የአምቡላንሱ ጩኸት ከእንቅልፌ አባነነኝ። ዓይኔን እያሸሁ ከአልጋዬ ስወርድ ከቤት ውጪ የእናቴ ድምፅ ይሰማ ነበር። ገና በደንብ አልነጋም፤ እናቴ ቤተክርስቲያን ለመሳለም ብትነሳም ከግቢ ወጥታ ለመሄድ አልደፈረችም። የአንቡላንሱ ጩኸት እጅግ አስደንግጧታል። ለራሴ፤ ሰው እንዴት በአንድ ነገር ሁሌ ይደነግጣል? ብዬ ፈገግ አልኩ። ከቤት ወጥቼ በረንዳ ላይ ቆሜ የአምቡላንስ ጩኸት በየጊዜው የሚያስደነብራትን እናቴን ማነጋገር ጀመርኩ።
እኔ፡- ምነው እናቴ? ቤተክርስቲያን አትሄጂም?
እናቴ፡- አምቡላንሱ ዋይ ዋይ! ሲል አትሰሚም፤ እንዴት ልሂድ?
እኔ፡- ድምፁ የሚሰማው ከሩቅ እኮ ነው።
እናቴ፡- እየቆየ መቅረቡ ይቀራል ብለሽ ነው? /ፊቷ ላይ የሐዘን ምልክት ይታያል/
እኔ፡- አንቺ እንደሁ ደህና ነሽ፤ ድምፁ ቢቀርብስ ምን ቸገረሽ?
እናቴ፡- ከሩቅ የሚሰማ ጩኸት አንቺጋ የማይደርስ መሰለሽ፤ ምንም እንኳ እኔ ደህና ብሆንም የሌላው ጉዳት ዘግይቶም ቢሆን እኔጋ መድረሱ አይቀርም።
እኔ፡- ታዲያ ምን ይደረግ። በሆነው ባልሆነው ጩኸቱ በረከተ። በትክክል ምን እንደተፈጠረ ሳታውቂ በተጮኸ ቁጥር ከደነበርሽ ሰውነትሽ ያልቃል። ከጩኸቱ ይልቅ የጩኸቱ ምክንያት ሊያሳስብሽ ይገባል።
እናቴ፡- ያው መቼም ጩኸቱን ሰምተሻል። ጩኸት ካለ አደጋ አለ።
እኔ፡- እኔ ከሌላ ጊዜው የተለየ ምንም የጩኸት ድምፅ አልሰማሁም፤
እናቴ፡- ጩኸቱን አልሰማሽም? እኔ፡- የምን ጩኸት አዲስ ነገር አለ? የተፈጠረውን አውቀሻል እንዴ? እናቴ፡- የተፈጠረውንማ አላወቅኩም።
እኔ፡- ሰዎች ጮኹ? እናቴ፡- አይ! የሰው ጩኸት አልሰማሁም። ግን የአምቡላንሱ መጮህ የሆነ ነገር መኖሩን ያመለክታል።
እኔ ፡- ታዲያ ምን አስጨነቀሽ? እናቴ፡- አምቡላንሱ እኮ ጮኸ፤
እኔ ፡- /ሳቄ መጣ/ የተለመደ እኮ ነው።
እናቴ፡- በደህና አልመሰለኝም፤ ልቤ ፈርቷል። የእናቴ ሁኔታን ሳስተውል ተገረምኩኝ። እርሷ እጅግ ተጨንቃለች። እኔ ደግሞ ምንም አልመሰለኝም። የእናቴና የእኔ ሁኔታ እጅግ ተቃራኒ ሆኗል።
እርሷ እየታያት ያለው ክፉ ነገር እየመጣ መሆኑ ነው። እኔ ደግሞ ምንም አዲስ ነገር የለም ባይ ነኝ። የእኛ ንግግር እና የአምቡላንሱ ድምፅ እየቀረበ መምጣት ዘግይቶም ቢሆን የቀሰቀሰው ወንድሜም ከእኛው ጋር ማውራት ጀመረ። እርሱም እንደኔው ሁሉ የአንቡላንሱ ድምፅ ቢቀሰቅሰውም አላስደነበረውም። እንዲያውም እናቴ በመደናገጧ ለመቆጣት ቃጥቶት ነበር።
ወንድሜ፡- ምንድን ነው? ምን በትንሹም በትልቁም እየተነሳሽ ትረበሺያለሽ?
እናቴ፡- አንተማ ምን አለብህ?
ወንድሜ፡- እውነቴን እኮ ነው። ድምፁን ከሆነ በተደጋጋሚ እየሰማነው ነው፤ ሁልጊዜ ለምን ክፉ ክፉውን ብቻ ታስቢያለሽ?
እናቴ፡- አምቡላንስ እየጮኸ ደግ ነገር ላስብ?
ወንድሜ፡- አዎ! ለምሳሌ ሰዎች ስራ ረፍዶባቸው በታመመ ሰው ስም አምቡላንስ ጠርተው ይሆናል።
እኔ፡- /ሳቄን ለቀቅኩት/ አልገባኝም፤ ያልታመሙትን ታመምን ብለው ሆስፒታል ሊሄዱ ነው። የማይመስል ነገር።
ወንድሜ፡- ሊሆን ይችላል፤ ወይም የቀይ መስቀል ሠራተኛ የሆነ ሰው እዚህ ሰፈር መምጣት ፈልጎም ይሆናል።
እኔ፡- በአምቡላንስ ?
