ማንኛውም ሰው ሲወለድ ጀምሮ ስኬታማ ኑሮ መኖርን ብቻ ሳይህን ኑሮው ወርቅና ምቹ እንዲሆንለት ይመኛል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቻችን ግን ሕይወት ደስታና ኀዘን የሚፈራረቅባት የትግል ሜዳ እንደሆነች ሳንረዳ ነው ፍላጎታችንን ብቻ ይዘን የምንጓዘው። ይህ ደግሞ አወንታዊውን ብቻ ተመልካች እንድንሆን ያደርገናል። በፈተና ውስጥ ማለፍም ይሳነናል። ከፍ ያለ ችግር ሲገጥመን ለመቋቋም ይቸግረናል። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው አሉታዊ ነገሮች በሕይወታችን እንደሚገጥሙን አስቀድመን መረዳት ሲሆን፤ ይህም ከብዙ ነገሮች ይታደገናል። ከዚህ አኳያ ይመስላል ብዙ ጊዜ ጎዳና ላይ የተወለዱ ልጆች ከሌላው፣ ከእነሱ በተሻለ ከሚኖሩት ጠንካራ ሆነው የምናያቸው። በጤና ጭምር እንደነ’ርሱ ብርቱ የለም። ይህ ደግሞ የሚያሳየን አቢይ ጉዳይ ቢኖር “ችግር ያጸናል” ወይም “ችግር ብልሀትን ይፈጥራል” የሚለውን ነውና በሚቀጥሉት የመንደርደሪያ አንቀፆች ወደ ዛሬው እንግዳችን ታሪክ እንለፍ።
ተለምዶ ሁለት እሳቤዎችን ይዟል። የመጀመሪያው መልካም ልምምድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ውድቀትን የያዘ ልምምድ ነው። እናም እንደተለማመድነውና ለኑሯችን መሰረት እንዳደረግነው እሳቤ ሕይወታችን ይቃኛል። ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም፤ ሰው አዋዋሉን ይመስላል እና የመሳሰሉት ምሳሌያዊ አገላለፆችም ከዚህ አንጻር ለጥቅስ የሚበቁ ናቸው፡፡
በሕይወታችን ላይ እነዚህ ተግባራት እውን ሲሆኑ፤ ከሁለት አንዱን ማለትም ወይ ጠንካራ አለያም ደካማ ሆነን እንገኛለን። ልምምድ ኃይል እንደሆነም እንመለከታለን። ይህ የሚሆነው ደግሞ ኑሮዋችን ላይ ነው። በእርግጥ ሕይወትን መርጠን አንኖራት ይሆናል። ነገር ግን ከፍ ስንል በልምምዳችን የተሻለና ድል የሞላባት ማድረግ እንችላለን።
ልምምዳችንን ሥራ ተኮርና የማሸነፍ ባህልን የምናዳብርበት ካደረግነው ከአሸናፊነታችን ገሸሽ የሚያደርገን ምንም አይነት ኃይል አይኖርም። ተሸናፊነትን ከተለማመድነውና አዕምሯችንን ከሳመንነው ግን መነሻም ሆነ መድረሻ አይኖረንም። አብዛኛውንም ጊዜም ከስኬት ማማ ላይ ወዳቂዎች መሆናችን አይቀርም። “አደርገዋለሁ” ሳይሆን “አልችለውም” ቋሚ መርሃችን ይሆናል። በዚህም ጥንካሬያችን ቦታውን ለድክመታችን አስረክቦት ልፍስፍስ ሆነን እንቀራለን። እናም ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት በጥልቀት ማሰብ ይኖርብናል። ይህንን ሃሳብ ያነሳነው ያለምንም ምክንያት አይደለም። ለዛሬ ‹‹ለሕይወት ገጽታ›› አምድ የመረጥናቸው ወይዘሮ መብሪ አበራ ለዚህ ጥሩ ማሳያ በመሆናቸውና የእርሳቸውን የሕይወት ተሞክሮ ልናጋራችሁ በመፈለጋችን ነው።
ከመብሪ አበራ ሕይወት ቤተሰብ የሚሠጠንና የሚያለማምደን እንዲሁም እንድንኖርለት የሚፈቅድልንን የኑሮ ሁኔታና የእኛ ፍላጎት አለመጣጣም ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል እናይበታለን፤ በራስ ልምምድና ጥንካሬ ደግሞ ምን ምን ነገሮች መለወጥ እንደሚችሉም በሚገባ እንማርበታልን። ምክንያቱም እርሳቸው ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ቢያሳልፉም “አይቻልም” የሚባለውን አስተሳሰብ ጭምር ችለዋል። በተለይም ባለቤትን ከሱስ ጥገኝነት ማውጣት እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ቢታመንም እሳቸው ግን አድርገውታል። ከዚያም በተጓዳኝ ቤት ማስተዳደርን ገና በልጅነታቸው ቢጀምሩትም በሚገባ ተወጥተውታል። ይህና መሰል የሕይወት ተሞክሯቸው ብዙዎችን የሚያስተምር በመሆኑ ከሰፊ ተሞክሯቸው ልምድን ትቀስሙ ዘንድ አንብቧቸው ስንል ጋበዝናችሁ፡፡
