አገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ እጅግ የገዘፈ ሚና ያለው የፋሽን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ደረጃ አሁን ላይ መጠነኛም ቢሆን ትኩረት የተሰጠው ይመስላል፡፡ ለፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች ከውጭ በመጣ ባለሙያ ስልጠና መሰጠቱም ይህን ያመለክታል፡፡
ስልጠናውን እየሰጠ ያለው ክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዩኒዶ ትብብር የተቋቋመ ልዩ የፈጠራ ስራና ሀሳብ ላይ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ የአገር ውስጥ አምራቾችና ኢንተርፕራይዞች የፈጠራና ምርት ስራዎቻቸውን አለማቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንዲያመርቱና ምርቶቻቸው ተወዳዳሪ ይሆኑ ዘንድ የዲዛይን ስልጠና መስጠትና ለምርታቸውም የገበያ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራን ይተገብራል፡፡
ወጣቶች በፈጠራ ስራቸው እምርታን እንዲያስመዘግቡና የተሻለ የፈጠራ ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል በዚህም በዲዛይንና ፋሽን ኢንዱስትሪው ብቁና ተወዳዳሪ በመሆን የላቀ ውጤት ላይ እንዲደርሱ በባለሙያዎች ስልጠናና ማማከር አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ በፋሽን ዲዛይን ዘርፍ ባለሙያ ዎችን አባል በማድረግ ምርትና አገልግሎታቸው በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪው አዲስ እንደ መሆኗ በዘርፉ የሚስተዋለውን የዲዛይን እና የምርት ጥራት ችግር ለመፍታት በዚህ ተቋም አማካኝነት በዘርፉ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የፋሽን ዲዛይን ስልጠና ይሰጣል፡፡
በተለይም ወጣቶች በግል ፈጠራና በአዳዲስ ዲዛይኖች አምርተው የሚያቀርቡትን ምርት መሸጫ ቦታ በማዘጋጀት ከደንበኞቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ላይም ይሰራል፡፡ ከመጋቢት 1 ቀን 2014 ጀምሮ ሜክሲኮ በሚገኘው ማዕከሉ ወጣት የፈጠራና የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች በፋሽን ዲዛይን ስራ ዘላቂነት ማስረፅ እንዲሁም ፈጠራና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የምርት ዲዛይን ወሳኝ መሆኑን በሚመለከት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
ወጣቶች በፋሽን ዲዛይን ዘርፍ ሲሰሩ ፈጠራና ቴክኖሎጂን መሰረት ባደረገ መልኩ የምርት ብክነትና አካባቢያዊ ተጽእኖን በሚቀንስ መልኩ አምርተው ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ስልጠናው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው የክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ ሃብ ስራ አስኪያጁ አቶ ተመስገን ፍስሀ ይገልፃሉ።
ስልጠናው ኢንተርፕራይዞችና ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች በስራቸው በተለይም በዲዛይን ላይ የራሳቸውን ክህሎት እንዲያሳድጉና ጥራቱን የጠበቀ ምርት አካባቢን በማይጎዳ መልክ ማምረት እንዲችሉ እንደሚያግዛቸውም ይገልፃሉ፡፡
እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ፤ የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የዲዛይን መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ስራዎቻቸውን እንዲሰሩ የፈጠራ አቅማቸውን በማሳደግ ገበያው የሚፈልገውን ምርት ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ መሰል ስልጠናዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ተቋማቸውም በዘርፉ አገራዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግና የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ለማጎልበት ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ዲዛይኖችን እንዲሰሩ በመርዳት ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡
ተቋማቸው ወጣቶችን በተለይ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ኢንተርፕራይዞችን በማሰባሰብ አቅምን በመገንባትና ምርትና አገልግሎታቸውን በተሻለ ጥራትና ተፈላጊነት ተወዳዳሪ ሆነው ገበያው ላይ እንዲገኙ ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚገልፁት ስራ አስኪያጁ፣ የባለሙያዎችን ክፍተት በመለየት ስልጠና መስጠት ወሳኝ መሆኑን በማመን ተቋሙ የተለያዩ ስልጠናዎች እየሰጠ መሆኑንና በዚህም ባለሙያዎች ለውጥ እያሳዩ መምጣታቸውን ያነሳሉ፡፡
