ክፍል ሁለት
ባለፈው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በጉለሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 01 የቤት ቁጥር 875 ጋር በተያየዘ የተፈጠረን ውዝግብ መሰረት አድርገን «ገላጋይ ያጡ ወንድማማቾች» በሚል ርዕስ አንድ የፍረዱኝ ዘገባ መስራታችን ይታወሳል፡፡
በዘገባው መጨረሻ ላይ እንደገለጽነው ዘገባው ክፍል ሁለት እንዳለውና በጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ ይዘን እንደምንቀርብ ቃል ገብተን ነበር፡፡ በገባነው ቃል መሠረት በዛሬው ዝግጅታችን ጉዳዩ የሚመለከታቸው አቤቱታ አቅራቢ በደል ፈጽመውብኛል ያሏቸውን አቶ ጥላሁን ሃይሌ፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 የመሬት ልማት አስተዳደር ያገኘናቸውን ሰነዶች እና የጉለሌ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ያገኘነውን መልሶች ይዘን ቀርበናል፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከሰነዶች እና ከሰዎች በጥልቀት መርምሮ ያገኛቸውን መረጃዎች እነሆ ብሏል፡፡ ህዝቡም ከሰው እና ከሰነድ የተገኙትን መረጃዎችን በማንበብ የግራ ቀኙን አይቶ የራሱን ፍርድ ይስጥ ፡፡ መልካም ንበብ ፡፡
ከቤት ቁጥር 875 ጋር ተያይዞ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት መካከል የአቤቱታ አቅራቢው በደል ፈጽመውብኛል ያሏቸው አቶ ጥላሁን ኃይሌ የተባሉት ግለሰብ አንዱ ናቸው፡፡ ግለሰቡ በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ቤት ቁጥር 875 ነዋሪ ሲሆኑ፤ ጉዳዩን በሚመለከት ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገናል፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከአቶ ጥላሁን ኃይሌ ጋር ያደረጋቸው ጥልቅ ምርመራዎች ዝግጅት ክፍሉ ጉዳዩን ከስሩ በማጣራት ለህዝብ በጥልቀት ለማስረዳት በማሰብ አቤቱታ ከቀረበባቸው ከአቶ ጥላሁን ኃይሌ ጋር በጥልቀት ተነጋግሯል፡፡ ንግግራችንም ክርክሮች የተስተዋለበት እና የምርምራ አካሄድ የተንጻበራቀበት ነበር ፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከአቶ ጥላሁን ጋር የነበረውን ምርመራ የቤት ቁጥር 875 የሚገኝበትን ቦታ እና የቤት ቁጥር 875 ቤተሰብዎት እንዴት አገኙት (በምሪት፣ በይዞታ፣ በዳረጎት) ? በሚል የጀመረ ነበር። ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ጥላሁን እንደገለጹት፤ በቀደመው ጊዜ ሰዎች ባዶ ቦታዎችን ሲያገኙ ባገኙት ባዶ ቦታ ላይ ቤት ይሰሩ ነበር፡፡ የአቶ ጥላሁን ቤተሰቦች በቀደመ ጊዜ ማንኛውም ሰው ያደርግ እንደነበረው በሽሮ ሜዳ አካባቢ የሚገኝ ባዶ ቦታ ባገኙ ጊዜ ባገኙት በባዶ ቦታው ላይ ቤት ሰርተው ተቀመጡ። በዚያው በሰሩት ቤት ለዓመታት ኖሩ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰነድ አልባ ቤቶች ጋር በተያያዘ በመንግስት የተለያዩ መመሪያዎች ወጡ፡፡ ይህን መመሪያ ተከትሎ ሰነድ አልባ ቤቶች ካርታ እንዲሰራላቸው ሆነ፡፡
የአቶ ጥላሁን እናት ወይዘሮ በላይነሽ አስፋውም የቦታውን ካርታ በዚያ መልኩ አገኙ፡፡ ቤቱ በ000 ቅጽ ላይ የተመዘገበ ኪራይ ቀመስ እንጂ በወይዘሮ በላይነሽ ስም አልተመዘገበም የሚሉ የሰነድ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ስለነዚህ ሰነዶች ምን ይላሉ? የሚለው ጥያቄ ከዝግጅት ክፍሉ ለአቶ ጥላሁን ኃይሌ ጥያቄ ቀረበ። ለዚህ ምላሽ የሰጡት አቶ ጥላሁን እንዳመላከቱት፤ የማንኛውም ሰው ይዞታ በቅጽ 000 ሊመዘገብ ይችላል።