የመጨረሻ ልጅነት
ተወልደው ያደጉት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሰላሌ ጅዳ ወረዳ፣ ስርጢ ከተማ ነው። አባታቸውን በልጅነታቸው ያጡ ሲሆን፤ በዚህም ብዙ ነገራቸው እንደተቀማ ይሰማቸዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱም ከእሳቸው ማግኘት የፈለጉትን እያገኙ አላማደጋቸው ነው። በተለይ የሚያዝኑት ትምህርት ቤት ወላጅ አምጡ ሲባሉ አባታቸውን ይዘው ባለመሄዳቸው ነው። ይሁን እንጂ እናታቸው ከአባታቸው በላይም ሆነው እንዳሳደጓቸው ያምናሉ። ምንም ጎሎባቸውም አያውቅም። ጠንካራ ተማሪና ጠንካራ ሴት እንዲሆኑ አድርገውም ነው ያሳደጓቸው። ይህ ደግሞ ለዛሬ ሕይወታቸው ብርታት እንደሆናቸው ያወሳሉ።
አብሪ እናታቸው አባትም ጭምር እንደነበሩ ያነሳሉ። ምክንያቱም 12 ልጆችን ሲያሳድጉ ያለአባት ማደጋቸውን እንዲያስቡት አላደረጓቸውም። ሁሉ ነገር በፕሮግራምና በሥርዓት መከናወን እንዳለበት እያሳዩ ጭምር ነው ያሳደጓቸው። እናታቸው የማይሰሩት ሥራ አልነበረም። ዋና መተዳደሪያቸው የሆነውን ግብርናን ሙሉ ለሙሉ ይከውኑታል። ከዚያ አልፈው አረቄና ጠላ እየሸጡ ቤቱ ምንም እንዳይጎድልበት ያደርጋሉ። ይህ ሲሆን ግን እንግዳችንም የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው። እንጀራና የአረቄ እንጀራ መጋገሩ፣ እንዲሁም አሻሮና እንኩሮ ማንኮሩ በዋናነት የሚተገብሩት ሥራ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የቤቱ የመጨረሻ ልጅ በመሆናቸውና ከእርሳቸው ከፍ ያሉት ልጆች ከበድ ያለውን ሥራ ስለሚከውኑ ለእርሳቸውም በአቅማቸው ይሆናል የተባለው የውጭ ሥራ ይሰጣቸዋል። ይህም ከብት ማገዱ ሲሆን፤ አጨዳና አረም በማረምም የሚያክላቸው የለም። ይሁን እንጂ በብዛት የከወኑት ተግባር ከብት የማገዱን ስራ እንደነበር ያነሳሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ምንም አይነት ሥራ ሥሩ ቢባሉ እንቢታን አያውቁምና እረፍት ሳይኖራቸው ጭምር የተባሉትን በፍጥነት ያከናውናሉ፤ ውጤታማም ይሆናሉ። በተለይ ለእናታቸው ፋታ ይሰጣል ብለው ያሰቡትን ተግባር መሥራት እጅጉን ያስደስታቸዋል። ከትምህርት ቤት መልስ ጭምር የማይሰሩት ሥራ የለም። ሥራውን ሲከውኑም አድምተው በመሆኑ ሁሉም ይደመምባቸዋል።
በባህሪያቸው እልኸኛ ልጅ በመሆናቸው ማንም እንዲነካቸው አይፈልጉም። በዚያው ልክ አልችለውም የሚል ነገርም የላቸውም። ይህ ደግሞ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ሥራ ሳይቀር እንዲከውኑ አስችሏቸዋል። የማይችሉትንና ከግብ አላደርሰውም ብለው የሚያስቡትን ተግባርም እንዳይጀምሩ አግዟቸዋል። ስለዚህም የጀመሩትን መጨረስ ልምድ ሆኖ አብሯቸው አድጓል፡፡
የወይዘሮ አብሪ ሙሉ ልጅነት ያለፈው በሁለት ተግባራት በመመስረት ላይ ሲሆን፤ እነሱም ትምህርት ቤት መሄድና የቤት ውስጥ ሥራን መከወን ናቸው። ከዚያ አለፈ ከተባለም ከብት ማገዱ ይካተታል። ይህ ደግሞ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ተጫውተው እንዳያድጉ አድርጓቸዋል። በዚህም ዝምተኛ ልጅ እንደነበሩ አጫውተውናል።
