ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር በማድረግ እውቅናን ለማትረፍ ወይንም ቀልድ ለመፍጠር የሚሞክሩ አንዳንድ ሰዎች በማይቀለድ ነገር ላይ በመቀለድ ፌዝና ቧልት ሲፈጥሩ ይስተዋላል።የሚገርመው ደግሞ ቧልትና ፌዙን ተቀብለው የሚያሰራጩት ናቸው።ወጥ ያለ ጨው እንደማይጣፍጥ ሁሉ ሰዎች ኑሩአቸውን ቀለል አድርገው ለመምራት ቀልድ፣ ሳቅና ጨዋታ እንደሚያስፈልጋቸው ይታመናል።
ይሁን እንጂ “በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት፣” አይነት ሆኖ፤ “ለሁሉም ልክ አለው” የሚያስብል ቀልድ ምሬትን ያባብስ እንደሆን እንጂ አያዝናናም።ሰው እንባውን እያፈሰሰ ምሬቱን የሚገልጽበት ጉዳይ በፌዝ መልክ እየቀረበ የላይክና ኮሜንት መሰብሰቢያ መሆኑን በግሌ እቃወማለሁ፡፡
ማሕበራዊ ድረ ገጽ (ሶሻል ሚዲያ) አንዱ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገድ መሆኑን ባምንበትም፣ ጠንከር ያለ ቁምነገር ከማስተላለፍና የማሕበረሰቡን ምሬት ከማንፀባረቅ ይልቅ ነገሩን በፌዝ ማቅረብ መለመዱና ሰሞነኛ ሆኖ ጉዳዩ መፍትሄ ሳያገኝ በቀልድና በቧልት በዋዛ መታለፉ ያሳስበኛል።
ብዙሃኑን እጅግ ያሳዘነና አንዳንዶችም በቴልቪዥን መስኮት ቀርበው እያለቀሱ በምሬት ሲናገሩ የሰማናቸው የሰሞነኛው የዘይት ጉዳይ እንደቃልኪዳን ጋብቻ ቀለበት ለፍቅረኛ፣ ለጥሎሽና ለተለያየ ድግስ በስጦታ ሲቀርብና በፈረንጆቹ ቃል ሰርፕራይዝ ሲደራረጉ በየማሕበራዊ ድረገጹ ተሰራጭቶ ሰዎች ፈገግ እንዲሉበት መደረጉ አግባብነት አለው አልልም።
ይህ ሰሞነኛው ቀልድ ‹‹ማሽላ እያረረ ይስቃል›› እንደሚባለው አይነት ነው የሆነብኝ፡፡ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የማህበረሰብ ቅሬታ የሆኑ ግን ደግሞ እንደዋዛ በቀልድ መልክ ተወስደው ቀልድ ሆነው የቀሩ ብዙ ናቸው።
ለአብነትም ከጀሶ ጋር ተቀላቅሎ የተጋገረ እንጀራ፣ ከአሸዋና ከሌላ ባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ለገበያ የቀረበ በርበሬ ሲቸበቸብ፣ ቅቤ ከሙዝ፣ ከቅልጥም፣ ከቫዝሊንና ከሌላ ባዕድ ነገር ጋር እንዲሁ ተደባልቆ ለበላተኛው ሲቀርብ፣ በየሉካንዳቤቱ ኢትዮጵያውያን ከሚመገቡት ውጭ ስጋ ቀረበ ሲባል ሰሞነኛው ቀልድና ፌዝ ይደምቃል።በላይክና ኮሜንት ደምቀው የአንድ ሰሞን ቧልት ሆነው የሕዝቡን ጩኸትና ምሬት ሲደብቁት ይስተዋላል።
ይህ‹‹ማሽላ እያረረ ይስቃል›› አይነት አካሄድ እንዳላዋጣ ከላይ የጀሶ እንጀራና መሰል ያነሳኋቸው ጉዳዮች ማሳያዎች ናቸው።ከቀልድ ባለፈ መንግሥት ለእርምጃ አነሳስተው የሕዝብ ጩኸትን ሲያስመልሱ አላየንም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሕዝብን ለማገልገል ወንበር የያዙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጉዳዩ ለቧልትና ለቀልድ ከመጋለጡ በፊት ቀድመው መሥራት እየቻሉ ችግሩ ሥር ከሰደደ በኋላ መገናኛ ብዙሃንን ጠርተው ሊሰሩት ስላሰቡት ሥራ መናገራቸው ነው።
