብሎም ይጠበቃል።
በተለይም በመስኖ ልማት፣ አሲዳማ አፈርን በማከም፣ ኮትቻ አፈርን በማንጣፈፍና ግብዓት ጨምሮ በማረስ የተሻለ ምርት ለማግኘት ሰፋፊ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን ባለፉት ሶስት ዓመታትም በአዋሽ፣ በሸበሌና በኦሞ ተፋሰስ ቆላማ አካባቢዎች ስንዴ የማምረት ሥራ ተጀምሯል-። ብዙ ሲነገርለት የቆየው የበጋ ስንዴ ምርት በርካታ ሂደቶችን በማለፍ ፍሬ አፍርቶ ጉዞውን ከእርሻ ወደ ጉርሻ ባደረገበት በዚህ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው የገበያው ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
በአገሪቱ የሚገኙት የግብይት ተዋናዮች በተለይም ህገወጥ የግብይት ስርዓትን የሚከተሉ ነጋዴዎች ሕጋዊ መንገድን በመከተል መታረም ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ አርሶ አደሩ ለፍቶና ደክሞ ባመረተው ምርት ሌሎች ምንም አይነት ድርሻ ያልነበራቸው ህገወጥ ነጋዴዎች የሚከብሩበት እንደሆነ አንስተው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት በአግባቡ ለገበያው ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን የሕብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው ይናገራሉ።
አርሶ አደሩ ለምርቱ ፍትሐዊ ዋጋ እያገኘ ካለመሆኑም ባለፈ ተጠቃሚውም በምርት ዋጋ መናር የኑሮ ውድነቱ ተጭኖት እያማረረ ያለው በዋናነት በግብይት ሥርዓቱ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ይሁንና የግብይት ስርዓቱን ለማስተካከል የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ተቀናጅተው ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው። በተለይም የግብርና ምርት ግብይት ላይ ያለውን ችግር በመፍታት አርሶ አደሩንና ሸማቹን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን በአሁን ወቅት እየተሰበሰበ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ጤናማ በሆነ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ማለፍ እንዲችል የኅብረት ሥራ ማህበራት እና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ መንግሥት የአገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ለማሟላት እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን፤ በተያዘው የምርት ዘመን ብቻ በ404,900 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ የስንዴ ምርት እየተመረተ ይገኛል። ከእዚህም 16 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት የሚጠበቅ ይሆናል። ከዚህ የስንዴ ምርት ውስጥም ለገበያ የሚቀርበው ዘጠኝ ነጥብ 63 ሚሊዮን ኩንታል ነው።
ለገበያ በሚቀርበው ምርት የአምራች አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኅብረት ሥራ ማህበራት ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑን ነው የገለጹት። የኅብረት ሥራ ማህበራቱም የተመረተውን የስንዴ ምርት ለማሰባሰብ ይቻላቸው ዘንድ ልዩ እቅድ አዘጋጅተው የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በዋናነት በበጋ መስኖ ልማት ተመርቶ ለገበያ ከሚቀርበው የስንዴ ምርት ውስጥ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል በኅብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ማሰባሰብ፤ የግብይት ፋይናንስ አቅርቦት ችግር ላለባቸው የኅብረት ሥራ ማህበራት ደግሞ ሶስት ቢሊዮን ብር ብድር ማግኘት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም በኅብረት ሥራ ማህበራት የተሰባሰበውን የስንዴ ምርት በቀጥታ ከአገራዊ ገዥዎች ጋር የግብይት ትስስር እንዲፈጠር የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ ።
በተያያዘም የስንዴ ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የስንዴ ምርት ፍላጎታቸውን በማወቅ በስንዴ ምርት ግብይት የሚታየውን አላስፈላጊ የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር የአምራች ኢንዱስትሪ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ። በመሆኑም በግብይት ትስስር አፈጻጸም ሂደቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በገበያው የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ይፈታል።
የአገሪቷን ልማት ለማፋጠን፣ የሕዝቡ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የተረጋጋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ያለው ህብረተሰብ ለመፍጠር ቁልፍ ተልዕኮ ያላቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርናው ዘርፍም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ይጠቅሳሉ።
የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን በማሰባሰብ እና እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አምራች አርሶ አደሩ የምርቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግም ጉልህ ድርሻ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁን ወቅት እየተሰበሰበ ካለው የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ጋር ተያይዞ ዋጋውን አስመልክቶ ገበያው ምን እንደሚመስል ላነሳነው ጥያቄ ዳይሬክተሯ ሲመልሱ፤ የስንዴ ምርትም ሆነ ሌሎች ምርቶች ነጻ ገበያ በመሆኑ የገበያውን ዋጋ እያስቀመጠ ያለው ገበያው ነው ብለዋል።