ልጅነታቸው ተስፋ ያለው ሰው እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውና ጥንካሬን እንዳላበሳቸው የሚያወሱት ወይዘሮ መብሪ፤ ለዚህ መሰረታቸው እናታቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ። እርሳቸው ሴት መሆን ለምንም ነገር አለመበገር እንደሆነ ኖረውት አሳይተዋቸዋል። በመሥራት መለወጥ እንደሚቻልም፤ ቤተሰብን ከማስተዳደር አልፎ ለሌሎች አርአያ ለመሆን እንደሚያበቃም ጭምር አረጋግጠውላቸዋል። ባለታሪካችንም ይህንን መሰረት ያለው ልምምዳቸውንና እድገታቸውን በመያዝ የዛሬውን ችግራቸውን ይፈቱ ዘንድ አስችሏቸዋል።
ከእናታቸው በተጨማሪ እንደእናት ሆና ያሳደገቻቸው እህታቸውም ለእርሳቸው ሌላዋ መምህርት ነበረች። ሁለተኛ እናታቸው ሆና አሳድጋቸዋለች። በተለይም የወንድ/የሴት ሥራ ሳትል መሥራቷ፣ በምንም አለመሸነፏ፣ “እችላለሁ” ማለቷና ማድረጓ ሁሌ እርሷን ለመሆን እንዲመኙ ያደረጋቸው ባህሪዬዋ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ወኔ ያላቸውና በሁሉም መስክ በልጠው የሚታዩ ልጅ እንዲሆኑ ብርታት ሰጥቷቸዋል። ነገር ግን በሁለት እናቶች እንዳደጉና ተሞላቀው ልጅነታቸውን እንዳሳለፉ ቢያምኑም ስለአባታቸው ደግነትና ሥራ ወዳድነት ሲሰሙ “ምነው ቢኖርልኝ” ማለታቸው አልቀረም። ምክንያቱም ከዚህ የበለጠ ቦታ ላይ እንደሚደርሱ ያስባሉና ነው።
ፈተና የተጋረጠበት ትምህርት
ስምንት ዓመታቸው ላይ ነበር ትምህርትን አሀዱ ብለው በዚያው በትውልድ ቀያቸው የጀመሩት። ትምህርት ቤቱ ሻምበል አበበ ቢቂላ ይባላል። እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስም ተምረውበታል። ነገር ግን ከስምንተኛ ክፍል በኋላ በትምህርታቸው የማይቀጥሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። ይህም በቤተሰብ የተመረጠላቸውን ባል በ16 ዓመታቸው እንዲያገቡ መደረጋቸው ነው። ይባስ ብሎ በ17 ዓመታቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ወለዱ። ይህ ደግሞ የበለጠ ትምህርታቸው ላይ ጫና አሳረፈባቸው። በእርግጥ ባለቤታቸው ሲያገባቸው አስተምርሻለሁ ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ሊያደርገው ቀርቶ ሊያስበውም አልፈለገም። እንደውም ልጄ ጠንከር ካለች በኋላ እገባለሁ ሲሉት ይናደድ እንደነበር አይረሱትም።
ባለቤታቸው ቃል የገባውን ያጠፈው በሁለት ምክንያት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ሱሰኛ መሆኑና የፈለጉትን ሊያደርግላቸው እንደማይችል ስለሚያምን ነው። ሌላው የእኔ ገቢ በቂ ነው ብሎ ማሰቡና “ትታኝ ትሄዳለች” ብሎ ማመኑ ነው። ይህ ደግሞ በበኩሉ የቤት እመቤት ሆነው ልጃቸውን እያሳደጉ እንዲቀመጡ ግዴታ ጥሎባቸዋል።
ባለቤታቸው የመጠጥ ሱሰኛ ስለነበረ ልጃቸውን ትተው መሄድ ስለማይችሉ በቀላሉ ተጋፍጠውት ለመማር አልቻሉም። ገንዘቡም ቢሆን ብዙ አይበቃውም። ስለዚህም ራሳቸው ሠርተው ወጪያቸውን እየሸፈኑ ካልተማሩ በስተቀር ሁሉም ነገር የሚሆን አይነት አልሆነላቸውም። እናም ባይወደውም እራሳቸው ወስነው በአዲስ አበባ ቄራ አካባቢ በሚገኘው ዳኒ ካፌ ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥረው እየሠሩ ያቋረጡትን ትምህርት መማር ጀመሩ።