ነጋዴው ሊወደዱ ይችላሉ ያላቸውን አቅርቦቶችና አገልግሎቶች ቀድሞ ተንብዮ፣ የሚደብቅበትንም ቦታ አመቻችቶ፣ ዋጋ ተምኖና መቼ ገበያ ላይ እንደሚያውለው አቅዶ ሲዘጋጅ አስፈጻሚው ግን ጉዳዩ ተቦክቶና ተጋግሮ ካለቀ በኋላ ነው ደርሶ ለእርምጃ የሚነሳው፡፡
እርምጃውም አንጀት ከማራስ ይልቅ አንጀት ማሳረሪያ ይመለሳል። የዘይት ዋጋ በአንድ ጊዜ ወደ አምስት መቶና ስድስት መቶ ብር ሲያሻቅብም ጩኸት ነበር።በወቅቱ እንዲሁ ነጋዴው በየጓዳው የደበቃቸውን ዘይቶች ማግኘቱን በየመገናኛ ብዙሃኑ እያስነገረ፣ ልክ እንዳሁኑ በሚሊዮን ሊትር የሚቆጠር ዘይት ከውጭ እንደሚገባ ቃል ተገባ፣ ገበያውን በወሬ ለማረጋጋት ሲሞክር ሰምተናል።
ሆኖም ግን ያኔም በቃ የዘይት ዋጋ ከተሰቀለበት ዳግም እንደማይወርድ እርግጠኞች ነበርን። እንደተነበይነው አልቀረም በወጣበት ቀጠለ። አሁን ደግሞ ሌላ የዋጋ ተራራ ላይ ወጣ።
የዘይቱ ዋጋ ከስድስት መቶ ብር እንዳይዘል ማድረጉን እንደ አንድ እርምጃ አስነገረ እንጂ ከዚህም በታች መቀነስ አለበት ብሎ ሰርቶ አላሳየንም።ይህ ደግሞ ከሰሞነኛው እንቅስቃሴ ሳያልፍ የዘይት ዋጋ በአንድ ሊትር የሶስትና የአራት መቶ ብር ጭማሪ ላይ እንዲደርስ መንገድ ከፍቷል።
የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ነጋዴው ከመደርደሪያው ላይ ጭርሱኑ ለእይታ እንኳን ማጥፋቱ ነው፡፡ የሩሲያና የዩኩሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ማግሥት ጀምሮ የሚወራው የነዳጅ ዋጋ መናር ነጋዴው ዋጋ የሚያመቻችበትን መንገድ ለማመቻቸት ዝግጁ እንዲሆን ሲያደርገው ገበያውን የሚቆጣጠረውና የሚከታተለውን የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋም ግን አላነቃም። ይሄ ችግር እንዳይፈጠር ልክ እንደ ነጋዴው ሁሉ አስፈጻሚውስ ነቃ ብሎ አስቀድሞ መፍትሄ አያዘጋጅም የሚል የሕዝብ ጥያቄ ያስነሳል።
የጾምና የተለያየ ወቅትን ተከትሎና ገና ለገና በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ሲከለስ ዋጋ ይጨምራል ብሎ አስቀድሞ ባስገባው ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚዘጋጅ ነጋዴ ባለበት አገር ከአገር ማዶ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ቀድሞ ለዋጋ ጭማሪ መዘጋጀቱ ምን ይገርማል፡፡
አሁን ከመንግሥት እራስ የማልወርደው ሥራውን የሚመለከታቸው አካላት ቀድመው መሥራት የሚገባቸውን ሥራ አልሰሩም ብዬ ነው።ምርትና አገልግሎት ደብቀው ያዝኳቸው ያላቸውን ነጋዴዎች፣ በመካከል ላይ ሆነው ዋጋውን በማናር ሚና አላቸው የሚባሉ ደላሎችን፣ በአጠቃላይ ሕገወጦች ላይ መድረሱን ከመናገር ባለፈ
ድርጊቱ እንዳይደገም አስተማሪ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ለተገልጋዩ ማሕበረሰብ እፎይታ የሚሰጥ ነገር አንሰማም፡፡ በግሌ ሸማቹን ማሕበረሰብ ለማገልገል በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት በሥነልቦናም በአቅምም የተደራጁ ናቸው የሚል እምነት የለኝም።