ኪራይ ቀመስ የሚል ካለ ግን ከወረዳ ወይም ከክፍለ ከተማው የባህር መዝገቡን አውጥቶ በማየት ማረጋጋጥ ይቻላል፡፡ ይህን ምላሽ ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 የቤት ቁጥር 875 በበላይነሽ አስፋው ስም ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም የአፈር ግብር እንደከፍሉ እና ቤቱም በአቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል የተመዘገበ እንደሆነ አቶ ኃይሌም ከአቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል እንደተከራዩ እንጂ አሁንም ቤቱ በቅጽ 000 ላይ ኪራይ ቀመስ መሆኑን የወረዳው ቤቶች አስተዳደር በቀን 01/06/2013፤ በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ1/አስ/ጽ/ቤት/457/2013 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል፡፡
ይህንኑ ደብዳቤ በማሳየት ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል ጠየቀ፡፡ ይህን ጥያቄ ተከትሎ ቤቱ ቅጽ 000 ላይ ከተመዘገበ ቀበሌ የኔ ነው ማለት ነው እንጂ የሚገባው የአከራይ እና የተከራይ ግለሰቦችን መጥቀስ እንደሌለበት አቶ ጥላሁን ይገልጻሉ፡፡
ቀደም ብለው 000 የሚለው ቅጽ ማንኛውም ሰው ይዞታ ላይ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በቅጽ 000 የመንግስት ቤቶች አስተዳደር እንጂ የአከራይ እና የተከራይ የግለሰቦች ስም መጠቀስ የለበትም ይላሉ፡ ፡ ይህ መጀመሪያ ከተናገሩት የሚጋጭ አይደለም ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ አቶ ጥላሁንን ጠየቀ፡፡ በባህር መዝገቡ አቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል አከራይ፤ አቶ ሃይሌ ወልደ ተክሌ ደግሞ ተከራይ የሚል ሰነድ የለም፡፡ ይህ ማስረጃ የእናት ማህደሩን ካለ አቅርቦ መመርመር እንደሚገባ አቶ ጥላሁን ይናገራሉ፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ስለዚህ የእርስዎ አባት አቶ ኃይሌ ምን የተከራዩት ቤት አልነበረም ? ሲል አቶ ጥላሁንን ጠየቀ፡፡ አቶ ጥላሁንም አባቴ ከማንም ቤት አልተከራየም፡፡ መረጃው ውሸት ነው በማለት መልሰዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በከፍተኛ ጥረት የቤት ቁጥር 875ን የእናት ማህደር በመመርመር አቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል አከራይ፤ አቶ ሃይሌ ወልደ ተክሌ ደግሞ ተከራይ የሚል ሰነድ ከእናት ማህደሩ ማግኘት ችሏል፡፡ ውድ አንባቢያን እዚህ ላይ ፍርዱን ለእናተው ትቸዋለሁ፡፡ በቦታው የአፈር ግብር ከመክፈል ጋር ተያይዞ ሁለት የተጣረሱ ዓመተ ምህረቶች መኖራቸውን ከሰነዶች አግኝተናል፡፡ አንደኛው 1985 ዓ.ም ይላል፤ ሌላኛው ደግሞ 1998 ዓ.ም መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል ዝግጅት ክፍላችን ለጠየቃቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ጥላሁን እንደገለጹት፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የሚለው ማስረጃ ውሸት ነው፡፡ ትክክለኛው ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የሚለው ነው፡፡ የቤት ቁጥር 875 እና ቦታው ወደ ግል ይዞታ መቼ ዞረ ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ አቤቱታ የቀረበባቸውን ግለሰብ ይጠይቃል፡፡