‹‹መማር እየፈለጉ ማግባት እጅግ ከባድና መሪር ኀዘን ውስጥ የሚከት ነው። በተለይም ሴት ሆኖ እንደ ግዴታ ካማያውቁት ጋር በትዳር መጣመድ ባለን ችግር ላይ ተጨማሪ የቤት ሥራ መቀበል ነው። በዚህም ማግባቴና ሌሎች ኃላፊነቶች ተደራርበው እንዲመጡብኝ መደረጋቸው ነገሮችን አክብደውብኝ እንድቆይ አድርገውኛል፡፡›› የሚሉት እንግዳችን፤ ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ከአካባቢያቸው ርቀው ስለሚሄዱ ከተማው ያማልላትና ታሰድበናለች ተብሎ ስለታሰበ ይህ ነገር እንዲሆን ተገደዋል። ግዳጃቸውን ለማስቆም ደግሞ እናታቸው እንዴት ለፍተው እንዳሳደጓቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ትዳሩን እንቢ ማለት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
እንግዳችን ከአገቡ በኋላ ብዙ ዋጋ እንደከፈሉ ያስረዳሉ። በተለይ የባለቤታቸው መጠጣትና መረበሽ ትምህርታቸውን እንኳን ቤት ውስጥ እንዳያነቡ አድርጓቸዋል። ማንበብን ካሰቡም በትምህርት ቤት እንጂ በሌላ ቦታ እንዳይሆንም አስገድዷቸዋል። ስለዚህም የተማሩትን አንብበው ለመሸፈን በክፍል ውስጥ በአግባቡ መከታተልን ብቻ ምርጫቸው አድርገው ነው እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት። ባስ ካለና ያልገባቸው ነገር ካለ ደግሞ በዚያው በትምህርት ቤት በጓደኞቻቸውና በመምህራን ታግዘው ለመረዳት ይሞክራሉ።
ባለታሪካችን ለልጃቸው ጠንካራ እናት መሆን እንዳለባቸው ያምናሉና ከትምህርታቸው ጋር ዳግመኛ ራሳቸውን ያገናኙት ልጃቸው አራት ዓመት ሲሞላት ነው። ይህም ቢሆን ቀን ስለማይመቻቸው በማታው ክፍለ-ጊዜ “አቢዮት ቅርስ” ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት በመግባት ነው። በማታው ፕሮግራም መማራቸውም ተጨማሪ ዓመት በትምህርት እንዲያሳልፉ ያደረጋቸው ሲሆን፤ ሁለቱን ክፍሎች ማለትም ዘጠነኛና 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁት በሦስት ዓመት ውስጥ ነው።
ወይዘሮ መብሪ በትምህርታቸው ጎበዝ ተማሪ ሲሆኑ፤ የ10ኛ ክፍል ውጤታቸው ጥሩ ነበር። ነገር ግን ቀጣዩን የትምህርት ጊዜ መከተታተል፤ ማለትም ፕሪፓራቶሪ ገብቶ መማር አልቻሉም። ምክንያቱም ትምህርት ወይም ልጅን መርጦ መቀጠል ግዴታ ሆነባቸው። ይህንን ማድረግ ደግሞ ለአንዲት እናት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ማንም ይገነዘበዋል። እናም እርሳቸውም ምርጫቸው ያደረጉት ማቆምን ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱንም የሚከውኑበትን አማራጭ ሲያገኙ ምንም አይነት ጊዜ ሳያባክኑ ገቡበት።
ይህም በ10ኛ ክፍል ውጤታቸው አድማስ ኮሌጅ መግባት ሲሆን፤ ዛሬ በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ በዴፕሎማ ለመመረቅ በቅተዋል።
የመማር ጉጉታቸው ሌላ እድሎችንም እንዳሳያቸው የሚናገሩት እንግዳችን፤ ዲፕሎማቸውን መያዛቸው ለሌላ የሥራ እድል አሳጭቷቸዋል። ከጽዳት ወደ አካውንታንትነት አስገብቷቸዋልም። እናም ይህንን ዋጋቸውን (በስራው ዓለም ተፈላጊነታቸውን) ከፍ ለማድረግ ዓመታት ቢያልፉም ዲግሪያቸውን ከመጀመር አላገዳቸውም ነበር። መብሪ ዛሬ ከጌጅ ኮሌጅ በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ የቢኤ ዲግሪ ምሩቅ ናቸው። ወይም፣ በአካውንቲን የጥናትና ሙያ መስክ ቢኤ (BA) ዲግሪ አላቸው።