የተፈጠረውን ችግር በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል በጥናት የተደገፈ ሥራ በመስራት አቅጣጫ አስቀምጦ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጫጫታው የበረታ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ የሚሰራውን የእሳት ማጥፋት ሥራ ከመሥራት እልፍ ብሎ የማያዳግም እርምጃ ስለመወሰዱ ሲነገር አልታዘብኩም፡፡
ነጋዴውም እንዲሁ ሲጠየቅ እርሱም ግራ እንደገባው ነው ሲናገር የሚሰማው።መንግሥት ጡንቻውን ማሳየት ካልቻለ፣ ነጋዴውም ግራ መጋባቱን ከተናገረና ሕዝቡም ከመጮህ ያለፈ ነገር ማድረግ ካልቻለ መፍትሄው ምንድነው? ዛሬ እንደምናየው ሳር ቅጠሉ ነጋዴ ሆኗል። በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የእግረኛ መንገድ ሳይቀር በንግድ ተይዟል።
የሚካሄደው ንግድ የማሕበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ወይ ብሎ መፈተሽና ንግዱን ማስተካከልስ አይጠበቅም? መንግሥትን ያሳጡ የመሰላቸው ግን ደግሞ ለመንግ ሥትም ለሕዝብም ጠቃሚ ያልሆኑ በሰው ምሬት ላይ በፌዝና በቧልት የተጠመዱ የማሕበራዊ ገፆች አርበኞች መረጃ ለማቀበል ከመሽቀዳደም መረጃው ሊያስከትል የሚችለውን ጠንቅ ሁለቴ ማሰብ ይበጃል እላለሁ።
ዛሬ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፌዝና ቧልት ሳይሆን፣ በጦርነትና በተለያየ መንገድ ከደረሰባት የኢኮኖሚ ቀውስና ኑሮ አልሞላ ብሎት የሚንገላታው ሕዝቧ እንዴት ተቋቁሞ እንደሚወጣ መንገድ መምራት ነው።
ሰውን ቀልድና ፌዝ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ በራሱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም።
ተስፋ የቆረጠ ማሕበረሰብ ለራሱም ለአገርም አይጠቅምም፡፡ ማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ በኑሮው ላይ እንዲያፌዝ ሲያደርገው፣ መንግሥትም አንጀቱን የሚያርስ እርምጃ ወስዶ ቅሬታውን ሳይፈታለት ሲቀር የሚከተለውን መገመት አያዳግትም፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩት ተሞክሮዎች የዘይት ዋጋ አሁን ካሻቀበበት ቀንሶ እንደማያገኙት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ እየሰማን ነው።ምንም እንኳን ትኩረቴን ማሕበራዊ ድረ ገጽ ላይ ባደርግም በመንግሥት ሥር የሚተዳደሩ የሕዝብ ሚዲያ የሚባሉትም ቢሆኑ ጥሩ እየሰሩ ነው የሚል መደምደሚያ የለኝም።ዛሬ በእጅ ላይ የሚገኘውን ቴክኖሎጂ በቀላሉ መጠቀም ስለሚቻል ማሕበራዊ ድረገጾች ምቹ በመሆናቸው ነው፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 /2014