ግለሰቡም መጀመሪያ ላይ ቤተሰቦቻቸው ለቤተ ክርስቲያን ግብር እየከፈሉ ቦታውን ያስተዳድሩት እንደነበር እና ቦታው ከቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲዞር ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የአፈር ግብር እየከፈሉ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ከአደጉ በኋላ ቤቱ የአባት እና የእናቴ መሆኑን እንጂ ቦታው መቼ ወደ ግል ይዞታነት እንደዞረ ግን እንደማያውቁ ይናገራሉ። ዝግጅት ክፍሉ የቤቱን ካርታ እንዴት እንዳገኙ በጠየቀ ጊዜ፤ ካርታ ያገኙት እንደማንኛውም ሰው በውዝፍ ፕሮጀክት ታይቶ መሆኑን እና የወረዳው ፕሮሰስ ካውንስል አጣርቶ፣ የካቢኔ አባላት በአካል ቦታው ድረስ በመውረድ ቦታው የቀበሌ ቤት አለው ? ወይስ የለውም ? የሚለውን አይተውና አጣርተው ካርታ መስጠታቸውን ይናገራሉ፡፡
እዚህ ላይ ውድ አንባቢያን አንድ ነገር ማለት እወዳለሁ፡፡ ይህም ቦታው በይዞታ የአፈር ግብር ሲከፈልበት የቆየ ነው እያሉ በተመሳሳይ ድግሞ በወረዳው ፕሮሰስ ካውንስል ታይቶ ነው የተሰጠን ማለት ከመመሪያ ውጭ ነው፡፡
ፕሮሰስ ካውንስል መቼ ነው በጋራ ተወያይቶ ቦታዎችን የሚፈቅድ ከተባለ ሰነድ አልባ ቤቶችን አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀዱ የተያዙ ቦታዎችን ለግለሰቦች ለማስተላለፍ በሚደረግ ሂደት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በይዞታ ተይዘው በቆዩ እና የአፈር ግብር በሚከፈልባቸው ቦታዎች ፕሮሰስ ካውንስል ውሳኔ ሊያሳርፍ አይችልም፡፡
ነገር ግን የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከቤት ቁጥር 875 በባህር መዝገብ ውስጥ አለመኖሩን ያረጋገጠውን አንድ ሰነድ አቤቱታ የቀረበባቸው ግለሰብ ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ዝግጅት ክፍሉ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አንድ ሰው አነጋግሮ ነበር፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኚህ ግለሰብ እንደተናገሩት መረጃው ስህትተ እና የተጭበረበረ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
ውድ አንባቢያን፣ በፕሮሰስ ካውንስል የተወሰነ ነው ተብሎ ለዝግጅት ክፍሉ የቀረበው ሰነድ በባህር መዝገቡ ያልተገኘ ነው፡፡ የቤቶች አስተዳደር ቤቱን ኪራይ ቀመስ ነው እያለ እንዴት ቦታውን ሊያገኙ ቻሉ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ አቤቱታ የቀረበባቸውን ግለሰብ ይጠይቃል፡፡ ግለሰቡም
ቤቱ ኪራይ ቀመስ ነው ተብለው በወረዳው የተጻፉት ደብደቤዎች ስህተት ናቸው፡፡ ይህ የቤቶች አስተዳደር ደብዳቤ ስህተት መሆኑ ታይቶ መታረሙን ይናገራሉ። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የወረዳው የቤቶች አስተዳደር የነበረበትን ስህተት አርሞ የፃፈውን ደብዳቤ አቤቱታ ለቀረበባቸው ሰው አሳየ፡፡
ደብዳቤውም የአፈር ግብር እንደሚከፍሉ እንጂ እስካሁን በ000 የተመዘገበ እና ኪራይ ቀመስ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ ጠየቀ፡፡ ግለሰቡም ይህን የጻፈው ግለሰብ ኪራይ ቀመስ ስለመሆኑ ከባህር መዝገቡ ሰነድ አምጣ ተብሎ ቢጠየቅ ሰነድ የለውም ሲሉ መልስ ሰጡ። ዝግጅት ክፍሉም ሰነድ አለመኖሩን እንዴት አወቁ? ሲል ጠየቀ፡፡ ግለሰቡም በቃ አውቃለሁ ሲሉ መለሱ፡፡
ወረዳው የጻፋቸውን ደብዳቤዎች የጻፉ ሰዎች መንግስት ስራውን ለማቀላጠፍ እና ለህዝብ ለማገልገል ያስቀመጣቸው ሰዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነኝህ ሰዎች ይህን ደብዳቤ ከምንም ተነስተው ነው የጸፉት እያሉ ነው? ሲል ዝግጅት ክፍሉ ግለሰቡን ጠየቀ፡፡ ግለሰቡም አዎ የሚል መልስ ሰጡ፡፡