“ሁል ጊዜ መማር የበለጠ ቦታና እድል ማግኘት” ነው የሚል መርህ ያላቸው ባለታሪካችን፤ ትምህርት ለሴት ልጅ መቆም የሌለበት ስንቅ ነው። ምክንያቱም እየተማረችና ራሷን እያበቃች ስትሄድ አለቃዋን በየቀኑ ትቀንሳለች። የሥራ ጫናዋንም እንዲሁ ለሌሎች ታካፍላለች። በዚህም ኑሮዋን ሙሉ ማድረግ ትችላለች። ፈተናዋም ቢሆን ይቀልላታል። ምክንያቱም ፈታኞቿ ጥጋቸውን ይይዛሉና። ስለሆነም የሁልጊዜ ተማሪ መሆን አለባት ይላሉ።
‹‹ከእኔ በላይ በትምህርቱ የተጠቀመ አለ ብዬ አላስብም። ከጽዳት መውጣት የቻልኩት በመማሬና ብቃት እንዳለኝ በማሳየቴ ነው። ልጄንም ባለቤቴንም ማስደሰት የቻልኩትም በምንም ሳልበገር ተምሬና ሠርቼ እዚህ ላይ በመድረሴ ነው። ስለዚህም ሁሌም ራሴን ከፍ ለማድረግ መማር እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ መብሪ፤ አሁንም የእርሳቸው ትምህርት የሚቆም እንደማይሆን ይናገራሉ። ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ ብዙም እንደማይቆዩ ያስረዳሉ። “ሌሎችም የትምህርትን ዋጋ በዚህ ልክ ቢረዱት ደስ ይለኛል” ባይም ናቸው።
አስተናጋጅዋ አካውንታንት
የሥራቸው ታሪክ የሚጀምረው በእናታቸው ትከሻ ላይ እያሉ ቢሆንም ኃላፊነት ተጭኖባቸውና ተጨናንቀው አልነበረም። ደስተኛ ሆነው ሌሎችን ለማገዝ ሽተው የሚያደርጉት ነው። በዚህ ግን የለመዱትና የተማሩት ብዙ ነገር እንዳለ ያምናሉ። የመጀመሪያው ቆራጥነትና የማልሠራው ነገር የለም ብሎ ማሰብ ነው። “ለሁሉም ሥራ ብቁ ነኝ” ብሎ ወደ ተግባር መግባትን አውቀውታል፤ ኖረውታልም። ስለዚህም በልጅነታቸው ተድረው የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሲሆኑም ይህንኑ ነበር የከወኑት። ፈተናቸውን በቀላሉ ማለፍ የቻሉትም ይህ የልጅነት ልምምዳቸው በመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
በቅጥር ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት “ዳኒ ካፌ” ውስጥ ሲሆን፤ ይህንን ያደረጉትም ለመማር ባላቸው ፍላጎት ነው። “ለራሴ ራሴ አላንስም” ብለው ልጃቸውን ጎረቤት እያስቀመጡ አራት ዓመታትን በቦታው አገልግለዋል። ይህ ሲሆን ግን ብዙ ፈታኝ ነገሮች እንደገጠሟቸው አይዘነጉትም። በተለይም ወጣት በመሆናቸው የማይጎነትላቸውና የማይተፋባቸው አልነበረም። በዚያ ላይ ባለቤታቸው ቤት ሲገቡ ያንገበግባቸዋል። ምክንያቱም ከካፌው ፊት ለፊት ተቀምጦ የሚያደርጉትን ነገር ይከታተላልና “ይህንን ስታደርጊ ነበር አይደል?” ይላቸዋል። ነገር ግን ለወሰኑት ሥራ ቁርጠኛ ናቸውና በምንም አይነት ሁኔታ አልተበገሩም። ዓላማቸውን ከግብ አድርሰውም ነው ሥራቸውን ያቆሙት።
ቀጣዩ የሥራ ምዕራፍ አሁን የሚሰሩበት መስሪያ ቤት ሲሆን፤ ብዙ ለውጥ ያመጡበትና ፈተናቸውን የቀነሱበት ነው። የሰሩበት መስሪያ ቤት በቀድሞ “ኦሮምያ ብድርና ቁጠባ ተቋም” በአሁኑ ስያሜው “ስንቄ ባንክ” ሲሆን፤ ምንም እንኳን የ10ኛ ክፍል ውጤታቸው ከፍተኛና ፕሪፓራቶሪ የሚያስገባቸው ቢሆንም ማስታወቂያ መውጣቱን ሲያዩ ሊያልፉት አልወደዱም። ስለዚህም ከካፌው ሥራ የሚሻል ነበርና በጽዳት ሰራተኝነት ተቀጥረው ገቡበት።