ስልጠናው የዲዛይነሮች አቅም ማሳደግና ምርቶቻቸው በአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚረዳም ያስረዳሉ፡፡ በስልጠና ዲዛይነሮች የተሻለ ልምድ ቀስመው እንደሚወጡና በቀጣይ ስራዎቻቸው እንደሚተገብሩትም አቶ ተመስገን እምነት አላቸው፡፡ አቶ ተመስገን እንደሚሉት፤ በፋሽን ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ ለመሆን ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት እጅግ ያስፈልጋል፡፡
የውጭውን ዓለም መስፈርት በማሟላት ምርቶቻችን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ምርቱ እንዴት? በምን አይነት ግብዓት ተመረተ? በምን አይነት መንገድ ቀረበ? የዲዛይኑ አዲስነትና የምርቱ ምቹነት ምን ይመስላል? በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት በሚያስችል መልኩ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ባለሙያዎቹን በስልጠና በመደገፍ ብቁ ማድረግ ይገባል፡፡ የተቋማቸው ተግባርም ዘርፉን የተሻለ ቁመና ላይ ማስገኘት ነው፡፡ ዲዛይነር ዳናዊት አለማ በዚሁ ስልጠና ተሳታፊና የክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ አባል ነች፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ በፋሽን ዲዛይን ትምህርትና በሙያው ላይ የቆየችው ዳናዊት፣ በክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ እየተሰጡ ባሉ መሰል ስልጠናዎች በተደጋጋሚ ተካፍላለች፡፡ በዚህ ስልጠናም በፋሽን ዲዛይን ስራዋ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚፈጥርላትን አዳዲስ ምልከታዎችንና የዲዛይን ስራ ፈጠራዎችን ማሰብ እንድትችል እንደረዳት ታስረዳለች፡፡
መሰል ስልጠናዎች በሙያው ላይ ያለህን ክህሎት ለማሳደግ እጅጉን ይረዳል የምትለው ዳናይት፣ ለእስዋም ጥሩ መነቃቃትና በስራዋ ላይ የተሻለ ለመፍጠር እንደሚረዳት እምነቱ አላት፡፡
በዘርፉ ካሉት መሰል ሙያተኞች ጋር እውቀትና ልምድን መለዋወጡ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የምትገልፀው ዲዛይነርዋ፣ በክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ እያተሰሩ ያሉ መልካም እንቅስቃሴዎች ለፋሽን ዘርፉ ትልቅና በጎ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ታስረዳለች፡፡
በእውቁ ጣሊያናዊ ዲዛይነር ጊሊዮ ቪናሻ (Mr.Giulio Vinaccia) እየተሰጠ ባለው በዚህ ስልጠና አዳዲስ የዲዛይን ስራዎችን በምን መልክ ማሰብና አካባቢያዊ በሆነ ጉዳይ ላይ በመመርኮዝ ዲዛይን መፍጠር እንዳስቻለት ዲዛይነር ዳናዊት ትገልፃለች፡፡
ከስልጠናው ያገኘችውን አዲስ ነገርም በስራዎቿ ለመተግበርና ልምዷን ለማሻሻል እንደምትጠቀምበትም ታስረዳለች፡፡ ዲዛይነር በፀሎት ዘውገ የ”ዘመናይ ክሎዚንግ” መስራች እና በዚህ በክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ በተዘጋጀው የዲዛይነሮች ስልጠና ተካፋይ ናት፡፡
ላለፉት አራት አመታት በፋሽን ዲዛይን መስክ የተለያዩ ስራዎች በራስዋ እየሰራች የቆየቸው ዲዛይነር በፀሎት፣ በስራዎቿ ውስጥ ታሪክን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ ፈጠራዎችን በማከል አዲስ በሆነ መንገድ እየሰራች ናት፡፡ ዓለም አቀፍ የዲዛይንና ፋሽን ኢንዱስትሪ ምርት መስፈርቶችን ባማሏ መልኩ አምርታ ለማቅረብ ሁሌም ጥረት ታደርጋለች፡፡
በዚህም አበረታች ውጤቶችን እየተመለከተች ናት፡፡ በክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ እየተሰጡ ያሉ ስልጠናዎች ደግሞ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱላት መሆኑን ትናገራለች፡፡
የአሁኑ ስልጠናም ወደፊት በዲዛይንና ፋሽን ስራዎቿ የተሻለ ፈጠራና ዲዛይኖችን በማከል ለመስራት እንደሚያስችላት ትገልፃለች፡፡ በተለይ በእያንዳንዱ የስራ ሂደት ውስጥ የራስን ፈጠራና ያልተቋረጠ የዲዛይን ለውጥ በሚያስፈልግበት የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ ልዩና አዳዲስ ፈጠራ ላይ ራስን ማስገኘት ወሳኝ ነው፡፡
በመሆኑም ራስን ሁሌም በፈጠራ ስራ ላይ ማስገኘትና በገበያው ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ግድ እንደሚልም በጸሎት ትናገራለች፡፡ መሰል ስልጠናዎች ደንበኞችን እንዴት መያዝና ምን አይነት ምርትና አገልግሎት እንደሚፈልጉ ለመለየት እንደሚያስችሉም ነው የምትናገረው።
ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራበት እጅግ የላቀ አገራዊ ፋይዳ ያለው የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለቤት መሆን ይቻላል፤ ለእዚህ ደግሞ እንደ ክሬቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ ያሉ መሰል ተቋማት የሚያደርጉት ተቋማዊ ድጋፍ የላቀ ፋይዳ አለው፡፡
በፋሽን ዲዛይን ሙያ ያለውን የባለሙያዎች ሰፊ የብቃት ችግር ለመፍታት ችግሮችን በመለየት በፋሽን ዘርፍ ስልጠናዎች እያዘጋጀ የሚሰጠው የክሪቲቭ ሃብ ኢትዮጵያ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፤ በስራችሁ ጠንክሩ ማለት እንወዳለን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 /2014