ዝግጅት ክፍሉም ከምንም ተነስቶ ስማችሁን ሲያጠፋ ኃላፊዎችን በህግ ለምን አልጠየቃችሁም? ሲል ግለሰቡን ጠየቀ። ግለሰቡም ሁኔታውን አይተው ዝም እንዳላሉ እና ደብዳቤውን የጻፉ ሰዎችን በህግ ለመጠየቅ ሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌላው ዝግጅት ክፍሉ ለአቶ ጥላሁን ያቀረበው ጥያቄ እርስዎ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ አንድ በፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ይሰሩ እንደነበር እና ቤቱን ወደ ግል ይዞታ ያዘዋወሩት በወረዳው ያለዎትን ስልጣን ተጠቅመው እንደሆነ አቤቱታ አቅራቢው ይናገራል፡፡ ስለዚህ ምን የሚሉት ነገር አለ? የሚል ነበር፡፡
ግለሰቡም ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ተቀጥረው እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ አይደለም በፖለቲካው ዘርፍ ይቅረና ወረዳ ውስጥ አንድም ቀን ሰርተው እንደማያቁ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በወረዳው የምክር ቤት አባል በመሆን ማገልገላቸውን ገልጸዋል ፡፡ በአካባቢዎት የሚኖሩ ሰዎች ቤቱ የቀበሌ ቤት ሆኖ ለቀበሌ ኪራይ ሲከፈልበት እናውቃላን ይላሉ። ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ ጠየቀ፡፡ ግለሰቡም ይህ ከእውነት የራቀ ስም ማጥፋት መሆኑን ይናገራሉ። በቁጥር 875 የተመዘገበው ቤት በ47/67 አዋጅ ተወርሶ እንጂ ከመወረሱ በፊት ቤቱን በጠብቁልኝ ለእነ ወይዘሮ በላይነሽ ሰጥተናቸው ነበር የሚሉ የአቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል ቤተሰቦችም አሉ፡፡
ስለዚህ ምን ይላሉ? አቤቱታ የቀረበባቸው ግለሰብም የአቶ ግርማ ወልደ ገብርኤል ቤት መንግስት ወርሶት የቤት ቁጥር 878 ተብሎ ስያሜ ተሰጥቶት ቀበሌ እያስተዳደረው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የካቲት 30 በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፍረዱኝ አምድ ላይ የተመለከተው በቀን 27/11/2013 ዓ.ም በቁጥር 01/ ቤ/አስ/035/2013 የተጻፈው ደብዳቤ ጋር ተያይዞ ቅሬታ አለኝ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ደብዳቤ ምን ይላሉ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ ግለሰቡን ጠየቀ፡፡ ይህ ደብዳቤ መጀመሪያ ሲጻፍ ስህተት ነው።
ሁለተኛ ይህንን ደብዳቤ ጻፈ የተባለው የጽህፈት ቤት ኃላፊ መዝገቦችን እና ፋይሎችን ሳያይ ዝም ብሎ በቀረበለት ማስረጃ ነው የጻፈው እንጂ ትክክለኛ ዶክመንት የለውም። ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ኃላፊው የጻፈው ትክክለኛ ዶክመንት ከእናት መዝገቡ (ከባህር መዝገቡ) ቢገኝ እርስዎ ኃላፊነት ይወስዳሉ? ሲል ጠየቀ፡፡ በባህር መዝገቡ መረጃው ከተገኘ በሚገባ ኃላፊነት እወስዳለሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ የሚጻፉ ተባራሪ ደብዳቤዎችን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል፡፡
የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች የጻፉት ደብዳቤ የመንግስት ማህተም አለው፤ ቁጥርም ተሰጥቶታል ይህንን መረጃ አምነን መቀበል ካልቻልን ምን አይነት ማስረጃዎችን ማመን እንችላለን? ይህን ሊያስረዱኝ ይችላሉ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ ይጠይቃል፡፡