የጽዳት ባለሙያ ሆነው እያገለገሉም ቢሆን ከባለቤታቸው ጋር መስማማት አልቻሉም። በዚህም ከዓመት በላይ ተለያይተው ቆይተዋል። ይህ ደግሞ ምንም እንኳን በሥራ ላይ ቢሆኑም የሚያገኙት ገቢ ልጃቸውንና እርሳቸውን የሚያኖር አልሆነላቸውም። እናም ሌላ አማራጭ መፈለግ ግዴታቸው ሆነ። ይህም የሚያስጠጋቸው ሰው መፈለግ ሲሆን፤ አየር ጤና አካባቢ የምትኖር እህታቸው ደግሞ ለዚህ ችግራቸው መፍትሄያቸው ሆነች። መኖሪያ የሚሆን አንድ ክፍል ቤትም ሰጥታቸው፤ እፎይ ያለ ኑሮም ወደ መኖሩ ገቡ። ይሰራሉ፣ ከልጃቸው ጋር በደስታ ያርፋሉም።
ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኖ ከዓመት በላይ ቢቆዩም አንድ ነገር ግን ህሊናቸውን ረፍት ነስቶታል። ይህም “ልጄን እንዴት ያለ አባት ላሳድጋት?” የሚለው ሲሆን፤ ሁኔታው ደስታቸውን ትተው ስቃዩን ለመቀበል እንዲወስኑ አድርጓቸዋል። ዳግም ከባለቤታቸው ጋር እንዲኖሩም ተገደውበታል። በዚህም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በርካታ ስቃይን አሳልፈዋል። ይሁን እንጂ ለልጃቸው ሲባል ያልቆፈሩት ድንጋይ አልነበረም። አንዱ ባለቤታቸውን ካለበት አዘቅት ውስጥ ማውጣት ነው። ሌላው ደግሞ በትምህርታቸው ከፍ እያሉ ሄደው የተሻለውን የሥራ መደብ ማግኘትና የገቢ ምንጫቸውን ማሳደግ ሲሆን አድርገውታልም። አሁን የተቋሙ ከፍተኛ አካውንታንት ሲሆኑ፤ በቀጣይ ደግሞ ከዚህ የበለጠውን የሥራ ድርሻ እንደሚይዙት፤ ከዛም አልፈው በግላቸው የመሥራት እቅድ እንዳላቸውም አጫውተውናል።
ጽናትና ሴትነት
የሰው ልጅ ልምምዱንና ኑሮውን ይመስላል። ልምምዱ ከአሸናፊነት ጋር የተያያዘ ከሆነ ሁሌም ጀግና መሆኑ አይቀርም። አቅመቢስ ቢሆን እንኳን ልቡ አይሞትምና በወኔ ይነሳል። በጅግንናውም የማይሞክረው ነገር የለም። ሙከራ ደግሞ ተደጋጋሚ ውድቀት ሊኖረው ቢችልም አንድ ቀን ግን የድል ባለቤት ያደርጋል። ለዚህ ማሳያው ኢትዮጵያዊነታችን ነው። በዓድዋ ምክንያት መቼም ለነጭ የማንበረከክ እንደሆንን አይተናል። አሸናፊነትን በልባችን አስቀምጠናል። ይህ ደግሞ ከማንም እንደማናንስ እያሳየን እንድንሄድ ያደረገን ነው። በተለይም የአዕምሮ ስሪታችን በመከራ ብንፈተንም የማንወድቅ እንደሆንን የምናረጋግጥበት ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የባህል ጫና ሳይቀር መቻልን ያለማመደ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ምክንያቱም በልጅነታቸው ተድረው የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሲደረጉ የሚገባቸውን ኃላፊነት በብቃት ይወጣሉ። ከአቅሜ በላይ ነው የሚሉት ሥራ ሳይኖርም ሲከውኑት ይታያሉ። ሰዎች የቤት ውስጥ ሥራን በቀላሉ ያዩት ይሆናል። ነገር ግን በአገራችን ሴትንና ወንድን በሚያበላልጠው ባህል ያደገ አንድ ወንድ ይህንን ማድረግ እንደማይችል በግልጽ ይታወቃል። እናም ሴት ልጅ በሥራ መጠንከርን፣ እችላለሁ ማለትንና ጽናትን ገና ከልጅነቷ ጀምሮ የምታውቀውና የለመደችው እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ይላሉ።
