ዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ ከአሜሪካ ተመላሽ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ድርጅት ነው። ዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ የፈጠራ ባለቤትነቱ መብት ያገኘበት የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤት ቤት ለቤት በመዞር የሚደረግን የቆጣሪ ንባብና አላስፈላጊ የውሃ ብክነትን የሚያስቀር፤ የውሃን ጥራት ለመጠበቅ የሚያስችልና ደንበኞች ስልካቸው ላይ በሚላክላቸው መልዕክት የውሃ ፍጆታቸው ምን የህል እንደቆጠረ እንዲያውቁ የሚያደርግ ስርዓት (ሲስተም) የያዘ ስማርት የውሃ ቆጣሪ ነው።
ድርጅቱ ስራውን የሚያከናውነው ጃክሮስ አካባቢ በሚገኘው ቆጣሪ ማምረቻውና ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የመረጃ ማዕከሉና ዋና መስሪያ ቤቱ ነው።ይህ አዲስ የሆነ የቴክኖሎጂ ውጤት የመጠጥ ውሃን ጥራት በመጨመር በውሃ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ለጤና ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ማለትም ሊድ፣ አርሴኒክ ፣ ፍሎራይድ ፣ አሞኒያ የመሳሰሉትን በመለየት ወደ ማእከላዊ የዳታ አስተዳደር ስርዓት (Meter Data Expert System) ሶፍትዌር መልዕክት በመላክ ለተጠቃሚዎች ውሃው መመረዙን ያሳውቃል። የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሕሊና ጌታቸው እንደሚገልጹት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በአስተማማኝ ሁኔታ ለዜጎች ለማቅረብ ብዙ ዓመታት ለፈጀባት ኢትዮጵያ ይህ መልካም የምስራች ነው። ስማርት የውሃ ቆጣሪው በመስመር ብልሽትም ሆነ በአግባቡ ባለመዘጋት ለሚፈጠር የውሃ ብክነት ዓይነተኛ መፍትሔ ይዞ መጥቷል። ማንኛውንም ዓይነት ያለአግባብ የተከሰተ ፍሳሽን በመለየት ወደ ማዕከላዊ የዳታ አስተዳደር ሥርዓት መረጃን በመላክ ለደንበኛው በማሳወቅ ብክነትን ይከላከላል።
ቴክኖሎጂው የውሃ ጥራትን ከመጨመር ባሻገር በቆጣሪው ላይ የሚደረግን ስርቆት ፣ ወደ ኋላ ተመልሶ መፍሰስን እንዲሁም የተዛባና ትክክለኛ ያልሆነ የፍጆታ ክፍያ መረጃን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎለታል። ብዙ ጊዜ በውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤትና በደንበኞች መካከል ቅሬታን የሚያስነሳው የፍጆታ ክፍያ ተመን መዛባት ችግርን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ከሰው የንባብ ግድፈት በፀዳ መልኩ የክፍያውን ተመን ፍጹም ትክክል በሆነ ሁኔታ ለተጠቃሚዎች የሚያሳውቅ ሲሆን፤ይህ ደግሞ የደንበኞችን የአገልግሎት ጥራት ከፍ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ ይጨምራል። ቴክኖሎጂው ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በተደረገ የሙከራ ሥራ ፍጹም ትክክል የሆነ የፍጆታ ንባብ በማድረግ የተሳካ ውጤት አስመዝግቧል። በዚህም ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ለሰው ኃይል የሚያወጣውን ወጪ ሙሉ በመሉ እንደሚያስቀር ተረጋግጧል።
ዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ በአሁኑ ወቅት “dSpirit TM” በሚል የንግድ ስያሜ የተመዘገበውን ስማርት የውሃ ቆጣሪ ለአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ላሉ ሃገራት ለገበያ ለማቅረብ የምርት ትእዛዝ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኢንጂነር ሕሊና ድርጅቱ ከውሃ ቆጣሪ በተጨማሪ ስማርት የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በማምረት ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል። አያይዘውም “ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤት እ.አ.አ. በ2017 በኒውዮርክ ከተማ በተካሄደው እንደ ጉግል፣ ማይክሮሶፍት፣ ጄፒ ሞርጋን ካሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሳተፍ እጅግ ውጤታማና ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራ መሆኑ ተመስክሮለታል። ይህም ዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ ጀማሪና ውጤታማ ከሆኑ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ አንዱ እንዲሆን አድርጎታል።
በአይሶ (ISO) 9001:2015 ብቃቱ ተረጋግጦ የምስክር ወረቀት አግኝቷል። በአሁኑ ሰአት 120 ሙያተኞችን ቀጥሮ በማሠራት ላይ ሲሆን፤በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥም 400 ቋሚ ሠራተኞች እንደሚኖሩት ዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል። የዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ማኔጀር የሆኑት ወይዘሪት ምስጋና ጎበዜ እንደገለጹት ድርጅቱ በከፍተኛ ውጤት ተመራቂ የሆኑ የኢንጂነሪንግ ተማሪዎችን በቀጥታ ከዩኒቨርስቲዎች ይቀጥራል። አሁን ካሉት ሰራተኞችም ከ90 በመቶ የሚልቁት መሀንዲሶች ናቸው። አዳዲስ ምርቶች በስፋት ወደ ገበያ ሲገቡ የሠራተኞችን ቁጥር በሶስት ዓመት ውስጥ ለመቅጠር ካቀደው በእጥፍ በማሳደግ የቴክኒክ ስራውን ብቻ የሚደግፉ 800 ሠራተኞችን በጊዜያዊነት ቀጥሮ በማሰራት የአገሪቱ ቁልፍ ችግር የሆነውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ተግቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም ድርጅቱ ምርቶቹን ለውጭ ሀገራት በመላክ በአማካኝ 100 ሚሊዮን ዶላር ወደ አገር ውስጥ በማምጣት አገሪቱን እያሰጋት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችለው አቅም አለው። ዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ ይህን ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤት ሲያበረክት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለውን የውሃ ፍላጎትና አቅርቦት ያለመጣጣም ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ነው። ድርጅቱ ወደ ስራ ሲገባ ጥናት ማድረጉን የሚጠቅሱት ኢንጂነር ሕሊና ጌታቸው፣ እንደ www.water.org ዘገባ 43% ኢትዮጵያውያን የውሃ እጥረት ችግር ሲኖርባቸው 72% የሚሆኑት ደግሞ ንጹህ ውሃ በአካባቢያቸው አያገኙም።
ይህ ቁጥር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከፍ እንደሚል ይገመታል። ከዚህ በተቃራኒው እንደ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የጥናት ውጤት ከሆነ ኢትዮጵያ በዓመት 122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ከትልልቅ ወንዞቿ ማግኘት የምትችል ሲሆን ወደ 6.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የሚጠጋ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እንዳላት ይገመታል። ይህ የውሃ ሃብት በአግባቡ ቢሰራጭ 1.575 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በዓመት ለአንድ ሰው ይደርሳል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ሦስት በመቶ ብቻ ነው በአገሪቱ ውስጥ ለመጠጥነት ጥቅም ላይ የሚውለው። ለዚህ የውሃ ሃብት ፍላጎትና ስርጭት አለመጣጣም ደግሞ በርካታ ተግዳሮቶች እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ ከነዚህም መካከል በከተማ ያለው የውሃ ፍጆታ መጨመር፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት፣ የውሃ ዑደት መዛባት፣ የመስኖ ልማት መስፋፋት እና ቴክኖሎጂን ያለመጠቀም ችግር እንደሆነ ይታመናል። ይህንን የአገራችንን ቁልፍ ችግር ለመቅረፍ ነው ከአሜሪካ ተመላሽ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን ይህ ቴክኖሎጂ የተፈጠረው። በአሁኑ ሰዓትም ሙሉ በሙሉ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ወደ ተግባር ሊገባ ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል።
አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ የውሃ አስተዳደር ሥርዓትን መጠቀም ለነገ የማይባል ተግባር ነው የሚሉት ኢንጂነሯ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጲያዊያንን ከውሃ እጥረትና ውሃ ወለድ ከሆኑ በሽታዎች መታደግ ግድ ይላል። የህዝብ ቁጥር መጨመር እና ተለዋዋጭ የሆነው የአየር ንብረት በተደጋጋሚ ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያን ለከፋ ደኅንነት በማጋለጥና እድገቷን የኋልዮሽ ሲጎትት ቆይቷል። አሁን ግን በቃ ልንለው ይገባል። በሙከራ የዳበሩ ልምዶችን በመያዝና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም አገራችንን ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን መትጋት አለብን።
የዚህ ቴክኖሎጂ ትግበራ “ንጹህ ውሃን ያለማቆራረጥ በአስተማማኝ ሁኔታ ለተገልጋዮች ማድረስ“ የሚለውን የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት መሥሪያቤትን ተልዕኮ ያሳካል ሲሉ እምነታቸውን ይገልጻሉ ። የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ገቢ የማይሰበሰብበት የውሃ ብክነትና ምርመራ ንዑስ የስራ ሂደት ኃላፊ የሆኑት አቶ አልታሰብ አዘዘው ተቋማቸው ከዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ ጋር ስላለው ገንኙነት በሰጡት ማብራሪያ ዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ በፓይለት ደረጃ ሙከራ እንዲያደርግ ቦታ መርጠን ሰጥተነው ሙከራውን አገባዶ ሪፖርት አቅርቧል።
በማንዋል እየሰሩ ባሉት ቆጣሪዎችና በስማርት ቆጣሪው መካከል ያለውን ልዩነት በሚያሳየው ሰነድ ላይም ተወያየተን አስተያየት ሰጥተናቸው የመጨረሻ ሰነድ እንዲያስገቡ ጠይቀናቸዋል እነሱም ከዚህ በኋላ የሚቀረው የገበያ ትስስር መፍጠር ስለሆነ ከከተማው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተን እናሳውቀችኋለን ብለውን መልሳቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል። ኃላፊው አያይዘውም ከዲቬንተስ ቴክኖሎጂስ ጋር ውል መግባት ደረጃ ሲደረስ ትግበራው በመጀመሪያ የሚጀመረው ትላልቅ ፍጆታ ካላቸው ደንበኞች ጋር ነው ። ስማርት ቆጣሪ የበለጸጉ ሀገራት የሚጠቀሙበት ዋጋው ውድ የሆነ ቴክኖሎጂ ስለሆነ በአንድ ጊዜ በከተማው የሚገኙትን 544 ሺ ቆጣሪዎች ለመተካት የሚያስችል አቅም የለም። ስለዚህ ወደተቀሩት ደንበኞች ለመድረስና ቆጣሪዎቹን ለመተካት ጊዜ ስለሚያስፈልግ ቀስ በቀስ በሂደት ውጤቶቹ ላይ በመነጋገር የሚገባበት ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2011
በየትናየት ፈሩ