ግለሰቡም ምንም አይነት ቁጥር እና ማህተም ቢኖረው ከባህር መዝገቡ ኮፒ ተደርጎ እስካልመጣ ድረስ እንደማይቀበሉት ይገልጻሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌ ክፍለ ከተማ የውዝፍ ስራዎችና ሬጉላራይዜሽን ፕሮጀክት ዴስክ በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ው/ይ/ሬ/ፕ/ዴስክ/10169/2004 በቀን 8/9/2004 ዓ.ም የጻፈውን ደብዳቤ እንደማይቀበሉ ጠቅሰዋል ሲል ዝግጅት ክፍሉ አቶ ጥለሁንን አስታውሶ ነበር፡፡ አቶ ጥላሁንም በድጋሚ ደብዳቤውን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት ያነሱት ደግሞ ከውዝፍ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ብዙ ወረቀቶች እየተጣሉ ይገኙ ስለነበር ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ አባሪ የሌለው እና ደብዳቤዎችን የጻፉት ሰው ፊርማ የተለያየ ስለሆነ በደብዳቤውን እንደማያምኑበት ገልጸዋል፡፡ ውድ አንባቢያን እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ይህም ቤቱ የተሰጣቸው በውዝፍ ፕሮጀክት ታይቶ እንደሆነ ከላይ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የውዝፍ ፕሮጀክት የጻፈውን ደግሞ እንደማይቀበሉት ይናጋራሉ፡፡ በ1958 ቤቱን ቤተሰብዎት በይዞታነት እንደተረከቡት የሚያሳይ አንድ የተጭበረበረ ሰነድ አለ፡፡ ስለዚህ ሰነድ ምን ይላሉ? ሲል ዝግጅት ክፍሉ ጠየቀ፡፡ ግለሰቡም ስለዚህ ሰነድ በፍጹም የሚያውቁት ነገር እንደለሌ ጠቁመው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ባህር መዝገቡ ይበርበር። ይህ ዶክመንት በባህር መዝገቡ አይገኝም፡፡
ይህ ሰነድ በባህር መዝገቡ ወይም እናት ማህደሩ ውስጥ ከተገኘ « ይህን ሰነድ እኔ አስገብቼው ሊሆን ስለሚችል እኔም ተጠያቂ መሆን አለብኝ፡፡» ሲሉ መልሰዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የዝግጅት ክፍሉ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ የተጭበረበረ ነው የተባለው ሰነድ ከባህር መዝገቡ ለማግኘት ችለናል፡፡ እዚህ ላይ ፍርዱን ለአንባቢያን ትቼዋለሁ፡፡ መቼ ነው ቤተሰብዎት ቦታውን የያዙት ? የሚል ጥያቄ በጠየቅን ጊዜ እርግጠኛ መሆን ያልቻሉት ግለሰቡ በግምት በ1964 ዓ.ም አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች ከሁሉም በፊት የሰነድ ማስረጃዎች ብለን ያቀረብናቸው ሰነዶች በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በቤት ቁጥር 875 የባህር መዝገብ ተመዝግቦ ከሚገኝ ሰነድ የተገኙ መሆናቸው ይታወቅልን፡፡ አጠቃላይ ከሰነዶች የተገኙትን መረጃዎች ዘርዘር አድርገን ለማሳየት እንዲቻል ሰነዶችን ቁጥር ሰጥተን መመልከቱ ተገቢ ነው።
አንደኛ፡- በሰኔ 14 ቀን 1974 ዓ.ም፣ በሰኔ 23/1974 ዓ.ም እና በቀን 22/11/1977 ዓ.ም በተጻፉ ደብዳቤዎች ወይዘሮ በላይነሽ የተባሉት ግለሰብ ከሰዎች ጋር እንደተጣሉ እና የተጣሏቸው ሰዎችም የሚኖሩበትን የመንግስት ቤት በድንጋይ እየደበደቡ ሊያፈርሱባቸው ስለሆነ የመንግስት ቤቱ ከመፍረሱ በፊት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ የደርግ መንግስትን መጠየቃቸውን ያመላክታሉ፡፡
ሁለተኛ፡- በቁጥር ወ2/ወ11/01151/87 በቀን 8 ሰኔ ወር 1987 ዓ.ም በክልል 14 መስተዳድር የወረዳ 11 ቀበሌ 02 አስተዳደር ጽህፈት ቤት በተጻፈው ደብዳቤ እንደተመላከተው ወይዘሮ በላይነሽ የቤት ቁጥር 875 የሆነውን ቤት ለመጠገን እንዲፈቀድላቸው በደብዳቤ እንደጠየቁ እና በጠየቁት ጥያቄ መሰረትም አንደኛ የጠየቁት ቤት ጥገና መልክ እና ቅርጹን ሳይለውጥ፣ ሳይጠብ ሳይሰፋ ባለበት ሁኔታ ብቻ እንዲጠግኑ፤ ሁለተኛም ማዕድ ቤት ደግሞ ከቤቱ ርቀት ሳይኖረው መጠኑ ሶስት በአምስት ብቻ የሆነ ማዕድ ቤት ለመስራት ፈቃድ እንደተሰጣቸው ያመለክታል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ይህም እስከቅርብ ጊዜ አንድ ሰው መንግስት ያከራየውን ቤቱን ለማደስ የእድሳት ፈቃድ በጠየቀ ጊዜ ቤቱ በቅርጹ እና አጠቃላይ ይዘቱ ሳይቀየር እንዲጠገን ፈቃድ ይሰጥ የነበረው በመንግስት ስር ለሚተዳደሩ ለቀበሌ ቤቶች ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ቤቱ በማን ስር ሲተዳደር ነበር ለሚለው ጥያቄ ፍርዱን ለህዝብ እሰጣለሁ፡፡