ይሁንና አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት አከማችቶ የሚያቆይበት መጋዘን የሌለው በመሆኑ በቶሎ ይሸጣል። ይህ ሁኔታ ደግሞ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ አያደርገውም። ስለዚህ አርሶ አደሩ ምርትን እንደተመረተ ከመሸጥ ይልቅ ምርቱን አቆይቶ መሸጥ እንዲችል የማከማቻ መጋዘኖችን የማመቻቸት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፋፊ የበጋ መስኖ እርሻ ተመርቶ የደረሰው የስንዴ ምርት በግብይት ሰንሰለት ውስጥ እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥ ፍጆታ በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲሆን ወሳኝነት ካላቸው አካላት መካከል የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤቶች አንደኛው መሆናቸውን የገለጹት በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ኡመድ ናቸው።
መንግሥት የአገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ለማሟላት እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በማስቀረት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን በተለያዩ ወቅቶች እየተካሄደ ከሚገኝ የስንዴ ልማት ሥራ በተጨማሪ የበጋ ወቅት የመስኖ ስንዴ ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅትም የሥራው ፍሬ ጎምርቶ ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።
አገሪቷ ካላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አንጻር ሰፊ የስንዴ ምርት ፍላጎት እንዳለ የሚታወቅ ቢሆንም ይህን ሰፊ የስንዴ ፍላጎት ለማርካት በበጋ የመስኖ እርሻ የተመረተው የስንዴ ምርት በአግባቡና በአጭር የእሴት ሰንሰለት ለተጠቃሚው ማህበረሰብና እሴት ለሚጨምሩ የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የግብርና ምርቶችን በማሰባሰብ እና ገበያ በማፈላለግ አምራች አርሶ አደሩም ሆነ ተጠቃሚው ማህበረሰብ በፍትሃዊነት የምርቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የኅብረት ሥራ ማህበራት ጉልህ ድርሻ አላቸው።
በዚህም መሰረት የኀብረት ሥራ ማህበራቱ በበጋ መስኖ የተመረተውን የስንዴ ምርት በመሰብሰብ ያለምንም ህገወጥ አዘዋዋሪዎች የገበያ ትስስር ፈጥረው ምርቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለአገር ውስጥ ገዢዎች ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠውና በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ገበያ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች በሚገኙ 47 የኅብረት ሥራ ዩንየኖች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር በበጋ መስኖ ልማት ተመርቶ ለገበያ ከሚቀርበው የስንዴ ምርት መካከል አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በእነዚሁ የኀብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለሀገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለው ጤናማ ያልሆነ የገበያ ስርዓት የምርት ግብይትና ተደራሽነትን እያዛባና እያመሰቃቀለ እንደሆነ ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በዚህ የተዛባ የገበያ ስርዓትም አርሶ አደሩ እና ተጠቃሚው ማህበረሰብ ተጎጂ አካላት ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩ ምርት ለጥቂቶች ሲሳይ የሚሆንበት የግብይት አሰራርን በማክሰም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ኀብረት ሥራ ማህበራት እና የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤቶች ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም በበጋ መስኖ ምርት የተገኘው የስንዴ ምርት ምርታማነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የአገር ውስጥ ፍላጎትን በአግባቡ በማርካት መንግሥት የወጠነውን ትልም ማሳካት እንዲቻል የአምራች አርሶ አደሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ይኖርበታል።
ስለሆነም አንድም ኩንታል ስንዴ ቢሆን እንኳን ያለአግባብ በህገወጥ ነጋዴዎች እጅ እንዳይገባ በጥንቃቄ መሥራትና ዓላማውን ከግብ ማድረስ ከእያንዳንዱ ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የኀብረት ሥራ ማህበራትና የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የአቅርቦት ፍላጎት፣ ጥራትና ጊዜን መሰረት ያደረገ ቀጥተኛ የግብይት ትስስርና ውል በመፈጸም የተሳለጠና ቀጣይነት ያለው የግብይት ስርዓት እንዲፈጠር በታማኝነትና በቅንነት ተወያይቶ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በመጨረሻም መንግሥት በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ያለ ቢሆንም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ሲሆን አይታይም። ለዚህም በአገሪቱ ያለው የግብይት ሥርዓት ህገወጥና ጤናማ የግብይት ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ በስፋት ይነገራል። ይህም መንግሥትን አመድ አፋሽ ከማድረግ ባለፈ ማኅበረሰቡም እንዲማረር አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በመሆኑ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ከሚሰራቸው ሥራዎች በተጨማሪ በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊውንና ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ጤናማ የግብይት ሥርዓትን መገንባት ምርጫ የሌለው አማራጭ ነው በማለት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2014