ወንድሜ፡- አዎ በአምቡላንስ፤ ሌላ መኪና ከየት ያምጣ? ወይም መንገዱ እንዲከፈትለት ፈልጎ ይሆናል?
እኔ፡- ገና ጠዋት ነው፤ መንገዱ አልተዘጋጋም፤ ደግሞስ ለበሽተኛ ማመላለሻ መሆን ያለበትን መኪና ለሌላ ጉዳይ ማዋል ይቻላል? ወንድሜ፡- እሱማ ትክክል ነው። አይደለም ብሎ መከራከር አያስፈልግም። አምቡላንስ ለሌላም ዓላማ ይውል እንደነበር ሰምተናል። የአምቡላንሱ ድምፅ ሲርቅ፤ የእናቴም ስጋት ቀነሰ። እናቴ ወደ ደጁ በር ስትጠጋ ወንድሜ ትከሻዋን ያዝ አድርጎ፡- ‹‹ ማሚ እሳት አደጋ ተነስቶ ይሆን፤ የመኪና አደጋ ይሆን ወይስ ሰው ታሞ ነው? ብለሽ አታስቢ፤ ቢያንስ እንደኛ ሰዎች አምቡላንሱን ለሌላ ዓላማ እያዋሉት ነው ብሎ ማሰብ ቢያዳግትሽም፤ አንዲት ነብሰ ጡር ምጧ መጥቶ ይሆናል? ብለሽ ገምቺ።›› እናቴ፡- እንግዲህ እንደሱ ከሆነም እናቲቱ በሰላም ትገላገል። ወንድሜ፡- አሜን እናቴ፤/ፈገግ አለ/። ገና የእናቴ እግር ከመውጣቱ የብዙ አምቡላንስ ድምፅ መሰማት ጀመረ። ወደ ወንድሜ ፊቴን አዙሬ ብዙ ወላዶች ብዙ አምቡላንሶችን ጠርተው ይሆን ? አልኩት። አሁን ወንድሜ አልሳቀም። ‹‹እውነትም የሆነ ነገር አለ። የትኛው የነፃ አውጪነትን ጭንብል የለበሰ ማንን ሊያፈናቅል ይሆን? አሁን ነው መደንበር ›› አለ እና ስጋቱን አጋባብኝ። የእሳት አደጋ መኪና እየጮኸ ሲያልፍ ይሄኔ ሁለታችንም በረዥሙ ተነፈስን።
ወንድሜ፡- አቦ እሳትስ ከሆነ ይጠፋል።
እኔ፡- ከባድ የእሳት አደጋ ሳይደርስ አልቀረም። ወንድሜ፡- ቢያንስ ሰው አይሞትም። እሳት እንኳን ንብረት እያወደመ ሰዎችን ሲምር፤ ሰዎች ግን ወንድምና እህቶቻቸው ላይ እየጨከኑ ውዱን የሰው ህይወት ያጠፋሉ። ወደ ቤት ገባ እና ወደ ሥራ ለመሄድ መሰነዳዳት ጀመረ። እኔም ከፈለገች በሳምንት ካልሆነም በአስራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ የምትመጣዋ ውሃ በአስረኛ ቀኗ በመምጣቷ ለመቅዳት በርሜሎችን ማጣጠብና ውሃ መደቀን ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ወደ ሥራ ለመሄድ የረፈደበት ወንድሜ ‹‹ደህና ዋይ›› ብሎ ከግቢው ወጣ። የቆመው የአምቡላንሱ ጩኸት የእርሱን መውጣት ተከትሎ ቀጠለ። ትንሽ እንደመስጋት ስል ቤተክርስቲያን የሄደችው እናቴ ተመለሰች። እኔ፡- ምንድን ነው? እናቴ፡- ቤተክርስቲያኑ አጠገብ የተሠሩት የቆርቆሮ ቤቶች ነደዱ።
እኔ፡- በምን ምክንያት ? እናቴ፡- ምን አውቃለሁ? ብቻ ማጥፋት አልተቻለም። በሃያ ሃያ ሊትር ጀሪካን ለሽያጭ ተዘጋጅተው የተቀመጡት አረቄዎች የእሳት አደጋውን አባባሱት። እሳቱ እየተንቀለቀለ ነው። ስልኬ ጠራ ወንድሜ ነበር። እሳቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ካበሰረኝ በኋላ ነገር ግን የሁለት ሰው ህይወት መጥፋቱን እንደሰማ ነገረኝ። ለእናቴ በስልክ የሰማሁትን ስነግራት የሁለቱ ሰዎች ሞት ቢያሳዝናትም ጉዳቱ ከዚያ በላይ ባለመዝለቁ ፈጣሪዋን ወደ ሰማይ አንጋጣ እያመሰገነች እፎይ አለች። በእርግጥ እናንተንስ የአምቡላንስ ጩኸት አልሰለቻችሁ ይሆን? ያሰለቻችሁ ይመስለኛል። ለሆነው ላልሆነው ሰው ማሸበር ቢቀር መልካም ነው። በተለይ አንዳንዴ ታክሲዎችም መንገድ ለማስከፈት የአምቡላንስ ድምፅ በማሰማት የሚያባንኑበት ጊዜ መኖሩን አስተውያለሁ። ጊዜው የሰላም ነው እና በሆነው ባልሆነው ጩኸት ይቁም እያልኩ ደህና ሰንብቱልኝ ብያለሁ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በ\ምህረት ሞገስ