ሶስተኛ፡- የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን በቁጥር 71ቅ/691/2000 በቀን 13/8/2000 ዓ.ም ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ለቀበሌ 19/20/21 ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ እንደተመላከተው የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀ19/20/21/6503 የካቲት 7 ቀን 2000 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ በጉለሌ ከፍለ ከተማ ቀበሌ 19/20/21 የቤት ቁጥር 875 በወረዳው ስር ለሚተዳደር የመንግስት ቤት አዲስ የመስመር ውሃ እንዲገባላቸው መጠየቃቸውን አስታውሶ ነገር ግን ቤቱን ወይዘሮ በላይነሽ አስፋው የተባሉ ግለሰብ ቤቱ የግላቸው እንደሆነ ስለጠየቁ ጉዳዩን ወረዳው አጣርቶ እንዲመለስላቸው የሚገልጽ ነው፡፡
ከላይ የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን እንደገለጸው የቤት ቁጥር 875 የመንግስት ቤት እንደነበር እና አዲስ የውሃ መስመር እንዲዘረጋ ወረዳው መጠየቁን አውስቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት ቤቱ የማን ነበር ? የሚለውን ፍርድ ለህዝብ ሰጥቻለሁ፡፡
አራተኛ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር እና ግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ጽህፈት ቤት በወረዳ የሚሞላ እና ለክፍለ ከተማ የሚላክ የይዞታና ቤት ቅድመ ማጣሪያ በወረዳ አንድ የተሞላው ቅጽ እንደሚያመላክተው ቦታው ቅጽ 000 እንዳለው፣ ቦታው የተሰጠበት (የተገኘበት) አግባብ መረጃ የሌለው መሆኑን ወረዳው በሞላው ቅጽ ተመላክቷል፡፡
አምስተኛ፡- በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዲዛይንና ግንባታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ1/ኮ/ ል/ጽ 2726/04 በቀን 17/09/2004 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለወረዳ አንድ ስራ አስኪያጅ በጻፈው ደብዳቤ እንደተመላከተው በቀድሞው ወረዳ 11 ቀበሌ 02 የቤት ቁጥር 875 ቅጽ 000 የሚያሳይ እና አቶ ሃይሌ ወልደ ተክሌ ጎሳ በሚል የተመዘገበ እና ኪራይ የሚያሳይ እና የአከራዩ ሰው ስም አቶ ግርማ ወ/ገብርኤል በሚል የተመዘገበ ነገር ግን በመንግስት ቤቶች ዝርዝር ላይ የሌለ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ እዚህ ላይ ቤቱ በይዞታ ወይዘሮ በላይነሽ ሲያስተዳ ድሩት ነበር የሚለውን ተቃርኖ እናገኛለን ፡፡ የሆነው ሆኖ ፍርዱን ለህዝብ ትቻለሁ፡፡
ስድስተኛ፡- ይህ ሰነድ አቶ ጥላሁን በማህደሩ ውስጥ ከተገኘ ልጠየቅብት ያሉት ሰነድ ነው፡፡ ይህ ሰነድ በቁጥር ከ/ል/ሚ/68342/06/79 በቀን 11/16/79 በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የተጻፈ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይህ ደብዳቤ ግማሹ በኮምፒውተር ግማሹ ደግሞ በታይፕ ራይተር የተጻፈ ነው፡፡ እዚህ ላይ ህዝብ እንዲገነዘበው የምፈልገው ነገር በ1979 ዓ.ም በኢትዮጵያ የነበረው የመንግስት አወቃቀር አሀዳዊ እንጂ ፌዴራላዊ መንግስት አለመሆኑን ነው፡፡