እሳቸው ጽናትንና በሥራ መጠንከርን ከልጅነታቸው ጀምሮ ባያውቁት ኖሮ ከደረሰባቸው ስቃይና መከራ አንጻር ተንከታክተው እንደሚወድቁም ያምናሉ። ምክንያቱም ወደ ትዳር የገቡት በ16 ዓመታቸው ነው። ለዚያውም ባልና ሚስቱ ሳይተዋወቁ። ይባስ ብሎም በ17 ዓመታቸው የልጅ እናት ሆኑ። ሁል ጊዜ ዱላ፣ ሁል ጊዜ እንቅልፍ ማጣትና ቤት ጥሎ ማደር የዘወትር ተግባራቸው በሆነበት የትዳር ዓለም መኖር ደግሞ እጅግ አዳጋች ነው። ግን አድርገውት አልፈዋል። ምክንያቱም እናት ሲኮን ዱላውንም መቻል ግዴታ እንደሆነ ተምረውታል። “ጎሽ ለልጇ …” የሚባለውንም እየተነገራቸው ነው ያደጉትና ጉዳዩ ብዙም አልገረማቸውም። እናም ለልጃቸው ሲሉ ሕመሙን ሁሉ ችለውታል።
ባለቤታቸው ዘወትር ሰክሮ ይገባል። በዚህም በተለይ አንዳንድ ጊዜ የሚያደርገው ነገር ጎረቤቱን ጭምር ያስፈራ ነበር። ኤሌክትሪክ መበጣጠሱና በዚያ ለመማታት መሞከሩ እጅግ ከባድ ነበር። ስለሆነም እስኪለውጡት ድረስ ጎረቤት ቤቴ ብለው ቆይተዋል። ይህም ታልፎ ለዛሬ የበቁት የሴት ልጅ ጽናት ጥግና ልክ ስለሌለው እንደሆነም ነግረውናል።
‹‹ካልተማርኩ ሁሌም የሰው ተገዢ መሆን ይኖርብኛል። ለያውም የሱሰኛው ወንድ ባለቤቴ። ይህ ደግሞ ልጄንም እኔንም እንደሚሰብረኝ በሚገባ አውቀዋለሁ። ስለዚህም ወገቤን ታጥቄ በማንም እየተጎነተልኩ ጭምር ዓመታትን አሳልፌያለሁ። ነገር ግን እጅ አልሰጠሁምና ዛሬ ላይ ደርሻለሁ›› ያሉን ወይዘሮ መብሪ “ሴት ልጅ ቀድማ ምን ላይ መድረስ እንደምትችል የምትተነብይ ነብይ ናት። ለዚህ ተግባሯ ደግሞ ሰለቸኝ ሳትል ትተጋለች። ግቧን ሳታሳካም መተኛት አትችልም። ከድል በኋላ እንኳን ሌላ ድልን ለማምጣት ትተጋለች እንጂ በቃኝ የምትልም አይደለችም፡፡” የሚል ፅኑ አቋምም አላቸው። እናም፣ ሁሌም ይህንን አቋማቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ያምናሉ።
ባለቤታቸው እጅግ የዋህና ደግ ነው። ምንም ሊያጎልባቸውም አይፈልግም። ሆኖም ጓደኛና መጠጡ በብዙ መልኩ አርቋቸዋል። በረብሻ ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል። አንድ ቀን ዓይኔን ቢያጠፋውስ፣ ልጄን አካል ጉዳተኛ ቢያደርግብኝስ፣ እኔንም የማልወጣው ስቃይ ውስጥ ቢከተኝስ የሚለው ስጋት ውስጥም ከቷቸዋል። ነገር ግን አብራቸው በምትኖረው እህታቸው፣ በጎረቤቶቻቸውና በጓደኞቻቸው፤ እንዲሁም በእርሳቸው ጽናትና “ለልጄ መኖር አለብኝ” ባይነት ሁሉ ነገር ድባቅ ተመትቷል።
ወንድ ልጅ በባህሪው አይደለም ተበልጦ በልጦ እንኳን ከጫና ውጪ ሴትን ልጅ ማስተዳደር አያውቅበትም። በዚህም ሁልጊዜ አታደርጊም እንጂ የፈለግሽው ይሁንልሽ ሲል አይሰማም። ይህ ደግሞ ብዙዎቹን ሴቶች ከቤት እመቤትነት እንዳይወጡ አድርጓቸዋል። በኃይልና በጫና ውስጥ ሆነው ካልወጡ በስተቀርም መቼም የልጆቻቸው እናትና አርኣያ መሆን አይችሉም። ስለሆነም ሴት ልጅ ማሰብ ያለባት ሁልጊዜ ወንዱን ማለትም ባለቤቷን እንዴትና በምን መልኩ መብለጥ እንዳለባት ነው። በእርሷ ፍላጎት እንዲመራ ካደረገችውና በፍቅር ከገዛችው ሁሉን ነገር ማስደረግ ትችላለች። ለዚህም ማሳያው የእኔ ሕይወት ነው ይላሉ። እርሳቸውም ሆኑ ልጃቸው ደስተኛ መሆን የቻሉት ባለቤታቸውን አሸንፈው ከሱሱ አላቀው የራሳቸው በማድረጋቸው ነው። እናም ሴቶች ብዙ የጥበብና የጽናት ተምሳሌት በመሆናቸው ብልህነታቸውን እንዲጠቀሙበት ይመክራሉ።
ሴቶች በአስተዳደግ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም የተቸራቸው ከወንድ የበለጠ ነገር አላቸው። ክፍተቱ መጠቀሙ ላይ ነው። ስለሆነም ተፈጥሯዊ ስጦታቸውን ችላ ሳይሉ በሕይወታቸው መራመድ አለባቸው። ሁል ጊዜም የበታች ሆነው እንዳይቀሩ በሁሉም መስክ ያላቸውን ልዩ ችሎታ መጠቀም ይገባቸዋል። በተለይም የገጠር ልጅነት ብዙ ነገር የሰጠን በመሆኑ በጎ ባህሉን መርጦ በመያዝና እንደ ባህልነቱ አክብሮ በመጠቀም ነገሮችን መለወጥና ራሳችንን ማሳደግ አለብን። ልምዳችንንና አቅማችንን ከተፈጥሯዊ ጸጋችን ጋር አዳምረን ብንጠቀምበት ደግሞ የሚከብደን ነገር እንደማይኖር እኔ ህያው ምስክር ነኝም ብለውናል።
