‹‹የሴት ልጅ ክብሯ ጓዳዋና ማዕድ ቤቷ ነው›› እየተባለ ለአደባባይ ሳይበቁ፣ በሕዝብ ዘንድ ሳይታወቁ፣ መስራት እየቻሉ እድል በማጣት ሳይሰሩና ምኞታቸውን ሳያሳኩ … የቀሩ ኢትዮጵያውያን እንስቶች ብዙ ናቸው::
ከዓመታት በፊትም ቢሆን የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነገር ስማቸው የሚነሳው እጅግ በጣም ጥቂት ሴቶች ናቸው:: እስካሁንም ድረስ ቢሆን ታሪካቸው ካልተነገረላቸውና እምብዛም በሕዝብ ዘንድ ከማይታወቁት የታላላቅ ስራዎች ባለቤት ከሆኑ ሴቶች መካከል አንዷ የሆኑት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን በጋዜጠኝነት፣ በደራሲነትና በጸሐፌ ተውኔትነት ልዩ ልዩ ተግባራት ያከናወኑ የአገር ባለውለታ ቢሆኑም፤ ስለእርሳቸውና ስለስራዎቻው የሚገልፅ ተሰንዶ የተቀመጠ በቂ/ሰፊ ማብራሪያ የለም::
የዚህ አምድ ዓላማ ለአገርና ለሕዝብ በጎ ተግባራትን ያከነናወኑና አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት ይብዛም ይነስም በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቁ ማድረግ በመሆኑ የወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን ታሪክ በመጠኑም ቢሆን እንዲታወቅና ስራቸውም እንዲለገለጥ ለማድረግ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘናቸውን የታሪክ ማስታወሻዎች በማደራጀት እንዲህ አቅርበነዋል::
ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሳሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ:: እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደገሙ:: ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተማሩ::
በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን ‹‹ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም›› የሚለውን ልማድ በጥረታቸውና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር::
በእርግጥ እንደዛሬው በብዛት አይሁን እንጂ ወይዘሮ ሮማነወርቅ የተማሩበት ወቅት ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ እድል ያገኙበት ዘመን ነበር:: ይሁን እንጂ የባህል ተፅዕኖው የጎላ ነበርና ‹‹ሴት ልጅ ለትዳር ቅድሚያ ትስጥ›› ይባል ስለነበር ሮማነወርቅ ገና የ16 ዓመት ልጅ ሳሉ ለትዳር ታጩ:: በለጋ እድሜያቸውም ወደ ትዳር ዓለም ተቀላቀሉና የአንዲት ሴት ልጅ እናት ለመሆን በቁ::
በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅት ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናትና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደ አደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በጥር ወር 1939 ዓ.ም በወቅቱ ‹‹የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር›› ተብሎ ይጠራ በነበረው መስሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ::
‹‹የሴት ልጅ ስራ ከማዕድ ቤት ነው›› የሚለውን የወቅቱን የኅብረተሰቡን አመለካከት በመጋፈጥ በእውቀታቸውና በክህሎታቸው አገራቸውን ለማገልገል ‹‹የወንድ ቦታ ነው›› ይባል ወደነበረው አደባባይ ብቅ አሉ:: ወይዘሮ ሮማነወርቅ በወቅቱ የጀመሩት ስራ ለሴት ልጅ እምብዛም ያልተለመደ ስለነበር ድርጊታቸው ከወንዶች ብቻ ሳይሆን ከሴቶችም ጭምር ነቀፌታዎች እንዲሰነዘሩባቸው ምክንያት ሆኖ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል::
እርሳቸው ግን ነቀፌታውን ተቋቁመው በሙያቸው ለማገልገል መታገላቸውን ቀጠሉ:: በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በተሰጣቸው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ስራቸው የተለያዩ ጽሑፎችንና ዜናዎችን በማዘጋጀት በማራኪ አንደበታቸው ሲያንቆረቁሩት በዜና አቀራረባቸውና በፕሮግራም ዝግጅታቸው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና አድናቆትን ለማግኘት ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር:: ስራውን ሲጀምሩ ነቀፌታ ገጥሟቸው የነበሩት ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት እንስት ጋዜጠኛ ለመሆን በቁ:: ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ በኢትዮጵያ የሬዲዮ አገልግሎት እንዳሁኑ ባልተስፋፋበት በዚያን ወቅት ይሰጡት የነበረው አገልግሎት እጅግ ከፍ ያለ ነበር::
በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሰርተዋል:: በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ አንድም ቀን ‹‹ሰለቸኝ›› ሳይሉ በየጊዜው ለአድማጭ አዲስ ነገር ይዞ በመቅረብ ለ25 ዓመታት ያህል ለሙያቸው በመታመን ያገለገሉት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ፣ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም (በተለይ ደግሞ ለጋዜጠኞች) አርዓያ መሆን ችለዋል:: ይህም ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትንና አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል:: በወቅቱም ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው በዝግጅቶቻቸው ላይ የተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ስራዎችን በማቅረብ ሕዝቡን ሲያገለግሉ በትምህርት ገበታ ላይ ለነበሩት ሴቶች ልጆች እንደብርቅዬና የበጎ ተግባር ምሳሌ በመሆን ይታዩ ነበር:: ከአድማጩ በሚደርሳቸው አድናቆትና ማበረታቻ በመታገዝ ለስራቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ሰው ነበሩ::
በዝግጅቶቻቸው የተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በወቅቱ በሴቶች ዘንድ ጫና የሚፈጥሩ አመለካከቶችን ለመፋቅ በመገናኛ ብዙኃን የራሳቸውንና የብዙ ሴቶችን ድምፅ አሰምተዋል:: ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን የመጀመሪያዋ እንስት ጋዜጠኛ ብቻ አልነበሩም:: ሴቶች ከወንዶች እኩል ተሰልፈው መስራትና ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ለኢትዮጵያውን ሴቶች ምሳሌና አርዓያ በመሆን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡ ሰው ነበሩ:: ከጋዜጠኝነት ሙያቸው በተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነት ነበረባቸው:: በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ በተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ጽሑፎችንም ያዘጋጁ ነበር::
አብዛኞቹ ጽሑፎቻቸውም የሴቶችን ማሕበራዊ ኑሮ ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ነበሩ:: በነዚህ ጽሑፎቻቸውም የሴቶች ኑሮ እንዲሻሻል ያበረታቱና ይቀሰቅሱ ነበር:: ከእነዚህ ስራዎቻቸው መካከል የበኩር ስራቸው የተጠናቀቀው በ1940 ዓ.ም ቢሆንም ይህን መጽሐፋቸውን ይዘው ወደ ሕትመት የሄዱት ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ በ1942 ዓ.ም ነበር:: ይህንን ጉዳይ አስመልከተውም በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ በማለት ስለሕትመቱ ጉዳይ በትህትና ገልጸዋል … ‹‹ … መጽሐፌን ጽፌ የጨረስኩት በ1940 ዓ.ም ነበር:: ከዚያ ወዲህ ሁለት ዓመታት ቆይቼ ሳነበው ከእርሱ የተሻለ ለመፃፍ የምችል ሆኖ ተሰማኝ:: በዚህ ምክንያት ተሳንፌ ማሳተሙን ለማቆየት ከቆረጥሁ በኋላ የሰው እውቀት የእድሜ ደረጃን ተከትሎ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ አዋቂ አለመሆንን በማሰብ ዛሬ የተሻለ መስሎኝ ብሰራም ነገ መናቄ እንደማይቀር ተረዳሁት::
ይህም የሰው አዕምሮ ያለማቋረጥ የሚሻሻል ለመሆኑ ዋና ማስረጃ ነው በማለት ይህን ሁሉ ካወጣሁና ካወረድሁ በኋላ ማመንታን ትቼ አሳተምሁት:: … ›› የመጀመሪያ ስራቸውን ለአንባቢ ያቀረቡት ወይዘሮ ሮማነወርቅ ለመጽሐፋቸው የመረጡት ርዕስ ‹‹ትዳር በዘዴ›› የሚል ነበር::
መጽሐፉ የገጠሩንና የከተማውን ትዳርና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲሆን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀርባል:: ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹ለትዳር ፈላጊዎች ምክር አለኝ›› በማለት ስለትዳር የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ሞክረዋል:: ሴቶች በማሕበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸው ጫናም በመጽሐፉ ተዳስሷል::
ወይዘሮ ሮማነወርቅ የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን ካሳተሙ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ በ1943 ዓ.ም ሁለተኛ ስራቸውን በትያትር መልክ በማዘጋጀት ለሕትመት አበቁ:: ይህ ስራቸው ‹‹ማህቶተ ጥበብ›› የሚል ስያሜ ሲኖረው፣ ታሪኩ በወቅቱ ሕይወታቸው ስላለፈው ስለ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ ሕይወት የሚያወሳ መጽሐፍ ነው:: ጋዜጠኛና ደራሲዋ ሮማነወርቅ ካሣሁን በዚህ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ ብለዋል … ‹‹ … እድለኛ ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተወደዱ የንጉሰ ነገሥቱ ልጅ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ ከልደታቸው ጀምሮ እስከ እረፍታቸው ድረስ የሰሩት ታካዊ ስራ እጅግ ከፍ ያለ ሲሆን ይህንኑ ስራቸውን ከብዙ በጥቂቱ፤ ከረጅሙ በአጭሩ ለመግለፅ አስቤ መልካም አርዓያነታቸውን ለመከተል እንዲመራን በሙሉ ባይሆን ዋና ዋናዎቹን የስራና የእውቀታቸውን ፍሬዎች ብቻ በመከታተል ይህን ትንሽ መጽሐፍ በትያትር እቅድ ስላዘጋጀሁት የዚህን ትያትር ተመልካቾችን የምለምነው በቅን ልቦና ተመልክተው በጎደለ እንዲያርሙኝ ነው::… ›› ወይዘሮ ሮማነወርቅ በሁለቱም መጽሐፎቻቸው ላይ አበክረው የሚመክሩት ነገር የሴቶችን ማሕበራዊ ሕይወትና ግንኙነት ስለማሻሻል እንዲሁም ማሕበረሰቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያደርገው ስለሚገባው ተሳትፎና እገዛ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም ወይዘሮ ሮማነወርቅ ጽሁፎቻቸውን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በማሳተም በሕትመት መገናኛ ብዙኃን ላይም የፋና ወጊነት ሚናን ተጫውተዋል::
እንዲሁም ማሕበረሰቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያደርገው ስለሚገባው ተሳትፎና እገዛ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም ወይዘሮ ሮማነወርቅ ጽሁፎቻቸውን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በማሳተም በሕትመት መገናኛ ብዙኃን ላይም የፋና ወጊነት ሚናን ተጫውተዋል::
የ‹‹መነን›› መጽሔት አዘጋጅ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የሴቶችን ሕይወት የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ (የምክር) ጽሑፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ በመፃፍም የታወቁና የተደነቁ ነበሩ::
ደራሲ ከበደ ሚካኤል በትምህርትና ስነ-ጥበብ ሚኒስቴር ኃላፊ በነበሩበት ወቅት በ1948 ዓ.ም ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ባደረጉት ንግግር ስለወይዘሮ ሮማነወርቅና ሌሎች በአርዓያነት ስለሚጠቀሱ ሴቶች እንዲህ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር … ‹‹ … ከጦርነት ወዲህ ግን በአዲስ አበባም ሆነ በየጠቅላይ ግዛቱ የሚታየው የሴት ተማሪዎች ቁጥር አስደሳች እየሆነ መጥቷል::
እነ ስንዱ ገብሩ፣ እነሮማነወርቅ ካሳሁን (ሬዲዮ አንባቢዋ) እነ ዮዲት እምሩ፣ እነአልማዝ ፋሲካ ከማዕድ ቤት ወጥተው በማኅበረሰቡ መካከል በመገኘት አገር እየረዱ ነው::
በተለይም የሮማነወርቅ ካሣሁን የሬዲዮ ትምህርት አቀራረብ የመማር እድል ላላገኙት ሴቶች ጭምር ተስፋ የሚሰጥ ስለሆነ የሕብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑ የሴቶች ትምህርት በብዛት እንዲቀጥልና ለትምህርት የሚመደበውም ገንዘብ ከፍ እንዲል በትህትና አሳስባለሁ …›› በየአቅጣጫው እየተጉ የሴቶችን በተፈጥሮ ደካማ ያለመሆን በስራ ያስመሰከሩት ወይዘሮ ሮማነወርቅ፣ በ1948 ዓ.ም ሦስተኛ መጽሐፋቸውን ለሕትመት አበቁ::
የመጽሐፉም ርዕስ ‹‹የሕይወት ጓደኛ›› የሚል ነበር:: በወይዘሮ ሮማነወርቅ መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚመላለሰው ርዕሰ ጉዳይ ሴት ዝቅ ተደርጋ የምትገመትበት ማሕበረሰባዊ የትዳርና የኑሮ ጣጣ ነበር:: ወይዘሮ ሮማነወርቅ በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦና ላሳዩት ከፍተኛ ስራ ብርታትና ትጋት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል::
ከሽልማቶቹ መካከልም ከኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም የደራሲያንን መታሰቢያ የብር ሜዳሊያ ይጠቀሳሉ:: በ1956 ዓ.ም የኢትዮጵያ ደራሲያን መታሰቢያ ሽልማትን ሲወስዱ የሽልማት ድርጅቱ … ‹‹ … ዛሬ እንዲሸለሙ የተመረጡት ዘመኑ ካፈራቸው ሴቶች መካከል ከወንዶች እኩል ተሰልፈው ሕዝቡን በሬዲዮና በመጽሔት ያስተማሩና ወደፊትም ያስተምራሉ ብለን ያሰብናቸው ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን ናቸው::
እኒህ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ በሬዲዮ ተናጋሪነትና በመጽሔት አዘጋጅነት የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑት ወይዘሮ፣ በአረጋውያት ዘንድ እንደደፋርና ባሕል አቆሻሽ ተደርገው ቢቆጠሩም ለወጣቱ የሔዋን ትውልድ ግን እንደፋና ወዲና አብይ ምሳሌ ሆነው የሚቆጠሩ ናቸው:: ስለዚህ በድርሰት ችሎታቸው የብር ሜዳሊያ ከሚሸለሙት ወንዶች በተጨማሪም ሮማነወርቅ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነው ተመርጠዋል::
በዚህም እንኳን ደስ አለዎት እንላቸዋለን …›› በማለት ለወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሳሁን በፃፈው የአድናቆትና ውዳሴ ምስክርነት ሰጥቷል:: ወይዘሮ ሮማነወርቅ ከላይ ከተገለጹት ጥረቶቻቸው በተጨማሪ የተለያዩ ድርጅቶችና ማሕበራት አባል በመሆን ለወገናቸው ሕይወት መቃናት የሃሳብ፣ የገንዘብና የጉልበት አስተዋፅኦ በማድረግም የታወቁ ሰው ነበሩ:: ለአብነት ያህልም የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ ስራ ማሕበር እየተባለ ይጠራ የነበረው ድርጅት አባል በመሆን የሚፈለግባቸውን የኢትዮጵያዊነት ግዴታ ተወጥተዋል::
በወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማሕበር (ወሴክማ)፣ በደራሲያን ማሕበር በሌሎች ማሕበራትና የማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በአባልነትና በተጋባዥ እንግድነት እየተገኙ ትምህርታዊ አስተያየታቸውንና ምክራቸውን ይሰጡ ነበር::
ወይዘሮ ሮማነወርቅ በህመም ምክንያት ሐኪም ቤት ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ‹‹ለወይዛዝርት›› የተባለውና በሳምንት ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚቀርበው ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነበሩ:: በዚህ ፕሮግራም ላይ በትያትርና በውይይት መልክ የሚያቀርቧቸው ትምህርታዊ መሰናዶዎች ስለ ቤት ባልትና፣ ስለ ልጅ አስተዳደግና ስለ መልካም ቤተሰብ ኑሮ ያወሱ ነበርና በአድማጮች ዘንድ ‹‹እውነትም ሮማነወርቅ›› አሰኝቷቸዋል:: ወይዘሮ ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም አረፉ::
ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንትና ሰራተኞች እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል::
ሞት ቀደማቸው እንጂ ‹‹ሔዋን››፣ ‹‹መልካም እመቤት››፣ ‹‹የቤተሰብ አቋም››፣ ‹‹የባልትና ትምህርት››፣ ‹‹የሕፃናት ይዞታ››፣ ‹‹ዘመናዊ ኑሮ››፣ ‹‹የኑሮ መስታዎት››፣ ‹‹ጋብቻና ወጣቶች››፣ እና ‹‹የባልና የሚስት ጠብ›› በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት እየጠበቁ ነበር::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 /2014