በዚህ ሰነድ እንደተመለከተው ቤቱ በወይዘሮ በላይነሽ የተመዘገ ስለመሆኑ እና የቦታው ስፋቱም 1ሺ 200 ካሬ ሜትር መሆኑን እና ከ1958 ጀምሮ በመዝገብ ቁጥር 682/42/06 እንደተመዘገበ የሚያሳይ የተጭበረበረ ሰነድ ነው፡፡ ይህ ሰነድ በእናት ማህደራቸው ከተገኘ አቶ ጥላሁን ልቀጣ ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀደም ብለው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሰባተኛ፡- ወይዘሮ በላይነሽ አስፋው በቀን 6/10/1975 ዓ.ም ለከፍተኛ 11 ቀበሌ 02 ጽህፈት ቤት የጠየቁት ማመልከቻ እንደሚያመለክተው ወይዘሮ በላይነሽ በቤት ቁጥር 875 ነዋሪ እንደሆኑ ገልጸው፤ በቀበሌው ምንም አይነት ቅርስ እንደሌላቸው፤ ገንዘብ የሚሰጣቸው እና የሚረዳቸው ሰው እንደሌለ ገልጸው መንግስት ለየካቲት 12 ሆስፒታል በነጻ የሚታከሙበትን እድል እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡
በዚህ ሰነድ እንደምናየው ወይዘሮ በላይነሽ በቀበሌው ምን አይነት ቅርስ እንደሌላቸው ነው፡፡ ቤት ደግሞ ቅርስ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ እዚህ ላይ አሁንም ቤቱ የማን እንደሆነ ፍርዱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትቸዋለሁ፡፡
ስምንተኛ፡- በቀን 27/3/79 አቶ ተሾመ ኃይሌ ለከፍተኛ 11 ቀበሌ 02 የከተማ ነዋሪዎች ማህበር ጽህፈት ቤት ባመለከቱት ማመልከቻ እንደጠቆሙት በቤት ቁጥር 875 እንደሚኖሩ ገልጸው፤ ቤቱ ግን ጣራው ተቀዳዶ ለመኖር አስቸጋሪ በመሆኑ በቀበሌው የሚገኝ ግ12 የሚባል ቤት የተዘጋ ስላለ በዚህ ቤት እንዲኖሩ እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ያሳያል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ሰው የሚኖርበት ቤት የራሱ ከሆነ ለመንግስት ጣራው እያፈሰሰበት በመሆኑ መቸገሩን እና ቅያሬ ቤት እንዲሰጠው እንዴት ሊጠይቅ ይችላል ? ፍርዱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ትቻለሁ፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ምላሽ ከዚህ በፊት በገባነው ቃል መሰረት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ምላሽ ይዘን እንደምንቀርብ ገልጸን ነበር።
የገባነውን ቃል ለመፈጸም እና ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር በተደጋገሚ ተገኝተን ጉዳዩ ምን ደረሰ ስንል ጠይቀናል። በመጨረሻም በጉለሌ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር መንግስት ቤቶች ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ሃይለማሪያም ሲሳይን አነጋግረን የሚከተለውን ምላሽ ይዘናል፡።
በጉለሌ ከፍለ ከተማ በወረዳ አንድ የቤት ቁጥር 875 በተመለከተ ከዚህ በፊት የመጡ ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብለው ለሚያስቧቸው ተቋማት ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው በማሰብ ደብዳቤዎችን ጽፈው እንደነበር አቶ ኃይለማሪያም ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቤቶች አስተዳደር ውጭ በደብዳቤያቸው ምላሽ የሰጠ አካል የለም፡፡ በዚህም መስሪያቤታቸው ስለጉዳዩ ሙሉ መረጃ እንዳይኖረን አድርጓል፡፡
ስለሆነም ደብዳቤ የሰጧቸው ሁሉም መስሪያ ቤቶች የተጠናከረ መረጃ በሰጡ ጊዜ መረጃውን ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ይፋ እናደርጋለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህንን እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ችግሮች በሚፈጥረባቸው ቦታዎች ድረስ በመሄድ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም አመላክተዋል፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2014