የሕይወት ፍልስፍና
ሁል ጊዜ የጠበቅነው ፈተና አይመጣም። ያልጠበቅነውም ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እናም “ለምን ተፈተንኩ?” ሳይሆን ማለት ያለብን “ፈተናውን እንዴት ልለፈው?” ነው። ያለዚያ ግን ሁሌም አማራሪና በችግር ውስጥ ያለ ሰው እንሆናለን የሚለው የመብሪ የመጀመሪያ ፍልስፍናቸው ነው።
ሌላው የሕይወት መርሃቸው ይቅርታ ማድረግ ሲሆን፤ ይቅርታ ከራስ የሚጀምር እንደሆነ ያምናሉ። ለራስ ይቅርታ ማድረግ ከስህተት መቆጠብ ነው፤ ከሕመማችን መፈወስ ነው ብለው ያስባሉ። ይቅርታ ማሸነፍም ነው። ተስፋ ማግኘት፣ ነገን ማየትና ለልጆች ስንቅ ማስቀመጥም ነው። ከምንም በላይ ያጡትን ማግኘትም እንደሆነ ያምናሉ። ትናንት ያቆሰለንን ዛሬንና ነገም እንዳይደገም ማስተካከያ መንገድ እንደሆነም ይሰማቸዋል። በዚህም በሕይወታቸው ያዳናቸው ለባለቤታቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ደጋግመው ይቅርታ ማድረጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እናም ለሌሎች ጭምር ይቅርታ ማድረግ ሕይወትን በደስታ ማቆም እንደሆነ እርግጠኛ ናቸው።
“ለወላጅ የሚመለስ ስጦታ ወይም ወቀሳ በምንም መልኩ የለም” የሚለውም ሌላው የሕይወት ፍልስፍናቸው ነው። በምክንያትነት የሚያነሱት ቤተሰብ በአሰበ ልክ ልጁን ያኖራልና ነው። ይህንን ሲያደርግ ደግሞ በጎ አስቦ ስለሚሆን መልሳችንን በልጆቻችን ፍላጎት ላይ ተንተርሰን ለልጆቻችን በማድረግ ማግኘት አለብን ይላሉ። መጥፎ ተግባር እንኳን ሆኖብን ካለፈ በእኔ ይብቃ ብሎ መተው አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ።
መልዕክት
ማንም ሰው ከእኔ እንዲማር የምፈልገው ጉዳቴን ሳይሆን ጥንካሬዬን ነው። ምክንያቱም ለእኔ የማይቻል ነገር አለ ብዬ አላምንም። ይህንን ደግሞ በወሬ ሳይሆን በተግባር አሳይቼዋለሁ። ስለዚህም ሰዎች በጉዳታቸው ውስጥ ጥንካሬያቸው እንዲታይ መሥራት አለባቸው የሚለው የመጀመሪያው መልእክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር ሴቶች በብዙ ፈተና ውስጥ ቢሆኑም በእምነታቸው ጠንካራ መሆን እንዳለባቸው ነው። ለዓላማቸው ቀድመው አቅደው መንቀሳቀስም ይገባቸዋል። ለዓላማ ሲባል መጽናትም ግድ ነው። እናም ማንም በመረጠልንና በአስተካከለልን ውስጥ ሳይሆን ራሳችን በመረጥነውና ይሆነናል ባልነው መርህ መጓዝ አለብን። የራስ የሆነ ዓላማን ይዞ ለግብ መስራት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። በተለይ ለራስ መሆን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መትረፍ መቻልን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህ ሲሆን በሰዎች ውስጥ ራስን ማየት ይቻላል። ስለዚህም እንደ ሴት የሚፈልጉትን ማወቅ፣ ያንን ነገር ጠንክሮ መስራትና ለሌሎች አርአያ መሆን የሚሉትን ነገሮች መርሃቸው ቢያደርጉት እንደሚጠቀሙበት ከነበራቸው ተሞክሮ በመነሳት ይመክራሉ፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም